Saturday, 27 March 2021 11:52

ሁከትና ብጥብጥ ላይ የከረሙት የሰሜን ሸዋና ወሎ አካባቢዎች በኮማንድ ፓስት እንዲተዳደሩ ተደርጓል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

 ከቅዳሜ መጋቢት 11 ቀን 2013 ጀምሮ በግጭት ውስጥ የቆየው ሸዋሮቢት አጣዬ፣ ከሚሴና ሌሎች አካባቢዎች በኮማንድ ፖስት እንዲተዳደሩ የተወሰነ ሲሆን በአንዳንድ አካባቢዎች ግጭቶች መቀጠላቸውን ምንጮች ለአዲስ አድማስ ጠቁመዋል፡፡
መነሻው በውል ባልታወቀው ሁከትና ግርግር በአጣዬ፣ ሸዋሮቢት፣ ሰንበቴ፣ ከሚሴ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በሳምንቱ መገደላቸውን የፀጥታ ሃይሎችም ሁኔታውን ለማረጋጋት ጥረት ሲያደርጉ መሰንበታቸውን ምንጮች አስረድተዋል፡፡
ባለፈው አርብ እለት በአጣዬ የጀመረው የታጠቂዎች ጥቃት በሂደት በአቅራቢያው ወዳሉት ከተሞች የገጠር መንደሮች መስፋፋቱን አብዛኛው ሰው የተኩስ ልውውጡን በመፍራት እቤት መቆየትን መምረጡን በአጣዬ ከተማ የሚገኙ ምንጮች ተናግረዋል፡፡
በአርብ ከምሽቱ 4 ሠዓት አካባቢ የጀመረው የተኩስ ልውውጡ እና ሁከቱ ቤቶችን ወደ ማቃጠል፣መንገድን ወደ መዝጋት መሸጋገሩን የገለፁት ምንጮች ታጣቂዎች በየቤቱ እየገቡ ዘረፋ እና ግድያዎችን ሲፈፅሙ እንደነበረ ገልፀዋል፡፡
የአማራ ክልል የፀጥታ ሃይሎች ሁኔታውን ለመቆጣጠር ጥረት ሲያደርጉ መሰንነበታቸውን ጦርነት በሚመስል መልኩም በታጣቂዎች በፀጥታ ሃይሎች መካከል ለቀናት የቆየ የተኩስ ልውውጥ መደረጉን እነዚሁ ምንጮች ጠቁመዋል።
አንዱ ከተማ የፀጥታ ሃይሎች ሲገቡ ታጣቂዎቹ ከዚያ ከተማ ሸሽተው ወደ ሌላው ከተማ በመንቀሳቀስ ግድያ ቤት ማቃጠልና ሁከት ይፈፅሙ ነበር የሚሉት ምንጮች ይህም ሁኔታውን በአፋጣኝ ለመቆጣጠር አስቸጋሪ አድርጎታል ብለዋል።
እሁድ መጋቢት 12 ቀን 2013 ዓ.ም ግጭቱ ወደ ከሚሴ ከተማ በመዛመትም መንገዶች የመዘጋትና ቤቶችን የማቃጠል ተግባር መፈፀሙን እንዲሁም ቀኑን ሙሉ ከተማዋ ከፍተኛ የተኩስ ልውውጥ ሲካሄድ መዋሉን ይህ ሁኔታም እስከ ሰኞ ድረስ መቀጠሉን ምንጮች ተናግረዋል።
ሰኞ አለት የፌደራል መከላከያ ሰራዊት ከሚሴ ከተማ መግባቱንና  ሁኔታውን ለማረጋጋት ጥረት ማድረጉን በዚሁ በከተማ የነበረው ሁከት መቆሙንና ከማክሰኞ ጀምሮ ከሚሴ ከተማ ወደ ሰላማዊ እንቅስቀሴ መመለሷን ምንጮች ገልጸዋል።
ታጣቂ ሃይሎች ከፍተኛ ጉዳት ከፈፅሙባቸው ከተሞች አንዷ የሆነችው ሸዋ ሮቢት ከተማ ከሃሙስ ጀምሮ ወደ መረጋጋት እየተመለሰች መሆኑንና ከተማ ወጣ ባሉ አካባቢዎች አልፎ አልፎ የተኩስ ልውውጦች መኖራቸውንም እነዚህ ምንጮች ተናግረዋል፡፡
ከትናንት በስቲያ በሰንበቴና በጂሌ ጥሙጋ አካባቢዎች ጠንከር ያለ የተኩስ ልውውጥ ሲደረግ እንደነበር ያስታወቁት ምንጮች ለሰአታት የቆየውን የተኩስ ልውውጥ ተከትሎ የፀጥታ ሃይሎች አካባቢውን መቆጣጠራቸውን አስታውቀዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በሁከት ላይ የሰነበቱት የሰሜን ሸዋና የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን አካባቢዎች በኮማንድ ፖስት ስር ሆነው የማረጋጋት ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነ መንግስት አመልክቷል፡፡

Read 11933 times