Saturday, 27 March 2021 12:41

የማስመሰል ዘመን...‘ማሰቢያ’ ከላይ ወደ ታች

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(2 votes)

    "ማስመሰል! ማስመሰል! ማስመሰል! እናላችሁ...አለ አይደል...ፎርጅድ ሰው መኖሩን እስካሁን ‘በማስረጃና በመረጃ’ እንደሚባለው
አይነት በማሳያነት የምናቀርበው ባይኖረንም፣ ፎርጅድ ባህሪ ግን መኖር ብቻ ሳይሆን የዘመናችን ዋናው መለያ ሆኗል፡፡-"
                
            እንዴት ሰነበታችሁሳ!    
የሆነ አገልግሎት መስጫ ስፍራ ነው። እና የሆነ ባለጉዳይ ከመግባቱ በፊት እጁን በሳኒታይዘር ሙልጭ አድርጎ ያጠዳል። እናም ልክ ወደ ውስጥ ሊዘልቅ ሲል ጥበቃው ጣልቃ ይገባል፡፡
“ጌታዬ ይመለሱ” እሱዬው ደነገጥ ይላል። መቼም የዘንድሮ ነገር ከምናውቀው የማናውቀው... አለ አይደል... ዘጠና አምስት ለአምስት ስለሆነ እንዲሀ አይነት ያልጠበቅነው ነገር ሲገጥመን ደንገጥ ብንል አይገርምም። እናንተ በዓይናችሁ አቧራው ገብቶባችሁ ስትጨናበሱ፣ “እከሌ  ሊጠቅሰኝ ሞከረ...” ብላ ምን የሚያካክሉ መደገፊያ ግንቦች ላሉት አጎቷ፣ ወይም “አጎቴ; ነው ለምትለው ሰው ብትነግር፣ የት ሊገባ ነው! 
“ጌታው እጅዎትን ይታጠቡ” ሰዉ ምን ነካው! ዓይኑ እያየ፣ ፊት ለፊቱ እኮ ነው በሳኒታይዘራችሁ እጃችሁን ያጠባችሁት፡፡
“ይኸው በሳኒታይዘር እኮ ታሸሁት"
“እይ፣ እሱ ፎርጅዱ ስለበዛ አያስተማምንም። አስተማማኙ ውሀና ሳሙና ነው”
እናላችሁ፣... አንዱ ደስ የሚለው ነገር ምን መሰላችሁ... ይህን ያህል ነገሬ ብለው የሚከታተሉ መኖራቸው፡፡ ወላ ጥበቃው በሉት፣ ወላ የሚጠበቀው በሉት፣ አብዛኛው ሰው እኮ ትቶታል! አንድ ብዙ ጊዜ የሚደጋገም ነገር አለ፡፡ “ለምንድነው የጸጥታ አስከባሪዎች ማሰክ የማያደርገውን ሰው የማይቆጣጠሩት?” ይባላል፡፡ ቢሆንማ አሪፍ በሆነ ነበር፡፡ ቢያንስ አንዳንዶቻችን አጉል ሽለላችንን በልክ እናደርገው ነበር። የሚገርም እኮ ነው...ማስክ ማድረግ ማለት እኮ... አለ አይደል... “ማድረግ ደስ ሳይለኝስ!” የሚባልበት ነገር ጨርሶ አይደለም! እሚገርም እኮ ነው፤ ድፍን ሀገር የሚጠቀመበትን ጎዳናና መገልገያ ስፍራ የፈለግነውን የምናነሳበት፣ ያልፈለግነውን የምንጥለበት የግል ጓዳችን  እናደርገዋለን፡፡ በጠፋ ብር ለዚህ ደግሞ ወርክሾፕ ምናምን የሚባል ነገር በየቀበሌው መዘጋጀት አለበት!
እናላችሁ... አዋጅ ተብሎ የወጣውን የሚያስከብሩ ቢኖሩ አሪፍ ነው፡፡ ግን ደግሞ ሌላው ቸግር ምን መሰላችሁ... ህጉን እንዲያስከብሩ የሚጠበቅባቸው ክፍሎች አካባቢ፣ ህጉን የማያከብሩ  መኖራቸው ግራ ያጋባችኋል፡፡ መአት ማስክ የማያደርጉ ፖሊሶች፣ መአት ማስክ የማያደርጉ ደንብ አስከባሪዎች፣ መአት ማስክ የማያደርጉ የጥበቃ ሠራተኞች፣ መአት ማስክ የማያደርጉ ቦሶች የሞሉባት ከተማ ነች፡፡ አለቆች በሥራችሁ ያሉትን ሠራተኞች ማስክ አደርጉ በሉልን፣ መጀመሪያ ግን ራሳችሁ አድርጉማ!!
ስሙኝማ... የፎርጅድ ሳኒታይዘሩ ነገርም እኮ አሳሳቢ ነው። ሰዋችን “ቢያንስ፣ ቢያንስ እጄን አጽድቻለሁ...” ብሎ አንዳይተማመን ያደርገዋል፡፡ ቀስ ብሎ ደግሞ ፈሳሽ ሳሙናውንም እንዳይተማመን ያደርገዋል፡፡ በሰው ስቃይ ትርፍ ለማግኘት መሮጥ፣ እንደ ብልጥነት የሚታይበት ዘመን!
ማስመሰል! ማስመሰል! ማስመሰል! እናላችሁ... አለ አይደል... ፎርጅድ ሰው መኖሩን እስካሁን ‘በማስረጃና በመረጃ’ እንደሚባለው አይነት በማሳያነት የምናቀርበው ባይኖረንም፣ ፎርጅድ ባህሪ ግን መኖር ብቻ ሳይሆን የዘመናችን ዋናው መለያ ሆኗል፡፡ እንደውም ወደፊት ዘመናት “አስራ ምናምነኛው፣” “ሀያ ምናምነኛው” እየተባለ በቁጥር መገለጹ አብቅቶ፣ እንደገና እንደ ቀድሞው “የድንጋይ ዘመን ምናምን መባል ከጀመረ፣በእኛው ዘመን ደግሞ ማንም የባለቤትነት ጥያቄ ሊያስነሳበት የማይችል “የአስመሳይነት ዘመን...” የሚባል ስም ያገኛል፡፡ ከዛማ ምን አለፋችሁ...
“የፊውዳሉ ትውልድ ሀገር እንዳታድግ ሲጎትታት ኖሮ...”  
“ያ ትውልድ ተስማምቶ እንደመሥራት እርስ በእርሱ ሲጨራራስ ኖሮ...” አይነት ፋክትና ፊክሽን ድብልቅልቃቸው እንደወጣባቸው የፖለቲካ... (ይቅርታ ‘የታሪክ’ ለማለት ፈልጌ ነው መሰለኝ!) ትርክቶች ይህኛው ዘመን ደግሞ በተራው...
“እውነትን መቀበል አቅቶት ማሰቢያውን ከጭንቅላቱ ወደ ሆዱ ያወረደው የአስመሳይነት ዘመኑ፣ አስመሳይ ትውልድ...” የማይባልበት ምክንያት የለም፡፡ በነገራችን ላይ ‘ተረኝነት’ የሚባለው ነገር የስልጣን ወንበር ላይ ወጥቶ ሀያ አምስት ሴንቲሜትር የምትሆነዋን ትከሻን ወደ ሜትር ከሀያ አምስት ማስፋት መሞከር ሳይሆን፤ ከስልጣን ሲወርዱም ሀያ አምስቷ ሴንቲሜትር ትከሻ፣ ከአስራ ስድስት ተኩል የማትበልጥ አይነት ስሜት መስጠት ስትጀምር ነው፤፡ (‘ሙልጭ’ እኮ ነው! ለክፋቱ ደግሞ ሹሮ ሜዳ ሰው ሁለት ትከሻ ያለው የሚያስመስሉ የክፉ ቀን ጃኬቶች እንደ ድሮው እንደልብ ላይገኙ ይችላሉ፡፡ (ነጠላ በነጠላ የሆነ ዘመን! እነ እንትና ይቺም ትርጉም ሰጥታ ከስሜ ፊት ‘ባለቅኔው’ የሚል ጨምሩልኝ አሉ!) 
እናላችሁ.... በዛኛው ዘመን ‘ልክ አሁን እንዳለው’ ሁሉ የሚመጣው (‘የሚጎርፈው’ ማለት ይቻላል፡፡ ስሙኝማ... እኛ ሀገር እኮ ከባድ ዝናብ ተከትሎ ከሚወርድብን ጎርፍ ይልቅ፣ የስልጣን ወንበር ፈልጎ የሚወርድብን የፖለቲከኛና የአክቲቪስት ጎርፍ በዛበንሳ!) እና... የሚመጣው ምድረ ፖለቲከኛና አክቲቪስት ምናምን የራሱን የበሰለ ሀሳብ ማቅረብ ሲያቅተው ...አለ አይደል...‘ውጉዝ ከመአርዮስ’ የሚያደርገው ትውልድ ያገኛል ማለት ነው፡፡
የምር አለ አይደል... የእኛ ሀገር ፖለቲካ ትልቁ ‘የጋራ ቋንቋ እኮ ትናንትን በተገኘው ሁሉ መቀጥቀጥ ነው፡፡
“አስመሳዩ ትውልድ ከሰፊ ሀገር ጠባብ ሆድ በመምረጡ...” የሚባል ክስ ቢመጣ መከላከል ያስቸግራል፡፡ የዚያ ዘመን ሰው፤ በሽ፣ በሽ መጽሀፍ ነው የሚያገኘው፡፡
‘አስመሳዩ ትውልድና እስከ ዛሬ ያልተነገሩት ምስጢሮቹ’
‘የአስመሳዩ ትውልድ ሴራ ዋጋ ያስከፈላት ሀገር’
‘የአስመሳዩ ትውልድ ዓለም አቀፍ ኔትወርክ —ከዋሽንግተን እሰከ ዌሊንግተን’
ምን አለፋችሁ.... የማይወጣ ርእስ አይኖርም። እናማ...አሁን በሆነ ባልሆነው የትናንቶቹንና የትናንቶች የምንላቸውን ትንፋሽ አሳጥተን ስንቀጠቅጥ ነግ በእኔ የሚለውን አባባል እናስታውስ፡፡
“የትናንት እናቶች ዶሮ ወጥ በአስራ ሁለት ቅመም ስለሠሩ እኛም መሥራት አለብን ማለት አይደለም፡፡ ኢት ኢዝ ሶ ፕሪሚቲቭ!” የምትል እንትናዬ በምናምን ሾው ላይ ብትቀርብ መገረም አያስፈልግም፡፡ በአሁኑ ጊዜ እዚቹ እኛ ሀገር ላይ ‘አስገራሚ’ የሚለው ቃል አገልግሎቱ ‘ኤክስፓየር’ ሊያደርግ ምንም ያህል አልቀረው፡፡
እናላችሁ... ከእግር ጥፍር እስከ ራስ ጸጉር እንደሚባለው አይነት...አለ አይደል...ማስመሰል የሌለበት ስፍራ ማግኘት አስቸጋሪ ነው፡፡ የምናስመስለውን ከመቶ ስንት ስንተኛ እንደሆንን ከማስላት ይልቅ የማያስመስሉትን ቁጥር ማስላቱ እጅግ በጣም ቀላሉ ሥራ ይሆናል። “ሁሉም ነገር አርቲፊሻል...” እንደሚባለው ነው። ደግሞ እኮ ብዙ ጊዜ ስናስመስል ‘እጅ ከፍንጅ’ እንደ መያዝ አይነት ፍጥጥ ነው፡፡
እሷዬ ለረጅም ጊዜ ሰላም ስትላችሁ የኖረችው ‘በቅንድቧ’ ነው፡፡ አለ አይደል... “ምን ፈለግህ?” አይነት የቅንድብ ሰቀላ፡፡ (‘ቅንድብ ሰቀላ’ የሚለውን ‘ፕሮግራማችሁ’ ውስጥ ማካተት ለምትፈልጉ የፈጠራ መብት ጥያቄ አላነሳም፡፡ በዚህ እንኳን፣ ‘ፈረንጅ’ እንደሚለው፤ ‘ፓርት ኦፍ ዘ ፖለቲካል ፐሮሰስ’ እንሁን እንጂ!) ታዲያላችሁ...የሆነ ቀን ከየት ዱብ አለች ሳትሏት፣ ብቻ ዱብ ትልና ዘላ ትጠመጠምባቸኋለች፡፡
“አንተ፣ እዚህ ሀገር አለህ! አንዴት እንደናፈቅኸኝ አታምንም፡፡” (ቅንድቦች አፍ ቢኖራቸው ኖሮ.... “ከትናንት ወዲያ እሱን ስታዪ ሰቅለሽን አልነበር እንዴ!” ባሉ ነበር!)
“እዚህ ላይ ነው ጨዋታው፣” የሚባለው ይሄኔ ነው፡፡ እንደው የዋህነታችሁ በዝቶ ወደ ሞኝነት የሚያስጠጋችሁ ከሆነ፣ ምን ይሆናል መሰላችሁ...“ስንትና ስንት ዘመን ምልክት ስሰጣት አልገባት ብሎ፣ በአስራ አንደኛው ሰዓት ሀንድሰምነቴ ተገለጠላት ማለት ነው! የሆነ ነገር አስባልኛለች...ማለት ነው...” ይባልና ምን ሆነ መሰላችሁ...“ሰውነቴ ላይ ጸጉር የተረፈኝ የት የት ቦታ ነው!” አይነት ምርምር ይጀመራል.፡፡ ‘ሲረፍድ’ እኮ መከራ ነው... (ቂ...ቂ...ቂ....)
ወንድም ዓለም.... ስማኝማ...አሰባልህ ሳይሆን አስባብህ ነው!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 1813 times