Print this page
Saturday, 03 April 2021 19:00

6ኛው አገራዊ ምርጫ 2013 ድንገት የታወቀው “እናት” ፓርቲ ከየት መጣ?

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

“ርዕዮተ አለማችን የተለያዩ ርዕዮተ አለሞች ውህድ ነው”

        ከተመሰረተ ከዓመት በላይ ያልገፋው “እናት” ፓርቲ፤ ከምርጫ ቦርድ  እውቅና ያገኘው ከሁለት ወር በፊት ነው። ከብልጽግና እና ኢዜማ ፓርቲ በመቀጠል ለምርጫው ብዙ እጩዎች በማቅረብ፣ በሶስተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ይፋ በተደረገ ወቅት ነው ብዙዎች ፓርቲውን ያወቁት፡፡ ለመሆኑ እናት ፓርቲ እንዴትና መቼ ተቋቋመ? ማን መሰረተው? በምን ዓላማና ግብ? ለምን ሳይታወቅ ቆየ?  ስለ ፓርቲው የተሻለ ለማወቅና ለማሳወቅ፣ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፣ የእናት ፓርቲ መስራችና  ም/ፕሬዚዳንት ከሆኑት የኢኮኖሚ ባለሙያው ዶ/ር ሰይፈ ስላሴ አያሌው ጋር ተከታዩን ቃለ ምልልስ አድርጓል፡-

               እናት ፓርቲ ማን ነው? እንዴትና መቼ ተመሰረተ?
እናት ፓርቲ አገር አቀፍ ፖለቲካ ፓርቲ ነው።  ከምርጫ ቦርድ እውቅና ያገኘነው ከሁለት ወር በፊት ነው። ጥር 10 ቀን 2013 ዓ.ም ማለት ነው፡፡ የመመስረቻ ጠቅላላ ጉባኤያችንን ያደረግነው ደግሞ ከአመት በፊት፣ በየካቲት 2012 ዓ.ም ነው። ፓርቲያችን ከአመት በፊት የተመሰረተና የዛሬ ሁለት ወር ገደማ የእውቅና ሰርተፍኬቱን ያገኘ  ነው።
ለምን እናት ፓርቲን መመስረት ፈለጋችሁ? የፓርቲያችሁ ዓላማ ምንድን ነው?
ለኛ ፓርቲ መመስረት ዋነኛው ምክንያት፣ ከኢትዮጵያ የፖለቲካ ሜዳ ሳይፈልግ ተገልሎ እንዲቀመጥ የተደረገ በፈረንጆቹ አባባል (Silent majority) ዝም ብሎ የተቀመጠ፣ ነገር ግን በሃገሪቱ ፖለቲካ ላይ ተፅዕኖ ሊፈጥር የሚችል እጅግ በጣም ብዙ ቁጥር  ያለው፣ የተማረና ሰፊ ልምድ ያካበተ ሃይል አለ። እስከ ዛሬ ይህንን ዝም ብሎ የተቀመጠ፣ ነገር ግን በሃገሩ ጉዳይ ተፅዕኖ ሊፈጥር የሚችል ሃይል አነቃቅቶ፣ ትርጉም ያለው ሚና በሃገሪቱ ፖለቲካ ላይ እንዲጫወት ማድረግ አልተቻለም ነበር። የትኛውም ፓርቲ ይሄን ሃይል በስሩ አሰባስቦ ትርጉም ያለው ሚና እንዲጫወት አላደረገም። ይህ ዝም ብሎ የተቀመጠ ማህበረሰብ አንዴ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ከገባ አገሪቱን ወደ ተሻለ ጎዳና እንድታመራ ያደርጋታል፡፡
እኛ ይሄን ከመምረጥም ከመመረጥም፣ በአጠቃላይ ከፖለቲካው ራሱን አግልሎ የተቀመጠውን ወሳኝ ሃይል፣ ወደ ፖለቲካው አምጥተን፣ ትርጉም ያለው ለውጥ ለማምጣት እየሞከርን  ነው።  በእርግጥም አሁን እየተሳካልን ነው።
“ዝም ብሎ የተቀመጠ” ሃይል የተባለው ማን ነው? እንዴትስ ነው የምታሰባስቡት?
በሃገራችን ላይ  ባለፉት 30 ዓመታት ፖለቲካው ይዘወር የነበረው ከጫካ በመጡ ሰዎች ነበር። ወደ ስልጣን የሚጠጉትም የፓርቲውን አላማ አምነው እስከተቀበሉ ድረስ እውቀትና ልምድ ኖራቸው አልኖራቸው፣ ጉዳዩ ያልነበረ መንግስት ነበረ። ያለፉት ሦስት አስርት ዓመታት ትምህርት፣ የስራ ልምድ፣ እውቀት ትኩረት የተነፈጉበት ዘመን ነበር። በዚህ ምክንያት አብዛኛው የተማረው የሰው ሃይል ራሱን ከፖለቲካው አርቆ ለመቀመጥ ተገደደ። ይህ የተማረ የሰው ሃይል፣ አሁን ፖለቲካውን ተቀላቅሎ መምጣት አለበት ብለን ነው የተነሳነው። ይሄ በእውቀት፣ በልምድና በአስተውሎት የበሰለ ሃይል፣ ፓርቲውን ተቀላቅሎ ሃገሩን ወደፊት እንዲያሻግር ነው ያለምነው። በዚህም መሰረት ተሰባስበን ፓርቲውን አቋቋምን፡፡
አደረጃጀታችሁ ምን ይመስላል?
ፓርቲያችን  አዲስ እንደ መሆኑ መጠን በመላው ሃገራችን እንደ ልብ ተንቀሳቅሰን አልሰራንም። ጠቅላላ ጉባኤ ባደረግንበት ወቅት እንደ አንድ ሃገር አቀፍ ፓርቲ ለመቆም ከአምስት የተለያዩ ክልሎች 10 ሺህ አባላት ሊኖሩን ይገባ ነበር። ከአንድ ክልል ቢያንስ 4 ሺህ፤ ከሌሎች አራት ደግሞ በትንሹ ከእያንዳንዳቸው 1500 አባላትን ማፍራት ይጠበቅብን ነበር። ከዚህ አኳያ እኛ ከአዲስ አበባ፣ ከአማራ ክልል፣ ከኦሮሚያ፣ ከደቡብ ክልል፣ ከድሬድዋ፣ ከሃረር፣ ከአፋር ከሚያስፈልገን በላይ 12 ሺህ አባላት መልምለን፣ ማመልከቻችንን ለምርጫ ቦርድ አስገባን፡፡ ይሄ ማለት እንቅስቃሴያችን በእነዚህ ክልሎች የተገደበ ነው ማለት አይደለም። ውስን ይሆናል እንጂ በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች ነው ፓርቲው የሚንቀሳቀሰው።
ጠንካራው የምርጫ ሜዳችሁ የቱ ነው?
አዲስ አበባ ላይ በጣም ጠንካራ አደረጃጀት አለን። በዚያው ልክ በደቡብ፣ አማራ፣ ሃረር ድሬድዋ ላይ ጠንካራ ነገር አለን። በኦሮሚያ ክልል በተወሰኑ ቦታዎች ላይ ነው ለጊዜው የምንቀሳቀሰው፡፡
ኦሮሚያ ላይ ለምን እንቅስቃሴያችሁ ተገደበ?
ኦሮሚያ ላይ አሁን ካለው የፀጥታም ሁኔታ ጋር በተያያዘ፣ ብዙ ለመንቀሳቀስ አላመቸንም። ሰላማዊ ሆኖ መንቀሳቀስ የሚቻልበት ቢሆን ኖሮ፣ በመላው ኦሮሚያ ብንንቀሳቀስ በወደድን ነበር። በደብረዘይት  በኢዜማ እጩ ላይ የደረሰውን እናስታውሳለን። እንደዚህ አይነት ነገሮች እጩዎቻችን በድፍረት ወደ ምርጫው እንዳይቡ አድርጎብናል። በአጠቃላይ የፀጥታው ሁኔታ ጥሩ አይደለም። ስለዚህ ኦሮሚያ ክልል ላይ አሁን በእጄ ላይ አሃዛዊ መረጃው ባይኖርም፣ የተወሰኑ መሆናቸውን መናገር እችላለሁ። በአጠቃላይ ግን በሃገር አቀፍ ደረጃ 582 እጩዎች አቅርበናል።
እናት ፓርቲ የታወቀው ብዙ እጩዎች በማቅረብ በሶስተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ይፋ ከተደረገ በኋላ ይመስለኛል? የት ተደብቆ ነው የከረመው?
ያለመታወቃችን ምክንያቱ መገናኛ ብዙኃን እኛን ማስተዋወቅ ስላማይፈልጉ ነው፡፡ ስለኛ ጉዳይ ለመዘገብ ፍላጎት ያልነበራቸው በመሆኑ እንጂ ከምስረታችን ጀምሮ ሁሉንም በየመግለጫዎቻችን ስንጋብዝ ነበር። ነገር ግን ሽፋን አልሰጡንም።  ለሚያውቋቸው ብቻ ነው የሚያስተጋቡላቸው። በዚህ ምክንያት እኛ ብዙም አልታወቅንም። እርግጥ ነው ለአብዛኛው ሰው የታወቅነው ያስመዘገብናቸው እጩዎች ብዛት ሲገለፅ ነው። እናት ፓርቲ ከዚህ  በፊት በየፖለቲካው መድረክ ላይ ከቆዩ ፓርቲዎች እንዴት በአጭር ጊዜ የተሻለ እጩ አስመዘገበ ከተባለ፣ እኛ አነሳሳችንም አመጣጣችንም፣ ጥራትና ልዩነት ለመፍጠር ነው። እኛ የመለመልናቸው ሰዎች ዝም ብለው ቆይተው  የነበሩ፣  ነገር ግን በእውቀትና በልምድ የዳበሩ፣ የጠራ ሃሳብ ያነገቡ፣ በኢትዮጵያዊነትና ኢትዮጵያ ጉዳይ ፅኑ አቋም ያላቸው ናቸው።  አስተሳሰባችንን ለማጠናከር የተጠቀምንበት አንዱ መንገድ፤ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አማራጭን ነው። በቴሌግራም ከ150 ሺህ በላይ አባላት የሚሳተፉበት የቡድን መገናኛ አውታር ዘርግተን፣ ኢትዮጵያዊነትን በደንብ ተነጋግረንበታል። የኢትዮጵያን የቀደመ ታሪክና ዛሬ ያለችበትን የደከመና የተጎሰቆለ ማንነት በተመለከተ ጉዳዩ ከሚያሳስባቸው ሰዎች ጋር በዚህ የመገናኛ አውታር በሰፊው ተወያይተናል፡፡ ወደ ምርጫም ስንመጣ በዚህ መንገድ ነው የምንቀጥለው።
ፓርቲያችሁ ለምን “እናት” ተባለ?
እናት ስንል ግልፅ ነው። ኢትዮጵያ የ110 ሚሊዮን ልጆች እናት ናት። 110 ሚሊዮን ልጆች አሏት፤ እነዚህ ልጆቿ የተለያየ ቋንቋ፣ እምነት ፣ ባህል የሚከተሉ ናቸው። ሁሉም የአንድ እናት ልጆች ናቸው። ከዚህች ሀገር ማህፀን ነው የተፈጠሩት። እውነታው ይሄ  ሆኖ ሳለ፣ ባለፉት 45 ዓመታት፣ ኢትዮጵያ ወስጥ ከፋፋይ የሆነ የፖለቲካ አካሄድ ሲራመድ ነበር። “የኛና የነሱ” በሚል ትርክት የተቃኘ ከፋፋይ ፖለቲካ ውስጥ የከረምነው። ይሄም ትርክት፣ ዛሬ ላይ ለምናየው መተራረድ፣ መገዳደል፣ መጠፋፋት፣ ማፈናቀል  ዳርጎናል። እናት ፓርቲ፤ ይሄንን “የእኛና የእነሱ” አጥፊ አካሄድ ለመለወጥ በቁርጠኝነት ትታገላለች።
ለእናት አጭሩም ልጇ ነው፣ ረጅሙም ልጇ ነው፣ ሃብታሙም ልጇ ነው፣ ድሃውም ልጇ ነው፣ ታታሪውም ልጇ ነው፣ ዳተኛውም ልጇ ነው። 110 ሚሊዮን እንደዚህ አይነት ልጆች አሏት- ኢትዮጵያ። ስለዚህ እናት አቃፊ ነች፤ አሳቢ ነች፤ በልጆቿ መሃል አታለያይም አታበላልጥም። እናትነት የሰብሳቢነት አቅም ስላለው ነው፣ እኛም ፓርቲያችንን  “እናት” ብለን የሰየምነው።
ምን አይነት የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም ነው የምትከተሉት?
እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ ባለፉት 45 ዓመታት፣ የኮሚኒዝም ርዕዮተ ዓለም ነው ስትከተል የቆየችው። ኮሚኒዝም በኢትዮጵያ አይደለም የተሰራው፤ በዚያው መጠን ለተሰራበትም ሃገር በእግሩ ቆሞ አልጠቀመም። ጠፋ። እኛንም አጠፋን። በኢኮኖሚ ኋላ ቀር ለሆኑ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ሃገራት የተሰራ ርዕዮተ አለም የለም። የምንወስደው ያደጉት፣ ለራሳቸው የሰሩትን ርዕዮተ አለም ነው። እነሱ ለራሳቸው ብለው የሰሩትን እኛ ወስደን ለመተግበር መሞከር፣ በኛ ልክ ያልተሰፋን ልብስ ለመልበስ እንደመጣር ነው። ልብሱ አያምርብንም ፣ ረዝሞ ጠልፎ ይጥለናል ወይም አጣብቆ አስጨንቆ ይይዘናል። እኛ አንድ ርዕዮተ አለም  ላይ ከምንለጠፍ፣ ለራሳችን የሚበጅ ነገር ከሁሉም ላይ ቢወሰድና በልካችን ብንሰፋው ይሻላል ብለን ነው ያሰብነው። ስለዚህ የኛ ርዕዮተ ዓለም፣ የተለያዩ ርዕዮተ አለማት ውህድ ነው። ከወግ አጥባቂነትና ከሶሻል ዴሞክራት እንዲሁም ከሊብራል ሃሳቦች የተውጣጣ ውህድ ርዕዮተ አለም ነው የምንከተለው።
ከዚህ ምርጫ ምን ትጠብቃላችሁ?
በእናት ፓርቲ ግምገማ፣ መንግስት እንደሚለው፣ ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ ከተካሄደ፣ 99 በመቶ ይቅርና 50 + 1 ብቻውን አግኝቶ፣ የተወካዮች ም/ቤትን የሚይዝ አይኖርም። ይሄ ከሆነ ደግሞ ትልልቅ የእጩ አቅርቦትና ድምፅ ያላቸው እናት ፓርቲን ጨምሮ፣ ሁለት ሶስት ፓርቲዎች፣ አብዛኛወን ፓርላማ ይይዙትና ቀጣዩ መንግስት ጥምር መንግስት ሊሆን ይችላል ብለን እናስባለን፡፡ እኛም የዚህ ጥምር መንግስት አካል እንሆናለን ብለን እንጠብቃለን፡፡
ፓርቲያችሁ የኦሮቶዶክስ እምነት ተከታዮች ብቻ የተሰባሰቡበት እንደሆነ ይነገራል---
አንድ ግልጽ አድርጌ መናገር የምፈልገው፣ የትኛውም የእምነት ተቋም ፓርቲ ማቋቋም የሚያስችለው ህግ የለም፡፡ ስለዚህ እናት ፓርቲ ከየትኛውም የእምነት ተቋም ወይም ድርጅት ጋ ምንም አይነት ግንኙነት የለውም። ግን እናት ፓርቲ ውስጥ የኦርቶዶክስ አሊያም የፕሮቴስታንት ወይም የካቶሊክ፣ ወይም የእስልምና እምነት ተከታዮች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ስለዚህ ኦሮቶዶክሳዊያንም ፓርቲው ውስጥ ሊኖሩ ይችላሉ ማለት ነው።
እምነትን እንደ አባልነት መስፈርት የመጠየቅ ጉዳይስ?
አንድ በእርግጠኝነት ልናገር የምችለው፣ ወደኛ ፓርቲ አባልነት የሚመጣ ሰው እምነቱ አይጠየቅም፤ ሃይማኖቱን አንጠይቅም፤ የት አካባቢ እንደተወለደ አንጠይቅም፤ ምክንያቱም ይሔ የት አካባቢ ተወለድክ? ምን ቋንቋ ትናገራለህ? ምንድን ነው እምነትህ? የሚሉ ነገሮች ናቸው እስከ ዛሬ ሲያፋጁን የኖሩትና ዛሬም እያገዳደሉን ያሉት፡፡ ስለዚህ ይሄን ነገር ለማስቆም የምንቀሳቀስ እንደመሆናችን፣ ማንነትን ፈፅሞ ለአባልነት መስፈርታችን አናደርግም።
በዚህ ምርጫ ተስፋና ስጋታችሁ ምንድን ነው?
ተስፋችን ወደ ምርጫው በገባንበት መልኩ፣ በውጤት እናጠናቅቀዋለን የሚል ነው። በተወዳደርንባቸው ቦታዎች ሁሉ ጥሩ ውጤት አግኝተን፣ አሸናፊ እንሆናለን ብለን  ተስፋ እናደርጋለን። ነገር ግን በዚህ መሃል አንድ ትልቅ ስጋት አለን። የሰላምና መረጋጋት ጉዳይ ነው። ከገባንበት የአለመረጋጋት ሁኔታ ለመውጣትም ምርጫው የግድ  መደረግ አለበት። ምክንያቱም ስልጣን ላይ ያለው መንግስት፣ የህዝብ ውክልና ያለው አይደለም። ጠ/ሚኒስትሩም ቀደም ሲል ወደ ስልጣን በመጡበት ወቅት፣ “ኮሮጆ ገልብጣችሁ  ነው የመጣችሁት እንባላለን” ብለው ነበር። በእርግጥም እንደዚያ ነው የሚባለው። ይሄን ሁኔታ ለመለወጥ የግድ ምርጫው ያስፈልጋል፡፡  ይሄ ሁሉ የሚሆነው ግን በከባድ የፀጥታ ስጋት ውስጥ ነው። በአሁኑ ወቅት ከአዲስ አበባ 150 እና 200 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ሳይቀር፣ የፀጥታ ስጋቶች እየተፈጠሩ ነው። ይሄ ትልቅ ችግር ነው። ነገር ግን ከዚህ ሁኔታ ለመውጣትም ቢሆን ምርጫው መካሄድ አለበት። ባለመረጋጋት ውስጥም ቢሆን ምርጫው ተደርጎ፣ ወደ ዘላቂ መረጋጋት የምንሻገርበት ሁኔታ መፈጠር አለበት፡፡


Read 3440 times