Print this page
Saturday, 10 April 2021 12:04

የሶማሌ ክልል የእስረኞች አያያዝ ልዩ ትኩረት ይሻል - ኢሰመኮ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 በሶማሌ ክልል የእስረኞችን አያያዝ በተመለከተ የተወሰነ መሻሻል የታየባቸው ቦታዎች ቢኖሩም፤ አሁንም ብዙ ማሻሻያዎች የሚስፈልጋቸው ጉዳዮችና ቦታዎች መኖራቸውን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አስታወቀ፡፡
 ኮሚሽኑ መጋቢት 13 ቀን 2013 ዓ.ም. በጅግጅጋ ከተማ ፖሊስ ጣቢያዎች ያደረገውን ፈጣን ክትትል ጨምሮ በተደጋጋሚ ጊዜያት በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የፖሊስ ጣቢያዎችንና ማረሚያ ቤቶችን በመጎብኘት፣ የእስረኞችን የሰብአዊ መብቶች አያያዝ ሁኔታ በተመለከተ ክትትል አድርጓል፡፡ ከእስረኞች፣ የፖሊስ መምሪያዎችና የማረሚያ ቤቶች ኃላፊዎች እንዲሁም ከሌሎች ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የክልሉ የሕግ አስከባሪና የአስተዳደር አካላትም ጋር መወያየቱ ተጠቁሟል፡፡  
በክትትሉ ከተጎበኙት ቦታዎች በተለይም በጅግጅጋ ከተማ ካውንስል ፖሊስ መምሪያ በተለምዶ ሃቫና ተብሎ በሚታወቀው የተጠርጣሪዎች ማቆያና በ04 ቀበሌ አቅራቢያ የሚገኘው የካውንስሉ ማቆያ የተጠርጣሪዎች አያያዝ እጅግ አሳሳቢ መሆኑን ኮሚሽኑ አመልክቷል፡፡
በእነዚህ እስር ቤቶች ተጠርጣሪዎች ንፅህናቸው ባልተጠበቀና በጣም በተጨናነቁ ክፍሎች ለጤና ጎጂ በሆነ መልኩ እንደሚያዙ፣ ከፍተኛ የምግብ እጥረት መኖሩንና በወንጀል ተጠርጥረው የታሰሩ ሕጻናት በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ አንቀፅ 172 መሰረት ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ በዋስ እንዲለቀቁ ቢጠበቅም፤ ከዚህ በተቃራኒ ከ 18 አመት በታች ያሉ ሕጻናት እስረኞች፣ ለአካለ መጠን ከደረሱ ሰዎች ጋር ተቀላቅለው እንደሚያዙ ኮሚሽኑ አረጋግጧል፡፡
በተጨማሪም፤ በጅግጅጋ ከተማ 04 ቀበሌ አቅራቢያ በሚገኘው የካውንስሉ ማቆያ የሚገኙ ተጠርጣሪዎች፤ የቤተሰብ ጉብኝት መከልከል፣ ፍርድ ቤት በጊዜ ያለመቅረብና በተወሰኑ እስረኞች ላይ ድብደባም ጭምር እንደደረሰባቸው ኮሚሽኑ ከታሳሪዎች አሳማኝ ምስክርነት መቀበሉን አስታውቋል፡፡
ኮሚሽኑ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በግንባር ካደረገው ውይይት በተጨማሪ ለሚመለከታቸው የከተማውና የክልሉ አስተዳደር አካላት በተጻፈ ደብዳቤ፤ ከላይ የተጠቀሱት የሰብአዊ መብቶች ጥሰት በአስቸኳይ እንዲታረሙ ምክረ ሃሳቦችን አቅርቦ ነበር። በተለይም የሃቫና ፖሊስ ጣቢያ ካለበት አስቸጋሪ ሁኔታ አንጻር በአፋጣኝ እንደሚዘጋ በተደጋጋሚ ለኮሚሽኑ ቃል የተገባ ቢሆንም፣ እስካሁን ድረስ ተግባራዊ አለመሆኑን አመልክቷል፡፡
ከሀቫና ፖሊስ ጣቢያ እስረኞችን ወደ ጎዴ ማረሚያ ቤት በመላክ የጣቢያውን መጨናነቅ ለመቀነስ የተሞከረ ቢሆንም፤ ይህ የተደረገው ከእስረኞችና  ከቤተሰቦቻቸው ጋር በቂ ምክክር ሳይካሄድ መሆኑንና የጎዴ ማረሚያ ቤት በራሱ ከፍተኛ መጨናነቅ ያለበት በመሆኑ ታሳሪዎች ቅሬታቸውን ለኮሚሽኑ ተናግረዋል፡፡ በጎዴ ማረሚያ ቤት 14 ክፍሎች ያሉ ሲሆኑ በጉብኝቱ ወቅት 470 እስረኞች እንደነበሩ ኮሚሽኑ ጠቁሟል።  
በወንጀል ውስጥ ገብተው በመገኘታቸው በፍርድ ቤት እስራት የተፈረደባቸውና ከ50 በላይ  የሆኑ ሕፃናት በጎዴ ማረሚያ ቤት ለአካለ መጠን ከደረሱ እስረኞች ጋር ተቀላቅለው እንደሚገኙ የጠቆመው ኮሚሽኑ፤ ይህም ወጣት አጥፊዎች (ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ሕጻናት) ለአካለ መጠን ከደረሱ እስረኞች ተለይተው መያዝ እንዳለባቸው የሚደነግገውን ህግ የሚጥስ በመሆኑ አፋጣኝ ትኩረትና መፍትሄ የሚሻ መሆኑን አሳስቧል፡፡   
በሌላ በኩል ኮሚሽኑ፣ በክልሉ ውስጥ ተዘዋውሮ ክትትል ባደረገባቸው የፖሊስ መምሪያዎች የሚገኙ ተጠርጣሪዎች አያያዝ ላይ የተደረጉ መሻሻሎች እንዳሉ መመልከቱን ጠቁሞ፤ ቢያንስ በአንድ ጣቢያ በተወሰኑ ታሳሪዎች ላይ ድብደባ ስለመፈጸሙ ቢገለጽም፤ ስልታዊና የተስፋፋ አካላዊ ጥቃት ስለመኖሩ መረጃ አልተገኘም ብሏል፡፡ በተለይ በጅግጅጋ ከተማ በሚገኙት የዞንና የክልል ፖሊስ ጣቢያዎች፣ ተጨማሪ የማቆያ ቦታዎችን በማዘጋጀትና በእስረኞች ሰብአዊ አያያዝ ረገድ አበረታች እርምጃዎች መታየታቸውን ኢሰመኮ ገልጧል፡፡    
እነዚህ አበረታች እርምጃዎች በሁሉም የእስር ቦታዎች እንዲስፋፉና በተለይም የንጽህና ችግርና የቦታ ጥበት መጨናነቅ ለመቅረፍ፣ የቤተሰብ ጉብኝት መብት በሁሉም ቦታዎች በተሟላ መንገድ ለማረጋገጥ፣ እንዲሁም ታሳሪዎች ፍርድ ቤት በጊዜው መቅረባቸውንና የጥፋተኛ ፖሊስ አባላትን ተጠያቂነት ለማረጋገጥ ተገቢውን እርምጃዎች ሁሉ መውሰድ ያስፈልጋል ብሏል -ኮሚሽኑ፡፡
በተጨማሪም በጅግጅጋ ካውንስል ፖሊስ መምሪያ ስር የሚገኙ በወንጀል ነክ ጉዳዮች ተሳታፊ ናቸው በሚል ተጠርጥረው የታሰሩ ሕጻናት፣ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ አንቀፅ 172 መሰረት በአፋጣኝ በዋስ ሊለቀቁ እንደሚገባ ኢሰመኮ አስታውቋል፡፡
የሶማሌ ክልላዊ መንግስት፣ ሰብአዊ መብቶችን በማክበርና በማስከበር ረገድ በወሰዳቸው እርምጃዎች የታዩ መሻሻሎች የሚያበረታታ መሆኑን የገለጹት የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ፤ በተለይ ወንጀል ውስጥ ገብተው የተገኙ ሕፃናት እስር ጉዳይ ልዩ ትኩረትና ፈጣን እርምጃ ያስፈልገዋል ብለዋል።

Read 1149 times
Administrator

Latest from Administrator