Saturday, 20 March 2021 13:30

የገጣሚው የዕንባ ዘለላ

Written by  ሳሙኤል በለጠ (ባማ)
Rate this item
(11 votes)

    (የአጭር አጭር ልብወለድ)


             ...ምንም ትንፍስ በማይልበት ሸለቆ ውስጥ ተጨብጦ ተቀምጧል። የሕይወትን ምስጢር የሚፈልግ ብኩን ባይተዋር ይመስላል።...ከኪሱ ሲጋራ አወጣና ለኩሶ ወደ ጠቆረው ከንፈሩ ለጠፈው፤ የሲጋራውን ጢስ ምጎ አንቅሮ ሲተፋው በአፉም በአፍንጫውም ጢስ ይወጣል። በዚያች ቅጽበት እንዴት ገጣሚ እንደሆነ አውጠነጠነ..
“ህም!”
“መለያየት ሞት ነው!”
“ታዲያ በየት በኩል ነው...?”
“ከሞት የምተርፈው!” እያለ ይብከነከናል
ገጣሚ የሆነበትን ምክንያት ደረሰበት። ከሚወዳት፣ ትወደደው አትውደደው እርግጠኛ ካልሆነባት ሴት የተለየ ዕለት  ነው። ገጣሚ ነኝ ያለው (ያሉት)።
ለነገሩ “የማይድን የማይገድልህ ነው” ካለ በኋላ ቅኔ ያጎደለ መስሎት አቀረቀረ። የሲጋራው ጢስ ዓይኑን አስለቀሰው፤ የዕንባው ዘለላ ነፍሱ ላይ ጠብ አለች፡፡
...በድጋሚ በሃሳብ ቸነፈር ተመታ፤ "ግጥም የነፍሴን ቅኝት ከመለየት፣ ሕመምና ከአሁን እኔነት ጋር እኩል  ይደረድርልኛል። ስታመም ያስታምመኛል" ብሎ በለሆሳስ ተናገረ፤ ሲጋራው ተጋምሶ ኖሮ ጣቱን ሲፈጀው ከሰመመናዊ ሕመሙና ሃሳቡ ባንኖ ነቃ፡፡
ያነሳው ሃሳብ መጨረሻ የለውም፤ዝም ብሎ ውስጡ ያለውን የስቃይ እሳት ይቆሰቁሳል። የዓለም ጽንፍ ይርቀዋል፤ ሲርቀው ኩርትምትም ብሎ ይቀመጣል። ከሚወዳት በመለየቱ ይናደዳል፤ ጺሙን ይነጫል፡፡
ትዝታ፤ መለየት፣ በመለየት ውስጥ ያለ ጠኔ፣ የፈሰሰ ሐሞቱን እያባበለ ‘ማንባት፣ እኒህ ሁሉ ነገሮች ህልው ሆነው እንደ  ውርጭ ቀጩት፤ ከግማሽ የደረሰውን ሲጋራ በእግሩ ደፈጠጠው፤ ሊሄድ ነበር ማለቂያ የሌለው ጉዞ፤ ኤጭ! ብሎ እንደ ቅጠል እረግፎ ከሸለቆው ጥግ ተቀመጠ፤ ምን አስቀመጠው? በራሱ ውስጥ ያየው መስታወት፣ በመስታወቱ ጥልቀት ዳር ያየው የመለየት ሕመም፡፡

Read 2184 times