Saturday, 10 April 2021 12:25

የትርጉም ሙያ ትምህርት በድግሪ ሊሰጥ ነው

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

  የትርጉምና አስተርጓሚነት ሙያን በዩኒቨርሲቲዎች በድግሪ ደረጃ ለማስተማር የሚያስችል ስርአተ ትምህርት ተዘጋጀ ሲሆን የትርጉምና ቋንቋን የተመለከቱ ሶስት ግዙፍ ተቋማትም በመቋቋም ላይ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ከአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲና ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በሃገሪቱ የመጀመሪያውን ትርጉምና አስተርጓሚነት የተመለከተ ብሄራዊ ኮንፍረንስ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርስቲ ሰሞኑን ተካሂዷል፡፡
በዚህ ኮንፍረንስ ከተለያዩ የሃገሪቱ ዩኒቨርስቲዎች የተውጣጡ የቋንቋና የስነ-ፅሁፍ እንዲሁም የታሪክ ምሁራን፣ የባህልና ቱሪዝም ሚንስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ሂሩት ካሳ የተገኙ ሲሆን በሃገሪቱ የትርጉምና አስተርጓሚነት ሙያ ደረጃንና የወደፊት እቅድን የተመለከቱ  ጥናቶች በምሁራን ቀርበው ውይይት ተካሂዶባቸዋል።
በመድረኩ ከቀረቡት ጉዳዮች መካከል ያ የትርጉምና አስተርጓሚነትን ሙያ በድግሪ ደረጃ በዩኒቨርስቲዎች ለማሰልጠን የተዘጋጀው ስርዓተ ትምህርት (ካሪኩለም) ይገኝበታል።
ስርዓተ ትምህርቱ 13 ሞጁሎች ያሉት ሲሆን በ4 ዓመት የዩኒቨርስቲ ቆይታው አንድ ተማሪ 14 ክሬዲት ሃወር (ክፍለ ጊዜ) ስልጠናውን  እንዲወስድ ይጠበቅበታል።
ስርዓተ ትምህርቱን ያዘጋጁት ከሰባት ዩኒቨርስቲዎች የተውጣጡ 8 መምህራን በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር አስተባባሪነት ሲሆን በስርዓተ ትምህርቱ ከተካተቱት መካከል 4 ኮርሶች የትምህርት አሰጣጡን በተግባር የታገዘ የሚያደርጉ ናቸው ተብሏል።
በመስኩ የሚሰለጥኑ ባለሙያዎች በሃገሪቱ በትርጉምና አስተርጓሚነት ከመሰማራታቸው በፊት ልክ እንደ ጤና ባለሙያዎች ትርጉምን ሳያዛቡ ለማቅረብ ቃለ-መሃላ የሚፈፅሙበት ሁኔታም ይኖራል ተብሏል።
ከዚሁ ከቋንቋ ልማትና ትርጉም ጋር በተያያዘ በቅርቡ የፀደቀውን የሃገሪቱን የቋንቋ ፖሊሲ መሰረት ያደረጉ ሶስት ተቋማት እየተቋቋሙ መሆኑንም በኮንፈረንሱ ላይ የተገኙት የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶ/ር ሂሩት ካሳው አስታውቀዋል።
የትርጉም ተቋሙ የትርጉም ስራ በስነ-ምግባር የተመራ፣ ከሃገሪቱ ህጎች ያልተቃረነ መሆኑን የሚከታተልና የሚቆጣጠር ይሆናል ተብሏል።
በቅርቡ በፀደቀው የሃገሪቱ የቋንቋዎች ፖሊሲ መሰረት ከአማርኛ በተጨማሪ አፋን ኦሮሞን፣ ሶማሊኛን ፣ አፋርኛና ትግርኛ የሃገሪቱ የስራ ቋንቋ እንዲሆኑ ታጭተዋል።
በአሁኑ ወቅት በሃገሪቱ ከሚነገሩ ቋንቋዎች መካከል 53 ያህሉ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት እየተሰጠባቸው መሆኑም በዚሁ ጉባኤ ላይ ተገልጿል፡፡
በዚህ ጉባኤ ላይ ሌላው የቀረበው ጉዳይ መስማት የተሳናቸው የሚጠቀሙበት የምልክት ቋንቋ ጉዳይ ሲሆን በሃገሪቱ ከሚያስፈልገው የቋንቋው ባለሙያዎች አንፃር የባለሙያዎች ቁጥር  በእጅጉ አናሳ መሆኑን የቀረበው ጥናት አመልክቷል።
በሃገሪቱ ከ5 ሚሊዮን ያላነሱ ቋንቋውን የሚጠቀሙ መስማት የተሳናቸው ያሉ ቢሆንም ከ80 በመቶ በላይ የሚሆኑት በቋንቋቸው ትምህርት  እየቀረበላቸው ባለመሆኑ ከትምህርት አለም መገለላቸው ተመልክቷል።
በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ሁለት የመንግስት ት/ቤቶች ብቻ ከደረጃ በታች በሆነ አቅም ትምህርቱን እየሰጡ እንደሚገኙ በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ደግሞ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ብቻ እየሰጠ እንደሚገኝና ከፍላጎቱ አንፃር በእጅጉ ዝቅተኛ መሆኑን ጥናት ያቀረቡ ምሁራን አስገንዝበዋል።


Read 908 times