Saturday, 03 April 2021 19:15

ፖለቲከኛም ጥበበኛም የሚያነበው መፅሐፍ

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(4 votes)

  የጠቅላዩን “የመደመር መንገድ” ዳሰሳ በአንድ ክፍል ለማጠናቀቅ እንዳልቻልኩ አይታችኋል። ለዚህ ነው አንድ ሳምንት ዘልዬ ዛሬ የተመለስኩት። በወጣቶች ላይ ከሚያጠነጥነው ፅሑፍ እንጀምር። “ኢትዮጵያ የወጣቶችና የአዳጊ ወጣቶች ሀገር በመሆኗ ለእድገትዋ ዋነኛ ሞተር የሆነውን ሃይል በሚገባ ሳይጠቀሙ ልማትም ብልጽግናም ይመጣል ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው።” ይላሉ - ዶ/ር ዐቢይ በመፅሃፋቸው።
በመለጠቅም ወጣቱ ሃይል ለበጎም ለክፉም ሊውል እንደሚችል ያብራራሉ፡- “በወጣትነት ውስጥ እሳትነትና ግለት አለ። ይህን እሳት ብረት ቢቀልጥበት፣ መስኖ ቢጠለፍበት፣ ተራራ ቢናድበት ግለሰቡንም ሀገርንም ይጠቅማል። ይህ እሳት ፋብሪካ ለመገንባት እንጂ ፋብሪካ ለማቃጠል ከዋለ ደግሞ ሁሉም ይከስራል። ድልድይ ለማነጽ እንጂ ድልድይ ለማፍረስ ከዋለ በከንቱ ይባክናል። ተዐምር ለመስራት እንጂ መአት ለማውረድ ከዋለ ትርጉም የለውም።” (ገፅ 95)
ግሩም ገለፃ ነው- እውነትና ውበት ያጣመረ!! ባለፉት ጥቂት ዓመታት ለበጎ ሳይሆን ለጥፋት ሲውል ያየነውን የወጣቱን ግለትና እሳትነት  ያስታውሰናል። ዛም ድረስ ከከተማ ስንወጣ በየቦታው የምናስተውላቸው የተቃጠሉ ቤቶች፣ ተሽከርካሪዎች፣ ፋብሪካዎች ወዘተ…. በእንባ የሚተርኩልን ይህንን ነው። በርካታ ስራ አጦች በሞሉባት ሀገር፣ ብዙ ቤተሰብ እንጀራ በልቶ የሚያድርበትን ሀብት ዶግ አመድ ማድረግ፣ ራን በራስ ከማጥፋት ተለይቶ አይታይም!?
ግን አሁንም ዋናው ነገር፤ ከዚህ ዓይነቱ የተበላሸ አውዳሚ አስተሳሰብና ስነ-ልቡና ሾልከን የምንወጣበት መንገድ ተዘጋጅቷል ወይ? የሚለው ነው። መቼም ጥፋቱ የአንድ ወገን ፍላጎት ባይሆን እንኳ፣ የሌላው ከሆነ፣ እንዴት አድርጎ ከዚህ ክፉ ደዌ መፈወስ ይቻላል?... መጽሐፉ መፍትሔው “መደመር” ነው ይላል።…
አንዳንድ ጊዜ ደረቅ እውነታዎችንና ፅንሰ ሃሳቦችን ለመግለፅና ለማብራራት ከመታገል ተረቶችንና ገጠመኞችን አሊያም አባባሎችን መጠቀም ያ ብልህነት ነው። የተፈለገውን መልዕክት በቀላሉ ከማድረሱም ባሻገር ስነ-ፅሑፋዊ ውበትን ከፍ ያደርጋል። “የመደመር መንገድ” መፀሐፍ ደግሞ  በዚህ አይታማም። ገፅ 161 ላይ  የቀረበውን የጥንዶቹን ታሪክ እንመልከት፡፡
ሁለት ወጣት ጥንዶች ዘወትር ማዕዳቸውን የሚቋደሱት በመስኮት አሻግረው ውጭውን እየተመለከቱ ነበር። አንድ እለት ሚስት ከወዲያኛው ኮንዶሚኒየም ልብስ የምታሰጣ ሴት ስታይ ቆይታ፣ “አየኻት ውዴ፣ ያች ሴት ልብሱ ሳይጸዳ ስታሰጣው? ሰነፍ ሰራተኛ መሆን አለባት” ትለዋለች። ባል ቀና ብሎ ተመልክቷት፣ መልስ ሳይሰጥ ተመልሶ ወደ ምግቡ  አቀረቀረ። ዝምታው ከክፋት አልነበረም። ሚስቱን አንድ ቁም ነገር ሊያስተምራት ፈልጓል። ሌላ ጊዜም ቁርሳቸውን እየበሉ ሳለ፣ ያችው ሴት ልብስ አጥባ ልታሰጣ ወጣች።  ሚስትም አሻግራ እያየቻት፤ “ይህቺ ሴትዮ ልብስ እንዴት እንደሚታጠብ የምታውቅ አይመስለኝም” አለች በብስጭት።
አንድ ቀን ግን ለራሷም እየገረማት፤ “ዛሬ ገና ልብሱን ንፁህ አድርጋ አጥባዋለች” ስትል ለባሏ ነገረችው። ባልየው ወደ ወጭ አሻግረው ወደሚመለከቱበት መስታወት እጇን ይዞ ይወስዳትና፡- “ይኸውልሽ ውዴ፤ ድሮም ቢሆን ሴትየዋ የምታጥበው ልብስ ንጹህ ነበር። መስኮቱን ዛሬ ጠዋት ነው በኦሞ የወለወልኩት! … ለዚያ ነው ድሮ በቆሻሻ መስታወት አሻግረሽ እያየሻት፣ ቆሻሻ ልብስ የምታሰጣ የመሰለሽ…”  ሲል እውነቱን ነገራት። ትልቅ ቁም ነገርም አስተማራት።
መጽሐፉ ውስጥ በተደጋጋሚ ከተወሱ ነገሮች አንዱ የጠ/ሚኒስትሩ የመጀመሪያው የፓርላማ ንግግራቸው ነው:: ለፓርላማ ንግግራቸው ለማቅረብ ያዘጋጁትን ፅሑፍ ለጥቂት ወዳጆቻቸው አሳይተዋቸው ነበር- ለአስተያየት፡፡ ብዙዎቹ ያልወደዱለት ታዲያ ለእናታቸው ያቀረቡትን ምስጋና እንደነበር ያስታውሳሉ። ምክንያታቸው ደግሞ ያልተለመደ ነው የሚል ነው። ጠ/ሚኒስትሩ ግን እናታቸውን በፓርላማው ፊት አመሰገኑ። የሰሙት ሁሉ ወደዱት።
በርግጥም ወላጅ እናታቸው ውዳሴና ክብር የሚገባቸው ጠንካራ ሴት ናቸው። የኤሌክትሪክ ብርሃን በሌለበት የገጠር ከተማ ውስጥ የሚኖሩ ሴት፣ ዓይናቸውን አርቀው፣ የዘመንን ግድግዳ ጥሰው፣ በቀጣዩ ዘመን “የሀገር መሪ ይሆናል” ያሉትን ልጃቸውን ለማይቀረው ሃላፊነት ለማዘጋጀት፣ መትጋታቸውና ተስፋ መለኮሳቸው  የሚደነቅ ነው።
የዶክተር ዐቢይ እናት፣ ልጃቸው የሀገር መሪ እንደሚሆን ጠንቅቀው አውቀው፣ ሌሎችም ይህን አምነው እንዲቀበሉ ማድረጋቸው ያስገርማል። የማታ ማታ ዶ/ር ዐቢይ ጠ/ሚኒስትር ሆነው ሲሾሙ ታዲያ ብዙዎች የሚያውቋቸው አልተደነቁም፡፡ የጠበቁት ነው የሆነው!
“መደመርና እርቅ” የተለያዩ ሀገራት ተሞክሮዎችን በማሳያነት በማቅረብ፣ ለእኛም ሀገር ቀጣይ ድልድይ ለመዘርጋት ሀሳብ የሚያመነጭ! ነው። በተለይ ከአንደበት የሚወጣ  ክፉ ቃል የሚያመጣውን መዘዝና ጣጣ ለማሳየት ይሞክራል።
ዶ/ር ዐቢይ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው በተሾሙ ማግስት ወደ ተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በመጓጓዝ ያደረጉት ንግግርና ህዝባዊ ውይይትም፣ ለዓመታት የተዘራውንና የተሰራጨውን የጥላቻና ቁርሾ ለመንቀል ያለመ ነበር- በበጎ ቃል ክፉውን በማርከስ።
“ብረሳሽ ቀኜ ይርሳሽ” … በሚለው ርዕስ  የተንጸባረቀው ሃሳብ፣  ሰው ሰው የሚሸትና ሆድ የሚያባባ ነው። አገር መሪነት የቤተሰብን መብትና ነፃነት የሚነጥቅ ሃላፊነት መሆኑን  ያሳየናል። ለህዝብና ለአገር ሲባል፣ ልጆችና ትዳርን ያህል ዋጋ መክፈል የግድ እንደሚልም እንገነዘባለን፡፡
ጠ/ሚኒስትሩ በሰኔ 16ቱ የድጋፍ ሰልፍ ላይ የሚያደርጉትን ንግግር  በመኖሪያ ቤታቸው ተቀምጠው ሲያዘጋጁ ከልጃቸው ጋር የተለዋወጡትን ሃሳብ ያነሳሉ፡-
“አባቢ ምን እየሰራህ ነው?” አለችኝ።
ፀጉሯን ዳበስ ዳበስ እያደረግሁ “ ነገ ብዙ ሰዎች የሚሰበሰቡበት ትልቅ ሰልፍ አለ… እዚያ ላይ ለሰዎቹ የምናገረውን ንግግር እያዘጋጀሁ ነው።”
“እንዴ ንግግር ይዘጋጃል እንዴ?... ለምን ዝም ብለህ አትነግራቸውም” ግራ በመጋባት ቆንጅዬ ዐይኖቿን ጠበብ ሰፋ እያደረገች አስተዋለችኝ። “ቆይ ደሞ ለምን ሌላ ሰው አይነግራቸውም?... አንተ ሁልጊዜ መስራት ብቻ ነው እንዴ? መቼ  ነው ከኛ ጋር የምትጫወተው?” ስትል ቅሬታ አዘል አስተያየቷን አከለች።…
ይህ እንግዲህ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ሞት ተደግሶ የነበረበት የመስቀል አደባባዩ ዝግጅት ነው። ህይወት በየመልኩ ሲታይ ደስ ይላል። አንዲት ሁሉን ነገር በራሷ ዓይኖች ብቻ የምታይ፣ ህዝብ ቤቷ ገብቶ አባቷን እንዲነጥቃት የማትፈልግ፣ “ከፈለገ ሌላ ሰው ይንገራቸው” የምትል፣ እምቦቀቅላ ህፃን ያስተዋውቀናል - ጽሁፉ።
“የቸገረው ዱቄት ከንፋስ ይጋባል” በሚል የቀረበው ክፍል፤ በለውጡ ሰሞን በሱማሌ ክልል ተፈጥሮ የነበረውን ቀውስና የመገንጠል ምኞት የሚዳስስ ነው። እጀ ረዥሙና ከስልጣን የተባረረው ቡድን ከፍተኛ የጥላቻ ፕሮፓጋንዳ በመንዛት፣ ሀገሪቱን በደም ሊነክራት የወሰደውን እርምጃ፣ የሸረበውን ሴራ፣ የቆፈረውን ጉድጓድ… እስከ ዛሬ ከምናውቀው በላይ  በጥልቀትና በስፋት ይነግረናል።
የደራሲው  ትልቁ ስኬት፤ መልዕክቶቹን በደንብ ማስተላለፍ የሚችልበትን የአጻጻፍ ስልት መምረጡ ነው። እንዳይሰለች በምሳሌያዊ ንግግሮች ያዋዛል። የታሪኩ ፍሰቱ አይደናቅፍም፡፡ በዚህም የትኛውም አንባቢ መልእክቱን በሚገባ የራሱ ማድረግ ይችላል።
በተለይ ደግሞ በተጠና መንገድ የተሰራውና ሙሉ የስነ-ልቡናዊ ስብራታችንን መነሻ የሚያሳየው “የማን ዘር ጎመን ዘር”፤ በእጅጉ የወደድኩትና ያደነቅሁት ክፍል ነው። ይህንን ክፍል ለመጻፍ ምናልባት ሀገራዊ ስነ-ቃሎችን ሆነ ብሎ መሰብሰብና ማጥናት ሳይጠይቅ አይቀርም።
“አባቱ ነበር ቀንበር አንጠልጣይ
ልጁ ደረሰ በጩቤ ዘንጣይ፣
አባቱ ነበር ዳዊት ደጋሚ
ልጁ ደረሰ በእርሳስ ለቃሚ፤
አባቱ ነበር ከብት አባራሪ
ልጁ ደረሰ ቅልጥም ሰባሪ፤”
ይህን የመሳሰሉ የጨፈገጉ... የመረሩ... በደም የተለቀለቁ አያሌ ስነ-ቃሎች ይኖሩበታል። የባሰም ደግሞ አለላችሁ፡፡ እነሆ፡-
“ጀግኔ ለጠላው ሰው፣ አያውቅም መሳሳት
ሚስቱን ባንድ ጥይት፣ ቤቱን በገል እሳት”
እነዚህንና መሰል የመገዳደል  ስነ-ቃሎች በመጽሐፉ ውስጥ ስናገናኝ፣ እንዴት ራሳችንን በራሳችን ስናሳብድ እንደኖርን ያረጋግጥልናል። የመጽሐፉ ከኤርትራ ጋር የተካሄደውን እርቀ ሰላም ጨምሮ ሌሎች ርዕሰ ጉዳዮችን እያነሳ፣ እስከ ኮሮና ፈተና ድረስ ይዞን ይዘልቃል። የሀገሪቱን አጠቃላይ የመደመር ጉዞ ከዋዜማው ጀምሮ የተረከበትና በምልሰት የበሻሻን ውብ ልጅነት የቃኘበት መንገድ በራሱ  የሚደነቅ ነው።
ዳሰሳዬን ከመቋጨቴ በፊት በነካ እጄ ጥቂት ለክፉ የማይሰጡ ጉድለቶችን ልጥቀስ።  ለምሳሌ ገጽ 72 እና ገጽ 128 ላይ የተደጋገሙት አንቀጾች፣ ቢያንስ ከአርታኢ ዓይን ማምለጥ አልነበረባቸውም።
በመጀመሪያው የመደመር መጽሐፍ ውስጥ የተስተዋሉ አንዳንድ ስህተቶች፣ በዚህኛው መደገማቸው ቀር ያሰኛል። “አውሮፓ” እና “አውሮጳ” ን እያቀያየሩ መጠቀም እንዲሁም “ማዕቀፍ” በማለት ፋንታ  “ማሕቀፍ” የሚሉ ዓይነት ስህተቶች አርታኢውን  የሚያስወቅስ ነው።
በማጠቃለያዬ “የመደመር መንገድ”ን ለማንበብ ፖለቲከኛ ወይም ካድሬ መሆን አያስፈልግም። ጠ/ሚኒስትሩን መውደድም መጥላትም አያስፈልግም። ለምን ቢሉ? ከፖለቲካው ውጭ ለጠቅላላ ዕውቀትም የሚነበብ መፅሐፍ ነው። ጥበብ አፍቃሪ ለውበቱና ለቋንቋው ሲል ሊያነበው ይችላል። እኔ በበኩሌ ደስ እያለኝና ወድጄው ነው  ያነበብኩት። እናም በአጭሩ አንብቡት እያልኳችሁ ነው።


Read 1074 times