Saturday, 20 March 2021 13:23

የአትሌቲክስ ፌደሬሽና የኦሎምፒክ ኮሚቴ ውዝግብ ቀጥሏል

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

    በጃፓን ለሚካሄደው 32ኛው ኦሎምፒያድ  125 ሲቀሩ አብዛኛዎቹ አገራት ወደ የመጨረሻው የዝግጅት ምዕራፍ እየገቡ ቢሆንም ኢትዮጵያ ውስጥ ግን አትሌቲክስ ፌዴሬሽንና ብሄራዊ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ውዝግብ ውስጥ ገብተዋል፡፡
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት፤ ሌሎች የስራ አስፈጻሚ አባላት፣ አሰልጣኞች አትሌቶች እንዲሁም የቴክኒክ ባለሙያዎች ከትናንት በስቲያ ሶስት ሰዓታትን የፈጀው ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።  የኦሎምፒክ ኮሚቴው አምባገነናዊ አሰራር እንደሚከተል የተገለፀ ሲሆን በቶኪዮ ኦሊምፒክ ዝግጅትና በሌሎች ጉዳዮች በየጊዜው የሚፈጠሩ አለመግባባቶች አሳሳቢ ደረጃ መድረሳቸውንም ማረጋገጥ ተችሏል፡፡ አትሌቲክስ ፌደሬሽኑ ለአለምአቀፉ የኦሊምፒክ ኮሚቴ፣ ለአለም አትሌቲክስ እና ሌሎች ለሚመለከታቸው አካላት በኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ላይ ቅሬታዎችን በማቅረብ  ምላሽ እየተጠባበቀ መሆኑም ታውቋል፡፡
ኦሎምፒክ በሚካሄድባቸው ዓመታት ብሄራዊ ኦሎምፒክ ኮሚቴው ከአትሌቲክስ ፌደሬሽን፤ ከአትሌቶች፤ ከአሰልጣኞች  እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በተለያዩ አጀንዳዎች መወዛገቡ በኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ተሳትፎ ላይ ተፅእኖዎችን እንደሚፈጥር ይታወቃል፡፡ በኦሎምፒክ በመሳተፍ ራሳቸውንና አገራቸውን ለማስጠራት ፍላጎት ያላቸው  አትሌቶችና አሰልጣኞች በእነዚህ ውዝግቦች ፈታኝ ሁኔታዎች ይገባሉ፡፡  የኦሎምፒክ ዝግጅታቸውንም በሙሉ ልብ እንዳያከናውኑም ያደርጋቸዋል፡፡
ለቶኪዮ 2020 ኢትዮጵያ በምታደርገው ዝግጅት ላይ ኦሎምፒክ ኮሚቴው ችግሮች መፍጠሩን  የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ኮሎኔል አትሌት ደራርቱ ቱሉ ስትወቅስ፤ አትሌቶች ሆቴል መግባታቸው የሚታወቅ ቢሆንም ሊሟላላቸው የሚገቡና የስልጠናው ዋና አካል የሆኑ መሠረታዊ ግብአቶች በወቅቱ አላደረሳቸውም ብላለች፡፡ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ  በተደጋጋሚ በአትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ ስራ ጣልቃ እንደሚገባና የዓለም አቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ መተዳደሪያ ደንብ እንደማያከብርም አሰልጣኞች፣ የቴክኒክ ባለሙያዎችና አትሌቶች በምሬት ገልፀዋል፡፡  ለቶኪዮ 2020 የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድንን መምረጥ ማሰልጠን እና ለውድድር የማዘጋጀት ሀላፊነት የፌዴሬሽኑ ቢሆንም ኦሊምፒክ ኮሚቴው ከተሰጠው ስልጣን እና ሀላፊነት ውጭ በቴክኒካዊ ጉዳዮች ላይ በተደጋጋሚ ጣልቃ መግባቱ ተችተው፤ ይህም የኦሎምፒክ ቡድኑን ዝግጅትና የአንድነት መንፈስ እንደረበሸው ነው ያስረዱት፡፡ ከዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ያልተላለፉ መመሪያዎችንም ብሄራዊ ኦሎምፒክ ኮሚቴው አስመስሎ እያቀረበ በእቅድ እንዳይሰራ አድርጓል ያሉት የፌደሬሽኑ ሃላፊዎች በተለይ የማራቶን ተሳታፊዎች የመጨረሻ ዝርዝር አስገቡ ተብሏል በሚል አትሌቶችን መረበሹን ጠቅሰዋል፡፡ ኦሎምፒክ ኮሚቴው ላለፉት አራት ወራት አትሌቶች በሆቴሎች ለነበራቸው ቆይታ ምንም አይነት ክፍያ እንዳልፈፀመና በቂ የልምምድ መስሪያ አቅርቦቶችን አለማሟላቱም ታውቋል፡፡ ለቶኪዮ 2020 የተሻለ ዝግጅት ለማድረግ አትሌቲክስ ፌደሬሽኑ በማሰብ የአትሌቲክስ ቡድኑን ወደሌሎች ሆቴሎች እንዳዛወረና ከ3.5ሚ ብር በላይ ውዝፍ የውሎ አበል ክፍያዎች እንደፈፀመም መግለጫው አመልክቷል፡፡ አትሌቲክስ ፌደሬሽኑ  ባሰማው ቅሬታ ኦሊምፒክ ኮሚቴው በአራት አመታት ጊዜ ውስጥ ወጪ የሚያባክኑ ሰባት ጠቅላላ ጉባኤዎችን ማካሄዱን፤  አብዛኞቹ ትክክለኛ አካሄድን ያልተከተሉ እና ህጋዊ የጎዳላቸው ነበሩ ብሏል፡፡
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን እንዳመለከተው የመረጣቸው 85 አትሌቶችና 17 አሰልጣኞች በሶስት የተለያዩ ሆቴሎች በመግባት  ያለፉትን አምስት ወራት ለቶኪዮ 2020   ጠንካራ ዝግጅት እየሰሩ ቆይተዋል፡፡ የአንድነት ስሜታቸውን ለማጠናከር መቻሉም ተገልጿል፡፡ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ቡድንን ለመምረጥ የመጨረሻ ዙር ማጣሪያዎች ማዘጋጀቱን የገለፀው ፌደሬሽኑ፤ ከወር በኋላ በዙሪክ ፤ ስዊዘርላንድ የ35 ኪሜ ውድድር ለማራቶን አትሌቶች እንዲሁም ለትራክ ሯጮች በሰኔ ወር በሄንግሎ ሆላንድ ላይ ከ800ሜ – 10000ሜ የማጣርያ ውድድሮች መኖራቸውንም ጠቁሟል፡፡

Read 1028 times