Print this page
Wednesday, 24 March 2021 00:00

ታንዛኒያ የመሪዋን ሞት ተከትሎ የመጀመሪያዋን ሴት ፕሬዚዳንት ልትሾም ነው

Written by 
Rate this item
(0 votes)

     ኮሮናን በአደባባይ በማናናቅ የሚታወቁትና በቫይረሱ መጠቃታቸው በስፋት ሲነገርላቸው የሰነበተው የታንዛኒያው ፕሬዚዳንት ጆን ማጉፉሊ ባለፈው ሃሙስ ከዚህ አለም በሞት መለየታቸውን ተከትሎ፣ በምክትልነት ሲያገለግሉ የነበሩት ሳሚያ ሃሰን በአገሪቱ የመጀመሪያዋ ሴት ፕሬዚዳንት ሆነው ስልጣኑን ሊረከቡ መዘጋጀታቸውን ኦል አፍሪካን ኒውስ ዘግቧል፡፡
ለሳምንታት ከአደባባይ ጠፍተው የሰነበቱትና በኮሮና ቫይረስ ተጠቅተው በህንድ በሚገኝ ሆስፒታል ህክምናቸውን ሲከታተሉ እንደነበር የተነገረላቸው የ61 አመቱ ማጉፉሊ፤ ከትናንት በስቲያ ከዚህ አለም በሞት መለየታቸውን የአገሪቱ ምክትል ፕሬዚዳንት ሳሚያ በይፋ አስታውቀው፣ የሞታቸው ሰበብ እንደተባለው ኮሮና ሳይሆን የልብ ህመም ነው ብለዋል፡፡ የ61 አመቷ ምክትላቸው ሳሚያ በመጪው ሳምንት ቃለ መሃላ ፈጽመው ስልጣኑን እንደሚረከቡና ለቀጣዮቹ 5 አመታት አገሪቱን እንደሚያስተዳድሩ ተመልክቷል፡፡
በ2015 በተካሄደ ምርጫ አሸንፈው ስልጣን የያዙትና ባለፈው አመት በተደረገ አወዛጋቢ ምርጫ በድጋሚ አሸንፈው ለ2ኛ የስልጣን ዘመን አገሪቱን በማስተዳደር ላይ የነበሩት ማጉፉሊ፤ በአጠቃላይ አገሪቱን ላለፉት 7 አመታት የመሩ ሲሆን  በጸረ ሙስና ዘመቻ የሚወደሱትን ያህል ተቃዋሚዎችን በማፈን ይታማሉ። ፕሬዚዳንት ማጉፉሊ በተወለዱ በ68 አመታቸው ማረፋቸውን ተከትሎ፣ በአገሪቱ ህገ መንግስት በተቀመጠው መሰረት፣ በምክትል ፕሬዚዳንትነት ሲያገለግሉ የቆዩት ሳሚያ፣ 6ኛዋ የታንዛኒያ ፕሬዚዳንት ሆነው መንበሩን እንደሚረከቡ ተዘግቧል፡፡
ቀጣዩዋ የአገሪቱ መሪ የፕሬዚዳንቱን ሞት በቴሌቪዥን ይፋ ባደረጉበት ወቅት የ14 ቀናት ብሔራዊ ሃዘን መታወጁን ያስታወቁ ሲሆን፣ ጎረቤት ኬንያም የ6 ቀናት ሃዘን ማወጇን ዘገባው አክሎ ገልጧል። የማጉፉሊን ሞት ተከትሎ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ማህመት ባስተላለፉት የሃዘን መግለጫ፤ ታንዛኒያ ቁርጠኛ የፓን አፍሪካኒስት መሪዋን አጥታለች ያሉ ሲሆን ጠ/ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድን ጨምሮ የተለያዩ የአፍሪካ አገራት መሪዎችም በግለሰቡ ሞት የተሰማቸውን ሃዘን መግለጻቸውን ቀጥለዋል፡፡
ከዚያው ታንዛኒያ ሳንወጣ የምናገኘው ሌላ ዜና ደግሞ፣ የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን ከመሰረቱት መሪዎች መካከል አንዱ የነበሩት የታንዛኒያ የመጀመሪያው ፕሬዚዳንት ጁሊየስ ኔሬሬ፣ በአፍሪካ ህብረት ጽህፈት ቤት ቅጽር ግቢ ውስጥ የመታሰቢያ ሃውልት ሊቆምላቸው እንደሆነ ያመለክታል፡፡

Read 1141 times
Administrator

Latest from Administrator