Saturday, 10 April 2021 12:52

ከአለመማራችንም ቢሆን እንማር!

Written by 
Rate this item
(6 votes)

አንድ ሰባ ሰማኒያ ዘመን የሆናቸው ሽማግሌ፤ ተማሪ ቤት ገብተው ሲማሩ አንድ ተማሪ፤
“አባቴ ፤ ዛሬ ተምረው ከእንግዲህ ወዲህ ሊሾሙበት ነው? ወይስ ሊከብሩበትና ሊታዩበት?” ቢላቸው፤ ሽማግሌው፡-
“ልጄ ልሾምበት፣ ልከብርበትና ልታይበትስ ብዬ አይደለም። ነገር ግን የማይቀረው ሞት ሲመጣ፣ መልአክ-ሞቱ ይዞኝ ወደ ፈጣሪ ሲቀርብ ወዴት አገኘኸው?” ሲለው “ከአትሮኑሱ (መጽሐፍ ማስቀመጫና መግለጫ ገበታ) እግር አገኘሁት” ብሎ እንዲመሰክርልኝ ብዬ ነው” አሉት።
ሽማግሌው “በየትኛውም እድሜ መማር ራሱ ጽድቅ ነው”፤ ነው የሚሉት። እውነት ነው። የድንቁርና ዳር ድንበር በየትኛውም እድሜ አለመማር ነው። መማር ግን ፊደል መፈደል ፣ ቀለም መቅለም ብቻ አይደለም። ከመከራችን መከር፣ ከአሳራችንም ሳር ለማብቀል ይቻላል። ደንቆሮ አእምሮዬን ይዤ ሰማይ ቤት አልገባም። እጌታም ፊት አልቀርብም ያሉት አዛውንት፤ ይህ ገብቷቸዋል። አንድ ጊዜ ደግሞ አንድ የዩኒቨርስቲ ተማሪ የአክስቱ ልጅ ወደአለችበት ሄዶ አንድ የምስራች ይነግራታል።
“ስሚ ዛሬ ምን ሰማሁ መሰለሽ?”
“ምን ሰማህ?”
“ዘንድሮ ሀሌ ኮሜት የተባለችው ኮከብ፣ በኢትዮጵያ ሰማይ ላይ ልትታይ ትችላለች” ሲሉ የጃፓን የስነ-ሊቃውንት ገለጹ አላት። የአክስቱ ልጅ የሳይንስ ተማሪ ናት። ዜናው እጅግ አስደሰታት። ከተቀመጠችበት ተነስታ አቅፋ ሳመችው። ይህ ሁሉ ሲሆን ቁጭ ብላ ከርቀት ታስተውል የነበረችው ታናሽ እህቱ፣ የ12ኛ ክፍል ተማሪ እንዲህ ያስፈነደቃቸው ነገር ምን እንደሆነ ለማወቅ ጓጉታ ስትሮጥ ትመጣና፤
“ምንድነው እንዲህ ያስደሰታችሁ? እስቲ ለኔም ንገሩኝ?” ብላ ትጠይቃቸዋለች። ታላቅ እህቷ እንዲህ ስትል አስረዳቻት፡-
“ምን መሰለሽ፤ ሃሌ ኮሜት ማለት በ76 ዓመታት አንድ ጊዜ በዓለም ላይ እንደ ፀሀይ ልታበራ የምትችል ብሩህ ኮከብ ናት። ታዲያ ይህቺ ኮሜት እንደ አጋጣሚ ዘንድሮ ኢትዮጵያ ላይ ልትታይ ትችላለች። ብለው ሳይንቲስቶች ገመቱ። የእኛ ትውልድ እድለኛ ትውልድ ነው። ከእንግዲህ እኮ ሃሌ ኮሜት በዓለም ለመታየት ሌላ 76 ዓመት ያስፈልጋታል። የእኔና የአንቺ ትውልድ ደግሞ አያያትም ማለት ነው። ደስ አይልም?”
“ግን ይቺ ኮከብ በመታየቷ ከሌላው ጊዜ ምን የተለየ ነገር ይኑራት?”
“ለውጡማ ምናልባት በዚያ ቀን 24 ሰዓት ሙሉ ብርሃን ይኖረናል። 24 ሰዓት ፀሀይ ይሆናል እንደ ማለት ነው።” እህትየዋም ፊቷን ቅጭም አደረገችና፤
“ወይ መከራ!! 24 ሰዓት ሙሉ ልንማር ነው ማለት ነው?” አለች ምርር ብላ።
ያለንበት ዘመን ትምህርት እንደ ጦር የሚፈራበት ሆኗል።
“በጠቅል ጊዜ ያልተማረ ማዘኑ አይቀርም እያደረ።” እያለ እየዘመረ ያደገ፣ ትንቢቱ ተፈጸመ እንዴ? ይል ይሆናል። ትምህርት በትምህርት ቤት የምናገኘው ብቻ አይደለም። የትምህርት ቤቱም ትምህርት ቢሆን ማጣጣሚያው ኑሮ ነው። የዛሬውን ከመስማት ከማየት እንደምንማር፣ የትላንቱን ከታሪክ መማር አለብን። ለዚህ ደግሞ የማንበብ ባህላችንን ማዳበር ግድ ይለናል። ያየነውን አላየንም፣ የሰማነውን አልሰማንም ያልን እለት ነው የመጨረሻ የድንቁርና ደረጃ። መማር ዘርፈ-ብዙ ነው። “ለምን ሆነ?” ማለት፣ “እንዴት ሆነ?” ማለት መልመድ አለብን። “ብልህ ሰው ትክክለኛ መልስ የሚሰጥ አይደለም። ትክክለኛውን ጥያቄ የሚጠይቅ እንጂ” እንዲሉ ትክክለኛ ጥያቄ መጠየቅ መልመድም አንድ የሚያስፈልገን ትምህርት ነው፤ በስተ እርጅናም ሆነ በወጣትነት።
የእያንዳንዷ ቀን ልምዳችን አስተማሪያችን ናት። ወህኒ ቤት ታስሮ የነበረ አንድ እብድ “ሞኝ ያስራል ብልጥ ይማራል!” ይል ነበር። ትምህርት የትም አለ። ከምንም ነገር መማር ይቻላል። ዋናው ማየት፣ ማስተዋልና ማዳመጥ ነው። ድርቁ ካደረሰብን ጥፋት መማር አለብን። ስለ ድርቁ ከማናገሩ የዘንድሮ ተመራጮችም። እህል አግኝተን ውሃ ማቅረብ ሲያቅተን ከማየትም መማር አለብን። እንደ ኢትዮጵያ ባለች የምርጫ መርህና አተገባበር ገና ጥሬ በሆነባት ሀገር ማሸነፍ ሳይሆን መወዳደር የነገር ሁሉ አሀዱ መሆኑን መማር ያስፈልጋል። የአሁኑ ምርጫ ተመረጥኩም አልተመረጥኩም ለመጪው 5 ዓመት ከዛሬው መዘጋጀት ጀምሬአለሁ ብሎ ማሰብ ብዙ ኪሳራ እንደሌለው መማር ተገቢ ነገር ነው። እጂን አጣጥፎ ከመቀመጥ፤ የተሻለ አወዳደቅን ማየትና መማር ይበጃል። ስርዓት መገንባት ሂደት እንጂ በአንድ ጀምበር ፊርማ “አበጀህ-አበጀሽ” ተባብሎ የሚያበቃ ጉዳይ አይደለም። ለስንት ማህበራዊ ድርና ማግ የተሳሰረን ህዝብ ጉዳይ “እኔ ነኝ መፍትሄህ! ምልክቴ ይሄ ነው! ይሄን እሰራለሁ” የሚለውን ፈሊጥ ለልመና ዜማ ብቻ ከተጠቀምንበት የወረቀት ጨዋታ ነው።
“እምነት ሲታመም ሺ ወረቀት መፈራረም!” እንዲል የሀገራችን ደራሲ።
“ሁሉ ነገር አልቆለታል” የሚል ተስፋ ቆራጭ አካሄድም ጨለምተኛ ነው። አገር ያለ ተስፋ የትም አትደርስም። ተስፋ ደግሞ ባካበትነው ልምድና የችግራችን ጓዳ ሁሉ ለመማር ካለን ዝግጁነት ይመነጫል። ለመማር እልህ እንጂ ቁጣ አያስፈልገንም። ከሰከነ መንፈስ ነው ጠንካራ ጥያቄ የሚወለደው። ጠንካራ ጥያቄ የሚለወጥ መንግስት፣ የሚያስብ ትውልድ ይፈጥራል። በዚህ መንገድ ላይ የሚማር፣ የሚወያይ ዜጋ ለማፍራት እድሉ አለን። በአለው አቅምና የእውቀት ጥሪት የመላወስ ሙከራ ማቆም የለበትም። የጠፋው ጠፍቷል- በቀረው መራመድ ያሻል። አንዲት አሮጊት እንዳሉት ነው፤ ጎረቤታቸውን ሊጠይቋት ጎራ ብለዋል። በጨዋታ መሃል፤
“ምነው መውለዱን አቆምሽ?” ይሏታል።
“ኧረ ምን በወጣኝ ብዙ ወልጃለሁ፤ ከእንግዲህ ንክችም አላደርግም” ትላለች፤ ጎረቤታቸው በምሬት።
አሮጊቷም፡- “አዬ ልጄ ተይ እንዲህ አትማረሪ!”
አሁን ከምትወልጅው ልጅ
ሞኝ ወጥቶለት
ክፉ ወጥቶለት
ሞት ወስዶለት
የሚተርፈው ትንሽ እኮ ነው!!” አሏት።
የተረፈንን የተማረ ሃይል አስተባብረን ለመማር ዝግጁ መሆን ያስፈልጋል። መልአከ ሞት “ከአትሮኖሱ እግር አገኘሁት” ብሎ እንዲመሰክር እንማር። እስካሁን ከአለመማራችንም ቢሆንም እንማር!!
የወቅቱ ጥቅስ፡- “ሁሉ ነገር አልቆለታል” የሚል ተስፋ ቆራጭ አካሄድም ጨለምተኛ ነው። አገር ያለ ተስፋ የትም አትደርስም።”


Read 12356 times