Saturday, 03 April 2021 18:26

ዋልያዎቹ ለአፍሪካ ዋንጫ ካለፉ በኋላ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(1 Vote)

 • የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር 5.6 ሚሊዮን ብር ሸልሟል
        • በ16 ወራት ውስጥ 30 ተጨዋቾች በዋልያዎቹ አሰላለፍ ላይ ተፈራርቀዋል
        • ኢትዮጵያ በአፍሪካ ዋንጫ መስራችነቷ ሁሌ በውድድሩ መገኘት አለባት ጌታሁን ከበደ ለሶከር ኢትዮጵያ
        • ባለፉት 10 የአፍሪካ ዋንጫዎች ኢትዮጵያ ባስመዘገበችው ውጤት 11ኛ ናት
        • የምድብ ድልድሉ ግንቦት መጨረሻ ላይ ይታወቃል
        • የአፍሪካ እግር ኳስን ወደትርፋማነቱ እመልሳለሁ ቢሊዬነሩ የካፍ ፕሬዝዳንት ፓትሪስ ሞትሶፔ


          የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከ6 ወራት በኋላ ካሜሮን ለምታዘጋጀው 33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ማለፉን ካረጋገጠ በኋላ አነጋጋሪ ሆኗል፡፡ ዋልያዎቹ በሳምንቱ አጋማሽ ላይ ወደ ኢትዮጵያ ሲመለሱ ደማቅ አቀባበል የተደረገላቸው ሲሆን በአዲስ አበባ ዋና ዋና ጎዳናዎች በክፍት የድል መኪናዎች በመዘዋወር ከህዝቡ ጋር ደስታቸውን ገልፀዋል፡፡ በዋልያዎቹ አስደናቂ ጥረት ኢትዮጵያ በታሪክ ለ11ኛ ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎን ያገኘች ሲሆን አራት አፍሪካ ዋንጫዎች ካመለጧት በኋላ ወደ አህጉራዊው መድረክ መመለሷ ነው፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለኢትዮጵያ ወንዶች ብሔራዊ እግር ኳስ ቡድን (ዋልያዎቹ) 5 ነጥብ 6 ሚሊየን ብር የማበረታቻ ሽልማት በማበርከት ቀዳሚው ሆኗል፡፡ የከተማው መስተዳደር ብሄራዊ ቡድኑ በአንድነት ተደምሮ ላስመዘገበው ውጤት እጅግ የላቀ ክብርና አድናቆት እንዳለው ምክትል ከንቲባ አዳነች አበቤ ሲገልፁ በጥረታችሁ ታሪክ ለማስመዝገብ በመብቃታቹህ፤ ለሃገራችሁ የተለየ የመነቃቃት ስሜት ፈጥራችኋል ብለዋል። የዋልያዎቹ ስኬት ታሪካዊ እና ትውልድን የሚያነቃቃ ለማድረግ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት አስፈላጊውን ሽልማት መስጠት የሚያስፈልግ ሲሆን ማበረታቻዎች ለብሄራዊ ቡድኑ ተጫዋቾች ብቻ ሳይሆን፣ አመራሮች፣ አሰልጣኞች፣ ተጠባባቂዎች፣ ወጌሻዎች፣ የህክምና ባለሙያዎች፣ አማካሪዎች፣ ደጋፊዎች  እና ሌሎች የቡድኑ አባላትም ላይ ማተኮር አለባቸው፡፡  በ2013 እኤአ ላይ የኢትዮጵያ ብሄራዊቡድን ከ31 ዓመታት በኋላ ወደ አፍሪካ ዋንጫ መመለሱን ተከትሎ ቡድኑ አባላት ዋና አሰልጣኝ በከፍተኛ የገንዘብ እና የስጦታ ሽልማቶች የተንበሸበሹ ሲሆን በወቅቱ እያንዳንዱ ዋልያ ቢያንስ ከ300ሺ ብር ጀምሮ እንዳገኘ ይታወሳል፡፡
በ16 ወራት ውስጥ 30 ተጨዋቾች በዋልያዎቹ አሰላለፍ ላይ ተፈራርቀዋል
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ዋንጫ  መስራችነቷ ሁሌ በውድድሩ መገኘት አለባት
ጌታሁን ከበደ ለሶከር ኢትዮጵያ
ዋልያዎቹ ባገኙት ስኬት ላይ አዲሱ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ጀግና ዋና አሰልጣኝ ውበቱ አባተና የብሄራዊ ቡድኑ አምበልና የምንግዜም ከፍተኛ ግብ አግቢ ጌታነህ ከበደ  ማንሳት ይገባል፡፡ የ33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ ባለፉት ስምንት ዓመታት ሲያሽቆለቁል የቆየውን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ደረጃን በከፍተኛ ደረጃ የሚያሻሽለው ነው፡፡ በወቅታዊው የዓለም እግር ኳስ ማህበር ፊፋ ወርሃዊ የእግር ኳስ ደረጃላይ ኢትዮጵያ  ከአፍሪካ 44ኛ ከዓለም 150ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡ ዋና አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ብሄራዊ ቡድኑ ወደ አፍሪካ ዋንጫ እንዲመለስ ባደረጉት ጥረት ከፍተኛ ምስጋና እያገኙ ሲሆኑ መላው ኢትዮጵያውያንን በአንድነት የሚያስተሳስር ድል በመመዝገቡ ተደስቻለሁ ብለዋል፡፡ ወደ 33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ  ባለፉት 16 ወራት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ባደረጋቸው 6 የምድብ ማጣሪያ  ጨዋታዎች ላይ ከ30 በላይ ዋልያዎች በተለያዩ የጨዋታ ስፍራዎች ተፈራርቀዋል፡፡ ጌታነህ ከበደ 3 ግቦችን፤ ሽመልስ በቀለና አማኑኤል ገብረሚካኤል ሁለት ሁለት ጎሎች እንዲሁም ሱራፌል ዳኛው፤ መስዑድ መሃመድና አቡበከር ናስር አንድ አንድ ጎሎች በማጣርያው ለኢትዮጵያ አስቆጥረዋል፡፡ ተክለማርያም ሻንቆ ኢትዮጵያ ቡና፣ አቤል ማሞ እና ምንተስኖት አሎ ሶስቱ ግብ ጠባቂዎች ናቸው።  አስቻለው ታመነ፤ ረመዳን የሱፍ፤ ያሬድ ባየ፤ ሱሌማን ሀሚድ፤ አህመድ ረሺድ፤ አሥራት ቱንጆ፤ አንተነህ ተስፋዬ እና ደስታ ደሙ በተከላካይ መስመር የተሰለፉ 8 ተጫዋቾች ሲሆኑ በአማካይ መስመር ላይ የተሰለፉት አስራ ሦስት ተጫዋቾች ደግሞ  ሽመልስ በቀለ፤ ሱራፌል ዳኛቸው፤ ይሁን እንደሻው፤ አማኑኤል ዮሐንስ፤ መስዑድ መሐመድ፤ ሀብታሙ ተከስተ፤ ታፈሰ ሰለሞን፤ ጋቶች ፓኖም፤ ሽመክት ጉግሳ፤ ሀይደር ሸረፋ፤ ከነዓን ማርክነህ፤ ጋዲሳ መብራቴ እንዲሁም ፍፁም ዓለሙ ናቸው፡፡ የቡድኑን ስድስት አጥቂዎች ደግሞ አቡበከር ናስር፤ አማኑኤል ገብረሚካኤል፤ ጌታነህ ከበደ፤ አዲስ ግደይ፤ መስፍን ታፈሰ እና ሙጂብ ቃሲም  ነበሩ፡፡
ጌታነህ ከበደ ብሄራዊ ቡድኑ ወደ አዲስ አበባ ከተመለሰ በኋላ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ባደረገው ቃለምልልስ “ወደ አፍሪካ ዋንጫ ማለፋችን ብዙ ፋይዳ ይኖረዋል። ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫን እንደ መስራችነቷ ሁሌ በውድድሩ መገኘት አለባት። ይህንን ደግሞ ለማድረግ አቅሙ አለን። በተለይ አሁን እየመጡ ያሉት ተጫዋቾች በጣም ጥሩ ጥሩ ናቸው። ዘንድሮ ደግሞ ሊጉ በዲኤስ ቲቪ መተላለፉ የጠቀመን ይመስለኛል። ስለዚህ የዘንድሮውን ማሳያ ይዘን በቀጣይ ረጅም ዓመታት ከውድድሩ ላለመራቅ እና ቋሚ ተሳታፊ ለመሆን መስራት አለብን።” የሚል አስተያየት ሰጥቷል፡፡
28ኛ ዓመቱ ላይ የሚገኘው ጌታነህ ከበደ ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በተሰለፈባቸው 55 ጨዋታዎች 30 ግቦችን በማስመዝገብ የምንግዜም ከፍተኛ ግብ አግቢ ሆኗል፡፡ የመጀመርያ ጎሉን ከ10 ዓመታት በፊት በዓለም ዋንጫ ማጣርያ ሶማሊያ ላይ ያስቆጠረ ሲሆን ታንዛኒያ፤ ሱዳን፤ ኒጀር፤ ደቡብ አፍሪካ፤ ማላዊ፤ ማሊ፤ ኮንጎ፤ አልጄርያ፤ ሌሶቶ፤ ሲሸልስ፤ ጅቡቲ፤ ብሩንዲ፤ ሴራሊዮን፤ ዛምቢያ፤ ማዳጋስካርና አይቬሪኮስት በሴካፋ ዋና ውድድር፤ በዓለም ዋንጫ እና በአፍሪካ ዋንጫ የማጣርያ ጨዋታዎች የጌታነህ ከበደን ጎል አስተናግደዋል፡፡
ባለፉት 10 የአፍሪካ ዋንጫዎች ኢትዮጵያ ባስመዘገበችው ውጤት 11ኛ ናት
ካሜሮን በምታዘጋጀው 33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ኢትዮጵያ በውድድሩ ታሪክ ለ11ኛ ጊዜ የምትሳተፍበት ነው፡፡ በ10 የአፍሪካ ዋንጫዎች ላይ በመሳተፍ ባስመዘገበችው ውጤት  ደግሞ 11ኛ ደረጃ ላይ ናት፡፡ ከፍተኛ ውጤቶቿም 1962 እኤአ ላይ ሻምፒዮን ከመሆኗ ባሻገር፤ በ1957 እኤአ ሁለተኛ፤ በ1959 እኤአ ሶስተኛ እንዲሁም በ1963 ና 1968 እኤአ ለሁለት ጊዜያት በአራተኛ ደረጃ በማጠናቀቋ ነው፡፡ በአጠቃላይ በ10 የአፍሪካ ዋንጫዎች ላይ ስትሳተፍ 27 ጨዋታዎችን አድርጋለች። 7 ድሎችን ያስመዘገበች ሲሆን፤ በ3 አቻ ወጥታ በ17 ጨዋታዎች ተሸንፋለች፡፡ 21 ጎሎች በተጋጣሚዎች መረብ ላይ ስታሳርፍ 62 ጎሎች ተቆጥሮባታል፡፡   
የምድብ ድልድሉ ግንቦት መጨረሻ ላይ ይታወቃል
ከምድብ ማጣርያ የመጨረሻ ጨዋታዎች በኋላ ለ33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በተደረጉ 6 ዙር የምድብ ማጣርያዎች 150 ጨዋታዎች ተደርገው 334 ጎሎች ከመረብ አርፈዋል፡፡ ወደ አፍሪካ ዋንጫው ያለፉት 23 አገራት የታወቁ ሲሆን 24ኛው ብሄራዊ ቡድን  ቤኒን ከሴራሊዮን ጋር በሚያደርጉት ተስተካካይ ጨዋታ ይወሰናል። ለ33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ድልድል ከ2 ወራት በኋላ የሚወጣ ሲሆን ካሜሮን  ለ20ኛ፤ ሴኔጋል ለ16ኛ፤ አልጄርያ ለ19ኛ፤ ማሊ ለ12ኛ፤ ቱኒዚያ ለ20ኛ፤ ቡርኪናፋሶ ለ12ኛ፤ ጊኒ ለ13ኛ፤ ጋቦን ለ8ኛ፤ ግብፅ ለ25ኛ፤ ጋና ለ23ኛ፤ ኢኳቶርያል ጊኒ ለ3ኛ፤ ዚምባቡዌ ለ5ኛ፤ አይቬሪኮስት ለ24ኛ፤ ሞሮኮ ለ18ኛ፤ ናይጄርያ ለ19ኛ፤ ሱዳን ለ9ኛ፤ ማላዊ ለ3ኛ፤ ጊኒ ቢሳዎ ለ3ኛ፤ ኬፕቨርዴ ለ3ኛ፤ ኢትዮጵያ ለ11ኛ እንዲሁም ጋምቢያ  ለመጀመርያ ጊዜ በአፍሪካ ዋንጫ የሚሳተፉ ይሆናል፡፡
የአፍሪካ እግር ኳስን ወደትርፋማነቱ እመልሳለሁ
ቢሊዬነሩ ፓትሪስ ሞትሶፔ
ደቡብ አፍሪካዊው ቢሊየነር፤ የንግድ ሰው እና የህግ ባለሙያ ፓትሪስ ሞትሴፔ ከሁለት ሳምንት በፊት የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን ፕሬዝዳንት ሆነዋል፡፡ በታሪክ 8ኛው የካፍ ፕሬዝዳንት ሲሆኑ የአህጉሪቱ የእግር ኳስ የበላይ አካል የ64 ዓመታት ታሪክ እንግሊዘኛ ተናጋሪ ሲሾም  የመጀመርያው ነው። ፓትሪስ ሞትሶፔ በሞሮኮ ራባት በተካሄደው 43 ኛው የካፍ ኮንግረስ ላይ በፕሬዝዳንትነት ከተሾሙ በኋላ የአፍሪካን እግር ኳስ በዓለም አቀፍ ደረጃ መነጋገርያ ሆኗል፡፡ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽንን በተሻሻለ አሰራር እና የአመራር መዋቅር በመመራት በአጭር ጊዜ ውስጥ ለውጥ እንደሚያመጣ ብዙዎች ተስፋ አድርገዋል፡፡ የፊፋ ፕሬዝዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ በኮንፌደሬሽኑ የተካሄደውን ምርጫ ሙሉ በሙሉ የደገፉት ሲሆን የዓለም አቀፉ እግር ኳስ ማህበር ጣልቃ ገብቷል ብለው አንዳንድ የአፍሪካ ሚዲያዎች ተችተዋል፡፡
አዲሱ የካፍ ፕሬዝዳንት ሹመታቸውን ባገኙበት ወቅት ባሰሙት ንግግር ‹‹አፍሪካ በጋራ ጥበብ ልትሰራ ይገባል፣ ለዚህም እያንዳንዱ አባል አገር እና የእግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት የላቀ አስተዋፅኦና አገልግሎት ማበርከት ይኖርበታል፡፡ ሁላችን በጋራ ስንሠራ በአፍሪካ እግር ኳስ ከመቼውም ጊዜ የላቀ  ስኬት እና እድገት ያጋጥመናል›› ብለዋል።
በሙሉ ስማቸው ዶክተር ፓትሪስ ትልሆፔን ሞትሴፔ ተብለው የሚጠሩ የ59 ዓመቱ ቢሊዬነር
የደቡብ አፍሪካውን ክለብ ሜመመሎዲ ሰንዳውንስ በባለቤት ከያዙ በኋላ ባለፉት 15 ዓመታት በአፍሪካ እና በደቡብ አፍሪካ እግር ኳስ ላይ ልዩ ልምድ ሲያካብቱ የቆዩ ናቸው። አፍሪካን ፈሬንቦው ሚኒራልስ በተባለ ኩባንያቸው በደቡብ አፍሪካ የማዕድን ኢንዱስትሪ በመሰማራት የመጀመርያው ጥቁር አፍሪካዊ ቢሊዬነር ለመሆን ሲበቁ የማዕድን ኩባንያቸው ከዓለም 12ኛ ደረጃ ላይ የሚጠቀስ ነው፡፡
ቢሊዬነሩ ፓትሪስ የአፍሪከ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽንን የተረከቡት በሙስና ክስ ተመስርቶባቸው ካሃላፊነት የተነሱትን የማላጋሲው አህመድ አህመድ በመተካት ነው።   በ2017 እኤአ ላይ በአዲስ አበባ በተካሄደ የካፍ ጉባኤ አህመድ ሲመረጡ ለ29 ዓመታት በካፍ ፕሬዝዳንትነት የቆዩትን ካሜሮናዊው ኢሳ ሃያቱ በመተካት ነበር፡፡ አህመድ አህመድ በካፍ ፕሬዝዳንትነት ሲሰሩ ቆይተው የስራ ዘመናቸው ሊያበቃ 1 ዓመት ሲቀር በፊፋ የስነምግባር ኮሚቴ ተከስሰው ከማንኛውም የእግር ኳስ እንቅስቃሴ ታግደው ቆይተዋል፡፡ ዓለም አቀፉ የስፖርት ክርክሮች ገላጋይ ፍርድ ቤት በማዳጋስካራዊው አህመድ ላይ ፊፋ ያስተላለፈውን ቅጣት በሁለት ዓመት ዓመት እና በ53440 ዶላር እንዲወሰን አድርጓል፡፡ ከፓትሪስ፤ አህመድ እና ሃያቱ በፊት ከ1957 እስከ 1958 ግብፃዊው አብድል አዚዝ አብደላህ ሳሌም የመጀመርያው ፕሬዝዳንት ሲሆኑ፤ ከ1958 እስከ 1968 እኤአ ግብፃዊው አብድል አዚዝ ሙስተፋ፤ ከ1968 እስከ 1972 እኤአ ሱዳናዊው አብደል ሃሊም ሞሃመድ፤ ከ197 እስከ 1987 እኤአ ኢትዮጵያዊው ይድነቃቸው ተሰማ እና ከ1987 እስከ 1988 እኤአ ሱዳናዊው አብድል ሃሊም ሞሃመድ  አገልግለዋል፡፡
የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን ከአህመድ በኋላ የተጋፈጣቸውን ብዙ ችግሮች ለመፍታት ቢሊዬነሩ ይጠበቃሉ፡፡  በተለይ ከ2 ዓመታት በፊት ተቀማጭነቱን በፈረንሳይ ካደረገው ላጋርዴ ስፖርት ኩባንያ ጋር በቴሌቭዥን ብሮድካስትና በማርኬቲንግ ለመስራት የነበረው ውል በመፍረሱ ኮንፌደሬሽኑን ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ ከቶታል፡፡ ካፍ ከፈረንሳዩ የብሮድካስት ኩባንያ ጋር አድርጎት የነበረው ስምምንት ከ2017 እኤአ ጀምሮ  ለ12 ዓመታት የሚቆይና እስከ 1 ቢሊዮን ዶላር የሚያስገኝ ነበር፡፡ ስፖርት ላጋርዴ በመጀመርያ ዓመቱ ከተለያዩ የንግድ አጋሮች እስከ 250 ሚሊዮን ዶላር ለአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን ማስገኘትም ችሎ ነበር፡፡
ከፈረንሳዩ ኩባንያ የነበረው ውል በአስተዳደር ችግር ሲፈርስ ካፍ በዓመት ሊያገኝ የሚችለውን እስከ  200 ሚሊዮን ዶላር አሳጥቷል፡፡ የአህጉራዊ ተቋም ዓመታዊ በጀት ከ136 ሚሊዮን ዶላር ወደ 103  ሚሊዮን ዶላር የወረደ ሲሆን፤ ባለፉት ሁለት የውድድር ዘመናት ላይ የካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ እና ኮንፌደሬሽን ካፕ፤ የአፍሪካ ዋንጫ እና የዓለም ዋንጫ ማጣርያዎች በቂ የስርጭት ሽፋን ሳያገኙ ቀርተዋል፡፡
 በማርኬቲንግ በብሮድካስት እና በውድድድር አስተዳደር ላይ  በከባባድ ችግሮች የተወጠረው ኮንፌደሬሽኑ  ከዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ጋር የሚሰራበትን እድል ማጣቱ መጭውን 33ኛው አፍሪካ ዋንጫ የሚያሳስብ ሆኗል። አዲሱ ፕሬዝዳንት በካፍ አገራት የሚካሄዱ አህጉራዊ የክለቦች ውድድሮች፤ የአፍሪካ ዋንጫ እና የዓለም ዋንጫ ማጣርያዎች ወደ ቴሌቭዥን ስርጭት እንዲመለሱ ከፍተኛ ስራ ሲጠበቅባቸው ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ለአፍሪካ እግር ኳስ ትኩረት እንዲሰጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ስልጣናቸውን ከተረከቡ በኋላ የአፍሪካ ዋንጫ በየአራት ዓመቱ ይካሄድ የሚለውን የፊፋ እቅድ በመሰረዝ በየሁለት ዓመቱ እንደነበር ይቀጥል የሚል ውሳኔ ያሳለፉት ፓትሪስ ሞትሶፔ፤ ካፍ 80 በመቶ ገቢውን ከአፍሪካ ዋንጫ ያገኝ እንደነበር በመጥቀስ የአህጉሪቱ ትልቅ እግር ኳስ ውድድርን ወደ ትርፋማነቱ ለመመለስ  አዳዲስ የንግድ አጋሮች እየፈጠርን ነው ብለዋል፡፡


Read 818 times