Saturday, 03 April 2021 18:14

በዚህ ሳምንት ብቻ ከ14 ሺህ በላይ ሰዎች በኮረና ተይዘዋል

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(0 votes)

 • 147 ሰዎች በአንድ ሳምንት ውስጥ በበሽታው ህይወታቸው አልፏል
          • የሃይማኖት ተቋማት ወደ ቀደመው የመከላከል ሳራቸው እንዲመለሱ ጥሪ ቀርቧል፡፡
             
            የኮቪድ 19 ወረርሺኝ በከፍተኛ መጠን እየጨመረ የመጣ ሲሆን በአንድ ሳምንት ብቻ 14ሺ በላይ ሰዎች በበሽታው መያዛቸው ሲረጋገጥ፤147 ሰዎች ደግሞ በበሽታው ሳቢያ ህይወታቸው ማለፉን የህብረተሰብ ጤና እንስቲቲዩት መረጃ ያመለክታል፡፡
ከመጋቢት 17 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ትናንት ድረስ ለ55 ሺ 748 ሰዎች በተደረገ የላብራቶሪ ምርመራ 14014 ሰዎች በበሽታው መያዛቸው መረጋገጡን ያመለከተው የኢንስቲቲዪቱ መረጃ፤ ሲዳማ  ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች የተገኘበት ክልል ሆኖ ተጠቅሷል- 55.9 በመቶ በመያዝ ኦሮሚያ በ35.5 በመቶ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ሲጋዝ፤ ሶማሊያ በ34.8 በመቶ የ3ኛ ደረጃነት ይዟል አዲስ አበባ ከተማ ደግሞ የስርጭቱ መጠን 24.9 በመቶ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ በሳምንቱ ውስጥ 7519 ሰዎች ከበሽታው ያገገሙ ሲሆን ይህም እስካሁን ከበሽታው ያገገሙ ሰዎች ቁጥር 158.109 ያደርሰዋል፡፡ 865 ሰዎች በፅኑ ህሙማን ክፍል እንደሚገኙም መረጃው አመልክቷል፡፡
የበሽታውን መስፋፋት ተከትሎ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሀን ምክር ቤት ባወጣው መግለጫ፤ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች የአገሪቱ ወቅታዊ ስጋት የሆነውን የኮቪድ-19 በሽታ ለመከላከል ግንዛቤ የመፍጠር ስራቸውን አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ብሏል፡፡
ም/ቤቱ አክሎም እንደገለፀው፤ መገናኛ ብዙሃን የሚያመለክቷቸው አካላት የሚያወጧቸውን መረጃዎች ለህብረተሰቡ በፍጥነት በመግለፅ ህብረተሰቡ ራሱን ከበሽታው ለመከላከል እንዲችል ግንዛቤ የመፍጠር  ስራን አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ገልጿል፡፡ ህብረተሰቡ ስለ በሽታው በቂ ግንዛቤ እንዲኖረው ለማድረግ የሚያስችል የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ቋሚ ሎጎ በማድረግ ህብረተሰቡ ትኩረት እንዲሰጥ ማድረግ፣ኮቪድ-19ና ጤና ነክ መረጃዎችን ራሱን በቻለ መልኩ ተለይቶ ዜና ኮቪድ ተብሎ እንዲቀርብ፣ በዜና መግቢያና መውጫ ሰዓቶች ላይ የኮቪድ-19 መልዕክቶችን ማቅረብ፣የጋዜጣና መፅሄት ህትመቶችንና ሎጎዎችን  በማተም ህይወት ማዳን የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል፡፡
የሃይማኖት ተቋማት ህብረት በበኩሉ የበሽታውን ስርጭት መስፋፋት ለመከላከል የሃይማኖት  ተቋማት ወደ ቀደመው የመከላከል ስራቸው እንዲመለሱ ጥሪ አቅርቧል፡፡

Read 1004 times