Saturday, 03 April 2021 18:29

የታዳጊዎች ወሲባዊና የስነ ተዋልዶ ጤና፡፡

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(1 Vote)

 አንዳንድ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ብዙ ታዳጊዎች በልማድና በአንዳንድ የህይወት ገጠመ ኛቸው አግባብነት በሌለው መንገድ እንደሚገለጹ እና ከጾታ እና ከእድሜአቸውም ጋር በተያያዘ በአሉበት ወቅትም ይሁን በወደፊት ህይወታቸው የሚጎዳቸው ነገር እንደሚገጥማቸው ግልጽ ነው፡፡ በእድሜም ይሁን በጾታ አማካኝነት የሚደርስባቸው ችግር በትምህርት ቤት፤ በቤት ውስጥ ወይንም በህብረተሰብ ውስጥ ሊሆን ይችላል፡፡ ለዚህ እትም የበቃው መረጃ የተገኘው March 11, 2019 ከወጣው ከSAGE Journal ነው፡፡ ጥናት የተደረገው በኢትዮጵያና በሩዋንዳ ሲሆን በኢትዮጵያ በአፋር፤ በኦሮሚያ ምእራብ ሐረርጌ እና በአማራ በደቡብ ጎንደር ነው፡፡ በሩዋንዳም ሶስት የተለያዩ ቦታዎች ላይ ጥናቱ አትኩሮአል፡፡
ታዳጊ የሚባለው እድሜ ከህጻንነት ወደ ወጣትነት የሚሸጋገሩበት እድሜ ሲሆን እንደ የአለም የጤና ድርጅት አገላለጽ በእድሜያቸው ከ10-19 አመት ድረስ ያሉ ናቸው፡፡ ይህ ጥናትም በኢትዮጵያ የተመለከተው በእድሜያቸው ዝቅ ያሉትን (10-12)መካከለኛ የሚባሉትን ደግሞ (13-15) ከፍ ያሉት ደግሞ (16-19) የሚሆናቸው ሴት እና ወንድ ልጆች ናቸው፡፡   
መረጃው እንደሚያሳየው ይህ የታዳጊዎችን ጾታዊ እና የስነ ተዋልዶ ጤና ሁኔታ የዳሰሰው ጥናት የተመለከተው በኢትዮጵያና እና በሩዋንዳ በሁለቱም አገራት ወንድ ልጆችና ሴት ልጆች በጾታ ወይንም በእድሜ ምክንያት የስነተዋልዶ ጤናቸው እንዴት እንደሚጎዳና በዚህም ምክን ያት የሚደርስባቸውን አካላዊም ይሁን ስነልቡናዊ ጤንነት እንዲሁም ጾታን መሰረት ባደረገ መልኩ የሚደርስባቸው ችግር ከምን አንጻር ነው የሚለውን ነው፡፡ ለመጥቀስ ያህልም ሴት ወጣቶች ፤ በወር አበባ ምክንያት፤ ያልተፈለገ እርግዝናን መከላከያ ስለመውሰድ፤ ስለ እርግዝና፤ ያልተፈለገ እርግዝና እና ጽንስን ስለማቋረጥ፤ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች እና ኤችአይቪን ጨምሮ የስነተዋልዶ ጤናቸውን ለሚጎዱ ነገሮች ይጋለጣሉ፡፡
ይህ በኢትዮጵያ እና በሩዋንዳ የተደረገ ጥናት እንደሚያሳየው የታዳጊዎች ወሲባዊ እና የስነ ተዋልዶ ጤና እና ደህንነታቸው በእድሜአቸው 15 አመት በሚሆኑ ታዳጊዎች ላይ በጣም ውስንነት አለው። በአካባቢያቸው ያለው ልማድ እና ባህል ያገቡ ወጣቶች በፍጥነት ልጅ እንዲወልዱ የሚያበረታታ ሲሆን ጋብቻ ያልፈጸሙ ሴት ልጆች ደግሞ ያልተፈለገ እርግዝና መከላከያ እንዲወስዱ አይበረታቱም። ልማድና ባህሉ የሴት ልጆችን ሞራል የሚነካ እና የሚያናንቅ ነገር ስላለው ሴት ልጆች ያልተፈለገ የእርግዝና መከላከያን እንደሚፈልጉ ለማሳወቅ ወይንም ለመጠየቅ  እንዳይችሉ ያደርጋቸዋል፡፡
ከላይ በተጠቀሱት እና በሌሎችም ምክንያቶች በወጣትነት እድሜ እርግዝና መከሰቱ እውን ነው። በኢትዮጵያ እድሜአቸው 19 አመት የሚሆኑ ልጃገረዶች ወደ (34%) የሚሆኑት ያልተፈለገ እርግዝና የገጠማቸው ሲሆን በእድሜአቸው ከ15-24 የሚደርሱት እኩዮቻቸው ከሆኑት ወንዶች ይልቅ በአምስት እጥፍ ለኤችአይቪ ተጋልጠዋል፡፡ በሩዋንዳም ሆነ በኢትዮጵያ ወሲባዊ ጥቃት ሪፖርት ካለመደረጉም በላይ ወጣት ሴት ልጆች በከፋ ሁኔታ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች (ግርዛት፤ የልጅነት ጋብቻ…) ለመሳሰሉት ይጋለጣሉ፡፡
በኢትዮጵያ እ.ኤ.አ ከ2000 አንስቶ በአገሪቱ በጠቅላላ የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም እንዲዝረጋና የጤና ባለሙያዎች ቤት ለቤት በሚባል ደረጃ ነጻ የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት እንዲሰጡ የሚያስችል አሰራርን በገጠሩና እጅግ እሩቅ ከሚባሉ መኖሪያ አካባቢዎች ተግባራዊ አድርጎአል፡፡ በዚህ ፕሮግራሙም ታዳጊዎችን የሚያካትት አሰራር ተቀዳሚ ቦታን ይዞአል፡፡ ከዚህ በመቀ ጠልም እ.ኤ.አ በ2007 ብሔራዊ የታዳጊዎችና የወጣቶች የስነተዋልዶ ጤና አገልግሎት እቅድ የወጣ ሲሆን ይህም ለታዳጊዎቹ እና ለወጣቶቹ ጥራት እና ተገቢ የሆነ የስነተዋልዶ ጤንነት አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል አሰራርን ያካተተ ነው፡፡ ይህ ጥረት የስነተዋልዶ ጤናን፤ የእናቶችን፤ የጨቅላ ሕጻናትን እና የህጻናትን ጤንነት ደህንነትን በማረጋገጥ ረገድ አሁን ለተደረሰበት ውጤት ያበቃ መሆኑ እሙን ነው። የኢትዮጵያ መንግስት በዚህ ረገድ ያለውን ትኩረት በማስፋት በፈቃደንነት እና ኃላፊነት በሚሰማው መንገድ እንዲሰራ ሁኔታዎችን በማመቻቸቱ ለወጣቶቹ ምቹ በሆነ መንገድ በመላው ሀገሪቱ አገልግሎቱን በማስፋት በአለም አቀፍ ደረጃ ቃል የተገባለትን (FP2020) ውጤት ላይ ለማድረስ ቃል የገባበት እና ስራውን በተደራጀ መንገድ እየሰራ መሆኑ ይስተዋላል፡፡ በእርግጥ ተግባራዊ በማድረጉ ረገድ አንዳንድ ችግሮች በተለይም ታዳጊዎቹ የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት በእኩል ማግኘታቸው እና ሌሎች ወሲባዊ እና የስነተዋልዶ ጤናን በሚመለከት ሊያገኙ የሚገባቸውን ያህል መረጃ አለማግኘታቸው እንዲሁም ሊሰጣቸው የሚገባውን አገልግሎት እና ትኩረት ማግኘታቸውን ለማረጋገጥ የሚያስችለው ማህበራዊ አወቃቀር እና አሰራር ችግር ያለበት መሆኑ ተጠቃሽ ይሆናል፡፡   
ሁለቱም ማለትም ወንዶች እና ሴት ልጆች በሩዋንዳም ይሁን በኢትዮጵያ ተደራራቢ በስነተዋልዶ በኩል ችግሮች የሚገጥሙዋቸው ሲሆን በተለይም ታዳጊነት ንና በዚያም ምክንያት ሊከሰት የሚችለውን ተፈጥ ሮአዊ ሁኔታ (አካላዊ፤ ማህበራዊ፤ ኢኮኖሚያዊ፤ ትምህርት) ለማወቅ የሚያስችለውን መረጃ አለማግኘታቸው ዋናው ነው። በተለይም በገጠሩ አካባቢ የሚኖሩ ብዙ ልጃገረዶች የወር አበባቸው በሚመጣበት ወቅት ምን ማድረግ እንደሚገባቸው ካለማወቃቸው በተጨማሪ ተፈጥሮአዊ ምንነቱን እንኩዋን ለማወቅ ይቸገራሉ። አንዳንድ አካባቢዎች በተለይም በትምህርት ቤት በወር አበባ ምክንያት የሚደረጉ ውይይቶች እንኩዋን ቢኖሩ እንደመቀለጃ የሚቆጠሩበት ሁኔታ አለ። አልፎ አልፎ ወንዶች በሚገናኙባቸው ክለቦች ውስጥ ስለ የወር አበባ የሚነሳበት አጋጣሚ መኖሩ እና ይህም በባህል ውስጥ ያለውን ዝምታ የሚሰብር እንዲሁም በግልጽ ስለ ወሲባዊ ሁኔታዎች ለማወቅ የሚረዳ በመሆኑ ይበረታታል፡፡
በዚህ ጥናት የተገኘው ውጤት እንደሚያሳየው ታዳጊ ወጣቶች በስነተዋልዶ ጤና እና ጾታዊ እድገታቸው ዙሪያ ባሉት ተፈጥሮአዊ ሁኔታዎች ግራ መጋባት እና መገለል እንዳይደርስባቸው የሚያደርጉ የህብረተሰብ ልማዳዊ እና ባህላዊ ተጽእኖዎች ይኖራሉ፡፡  በዚህም ምክን ያት  ለአንዳንድ ልጃገረዶች በድንገት ወደ ወጣትነት እና እድሜያቸው ሳይደርስ ትዳር ወደመያዝ ብሎም እናት ወደመሆን እንዲያመሩ ያደርጋቸዋል፡፡
ታዳጊ ሴት ልጆች በተለይ ወሲባዊ እና የስነተዋልዶ ጤናን በሚመለከት ተፈጥሮአዊ ሂደቱ ንና እድገቱን ማለትም ከወር አበባ ጀምሮ እስከ ግርዛት፤ በትዳር ጉዳይ እድሜን እና ማንን ለማግባት እፈልጋለሁ የሚለውን፤ ያልተፈለገ እርግዝና መከላከያ ስለመውሰድ፤ ጽንስ ማቋረጥ የመሳሰሉትን በሚመለከት በከፍተኛ ሁኔታ ለማወቅና ለመስማማት የሚያስችላቸውን አቅማቸውን ማጎልበት እንዳለባቸው መረጃው ይጠቁማል፡፡
በብሔራዊ ደረጃ ፖሊሲዎች እና አደረጃጀቶች ታዳጊ ወጣቶችን ለመደገፍ የተዘጋጁ ቢሆንም አፈጻጸሙ ላይ ግን ችግር ይስተዋላል፡፡ በህብረተሰብ ደረጃ ያለውን ልማድና አጉል ስም መስጠት ወይንም መጠቋቆሚያ ማድረግን ከሚሰጠው አገልግሎት ጋር ማዳመር እና አገል ግሎት ሰጪዎች ታዳጊ ወጣቶችን የማግኘት ፍላጎት በማጣትም ይሁን የአቅም ማነስ ቢኖራቸው በስነ ተዋልዶ እና በጾታ ላይ ያለውን የተሳሳተ ግንዛቤ ወይንም ልማድ የታዳጊዎቹ ትውልድ በግድ በግፊት፤ መጠቋቆሚያ በመሆን፤ እና ያልተስተካከለ የጤና ሁኔታ ሆኖ እንዲቀበሉት ይገደዳሉ፡፡ ታዳጊ ልጃገረዶች በእድሜ ከማይመጣጠናቸው ሰው ጋር ከጋብቻ ውጭ ወይም በጋብቻ ወሲብ መፈጸም እንዳለባቸው የሚያውቁበት ወይንም የሚስማሙበት እድል ስለማይኖራቸው ብዙ ጊዜ ይጎዳሉ፡፡
ጽንስን ባልተገባ መንገድ ለማቋረጥ መገደድ፤ በልጃገረዶች ላይ የሚፈጸም ጠለፋ ወይንም አስገድዶ መድፈር፤ በታዳጊ ሴቶች የስነተዋልዶ ጤና አገልግሎት የመሳሰሉት በስፋት ጥናት ሊደረግባቸውና መፍትሔ ሊጠቆም እንደሚገባው እንደሚያምን ጥናቱ ያሳያል፡፡
ታዳጊዎች ሁሉም ተመሳሳይ ስላልሆኑ ሁሉም በግል ህይወታቸው የተለያዩ ነገሮችን ማለትም በመኖሪያ ቤታቸው፤ በህብረተሰቡ እና በመንግስት ደረጃም ጭምር የሚፈልጉትን አገ ልግሎት ማግኘት ይገባቸዋል፡፡ በተለይም ከሰሀራ በታች ያሉ ዝቅተኛ በሆነ ደረጃ የሚኖሩ የአፍሪካ ሀገራት አስቸጋሪ የሆነውን ማህበራዊ ልማድ እና አመለካከት በማስቀረት ለወጣቱ አስፈላጊ የሆነውን የስነተዋልዶ እውቀትና አገልግሎት ማድረስ እንዲሁም ወጣቶቹ አውቀውና አምነው ሁሉንም ነገር መፈጸም እንዲችሉ የሚያስችላቸውን መረጃ በተገቢው መንገድ ማግኘታቸውን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ ታዳጊዎችና ወጣቶች የሁሉንም ትኩረት ይሻሉ፡፡ 

Read 11110 times