Saturday, 27 March 2021 14:13

32ኛው ኦሎምፒያድ ዓለም አቀፍ ተመልካች አይኖረውም

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

    1.8 ቢሊዮን ገቢ ያስቀራል፤ የጃፓን ኢኮኖሚን እሰከ 22 ቢሊዮን ዶላር ያሳጣል

            የቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ ኮቪድ-19 ወረርሽኝ በሚፈጥረው ስጋት ዓለም አቀፍ ተመልካቾች እንዳማይኖረው ተወስኗል፡፡ በታላቁ የስፖርት መድረክ ላይ ወረርሽኙን ለመቆጣጠር ሲባል በጃፓን የኦሊምፒኩ አዘጋጅ ኮሚቴ የተለያዩ አዳዲስ ደንቦችን ደሲወጡ ሰንብተዋል፡፡ በመጨረሻም  32ኛው ኦሎምፒያድ ዓለም አቀፍ ተመልካች እንዳያስተናግድ መወሰኑ ለስፖርቱ ዓለም ትልቅ ዱብ እዳ ሆኗል፡፡ በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ያጋጠመውን ይህ ሁኔታ ዓለም አቀፉ የኦሊምፒክ ኮሚቴና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን  እያስተቸ ሲሆን ለጃፓን ደግሞ ከፍተኛ ኪሳራ አስከትሎባታል፡፡
ባለፈው ሳምንት ላይ ውሳኔውን ለማሳለፍ አምስት የኦሊምፒኩ ባለድርሻ አካላት  በቪድዮ ኮንፍረንስ ስብሰባ አድርገዋል፡፡ ከዚያ በኋላ ባወጡት መግለጫ  የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሁኔታ በጃፓንና በሌላው ዓለም ክፍል ለውጥ አለማሳየቱን፤  በበርካታ አገራትም የተለያዩ  የጉዞ እገዳዎችን መደረጋቸውን በመጥቀስ ውሳኔውን ለማሳለፍ ተገደናል ብለዋል፡፡  ጃፓን ውስጥ በኮቪድ 19 የሞቱት ከ9ሺ በላይ  ሲሆን በአገሪቱ እስካሁን ክትባት መሰጠት አልተጀረም። አዘጋጆቹ ዓለም አቀፍ ተመልካቾችን ወደ ጃፓን ላለማስገባት ከመወሰናቸውም በላይ በኦሎምፒኩ ወቅት ካስቀመጧቸው ገደቦች መካከል ወደ ቶኪዮ የሚያቀኑ አገራት  ከአትሌቶች እና ከባለሙያዎች የልዑካናቸውን  ቁጥር እንዲቀንሱ፤ 72 ሰዓት ያለለፈው የኮቪድ-19 ምርመራ ውጤት እንዲይዙ እና በስፖርተኛ ፍቃድ ወደ ቶኪዮ መግባትን በጥብቅ መከልከላቸው ይገኙበታል፡፡
ዓለም አቀፍ ተመልካቾችን ከኦሎምፒክ መድረክ የሚያግደው ውሳኔ የተለያዩ ኪሳራዎችን ያስከትላል፡፡ የመጀመርያው በመላው ዓለም የሚገኙ ስፖርት አፍቃሪዎች በታላቁ የስፖርት መድረክ አለመገኘታቸው የውድድሩን ድባብ እንዳያቀዘቅዘው መሰጋቱ ነው፡፡   የዓለም አትሌቲክስ ፕሬዝዳንት ሴባስቲያን ኮው ዓለም አቀፍ ተመልካቾች በኦሎምፒኩ ላይ በተወሰነ ደረጃ መሳተፍ አለባቸው በሚል አቋማቸው የሚመለከታቸውን ተማፅነው ነበር። ውድድሮችን በሚያስተናግዱ ስታድዬሞችና የውድድር ስፍራዎች ላይ ተመልካቾች መገኘታቸው ሁሉም የኦሎምፒክ ባለድርሻ አካላት ስለሚፈልጉት ፍፁም ከመከልከል መፍትሄ እንፍጠር ብለው ተሟግተዋል።  በስፖርት ውድድር ስፍራዎች የኮቪድ 19 መቆጣጠርያ ደንቦችን ተግባራዊ በማድረግ የተሻለ ለውጥ የገለፁት ፕሬዝዳንቱ፤ በኦሎምፒክ መርህ ሁሉንም በማሳተፍ ታላቁን መድረክ ማድመቅ አለብን ሲሉም ተከራክረው ነበር።  በውሳኔው ምክንያት በ32ኛው ኦሎምፒያድ  ላይ አዘጋጅ ኮሚቴው እስከ 630ሺ እንዲሁም የጃፓን መንግስት እስከ 1 ሚሊዮን የውጭ ጎብኝዎችና የኦሎምፒክ እንግዶችን ለማስተናገድ የነበራቸው እቅድ ተበላሽቷል፡፡ ይህም ከ870 ሚሊዮን እስከ 1.8 ቢሊዮን ዶላር ገቢ እንደሚያሳጣ ነው የተዘገበው፡፡ ዘጃፓን ታይምስ ሰሞኑን ባወጣው ዘገባ ውሳኔው ከ3.6 ሚሊዮን በላይ ትኬቶችን እንዳይሸጡ የሚያደርግ ሲሆን በጃፓን ኢኮኖሚ በቀጣይ ዓመታት ሊንቀሳቀስ የሚችለውን እስከ 22 ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ መዋዕለንዋይ እንደሚያሳጣ አትቷል፡፡ በጃፓን ቱሪዝም ኢንዱስትሪ ላይ የተሰማሩ እና በታላቁ የስፖርት መድረክ ብዙ ገቢ ለማግኘት ሲሰሩ የቆየቱም በውሳኔው እየተማረሩ ናቸው፡፡  በ2019 እኤአ ላይ ጃፓን የዓለም የራግቢ ዋንጫን ካስተናገደች በኋላ የቱሪዝም ኢንዱስትሪዋ ከፍተኛ መነቃቃት አሳይቶ ነበር። በ2019 እኤአ ላይ ከ31.9 ሚሊዮን በላይ ዓለም አቀፍ ጎብኝዎችን መቀበሏ አዲስ ሪከርድ ሆኖ ሲመዘገብ  እስከ 2021 ከኦሎምፒክ ጋር በተያያዘ  የጎብኝዎቿን ብዛት በዓመት እስከ 40 ሚሊዮን እንደሚደርስም እቅድ ነበር፡፡  ዓለም አቀፍ ተመልካቾችን ላለማስገባት በመወሰኑ ግን በአጠቃላይ በቱሪዝም ኢንዱስትሪው ላይ ያልተጠበቀ ኪሳራ ያስከትላል፡፡
ለ32ኛው ኦሎምፒያድ ከጅምሩ 10 ሚሊዮን ትኬቶች ለሽያጭ የቀረቡ ሲሆን በመጀመርያ ዙር ከ600 ሺ በላይ የኦሎምፒክ ትኬቶች ለዓለም አቀፍ ተመልካቾች እንዲሁም ከ4.6 ሚሊዮን ለጃፓናውያን ተሸጠው ነበር፡፡ ከውሳኔው በኋላ አሎምፒኩን ለመታደም ትኬቶችን የገዙ ዓለም አቀፍ ተመልካቾች  ገንዘባቸው እንደሚመለስላቸው ቢገለፅም  የዓለም አቀፉ የስፖርት መድረክ  ተዓማኒነት እንደሚያጎድል ተሰግቷል፡፡ የጃፓን መንግስት በኦሎምፒኩ ዋና አዘጋጅ ከተማ ቶኪዮ ላይ ወረርሽኙን ለመቆጣጠር በሚወስዷቸው ርምጃዎች ከ960 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ ማድረጓን መረጃዎች ይጠቁማሉ።የቶኪዮ 2020 ኦሎምፒክ በ16 ወራት መራዘሙ የዝግጅት ወጭውን በ2.8 ቢሊዮን ዶላር የጨመረው ሲሆን በአጠቃላይ  25 ቢሊዮን ዶላር በማስወጣት የምንግዜም ውዱ ኦሎምፒክ ሊሆን በቅቷል፡፡ የጃፓን ህዝብ 6.7 ቢሊዮን ዶላር እንዲሁም የጃፓን ትልልቅ ኩባንያዎችም  ለዝግጅቱ እስከ 3.5 ቢሊዮን ዶላር አፍስሰዋል፡፡

Read 762 times