Saturday, 20 March 2021 13:11

የ3 ደቂቃ የህሊና ፀሎት የሚነፈጉም አሉ!

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(9 votes)

   “የአንዳንዶች ሞት እንደ ኮላተራል ዳሜጅ ይቆጠራል”
                         በዚች ዓለማችን ላይ የሰው ልጆች ሁሉ እኩል ዋጋ አላቸው የሚል ሰው ካለ፣ እኔ ፈጽሞ አልስማማም። ጥቂቶች እጅግ ይከበራሉ፤ የሚሰጣቸውም ግምት የላቀ ነው። አያሌዎቹ ግን ከእነ መፈጠራቸውም የሚያስታውሳቸው የለም - ማንም ከሰው ተርታ አይቆጥራቸውም።
ይህን የምለው ደግሞ ከባዶ ተነስቼ አይደለም። በበቂ መረጃና እማኝነት ላይ ተመርኩዤ ነው። ለምሳሌ የኒውዮርኩ የንግድ ማዕከል በቦምብ ከመጋየቱ አንድ ሳምንት ቀደም ብሎ በአንጎላ በባቡር ይጓዙ የነበሩ 500 ሰዎች በጅምላ ተጨፍጭፈዋል- በUNITA። ለነዚህ የጅምላ ጭፍጨፋ ሰለባዎች ግን የ3 ደቂቃ የህሊና ጸሎት እንኳ አልተደረገም። የአሜሪካው ኩባንያ /Union Carbide/ ለ15 ሺ ህንዳውያን ሞት ተጠያቂ ቢሆንም ኩባንያውን ያወገዘ ግን የለም። ሟቾቹም… እንኳንስ የህሊና ጸሎት ቀርቶ ካሳ ያሰበላቸው የለም። መቼም ይሄ አንዲ ዋርሆል የተባለ ሰው፤ “እያንዳንዱ ሰው በህይወቱ የ15 ደቂቃ ዝና ይኖረዋል” ሲል በጭንቅላቱ ከነጭ ሌላ የሰው ዘር እንዳላሰበ አያጠራጥርም፡፡  
እውነቱን እንነጋገር ካልን… በአልጀሪያ በርካታ ህጻናትና እንስቶች በአክራሪ ቡድኖች አንገታቸው ሲቀላ ማን አስታወሳቸው? መቼስ የህሊና ጸሎት ተደረገላቸው? ብራዛቪል፤ በታጠቁ ሃይሎች ከካርታ እስከ መፋቅ ስትደርስ ማን ተናገረ? ምንም እርባና በሌለው በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት  ለሞቱት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የሁለቱ ሀገር ዜጎች… ዓለም መቼ የ3 ደቂቃ የህሊና ጸሎት አደረገ? በሶማሊያ ከ20 ዓመታት በላይ በተደረገ የእርስ በርስ ጦርነት ለተፈጁት ሶማሊያውያን ማን ተሟገተ? ማንስ አስታወሳቸው? ማንም ለ3 ደቂቃ እንኳን ያሰባቸው የለም!! እነ ሴራሊዮንን… እነ ፍልስጤምን ማን አስታወሷቸው ያውቃል?
እንግዲህ አንድ ጊዜ ጀምረነው የለ…እንቀጥል - እውነት እውነቱን። በ1977 በኢትዮጵያ በተከሰተው ረሀብ ላለቁት አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎች፣ አንድ ዜማ ብቻ ነው የተለቀቀው- “we are the world” የሚለው። በሴፕቴምበር 9/11 ያሸባሪዎች ጥቃት በኒውዮርክ ለሞቱት አሜሪካውያን ከወጣው የማስታወሻ ዜማ ጋር ካወዳደራችሁት… ልዩነቱ በደንብ ይገባችኋል። በአንድ ጀምበር´ኮ በዓለም ዙሪያ አያሌ የወዳጆች ማጽናኛ አግኝተዋል- በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜማዎችም ተለቀዋል። ለምን ብዙ አጽናኝ አገኙ እያልኩ አይደለም… ልዩነቱን ለማሳየት ያህል ነው! ጉዳዩን በሂሳባዊ ስሌት ለማየት ከፈለጋችሁ፣ ይሄ ምን ማለት መሰላችሁ? 333 ኢትዮጵያውያን የአንድ አሜሪካዊ ዋጋ አላቸው እንደ ማለት ነው። እስቲ ግን የአሜሪካውያንንና ኢትዮጵያውያንን የኑሮ ደረጃ ልዩነት አስቡት። እኔም ይሄን ካሰብኩ በኋላ ነው የተረጋጋሁት። /አንድ የአሜሪካ የመከላከያ ሀይል ባለስልጣን፣ አሜሪካ በሩዋንዳ የምታደርገውን ወታደራዊ ጣልቃ-ገብነት ተገቢነት ያስረዱት፣ የ80 ሺ ሩዋንዳውያን ሞት ከአንድ አሜሪካዊ ሞት ጋር እኩል መሆኑን በመግለጽ ነበር/
መቼም ጤናማ አእምሮ ያለው ሰው፣ ለየትኛውም ተጎጂ /ሰለባ/ የሆነ የሰው ዘር ሁሉ እኩል ልብ ይኖረዋል ብዬ አስባለሁ። ይሄኔ ነው በፈረንሳይ 76 ሰዎች ብቻ ያሉበት ትንሽዬ መንደር ከንቲባ ለሆኑት ፈረንሳዊ ድጋፋችንን የምንቸረው። እኚህ ከንቲባ ለአሜሪካውያን ሰለባዎች ብቻ የህሊና ጸሎት እንዲደረግ ተጠይቀው “አይሞከርም” ነው ያሉት። “አሜሪካውያን ሰለባዎች ከሌላው ሀገር ዜጋ ይበልጣሉን? የበለጠስ ክብር አላቸውን?” ሲሉ ሞግተዋል። ከንቲባው ከትንሿ መንደራቸው ውጪ ስለሚከናወነው ጉዳይ ጠንቅቀው ያውቃሉ ማለት ነው።
ይኼውላችሁ… በዚች በምንኖርባት ዓለም ሁሉም ሰው እኩል ዋጋ የለውም። አንድ አሜሪካዊ… ሲሆን ሲሆን የሺ አልያም የ100 አፍሪካውያን ያህል ነው - ግምቱ ወይም ዋጋው። አንድ እስራኤላዊ  ከ12 ዓረቦች የበለጠ ዋጋ አለው። በዚምባቡዌ አንድ ነጭ ገበሬ፤ ከወርቅ መብለጥ ብቻ ሳይሆን ከ100 ጥቁር የዚምባቡዌ ዜጎችም ይበልጣል። ይህቺ ናት እንግዲህ ዓለማችን! ይሄ ነው ያልተለወጠው የዓለማችን የአኗኗር ስርዓት። ይሄ ነው በአንድ ዓለም ሁለት መለኪያ ወይም ሚዛን (Double Standurd) አለ የሚያስብለን። ዓለም ለሁሉም እኩል እንዳልሆነች ወይም ሁሉንም በአንድ ዓይን እንደማታይ ለማወቅ ብዙ ጥናቶች አያሻንም። የእስራኤሉ ኤርያል ሻሮን መቼ ታሰሩ? ሂነሪ ኪሲንጀር በዘር ማጥፋት ወንጀል ተከሰው መቼ ዓለማቀፍ ፍ/ቤት ቀረቡ? የኦሳማ ቢንላደን ቡድን በናይሮቢና ዳህሬ ሰላም ያሉትን የአሜሪካ ኤምባሲዎች በቦምብ አጋይተው፣ 200 አፍሪካውያንን ሲገድሉ ነው እንዴ አሜሪካ አፍጋኒስታንን የወረረችው? ወደድንም ጠላንም እንግዲህ የምንኖርባት ዓለም ይህቺ ናት… እናም አውሮፕላን ሙሉ ሰው ጭነው በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ያሉበት ህንጻ ላይ የሚላተሙ… አክራሪዎች ቢፈጠሩ ያን ያህል መደነቅ አይገባንም። እንዴ የዓለም ስርአት የራሱ አክራሪ ጠላቶች እየፈጠረ እኮ ነው።
ከዚያ ደግሞ ምን የሚባል ነገር አለ መሰላችሁ? ኮላተራል ዳሜጅ! /በባንክ አሰራር አንድ ሰው የእናንተን ንብረት አሲዞ ገንዘብ ይበደራል። በኋላ ኪሳራ ይደርስበትና ንብረቱ ይወረሳል፤ እናንተም ትከስራላችሁ- ይሄ ነው ኮላተራል ዳሜጅ/ አንድ በተጨባጩ ፖለቲካ የነቃሁ የበቃሁ ነኝ የሚል ወዳጄ ሲያጫውተኝ፤ “በዓለም የንግድ ማዕከል ላይ በደረሰው ጥቃት የሞቱት ሰዎች፣ ሰለባዎች ወይም ተጎጂዎች አይባሉም” አለኝ።
ግራ ገብቶኝ “ምን ማለትህ ነው?” አልኩት።
“ኮላተራል ዳሜጅ” ናቸው- አለኝ። የአሜሪካ የኢምፔሪያሊስት ፖሊሲ “ኮላተራል ዳሜጅ” ናቸው እንደ ማለት ነው።  ልክ አሜሪካ በኢራቅ ላይ ማእቀብ ስታደርግ፣ ህጻናቱ እያለቀሱ፣ ሳዳም ሁሴን ጠግበው በሰላም ወደ አልጋቸው ይሄዱ እንደነበረው ማለቱ ነው። ያኔ በዋሽንግተን፣ በፓሪስና በለንደን የሚደገፈው የአፓርታይድ ስርዓት ሰለባዎች እንደ ማለት ነው- ኮላተራል ዳሜጅ!
አንድን ሰው ወይም ወገን "ኮላተራል" ነው ብላችሁ ከበየናችሁ… ምን ማለት መሰላችሁ? ብትገድሉት ወይም በቦምብ ብታጋዩት መብት አላችሁ እንደ ማለት ነው። እሱን ማንም እንደ ሰው ልጅ ወይም እንደ ተጎጂ አያየውም።
አሁን ማን “ኮላተራል” እንደሚባል የገባችሁ ይመስለኛል። ብዙም የሚከብድ ነገር አይደለም። ኮላተራል በመጀመሪያ ነጭ አይደለም። ብዙ ጊዜ ጥቁር ፣ ጠይም ወይም ቢጫ ቀለም ያለው የሰው ዘር ነው። እንደ ፒኖቼ ፣ ሞቡቱ፣ ቮርስተር ፣ ኪሲንጀር አይነቶቹ የፈለጉትን ቢገድሉ፣ የገደሉት ወገን ወዲያውኑ “ኮላተራል” ይባልላቸዋል። ምክንያቱም ለሚፈጽሙት ተግባር ሁሉ የዋሽንግተን ቡራኬ አላቸውና!  የቀድሞው የሱዳን አምባገነን መሪ ግን ይቺን ቀላል እውነት ለመረዳት አመታት ፈጅቶባቸዋል። ዘግየት ነው የነቁት፡፡ ከዚያም ከእነ ክፉ ድርጊቶቻቸውና አምባገነንነታቸው “የሰለጠነው” ዓለም አካል ሆነዋል።
ድሮ ድሮ የአፍሪካ አምባገነን መሪዎች፣ ከአሜሪካ ገንዘብ ማግኘት ሲፈልጉ፣ እየተነሱ ወደ ሞስኮ መብረር ብቻ ነበር የሚጠበቅባቸው። እንዲህ የሚያደርጉት ከሩሲያ ጋር ወዳጅነት የፈጠሩ በማስመሰል ከአሜሪካ ያሻቸውን ለማግኘት ነው። አልያም ደግሞ በዓለም ባንክና በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ስም መማል መገዘት ይጀምራሉ- ያኔ ዶላሩ ይፈስላቸዋል። ክሊንተን የዲሞክራሲን አስፈላጊነት ለአፋቸው ያህል በተናገሩ ጊዜ፣ አምባገነኖቹ የአፍሪካ መሪዎቻችን፣ በክፍት መኪና ላይ እየዘለሉ ስለ ዲሞክራሲ ደስኩረዋል - ለፍፈዋል። ይታያችሁ…እነ አያ-ዴሙን፣ እነ ሙሴቪኒ -- በዲሞክራሲ ስም ሲምሉና ሲገዘቱ ኖረዋል። አሁን ደግሞ ጨዋታው ተለውጧል። ሁሉም የአልቃይዳን ህዋስ እየፈለጉና እያሰሱ ነው። ይሄ ነዋ አሁን የሚፈለገው።
“ኮላተራል ዳሜጅ” የሚለው ስያሜ ለአፍሪካ አምባገነኖች የተመቸ ቃል ነው። አሜሪካ የዚህ ስያሜ ፈጣሪ እኔ ነኝ ብላ ታስብ ይሆናል….ሆኖም የአፍሪካ አምባገነኖች ናቸው በሚገባ ጥቅም ላይ ያዋሉት። እንግዲህ እንደምናየው መላው አህጉራችን በ”ኮላተራል” እና “ሰለባ” ለመሆን አይበቁም የሚባሉ ህዝቦች ተሞልቶ ሳለ፣ መሪዎቻችንን ምን እንደሚያስፈራቸው አይገባኝም። የፓኪስታኑን ጄነራል ታስታውሱታላችሁ? ኩዴታ ፈጻሚው ይሄ ጄነራል፤ የታሊባኖች ደጋፊ እንደነበር ይታወቃል። ከዚያስ አትሉኝም… ከዚያማ የምዕራቡ ዓለም ወዳጅ ሆነላችሁና ገንዘብና ሌሎች ድጋፎች ይጎርፉለት ጀመር። በፓኪስታንና በመላው አካባቢዋ ዲሞክራሲን ስላካተተው ኮላተራል እርሱትና፣ በአንድ ዓለም ሁለት ሚዛን ወይም መለኪያ ይሏል ይሄ ነው። ራሱ “የዓለም ሰላም” የሚባለው “ኮላተራል” መሆኑ አይቀሬ ነው። ከሁሉም የሚያሳዝኑን ግን አፍጋኒስታኖች ናቸው- እጣ ፈንታቸው ማብቂያ በሌለው ጦርነት ውስጥ “ኮላተራል ዳሜጅ” አድርጓቸዋልና! ማንም እዚያ ቢሞት በቃ “ኮላተራል ዳሜጅ” ነው የሚባለው። አያችሁልኝ… ዓለም ለሁሉም እኩል እንዳልሆነች!
የ3 ደቂቃ የህሊና ጸሎትም ቢሆን ለሁሉም እኩል አይደረግም፤ የሚደረግላቸውና የማይደረግላቸው አሉ። የህሊና ፀሎትም የሚነፈጉ ሰዎች ወይም የህብረተሰብ ክፍሎች መኖራቸው ግን አይገርምም? ቢገርምም ግን እውነት ነው!!
(#አፍሪካን በስላቅ; ከሚለው መጽሐፍ የተወሰደ፤2002)

Read 3207 times