Saturday, 27 March 2021 12:12

መመካከር የቤተሰብ ምጣኔን ሲፈልጉ ለመጠቀም ያስችላል፡፡

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(1 Vote)

    የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት በኢትዮጵያ ለሁሉም ማለትም ለሚፈልጉት ሴቶች ሁሉ ተደ ራሽ መሆን ችሎአል ወይንስ? የሚለውን የተለያዩ ጥናቶችን በመፈተሸ ጠቅለል ያለ ሀሳብ ያቀረቡት ሰለሞን አዳነው ወርቁ፤ዮሐንስ ሞገስ ምትኩ እና አባተ ዳረጌ ውበቱ ናቸው፡፡ መረ ጃው ለንባብ የቀረበው contraception volume 5, Article number: 21 (2020) እ.ኤ.አ በ (November 2020) ነው፡፡
በእንግሊዝኛው Unmet need የሚባለው ልጅ መውለድ የሚችሉ ሴቶች በተለያዩ ምክንያቶች እርግዝናቸው እንዳይከሰት ቢፈልጉ፤ ወይንም ልጆቻቸውን አራርቀው መውለድ ለሚፈልጉ፤ ወይንም እስከጭርሱኑ ልጅ መውለድ አልፈል ግም …ይበቃኛል የሚሉ ሴቶች የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎትን እየፈለጉ አለማግ ኘት ወይም አገልግሎቱን ማግኘት አለመቻላቸው ነው፡፡  
ከላይ በተጠቀሰው ቁምነገር ዙሪያ የተለያዩ ጥናቶች የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት ምን ያህል ተደራሽ አልሆነም ሲሉ በኢትዮጵያ ያለውን እውነታ ፈትሸው በአገልግሎቱ አሰጣጥ እንዲሁም ልጅ በመውለድ እድሜ ላይ ያሉ ሴቶች እውቀትና ፍላጎት እንዲሁም ሴቶቹ ምን ያህል ከባሎ ቻቸው አሊያም ከወንድ ጉዋደኞቻቸው ጋር በጉዳዩ ላይ ይወያዩበታል? የሚለውን በግልጽ ፈትሸዋል፡፡
እነ ሰለሞን አዳነው ወርቁ ወደ 9 የሚሆኑ የጥናት ስራዎችን የዳሰሱ ሲሆን በእነዚህ ጥናቶች ላይ ወደ 9785 የሚሆኑ ተሳታፊዎች አገልግሎቱን ባለማግኘት ዙሪያ መልስ ሰጥተዋል፡፡
በኢትዮጵያ ልጅ የመውለድ እድል ያላቸው 34.90% የሚሆኑ ሴቶች የቤተሰብ እቅድ ዘዴን አገልግሎት ማግኘት እየፈለጉ ነገር ግን እንዳልቻሉ ታውቆአል፡፡ ጥናቱ ለምሳሌ ያህል የጠቀሰው የአማራ ክልልን ሲሆን በአማራ ክልል 32.98%ያህል መውለድ የሚችሉ ሴቶች አገልግሎቱን እንዳላገኙ ተገልጾአል፡፡ ይህ በዝርዝር ሲታይ ያገቡት ወይንም የቤት እመቤት የሆኑት ሴቶች በስራ ላይ ካሉት ያገቡ ሴቶች ይልቅ 1.6 ጊዜ ያህል አገልግሎቱን እየፈለጉ አለማግኘታቸው ተጠቁሞአል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የቤተሰብ እቅድን መጠቀም መቻል አለ መቻልን በሚመለከት ከባለቤቶቻቸው ወይንም ከወንድ ጉዋደኞቻቸው ጋር መወያየት አለመቻ ልን በሚመለከትም መወያየት የማይችሉት ከሚወያዩት በ1.87 ጊዜ ያህል ቁጥራቸው ከፍ ብሎ ይታያል፡፡
ከሰሀራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገራት ልጅ በመውለድ እድሜ ላይ ያሉ 25% የሚሆኑ ሴቶች ትዳር ያላቸው ወይንም ባይኖራቸውም ወንድ ጉዋደኛ ያላቸው የቤተሰብ ምጣኔ ለመጠቀም አለመቻላቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በላቲን አሜሪካን እና በካሪቢያን አራት ሀገራት እንዲ ሁም በኤሽያ ስምንት ሀገራት ወደ 20% ያህል ሴቶች የቤተሰብ እቅድ ዘዴ አገልግሎትን ማግ ኘት እንዳልቻሉ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡
መረጃው እንደሚገልጸው ያልተፈለገ እርግዝናን ለመከላከል የሚያስችሉ መከላከያ ዎችን መጠቀም እየፈለጉ አለማግኘታቸው ኢትዮጵያ በአፍሪካ ከፍተኛ ቁጥር አላቸው ከሚባሉት ሀገራት መካከል ናት፡፡ በ2011/የተደረገው (EDHS) እንዳረጋገጠው ከሆነ 25% የሚሆኑ ሴቶች ያልተፈለገ እርግዝና መከላከያን ያላገኙ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ ወደ 16.3% የሚሆኑት ልጅን ማራራቅ የሚፈልጉ እንዲሁም ወደ 9% የሚሆኑት ደግሞ የልጅን ቁጥር ለመመጠን የሚ ፈልጉ ነበሩ።  ይህ መረጃ እንዳረጋገጠው በየትኛውም አቅጣጫ አገልግሎቱን የሚፈልጉ እና ማግኘት ያልቻሉት ሴቶች ከከተማው ይልቅ በገጠሩ ቁጥራቸው ከፍ ይላል። በአጠቃላይም አገልግሎቱን እየፈለጉ አለማግኘትን በሚመለከት EDHS 2016 እንደገለጸው ከሆነ ወደ 58% የሚሆኑ እድሜያቸው ከ15-49 የሆኑና በቅርብ ጋብቻቸውንም የፈጸሙ የቤተሰብ ምጣኔ ወይ ንም እቅድን አገልግሎት ተጠቀሚ ለመሆን የጠየቁ ሲሆን ወደ 36% የሚሆኑትም ያልተፈለገ እርግዝናን መከላከያዎቹን እየተጠቀሙ መሆኑ ታውቆአል፡፡ መከላከያዎቹን እየፈለጉ አለማግ ኘት በአዲስ አበባ ዝቅተኛ ማለትም 11% ሲሆን በኦሮሚያ ደግሞ ከፍተኛ ማለትም 29% መሆኑ ታው ቆአል፡፡  
ጥናቱ ከላይ በተጠቀሱት አካባቢዎች ብቻ የተወሰነ አልነበረም፡፡ የቤተሰብ ምጣኔ አገልግ ሎትን አለማግኘት በአማራ 32.98% በትግራይ 31.53% ሲሆን ከዚህም ውስጥ ያገቡት ሴቶች 32.83% እን ዲሁም እድሜአቸው ለመውለድ የደረሱ ሴቶች ልጅ መውለድን ያልፈለጉ ወደ 35.29% የሚሆኑት መከላከያዎችን አለማግኘታቸውን የጥናቱ አቅራቢዎች አሳይተዋል፡፡
ይህ ጥናት የተመለከታቸው ሌሎች መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በአብዛኛው ያልተፈለገ እርግዝና መከላከያን እየፈለጉ ያለማግኘት ምክንያት በባልና ሚስት ወይም በሴትና በወንድ ጉዋደኛሞች መካከል መወያየት ወይንም መመካከር ባለመኖሩ መሆኑን ያሳያል፡፡ ሴቶች ከባሎ ቻቸው ወይንም ከወንድ ጉዋደኞቻቸው ጋር የማይወያዩ ከሆነ ከሚወያዩት ይልቅ በ1.87 ጊዜ ያህል እድሉን እንደማያገኙ ተረጋግጦአል፡፡ ይህ በኢትዮጵያ የተደረገው ጥናት እንደሚያሳ የው በሌሎች አገሮች ከተደረጉ ጥናቶች ጋር የሚመሳሰል ሲሆን ለመጥቀስ ያህልም ቦትስዋና፤ በካሜሩን ገጠር አካባቢ፤በካሜሩን ሰሜን ምእራብ አካባቢ የታዩ ተመሳሳይ እውነታዎች አሉ፡፡
ባለትዳሮች በኑሮአቸው፤ በልጆቻቸው፤ በኢኮኖሚያቸው በመሳሰሉት ጉዳዮች የመነጋገርና የመ ወያየት ልምድ አለማዳበራቸው ከተለያዩ ነገሮች ጋር ተያይዞ ሲነሳ ይስተዋላል፡፡ ተግባራዊ በማድረጉ ረገድ ግን ገና ብዙ መሰራት ያለባቸው ነገሮች መኖራቸውን የሚያሳዩ የተለያዩ ጥናታዊ ስራዎች በየጊዜው ይፋ ይደረጋሉ፡፡ ባለትዳሮች ወይንም ጉዋደኛሞች የእርስ በእርስ ግንኙነታቸውን በሚመለከት ግልጽ ውይይት ማድረግ ካልቻሉ በተለይም የሚኖሩአቸውን የልጆች ቁጥር ለመወሰን እንደሚቸገሩ በግልጽ የሚነገር እውነታ ነው፡፡ ብዙው ጊዜ በኑሮአቸው በተለይም ልጆቻቸውን በሚመለከት ምን ያህል ቁጥር ልጅ እንፈልጋለን፤ በስንት አመት መራራቅ አለባቸው የሚለውን ለመወሰን በግልጽ የሚነጋገሩ የትዳር አጋሮች በቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት ተጠቃሚ እንደሚሆኑና ያልተፈለገ እርግዝናን ለመከላከል የሚያስችሉትን መከላከያዎች እንደሚጠቀሙ ጥናቶች ይፋ አድርገዋል፡፡
ባለትዳሮች ወይንም ጉዋደኛሞች እርግዝና ከመከሰቱ በፊት ወደፊት ሊኖሩአቸው ስለሚፈልጉ አቸው ልጆች በመመካር የሚወስኑ ከሆነ በተለይም ሴቶቹ በእቅድና ዘዴ በመመራት ያልተፈለገ እርግዝናን ለመከላከል ሊያደርጉ ስለሚገባቸው ነገር ከህክምና አማካሪዎቻቸው ምክር እንዲያገኙ ስለሚያስችላቸው ሕይወታቸውን በደስታ ለመምራት፤ ቤተሰባቸውንም በእቅድ በመምራት መኖር ይችላሉ፡፡ ወንዶችም  ቤተሰባቸውን ለመመጠን ከሚስቶቻቸው ወይንም ከሴት ጉዋደኞቸው ጋር በመስማማታቸው በደስታ ኑሮአቸውን ሊመሩ ይችላሉ፡፡
በሌላም በኩል ጥናቱ የተመለከተው ነገር ኢኮኖሚን ነው፡፡ አንዳንድ ሁኔታዎች የሚጠቁሙት በአብዛኛው የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎትን ማግኘት እየፈለጉ ነገር ግን የማያገኙ ሴቶች የቤት እመቤቶች ናቸው፡፡ ብዙውን ጊዜ በባሎቻቸው ኢኮኖሚ ላይ ተንተርሰው ኑሮአቸውን የሚመሩ ሴቶች እራሳቸው የሚያገኙት ገቢ ስለሌላቸው አብዛኛውን ጊዜ ስለሁሉም ነገር የሚወስኑት ወንዶቹ ይሆናሉ፡፡ ምንም እንኩዋን የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት ከገንዘብ ጋር ብዙም የሚገናኝ ባይ ሆንም አስተዳዳሪው እኔ ነኝ አርፈሽ ተቀመጭ የሚል ወንድ የሚያስተ ዳድራት ሴት ከሆነች ውሳኔውን ጥሳ ወደአገልግሎት መስጫው ብትሄድ የባልዋን ሃሳብ እንደተቃወመች ስለሚቆጠርና በወደፊቱ ሕይወትዋ የሚደርስባትን ችግር በመፍራት እራስዋን ታገልላለች፡፡ ምናልባትም ለትራንስፖርት እና ለመሳሰሉ ነገሮች ገንዘብ ብትፈልግም ባልዋ የማይሰጣት ከሆነ ከቤትዋ ለመውጣትም ትቸገ ራለች። ይህ አይነቱ አኑዋዋር በተለይም በአፍሪካ ኢትዮጵያን ጨምሮ በገጠሩ ክፍል በስፋት የሚታይ ነው፡፡
ሌላው የቤተሰብ ምጣኔን ወይንም እቅድን ማግኝት እየፈለጉ የማጣታቸው ምክንያት ሴቶቹ ትምህርት አለመማራቸው መሆኑን ጥናቱ አረጋግጦአል፡፡ ትምህርት ያልተማሩ ሴቶች ልጅን ላለመውለድ የመከላከያ መድሀኒትን መውሰድ ጠቃሚ መሆኑን ለመረዳት እንደተማሩት ሴቶች ቀላል አይሆንላቸውም፡፡ እንዲያውም እንደ ሀጢአትና ከእግዚአብሔር እንደመጣላት አድርገው ሊቆጥሩት ስለሚችሉ ተግባሩን ላይደግፉ ይችላሉ፡፡
ባጠቃላይም ልጅ የመውለጃ እድሜ ላይ ያሉ ሴቶች ልጆቻቸውን በምን ያህል እርቀትና ብዛት መውለድ እንዳለባቸው ለመወሰን ከትዳር አጋሮቻቸው ጋር በቅርብ መወያየትና በምላሹም የትዳር አጋሮቻቸው ተሳትፎና ድጋፍ በእጅጉ ያስፈልጋቸዋል፡፡ በተጨማሪም ሴቶቹም ሆኑ ወንዶቹ ተገቢው እውቀት እንዲኖራቸው ማስተማር ከሚመለከታቸው ሁሉ ይጠበቃል፡፡ በተለ ይም የመገናኛ ብዙሀን፤ ትምህርት ቤቶች፤ የጤና ተቋማት ከፍተኛ ኃላፊነት አለባቸው፡፡  


Read 11789 times