Saturday, 27 March 2021 11:38

ኮሚሽኑ በትግራይ የፀጥታ ሃይሎች ያልተመጣጠነ ሃይል እንዳይጠቀሙ አሳሰበ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

   በትግራይ  የተካሄደውን “የህግ ማስከበር ዘመቻ” ተከትሎ በአክሱም ከተማ ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት መፈጸሙን በቀዳሚ ሪፖርቱ ያስታወቀው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከ100 በላይ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን ያስታወቀ ሲሆን የጸጥታ ሃይሎች  ያልተመጣጠነ ሃይል እንዳይጠቀሙ አሳስቧል።
ኮሚሽኑ ከየካቲት 20 እስከ 26 ቀን 2013 ዓ.ም ቀደም ሲል በአለማቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾቹ አመነስቲ ኢንተርናሽናልና ሂውማን ራይትስዎች የምርመራ ሪፖርት ወደቀረበበት አክሱም ከተማ የምርመራ ቡድን አሰማርቶ ባካሄደው ጥናት የተፈጸመው የዜጎች ግድያ ምናልባትም በጦር ወንጀለኝነት የሚያስጠይቅ ነው ብሏል።
የኮሚሽኑ የምርመራ ቡድን አባላት፣ ለምርመራው ጉዳት የደረሰባቸውን ግለሰቦች ጨምሮ 45 ተጎጂ ቤተሰቦች ፣ የአይን እማኞችና የሃይማኖት አባቶችን ማነጋገሩን እንዲሁም 20 ሰዎች የተሳተፉበት የቡድን ውይይት ማካሄዱን አስታውቋል።
በሂደቱም ከተጎጂው ቤተሰቦች ከአክሱም ቅድስት ማርያም ሆስፒታል፣ ከአክሱም ሪፈራል ሆስፒታል፣ ከሚመለከታቸው የቀበሌ መስተዳደሮች እንዲሁም ከሃይማኖት ተቋማት የምስል የድምጽ እንዲሁም የሰነድ ማስረጃዎች  ማሰባሰቡንም አመልክቷል።
ኢሰመኮ በቀዳሚ ሪፖርቱ ከ1መቶ በላይ  የሞቱና ሌሎችም ብዛት ያላቸው የተጎጂ መረጃዎች ማሰባሰቡንና፣ በሌሎች ተጨማሪ መሰል ጉዳት ስለመድረሳቸው ጥቆማ ባገኘባቸው የገጠር አካባቢዎች ተጨማሪ ጥናት እያከናወነ መሆኑንም አስታውቋል።
ኮሚሽኑ የ100 ሟቾችን ሁኔታ ማጣራቱን ይህም አጠቃላይ የተጎጂዎችን ቁጥር የሚያመላክት አለመሆኑንና ተጨማሪ ምርመራዎች እየተደረጉ እንደሆነ አስገንዝቧል።
በመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርቱ በንጹሃን ላይ ስለተፈጸመው ግድያ እንጂ ሌሎች የጾታዊ ጥቃቶችና ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶችን ያካተተ አለመሆኑን ኮሚሽኑ አስታውሶ በቀጣይ  በሚቀርበው የተሟላ የምርመራ ሪፖርቱ እነዚህን ጉዳዮች እንደሚያካትት አስታውቋል።
በአክሱም ከተማ በተለይ ህውሃት ከከተማ ከወጣበት ከህዳር 9 እስከ ህዳር 15 ቀን በነበረው ጊዜ በጸጥታ ሃይሎች በተተኮሱ ከባድ መሳሪያዎች ከሞቱት መካከል አምስቱ ማንነታቸውን እንኳ መለየት ባልቻለበት ሁኔታ መገደላቸውን፣ በርካታ ሰዎች በጉዳቱ እጃቸውና እግራቸው መቆረጡን ፣ አንዲት የ70 ዓመት አናት አፋቸውና መንጋጋቸው ሙሉ በሙሉ በመገንጠሉ  ህክምና ለመስራት አስቸጋሪ የሆነ አሰቃቂ ጉዳት እንዳጋጠማቸውና በኋላም ህይወታቸው ማለፉን ሪፖርቱ ያሳያል።
በተጨማሪም ሪፖርቱ ከህዳር 9 እስከ 11 ባለው ጊዜ በኤርትራ ወታደሮች 41 ሰዎች መገደላቸውንና ከ126 በላይ ከባድና መካከለኛ ጉዳት እንደደረሰባቸው ያመለከተ ሲሆን በጊዜው ሆስፒታል ሳይወሰዱ በያሉበት ሞተው የቀሩ ሰዎችም  እንዳሉ ማጣራቱን ኢሰመኮ ተጠቅሷል።
በአክሱም ከተማ ከተፈጸሙ ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶች መካከል የተገደሉ ሰዎችን አስክሬን ቤተሰብ ከሜዳ ላይ እንዳያነሳ መከልከሉ ተጠቅሷል በሪፖርቱ።
ህዳር 16 ቀን 2013 ዓ.ም የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አክሱምን ለቆ መውጣቱን፣ ህዳር 17 እለት አክሱም ከማንኛውም ወታደራዊ አንቅስቃሴ ነጻ ሆና መዋሏን ነገር፤ ግን በነጋታው ህዳር 18 ቀን የኤርትራ ወታደሮች በሶስት ቦታዎች ሰፍረው ከተማዋን መቆጣጠራቸውን፤ ከህዳር 19 ጀምሮም የአካባቢው ሚሊሻዎች በኤርትራ ወታደሮች ላይ ተኩስ መክፈታቸውን ተከትሎ፤ የኤርትራ ወታደሮች ሰላማዊ ሰዎችን ጭምር ወደ መግደል መግባታቸውን ተመልክቷል።
ህዳር 19 ቀን የተገደሉ ሰዎችን ለመቅበር ህዝቡ ቢንቀሳቀስም “የኛ ሰዎች ሳይቀበሩ የእናንተ ሰዎች ሊቀበሩ አይችሉም” በሚል ምክያንት በቀባሪዎች ላይ ተኩስ መከፈቱንና መበታተናቸውን የሚያመለክተው ሪፖርቱ፣ በዚህም በከተማዋ አስክሬኖች መሽተታቸውንና በጅብ እስከ መበላት መድረሳቸውን፣ አስክሬኖች ቤተሰቦቻቸው ሳያገኟቸው በተለያዩ ቤተክርስቲያኖች በተዘጋጁ የጅምላ መቃብሮች መቀበራቸው ተገልጿል።
በጸጥታ ሃይሎች ከተፈጸሙ ግድያዎች ባሻገር ሆስፒታሎችን ጨምሮ የተለያዩ የግልና የህዝብ ተቋማት መዘረፋቸውም በሪፖርቱ ተመልክቷል።
ኮሚሽኑ የጸጥታ ለሃይሉን ያካተተውን የተጣራ ሪፖርት በቅርቡ ይፋ እንደሚያደርግ፤ ነገር ግን የፀጥታ  ሃይሎች ያልተመጣጠነ ሃይል አጠቃቀም በአስቸኳይ ሊቆም እንደሚገባው አሳስቧል።
መንግስት የተጎዱ ቤተሰቦችን የመጠገንና መልሶ የማቋቋም እንዲሁም ሰብአዊ እርዳታ የማዳረስ ስራ እንዲሰራ ፣ የህክምና ተቋማት በአስቸኳይ ተመልሰው እንዲቋቋሙ ምክረ ሃሳብም አቅርቧል።
ጠ/ሚር ዶ/ር አብይ ዐቢይ አህመድ በፓርላማ ውይይት ወቅት በትግራይ ማንኛውም የሰብአዊ መብት ጥሰት የፈጸሙ የፀጥታ ሃይሎች ተጣርቶ በህግ ይጠየቃሉ ማለታቸው አይዘነጋም።

Read 363 times