Sunday, 04 April 2021 00:00

የዜጎች አሰቃቂ ግድያ በምዕራብ ወለጋ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

ኦነግ እና አብን ስለ ጥቃቱ ምን ይላሉ?
                        

                  “የዚህ ሁሉ መከራ ስረ መሰረት ፀረ አማራ የሆነው ህገ-መንግስት ነው”
                       አቶ በለጠ ሞላ የአብን ሊቀመንበር


            መንግስት በዘር እየተመረጡ የሚገደሉ አማራዎችን ጉዳይ ለማስቆም አጥፊዎችን በቁጥጥር ስር ማዋልና ተገቢውን ቅጣት መስጠት አለበት ሲሉ የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን) ሊቀ መንበር አቶ በለጠ ሞላ አሳበቡ። መንግስት አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ አጥፊዎቹን አያውቅም ማለት አይቻልም ያሉት ሊቀ መንበሩ፤ ታጣቂዎች ወይም ኦነግ ሸኔና ሌላም ስያሜ ቢሰጣቸውም  እነዚህ ሀይሎች ከመንግስት የተሰወሩ አይደሉም ይላሉ።
ሊቀመንበሩ አክለውም፤ “ለዚህ ሁሉ ግድያና እልቂት የኦሮሚያ ክልላዊ፤ መንግስት የችግሩ አካል ነው ብለን እናምናለን” የክልሉ አመራሮች በአደባባይ የሚሰጧቸው ሃላፊነት የጎደላቸው ንግግሮች፣ ለሚፈፅሙት ጥቃቶች የክልሉን ርዕሰ መስተዳድር “ሽመልስ አብዲሳን ጨምሮ በየደረጃው ያሉ አመራሮች የሚሰጧቸው መግለጫዎች ለአጥፊዎች መነሳሳትን ፈጥሮላቸዋል ብለን እናምናለን ይላሉ። የአመራሮቹ ንግግሮች ህዝብን በመከፋፈል ገዳይና ተገዳይ አድርጎ በመሳል እንዲሁ እንዲህ አድርገውን ነበር የሚል የውሸት ትርክት በመፍጠር አማራን ሲኮንኑና በህግ እውቅና ያላቸውን አብንንና ባልደራስን አሸባሪ እያሉ ሲፈርጁ ቆይተዋል ያሉት አቶ በለጠ ይህ ሁሉ ውንጀላ ከነበረውና ካለው ፀረ-አማራ ትርክት ጋር ተዳምሮ ለንጹሃኑ የአማራ ህዝብ  ህልፈት ምክንያት በመሆኑ የክልሉ አመራሮች ቀጥተኛ ተዋናዮች ናቸው ብለን እናምናለን ብለዋል።
ይህ ጉዳይ በዚህ መቀጠል ስለሌለበትና ስለማይቀጥልም፣ ለህዝብ የሚጨነቅ አካል ካለ አጥፊዎቹን በቁጥጥር ስር አውሎ፣ ተገቢውን ቅጣት መስጠት ግዴታ ነው ሲሉ አሳስበዋል። ጉዳዩ ከመንግስት አቅም በላይ ነው ብለው ያምናሉ ወይ? በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ አቶ በለጠ ሲመልሱ፤ “ነገሩ ከመንግስ አቅም በላይ ሆኗል ብዬ አላምንም፤። ነገር ግን የኦሮሞ ብልጽግና በውስጡ ያልጠራ ብዙ ጉዳይ አለው፤ ኦነግ ሰፊ የሆነ ፀረ-አማራ ትርክት ሲያስራጭ የኖረ ድርጅት መሆኑ ይታወቃል፤ ይህ የኢትዮጵያን አንድነትና ሰላም ለመበተን ሲሰራ የነበረ ድርጅት ለውጥ የሚባለው  ከመጣ በኋላ አመራሮቹ በየደረጃው አማካሪ ሆነው ቤተ-መንግስት ውስጥ ተሰይመዋል፣ በኦሮምያ ብልፅግናም ውስጥ ተሰባጥረው ይሄንን ፀረ-አማራ ትርክት በሰው አእምሮ እያሰረፁ እንደሆነ በግልፅ እያየን ስለሆነ መንግስት ለቀውሱ እልባት መስጠት ከበደው ከተባለ ከዚህ አንፃር ነው ሊሆን የሚችለው” ብለዋል።
“መንግስት አጥፊዎቹን ለመቅጣት አቅም አጥቻለሁ ቢል እንኳን ቢያንስ ዜጎች በማንነታቸው እየተመረጡ ሲገደሉ ሲፈናቀሉና ሲጎዱ፣ የሀዘን መግለጫ መስጠት፣ ብሄራዊ ሀዘን ማወጅና የተጎዱና የተፈናቀሉትን መልሶ የማቋቋም ስራ መስራት ነበረበት” ያሉት የአብን ሊቀ መንበር፤ “ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀምሮ ይህንን ሲያደርጉ አይተን አናውቅም፤ የአማራ ሞት ሀዘናቸው ሆኖም አያውቅም ፤ ይሄ እንደ ሀገር በጣም የሚያሳዝን ነው” ሲሉ አማርረዋል።
የአማራ ክልልን የሚመራው የአማራ ብልፅግናን በተመለከተም በሰጡት አስተያየት “የአማራ ንፁሃን ወገኖች በተደጋጋሚ በማንነታቸው እየተመረጡ  ሲገደሉ ብልፅግና የሚባለውን ፕላት ፎርም ገምግሞ ድርጊቱን ተቃውሞ አቋርጦ መውጣት ነበረበት” ያሉት አቶ በለጠ በትክክል የህዝቡ ብሶትና መገፋት  የሚሰማው ቢሆን ኖሮ፣  ችግር በተከሰተ ቁጥር አንዳንዶች በቲዩተር ወይም በፌስቡክ ገጻቸው ተራ አክቲቪስት የሚፅፈውን  ከመጻፍ ባለፈ የኦሮሞ ብልፅግና አቻዎቻቸውን ሞግተውና ጥፋታቸውን አጋልጠው ህግ ፊት እንዲቀርቡ ማድረግ ይችሉ ነበር ሲሉ ወቅሰዋል። አማራ በተደጋጋሚ በየቦታው ሲገደልና ሲሰቃይ ሌላ ማድረግ ባይችሉ በክልል ደረጃም ቢሆን ብሄራዊ ሀዘን ማወጅ፣ የተፈናቀሉትን መልሶ ማቋቋምና ህልውናቸውን ማረጋገጥ በቻለ ነበር፤ ይህንን ባለማድረጋቸው የአማራ ብልፅግናዎች ከተጠያቂነት አይድኑም” ብለዋ አቶ በለጠ ሞላ።
“ኢትዮጵያ ለሁላችንም የምትበቃ ሀብታም፤ አየሯም ተስማሚ አገር ናት፤ ሆኖም የዚህ ሁሉ መከራ ስረ-መሰረት ጸረ አማራ የሆነው ህገ-መንግስቱ ነው” የሚሉት የአብን መሪ፣ “ይህ ህገ-መንግስት ጸረ አማራነትን የተላበሰ ስለመሆኑ በዝርዝርና በግልፅ ተቀምጧል። ይህንንም በተደጋጋሚ ባገኘነነው አጋጣሚ ስንገልፅ ቆይተናል” ብለዋል። ለዚህም ማሳያ የሚሆነው በህገ-መንግስቱ መግቢያ ላይ በግልፅ የተቀመጠው “የዚህ ህገ-መንግስት መውጣት አስፈላጊ ከሆነባቸው ምክንያች አንዱ፤ በህዝቦች መካከል የነበረውን የተዛባ ግንኙነት ለማስተካከል ነው” የሚለው አንደኛው ነገር በህዝቦች መካከል ያለውን የተዛባ ግንኙነት የሚለው ተተርጉሞ እየተተገበረ ያለው አማራው ጨቋኝ ሌላው ተጨቋኝ የሆነበትን ሚዛን ለማስተካከል ነው የሚል አንድምታ ይዞ አማራውን ዋጋ እያስከፈለው ነው ሲሉ ይተቻሉ።
ፓርቲያችን የመንግስት ቁመና ቢኖረውና አገር የመምራት ዕድል ቢገጥመው በመጀመሪያ የሚሰራው ሁሉም ህዝቦች ይሁንታ የሰጡትንና የተሳተፉበትን ህገ-መንግስት ማፅደቅ ነው ያሉ ሲሆን ሌላው የክልሎች ህገ-መንግስትም ከሌላ አካባቢ የመጣን ዜጋ “ሰፋሪ የሚል ህገ-መንግስት በመሆኑ መሻሻል አለበት ብለዋል።
ዘር ተኮር ግድያ እስከ መቼ ይቀጥላል? እንዴትስ ነው የሚቆመው ብለናቸው የነበረ ሲሆን፣  “ግድያው በዚህ አይቀጥልም፣ የአማራ ህዝብ የራሱን አማራጭ ይወስዳል” ሲሉ ቁርጥ ያለ መልስ ሰጥተዋል።
እስካሁን ለጠፋው ህይወት በዋናናት ተጠያቂው ማን ነው ላልናቸውም “ይህን ተጠያቂነት የሚወስደው ተለውጫለሁ  የሚለው መንግስት ነው፣ በመሰረቱ መንግስት አልተለወጠም  ዛሬም ድረስ የትህነግ አይዲዮሎጂ፣ ትርክትና መንፈሱም በመንግስት መዋቅር ውስጥ መሪ ሆኖ እያየነው ነው ካልተለወጠ  መንግስት የተለወጠ ነገር ማየት አይቻልም ብለዋል።”_______________                 “ኦነግ ሸኔ በሚል አደረጃጀት የሚንቀሳቀስ ሀይል አላውቅም”
                           አቶ ቀጄላ መርዳሳ የኦነግ ም/ሊቀመንበር


            “ባለፈው ማክሰኞ በምዕራብ ወለጋ በነዋሪዎች ላይ የደረሰውን አሰቃቂ ግድያ እኛም በሚዲያ ነው የሰማነው” ያሉት የኦነግ አዲሱ ም/ሊቀመንበር አቶ ቀጀላ መርዳሳ፤ መንግስት ሰላም የማስከበርና ወንጀል የመከላከል ሀላፊቱነቱን መወጣት አለበት ብለዋል።
በተለይ በምዕራብ ወለጋ አካባቢ ንፁሀንን የሚገድሉት እነማን እንደሆኑ አጥንተንና ተከታትለን፣ በአካባቢው ሰላም እንዲሰፍን የበኩላችንን መወጣት አለብን ብለን እናምናለን ብለዋል፡፡
በምዕራብ ወለጋ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ በአገሪቱ ያለው ችግር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የሚፈታበት መንገድ በሁሉም አካላት ተፈልጎ መፈታትና መቋጫ ማግኘት አለበት ሲሉም አክለዋል፡፡
በምዕራብ ወለጋ በተደጋጋሚ በአማራ ተወላጆች ላይ የተፈጸመውን ዘር ተኮር ግድያ ጉዳዩ ከመንግስት አቅም በላይ ነው ወይ የሚል ጥያቄ አነሳንላቸው። “ንፁሀንን ለመግደልና ለማጥቃት ያን ያህል ብዙ ሀይል ያስፈልጋል ብለን አናምንም” የሚሉት አቶ ቀጄላ፣ይህንን ድርጊት የተወሰኑ ታጣቂ ሀይሎች ሊፈጽሙ ይችላሉ  “ነገር ግን የአማራ ተወላጆችን ብቻ ተጠቂ አድርጎ መውሰዱ ትክክል አይደለም፤ በአካባቢው የአማራ ተወላጆች ብቻ ሳይሆኑ በየቀኑ ብዙ ንፁሀን የኦሮሞ ተወላጆችም ይሞታሉ” ሲሉ ሞግተዋል።
“እኔ እንደሚገባኝና እንደማውቀው፣ በዚያ አካባቢም ሆነ በሌላ ቦታ፣ ማንነታቸው በማይታወቅ ሰዎች የሚገደሉት ኦሮሞዎች ናቸው” የሚሉት ም/ሊቀመንበሩ እንደ አጋጣሚ ሆኖ አሁን ሰው ተገደለ የሚባልበት ምዕራብ ወለጋ የተወለዱበት አካባቢ እንደሆነና በዚያ አካባቢ በየጊዜው  ብዙ ወጣቶች እንደሚሞቱ መረጃው አለኝ ብለዋል።
“ከዚህ አንጻር ሰኞ ዕለት የተገደሉ የአማራ ተወላጆች ብቻ ናቸው ብለን አናምንም፤  በአካባቢው ሰፍረው የሚኖሩት ለብዙ አመታት የኖሩ በተለይ በደርግ ጊዜ በሰፈራ የሄዱ የወሎ፣ትግራይ ሌሎችም የሰሜን ኢትዮጵያ ተወላጆች ሲሆኑ ብዙዎቹ እዛው ተወልደው ያደጉ፣ ከህብረተሰቡ ጋር ተጋብተው የወለዱ፣ ቋንቋውን የሚችሉ በመሆናቸው አንድ ብሔረሰብ ብቻ ለይቶ ተገደለ የሚለው አገላለጽ አደገኛ ህዝቦች አንድነትና አብሮነት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ የሚፈጥር ነው” ብለዋል፡፡
ከሞት የተረፉት ሰዎች ለሚዲያ እየደወሉ በአማራነታቸው እየተመረጡ ግድያ እንደሚፈጸምባቸው በግልፅ እየተናገሩ እንዴት በማንነታቸው ተመርጠው አልተገደሉም ማለት  ይቻላል? በሚል ተጠይቀውም ሲመልሱ፤ “ኦሮሞዎች በየጊዜው እየተገደሉ መሆኑን በግሌ ስለማውቅ አማራ ብቻ እየተገደለ ነው የሚለው አያስኬድም” ሲሉ አቶ ቀጀላ ተከራክረዋል፡፡ እንደ እርሳቸው ገለፃ፤ እንኳን በገጠርና በወረዳ ቀርቶ እንደ ነቀምትና ደምቢዶሎ ባሉ ከተሞችም ኦሮሞዎች እየተገደሉ ቢሆንም፣ ለሚመለከታቸው አካላት ሪፖርት እንደማይደረግና ማን እንደገደላቸውም እንደማይታወቅ ገልፀዋል፡፡
በሌላ በኩል፤ እንዲህ አይነት ችግሮች ሲፈጠሩ አገርን ለማተረማመስ የሚፈልጉ ሀይሎች ጉዳዮቹን በማጋነን በአገር ላይ ቁማር ለመጫዋወት እንደሚጠቀሙበት የገለፁት አቶ ቀጄላ፣ “ለምሳሌ ሰሞኑን በምዕራብ ወለጋ ከ100 በላይ ሰው እንደተገደለ ሲናፈስ የነበረ ቢሆንም ጉዳዩ በመንግስት ሲጣራ ግን የሞተው 28 ሰው ነው”፤ እኛ ግን እንኳንስ 28 ሰው  አንድም ሰው መሞት የለበትም ብለን ስለምናምን፣ ጉዳዩን እናወግዛለን” ብለዋል “ሁሉም ችግር ሲፈጠር ከማጋነንና የተሳሳተ መረጃ ከመስጠት እና አገርን ወደ ባሳ አደጋ ከመክተት ይልቅ በሰከነ መንገድ መፍትሔ መፈለግ ተገቢ ነው” ሲሉም መክረዋል።
ለምን ፓርቲዎች በጋራ ጉዳዩን አያወግዙም? በሚል  ለጠየቅናቸው “ይሄንን ጉዳይ ፓርቲዎች ብቻ ሳይሆኑ ሁሉም ዜጋ፣ ሁሉም አካል በጋራ ማውገዝ አለበት፤ ሊወገዝም ይገባል የሰው ልጅ በሕይወት የመኖር መብቱ በሰብአዊ መብቶች የተደነገገ በመሆኑ ግድያውና ጥቃቱ መወገዝ አለበት፤ ግድያውን ማንም ይፈፅመው ማን፣ ድርጊቱ መወገዝ አለበት፤ ይሔ የኔ ወገን ነው፤ ያኛው የኔ ወገን አይደለም ሳይል ለጠፋው የሰው ልጅ ህይወት ውግዘት ያስፈልገዋል፤ ብለዋል፡፡
እንደ ኦነግ እናንተስ  አውግዛችኋል ወይ በሚል ለጠየቅናቸው “እናወግዛለን ከዚህም በፊት በጉሊሶና በሌሎችም ቦታዎች የተገደሉ ንፁሃንን አስመልክተን አውግዘናል” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ገና ጉዳዩ በተከሰተ ማግስት ስለጠየቅሽኝ እንጂ መንግስትም እኛም ጉዳዩን ካጣራን በኋላ መግለጫም እናወጣለን እናወግዛለንም ብለዋል፡፡
“በምዕራብ ወለጋ ህዝብ የሚሞተው በሁለት ወገን ነው” የሚሉት አቶ ቀጄላ ህግ ለማስከበር ወደ ቦታው የሚላከው የመንግስት ታጣቂም ሆነ ከጫካ ሆኖ የታጠቀው በሁለት በኩል በህዝቡ ላይ ግድያ ይፈፅማል” ብለዋል፡፡ “የመንግሰት ህግ አስከባሪ ቀጥታ ከገዳዮቹ ጋር ሄዶ መግጠም ሲገባው አንተ ከገዳዮች ጋር ግንኙነት አለህ” በሚል ጥርጣሬ የሚገደሉ ብዙ ናቸው የሚሉት የኦነግ ም/ሊቀ መንበር ፤ ከጫካ በኩል ባሉት “አንተ የመንግስት ሰላይ ነህ፤ መረጃ ታቀብላለህ” በሚል የሚገደሉትም ቁጥር ቀላል አይደለም ፤ ይሔ ድርጊት መቆም አለበት፤ በመሃል ቤት የሚሰቃየው ህዝብ አፎይታ ማግኘት አለበት ሲሉ አሳስበዋል፡፡
የእናንተ ፓርቲ ኦነግ መንግስት ቢሆን እንዲህ አይነት ጥቃቶችን በምን መልኩ ያስቆማል ስንል ለጠየቅናቸውም “ይሔ የፀጥታና የሀገር ደህንነት ጉዳይ በመሆኑ ጠበቅ ያለ እርምጃ በመውሰድ የህዝቡንና የሀገርን ደህንነት ማስጠበቅ የግድ ይላል ፤ ሌላው የፖለቲካ ችግሮችን መፍታት ነው ያሉ መንግስትን የሚቃወሙና በትጥቅ የሚፋለሙትን ሀይሎች መንግስት ተነጋግሮ እነዚህን ሀይሎች ወደ ሰላማዊ መንገድ እንዲመጡ ማድረግ እንጂ ችግሩን በመሳሪያ ሀይል ብቻ እፈታለሁ ማለት አስቸጋሪ ነው ብለዋል። ለችግሩ የፖለቲካ መፍትሔ መፈለጉ  የግድ ነው ሲሉም አክለዋል፡፡ እንደ አቶ ቀጄላ ገለፃ ፤ጉዳዩ በምዕራብ ወለጋ ላይ ብቻ ሳይሆን በመላው ሀገሪቱ ስላለ ትኩረት ማግኘት እንዳለበትና በቅርቡም በሰሜን ኢትዮጵያ ሰሜን ሸዋ አጣዬና አካባቢው ላይ የተፈፀሙት ጥቃቶችና ግድያዎች ቀላል ስላልሆኑ ችላ ሊባል እንደማይገባው አስምረውበታል፡፡ እንደነዚህ አይነት ጥቃቶች በመላ አገሪቱ መወገዝም መወገድም አለባቸው ብለዋል። ኦነግ ሸኔ ማነው? በሰሜን ሸዋም ሆነ በምዕራብ ወለጋ እነዚህን ጥቃቶች ኦነግ ሸኔ የተባለ ታጣቂ ሀይል ስለማድረሱ ይነገራል በዚህ ላይ ምን አስተያት አለዎት ስንል ጠይቀናቸው ሲመልሱ፤ “እኔ ኦነግ ሸኔ የሚባል ስም ይዞ የሚንቀሳቀስ ደርጅት መኖሩን አላውቅም፤ የለምም ብዬ ነው የማምነው” ያሉት አቶ ቀጄላ፣ በዚህ ስም ራሱን የሚጠራ ድርጅት እስከሌለ ድረስ አለ ለማለት እቸገራለሁ፤ ሆኖም የመንግስት አካላት ይህንን በተደጋጋሚ ሲጠሩ እሰማለሁ ነገር ግን ቀደም ሲል “የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት” ለተባለ አካል ስያሜውን የተባለ ሀይል የሰጡ ይመስለናል የሚሉት ም/ሊቀ መንበሩ፣ ነገር ግን ይሔ ቡድን በመላው ኢትዮጵያ ተሰራጭቶና አገሪቱን አዳርሶ ከጫፍ እስከ ጫፍ እየተንቀሳቀሰ ነው፣ ለሁሉም ጥቃቶች ይሄ ቡድን ተጠያቂ ነው ብለን መናገር ያስቸግረናል ብለዋል፡፡ እነዚህ ታጣቂዎች በተወሰነ ቦታ ሆነው እንቅስቃሴያቸውም የተወሰነ ይሆናል እንጂ በመላው ኢትዮጵያ  ይህን ሊያደርጉ ስለማይችሉ ጉዳዩ በደንብ መፈተሸና እንደ ሀገር ችግሩ መፈታት አለበት፣  ጥቃት  ፈጻሚዎቹ በተለያየ አካባቢ ስለሚኖሩ መንግስት ይህንን አጣርቶ ዘላቂ መፍትሄ መፈለግ አለበት።  ለምሳሌ ወሎ ላይ ኦነግ ሸኔ እንደሌለ እናምናለን ያሉ ሲሆን ያንን ጥቃት ያደረሰው አካል ማን እንደሆነ መጣራትና መጠናት ይገባዋል ብለዋል፡፡
እስካሁን ለደረሱት የንፁሀን ግድያዎችና ጥቃቶች ማን ሀላፊነቱ እንደሚወስድ አላውቅም ያሉት ም/ሊቀመንበሩ እዚህ አገር ላይ ብዙ የተለያዩ ፍላጎቶችና በጣም የተለያየ አላማ ያላቸው ቡድኖች ስላሉ አንድ እርምጃ በሚወስድበት ጊዜ ሀላፊነቱን የምወስደው እኔ ነኝ ብሎ መግለጫ እስካልተሰጠ ድረስ እከሌ ነው ብሎ ማለት ይከብዳል፡፡ ይሄንን መንግስት አጣርቶ ይፋ ማድረግ አለበት፤ በሌላ በኩል መንግስት ጥቃቱ እንዳይደርስ ቀድሞ በመስራት መካከል ነበረበት ይህንን ባለመስራቱ ችግሮቹ ተከስተዋል ለወደፊትም ይሔንን ባለመስራቱ ችግሮቹ እንዳይከሰቱ መሰራት አለበት ሲሉ አሳስበዋል።__________________
                            የህግ ባለሙያ ስለ ጥቃቱ ምን ይላሉ?

                   “ድርጊቱን በተደጋጋሚ ኦነግ ሸኔ ፈፀመው እያሉ ማለፍ አጉል መደበቂያ ነው”“ድርጊቱን በተደጋጋሚ ኦነግ ሸኔ ፈፀመው እያሉ ማለፍ አጉል              መደበቂያ ነው”
                     አቶ ሞላልኝ መለሰ የህግ ባለሙያ


            በምዕራብ ወለጋ በተደጋጋሚ የሚፈፀመውን ጥቃትና ግድያ ኦነግ ሸኔ ፈፀመው እያሉ ማለፍ አጉል መደበቂያና ማምለጫ ነው የሚሉት የህግ ባለሙያው አቶ ሞላልኝ መለሰ፤ በዚህ ጉዳይ ላይ ሰፊና ጥልቅ ምርመራ ተደርጎ ትክክለኛ አጥፊዎቹን ለህግ በማቅረብ ችግሩ እልባት ማግኘት አለበት ብለዋል። የግድያው ሁኔታ፣ የገዳዮቹ ትክክለኛ ማንነትና እውነታው ሳይጣራ ቀድሞ አጥፊው“ኦነግ ሸኔ ነው” ብሎ መፈረጅ ድርጊቱ ከምንጩ እንዳይደርቅ መደበቂያና ማምለጫ መንገድ ነው ብለዋል የህግ ባለሙያው፡፡
ዜጎች በየትኛውም ቦታ በሰላምና በተረጋጋ ሁኔታ የመኖር መብት እያላቸው መብታቸው ተጥሶ ሲገደሉና ሲጠቁ የሰብአዊ መብት ጥሰት ወንጀል ሊባል ይችላል ያሉት አቶ ሞላልኝ፤ ነገር ግን አሁን እንደሚሰማው በዘራቸው፣ በማንነታቸውና በብሔራቸው ምክንያት ተለይተው ከተጠቁና ከተገደሉ ጉዳዩ የዘር ማጥፋት ወንጀል ሊባል ይችላል ነገር ግን ይህም ቢሆን በምርመራ መረጋገጥ ያስፈልገዋል ይለዋል፡፡
በሌላ በኩል ድርጊቱን ማንም ይፈፅመው ማን፣ የሰብአዊ ጥሰት ወንጀልም ይሁን የዘር ማጥፋት አሊያም ተራ ግድያ እጅግ አሳፋሪና ሊወገዝ የሚገባው ድርጊት ነው ብለዋል፡፡ ሰሞኑን ከተለያየ አካለት የሚወጡ የተለያዩ መግለጫዎችና መረጃዎች ለጉዳዩ ያለው አረዳድ ወጥና አንድ አይነት እንዳልሆነ ይጠቁማል የሚሉት አቶ ሞላልኝ፤ ይህ የሚያሳየው ድርጊቱና የተፈጸመበት መንገድ በጥልቀት መፈተሽና መመርመር እንዳለበት ነው ብለዋል።
ድርጊቱን  የፈጸመው ማን ነው የሚለው ነው ጥያቄውን የሚፈታው ሚሉት የህግ ባለሙያው ይሄ ድርጊት  የሰሞኑ ብቻ ሳይሆን ባለፉት 3 ዓመታት ሲፈፀም መቆየቱን አስታውሰው፣ ይሄ በተለያየ አካባቢ የሚፈጸም አሰቃቂ ጥቃት ሁላችንም በያለንበት ጭንቀት ውስጥ እንድንገባ የሚያደርግ ነውም ሲሉ፤ አስቸኳይ እልባት እንደሚስፈልገው ጠቁመዋል፡፡
ድርጊቱ ከጭንቀትም ባለፈ ሀገራችንን ወደ ባሰና ወደተወሳሰበ ግጭት በሚያስገባ ደረጃ እየተስፋፋና እየተባባሰ መምጣቱን ገልጸው ይሄንን የድርጊት ሚፈጽሙትን መያዝና በህግ ፊት ማቅረብ ያልተቻለበት ምክንያት ምንድነው ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው ብለዋል፡፡
“እዚህ አዲስ አበባ ውስጥ የተለያየ መሳሪያ ይዘው የሚንቀሳቀሱ ሰዎች እየተያዙ ነው” ያሉት የህግ ባለሙያው፤ እነዚህ እጅግ ዘመናዊ መሳሪ ታጥቀው በየክልሉ ግድያና ጥቃት የሚፈጽሙ ቡድኖች ከተማ ውስጥ እንደሚያዙት  ሁሉ ለምን ተይዘው ለፍርድ አይቀርቡም” ሲሉም አጠንክረው ጠይቀዋሉ። አክለውም ጉዳዩ ከመንግስት አቅም በላይ ሆኖ ሳይሆን በመንግስት መዋቅር ውስጥ ለነዚህ ሃይሎች ድጋፍ የሚሰጥ አካል ሊኖር ይችላል ብለው እንደሚጠረጥሩ ገልፀዋል፡፡
እንዲህ አይነት ድርጊቶች በተፈፀመ ቁጥር እርምጃ ይወሰዳል ሲባል እንጂ  አጥፊ አካል ተይዞ ለፍርድ ሲቀርብ አናይም የሚሉት አቶ ሞላልኝ፤ ይህም ጉዳይ በእጅጉ እንደሚያሳስባቸው ተናግረዋል፡፡
እስካሁን ለተከሰተው ጉዳት፣ ሞትና መፈናቀል ማን ነው ተጠያቂና ሀላፊነቱን የሚወስደው  ብለን ላቀረብንላቸው ጥያቄ አቶ ሞላልኝ ሲመልሱ፣ “ይሄንን ሃላፊነት የሚወስደው እከሌ ነው ብለን አሁን የምንደመድም ከሆነ፤ ነገ በጉዳዩ ላይ ፍርድ ቤት በሚደረገው ምርመራ ነጻነትን አንሰጥም ማለት ነው” ሲሉ ሙያዊ አስተያየት የሰጡ ሲሆን፣ ምርመራው ነፃ በሆነ መንገድ ተካሂዶ በሚመጣው ውጤት ለዚህ ጥፋት ሃላፊነት የሚወስደው ማን ነው ለሚለው ምላሽ ይሰጠናል ብለዋል።
አክለውም፤ “ብዙ ጊዜ እንዲህ አይነት ድርጊቶች ተጠያቂ አልባ የሚሆኑት ከምርመራና ከማጣራት በፊት፤ ይሄንን ድርጊት የፈጸመው ኦነግ ሸኔ ነው እገሌ ነው እየተባለ ስለሚፈረጅ ተድበስብሶ ያልፋልና እንዲህ ዓይነት ከምርመራ በፊት የሚሰጡ ፍረጃዎች ትክክል አይደሉም፤ መቆምም አለባቸው ሲሉ ሙያዊ አስተየታቸውን ቋጭተዋል አቶ ሞላልኝ መለሰ።”

Read 2281 times