Print this page
Saturday, 03 April 2021 00:00

ከቴአትር የተኳረፈው ተመልካች እንዴት ይመለሳል?

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

  የቴአትር ሥርአተ ትምህርት ክለሳ እየተደረገበት ነው

          የቴአትር ጥበብ የአንድ ሀገር ታሪክ፣ ባህል፣ የማህበረሰብ ስነ-ልቦና የአኗኗር ዘይቤና አጠቃላይ ማንነት የሚንጸባረቅበት ዘርፍ ቢሆንም የጠቀሜታውን ያህል ትኩረት አለማግኘቱን የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ። በዚህም ምክንያት ከጊዜ ወደ ጊዜ የቴአትር ተመልካቹ ፊቱን ከቴአትር እየመለሰ ሌሎች የመዝናኛ አማራጮችን ማማተር ከጀመረ ከራርሟል።
ታዲያ ይሄን የቴአትር ተመልካች ለመመለስና ዘርፉን ለማሳደግ ምን መደረግ አለበት? በዩኒቨርስቲዎች የሚሰጠው የቴአትር ትምህርት ወጥነት የሌለውና በዘፈቀደ እንደ ዩኒቨርስቲዎቹ ፍላጎት የተቀረፀ መሆኑ ምን ጉዳት ያመጣል? የቴአትር ስርዓተ ትምህርት በአገር አቀፍ ደረጃ በተሰራው የትምህርት ፍኖተ ካርታ ውስጥ የታየ ሲሆን አንጋፋው አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ሁሉንም ያማከለ የቴአትር ስርዓተ ትምህርት ቀርፆ እንዲያቀርብና ሁሉም ቴአትር የሚያስተምሩ ዩኒቨርሲቲዎች እንዲጠቀሙበት በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሃላፊነት ተሰጥቶት የነበረ ሲሆን ዩኒቨርሲቲው ያረቀቀው ስርዓተ ትምህርት ግን በሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ይሁንታን አላገኘም- የሌሎችን ዩኒቨርሲቲዎች ነባራዊ ሁኔታ ያላገናዘበ ነው በሚል ይሄን ተከትሎም ስርዓተ ትምህርቱ በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት እንደገና እንዲከለስ ሚኒስቴሩ ያሳሰበ ሲሆን በዚህም መሰረት መጋቢት 13 እና 14 ቀን 2013 ዓ.ም በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የክለሳ አውደ ጥናት ተካሂዷል። በዚህ አውደ ጥናት ላይ 14 ዩኒቨርሲቲዎችና የሁለት አንጋፋ ቴአትር ቤቶች ተወካዮች ተሳትፈዋል። በአውደ ጥናቱ ላይ የተገኘችው የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ በጉዳዩ ዙሪያ የቴአትር ቤቶች ተወካዮችንና የዩኒቨርሲቲ ሃላፊዎቹን አነጋግራለች። ሃሳባቸውም እንደሚከተለው ቀርቧል።               “የበፊቱ ሥርዓተ ትምህርት ገበያውን ያማከለ አልነበረም”
                       (አብዱልከሪም ጀማል፤ የሀገር ፍቅር ቴአትር ሥራ አስኪያጅ)


            እኛ  ዩኒቨርስቲ ገብተን ቴአትር በምንማርበት ጊዜ የነበረው ስርዓተ ትምህርት ገበያውን ማዕከል ያደረገ አልነበረም። ለምሳሌ እኔ ዩኒቨርስቲ የገባሁት በ1996 ዓ.ም ሲሆን የተመረቅሁት በ2000 ዓ.ም ነው። እና በእኛ ጊዜ የነበረው ትምህርት ኢንዱስትሪውን ያማከለ ባለመሆኑ ተማሪዎች አራት ዓመት ተምረው ይወጣሉ፤ ከዚያ በኋላ ገበያውን ሲቀላቀሉ ያለው ከባቢና እነሱ ያጠኑት ትምህርት ይለያይና ለሁኔታዎች ባዕድ ይሆኑ ነበር። አሁን ያንን ለማስታረቅ ነው በወልቂጤ ዩኒቨርስቲ አስተናጋጅነት ይሄ አውደ ጥናት የተዘጋጀው።
አውደ ጥናቱን ያዘጋጀውን ወልቂጤ ዩኒቨርስቲን የማመሰግነው ደግሞ “የቴአትር ቤቶች ልምድ ይጠቅማል፤ ግብአት እናገኝ ይሆናል” በሚል ከኢንዱስትሪው ማለትም ከቴአትር ቤቶች ሰው ጋብዟል። እኔም የተጋበዝኩት ከአንጋፋው ሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት  ነው። ኢንዱስትሪው ላይ ምንድን ነው ያለው?
ገበያው ምን ይፈልጋል፣ መጫወቻ ሜዳው ምን ይመስላል? የሚለውን እንደ ግብአት መውሰድ መፈለጉ ትልቅ ነገር ነው። እኛም የምንገነዘበው ነገር አለ። ተማሪዎች ተመርቀው ሶስተኛ ዓመትም ሆነው እንደ አፓረንትሽፕ ለጥናትም ወደ እኛ ይመጣሉ። ትምህርት ቤት ውስጥ ያለው የፕሮዳክሽን ሂደት እዚህ እኛ ጋር ካለው እውነታ ጋር ሙሉ በሙሉ ይለያያል። ያንን ነገር ለመላመድ ረጅም ጊዜ ይወስድባቸዋል። ይሄ ችግር መቀረፍ አለበት። ለምን? ተምረው ወደ ገበያው ነው የሚቀላቀሉት። ሲቀላቀሉ ደግሞ ለኢንዱስትሪው እንግዳና ባዕድ ሆነው መቆየት የለባቸውም። ስለዚህ ተምረው እንደገና መሬት ላይ ያለውን ተግዳሮት መቋቋም አቅቷቸው ወደ ሌላ መስክ ከሚሄዱ ቀድሞ ስርዓተ ትምህርቱ ላይ ተነጋግሮና ልዩነቶቹን አስታርቆ የሚያስኬድ ስርዓተ ትምህርት መቀረጽና በወጥነት የሚዘልቅ ሁኔታን ለመፍጠር ነው ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ሁሉንም ያሳተፈ አውደ ጥናት ያዘጋጀው። በዚህ በሁለት ቀን መድረክ አንቀጽ በአንቀጽ ተወያይተን ጥሩ መግባባት ላይ ደርሰናል። ከእኛም የወሰዱት ጥሩ ግብአት አለ።
ምርት አለ፤ ገበያው ምርቱን የመሸከም አቅም አይታይበትም ያልሽው ትክክል ነው። ትልቁ ፈተናም ይሄው ነው። አሁን እየተወያየንበት ያለውም የስርዓተ ትምህርትና ተያያዥ ጉዳይ ከዚሁ ጋር የተገናኘ ነው። ለምሳሌ አራት ዓመት ዩኒቨርስቲ ተምረሽ ስትወጪ የቴአትር ተመልካችን በተመለከተ ምንም ግንዛቤ ሳይኖርሽ ነው የምትወጪው፤ ይሄ አደገኛ ነው። አንድ ምርት ስትመርጪ ገበያውን ማዕከል ማድረግ የግድ ነው። ገበያ ከሌለ ወይም የገበያ ጥናት ሳታደርጊ ማምረት ኪሳራ ነው። ይህንን ማዕከል ያደረገ ትምህርትም በዩኒቨርስቲ የለም። ቅድም ከብሄራዊ ቴአትር የመጡት አንጋፋው የቴአትር አዘጋጅም ያቀረቡት አንኳር ሀሳብ ይሄው የተመልካች ጉዳይ ነው። ዩኒቨርስቲ ገባሽ ፤የቴአትር ፕሮዳክሽን ምንድን ነው? ቴአትር እንዴት ይጻፋል? አክቲንግና ዳይሬክቲንግ ምንድን ነው? እንዴት ይተወናል? እንዴት ዳይሬክት ይደረጋል? የሚለው ላይ ብቻ ነው ትምህርቱ የሚሰጠው። ስለዚህ ውይይቱና አውደ ጥናቱ ጠቃሚ ነው የምልሽ እንደ ቴአትር ቤት ብዙ የምናነሳቸው ጉዳዮች ስላሉ ነው፡፡ ተመልካች ለምን እራቀ? ለምን እንደ ድሮው አልሆነም? የሚሉትን ጉዳዮች ስናነሳ ብዙ ጥናትም ይፈልጋል፤ ብዙ ድርሻ የሚወስዱም ጉዳዮች አሉ፡፡ አሁን ባለንበት የዓለማችን ብሎም የሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር፣ የመዝናኛው ኢንዱስትሪ በአማራጭ የተሞላ ሆኗል፡፡ ብዙ ሚዲያዎች አሉ፡፡ ማህበራዊ ትስስር ሚዲያዎችም የህዝቡን ትኩረት አግኝተዋል፡፡
ቴአትርስ ብለሽ ከጠየቅሽኝ በቴክኖሎጂውና በመሰል እንቅስቃሴዎች ራሱን እያሻሻለና እያሳደገ መራመድ አልቻለም፡፡ ይሄ ደግሞ ራሱን የቻለ ትንታኔና ገለጻ ይፈልጋል፡፡ ነገር ግን ደግሞ ያሉት የቴአትር ቤቶች ካለው ህዝብ ቁጥር ጋር ሲታይ አለመመጣጠን፣ የከተማ መስፋፋትና ያሉትም ቴአትር ቤቶች በአንድ አካባቢ ላይ መገኘት፣ የኮቪድና የሀገራችን ያለመረጋጋት እንዲሁም ሌሎችም ተጨምረው ቴአትሩ ተጎድቷል። እንግዲህ እነዚህን ችግሮች ከስር መስረታቸው ለመፍታትና የቀደመ የቴአትር ተመልካች እንዲመለስ ጥናትና ምርምር መድረግ ስለሚያስፈልግ ፣ከስርዓተ ትምህርቱ ጀምሮ መስተካከል ያለባቸው ነገሮች ከወዲሁ መስተካከል አለባቸው። በዚህ ላይ በደንብ ተወያይተን በመጨረሻ ጥሩ መግባባት ላይ ደርሰናል፡፡ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት የእኛን ስምምነት ካየ በኋላ አንድ ወጥ የሆነ የቴአትር ሥርአተ ትምህርት ይኖረንና ሁሉም ዩኒቨርስቲዎቻችን በአንድ ስርዓተ ትምህርት ማስተማራቸውን ይቀጥላሉ የሚል እምነት አለኝ፡፡______________          “ተመልካቾችን ግምት ውስጥ ያስገባ ቴአትር ተሰርቶ አያውቅም”
                   (ተስፋዬ ገብረ ማሪያም ፤ የብሔራዊ ቴአትር ከፍተኛ የቴአትር አዘጋጅ)


            አውደ ጥናቱ ተገቢና ወሳኝ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ በዩኒቨርስቲዎቹ ውስጥ በተናጠል ባልተናበበ መልኩ የሚሰጠውን ትምህርት በአንድ አይነት በተመሳሳይ መልኩ ለመስጠት ያለመ በመሆኑ ጠቀሜታው የሚያጠራጥር አይደለም። ከዚህ በተጨማሪ የሀገራችንን ተጨባጭ ሁኔታ ከግምት ውስጥ ለማስገባትም ጥሩ አጋጣሚን ይፈጥራል ብዬ አምናለሁ፡፡ ምክንያቱም ተማሪዎቹ ሲመረቁ በዚሁ በአገራችን ላይ ነው ተሰማርተው የሚሰሩት፡፡ ስለሆነም የሚማሩት ልጆች የሀገራችንን ተጨባጭ ሁኔታ አውቀው በእውቀትም በስነ ልቦናም ዝግጁና ብቁ እንዲሆኑ ሥርዓተ ትምህርቱ መከለሱና እንዲህም ለውይይት መቅረቡ የሰለጠነ አካሄድ ነው፡፡
ለእኔ ግልፅ ባልሆነ ሁኔታ የተመልካች ጉዳይ ከድሮም ክፍተት ያለበት ክፍል ነው። ቴአትር ያለ ተመልካች የለም፡፡ ቴአትርን ቴአትር የሚያደርገው ዋናው ተመልካች ነው፡፡ ስለሆነም ተመልካች ቀደም ሲልም የስርዓተ ትምህርቱ አካል መሆን ነበረበት፡፡ የተመልካች ልማት በጣም ትኩረት ሊያገኝ ይገባዋል፡፡ የቴአትር ትምህርት ክፍሎች ተመልካችን የሚመለከት ትምህርት ኮርስ የላቸውም። እርግጥ የቴአትር ተመልካች አለ፡፡ የቴአትር ተመልካች አነሰ በሚባልበት ጊዜ አንኳን እኔ የቴአትር ተመልካች አለ የሚል ጠንካራ እምነት ነው ያለኝ፡፡
ነገር ግን ቴአትር በሚሰሩትና በተመልካቹ መካከል ያለው ድልድይ ነው የሳሳው፡፡ ቴአትር ቤቶች በጣም ኋላ ቀርና ልማዳዊ በሆነ መልኩ  ነው ቴአትሮቻችን ተመልካች ጋር እንዲደርሱ የምንፈልገው፤ ግን አሁን ዘመን ተቀይሯል፡፡ ለምሳሌ አገራችን ውስጥ ያሉ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ዘመኑንና ቴክኖሎጂውን ተከትለው ሲዘምኑ፣ ቴአትር ቤቶች ያንን አልተከተሉም፡፡
ለምሳሌ ከዚህ በፊት ጥሩ ተመልካች ያገኘንበት ጊዜ አለ፡፡ ታዲያ በቴአትር ስራዎችና በተመልካች መካከል የነበረው ድልድይ በተወሰነ መልኩም ቢሆን ጥሩ ነበር ማለት ነው፡፡ ተሻሚም አልነበረም። ማህበራዊ ትስስር ሚዲያውም አማራጭ ሚዲያዎችም አልተስፋፉም ነበር፡፡ እነዚህ በተስፋፉበት ዘመን ደግሞ እነዚህን ሚዲያዎችን ተጠቅመን ለተመልካች መድረስ እንችል ነበር፡፡ ይህን ባለመስራታችን የተፈጠረው ክፍተት በግልጽ የሚታይ ነው።
ቴአትር ቤቶች አሁንም እንደ ጥንቱ በሳምንት የ30 ሰከንድ ወይም የአንድ ደቂቃ ማስታወቂያ እየለቀቅን ነው ተመልካች እንዲመጣ የምንፈልገው፡፡ ይሄ ሁሉ ቴሌቪዥን ብዙ ፍላጎት ባለበት እንዴት ያንን ተቋቁመን ተመልካች ጋር መድረስ አለብን የሚለው በጣም ሊተኮርበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ ተመልካች በጣም ሰፊ ህዝብ ነው፡፡ ይህንን ተመልካች ችላ ማለት የለብንም፡፡ ተመልካች ደግሞ በየዕለቱ በየወሩ በየዓመቱ የሚቀያየር አዳዲስ ሰው ነው፡፡ በዚያው ልክ ፍላጎቱም ስሜቱም የተለያየ ስለሆነ ዳይናሚዝሙ ከባድ ነው። እኛ ደግሞ ይሄንን መከተል አልቻልንም፡፡ ይሄንን መከተል እንዲያስችል ነው በስርዓተ ትምህርቱም ላይ “የተመልካች ልማት” የሚል ኮርስ እንዲጨመር እንደ ግብአት አስተያየት የሰጠሁት። አስተያየቱንም በጣም በጥሩ ሁኔታ ተወያይተው ዩኒቨርስቲዎቹ ተቀብለውታል። በዚህ ሀሳብ ላይ ለማስተማር ሙከራ ይደረጋል ብዬ አምናለሁኝ፡፡
ተመልካች መታቀድ አለበት፣ ተመልካችን የምንደርስበት ስትራቴጂ መታቀድ አለበት፣ የተመልካችን ፍላጎት የምናውቅበት ዘዴ (መንገድ) መዘጋጀትና መጠናት አለበት፡፡ ሌላው ቀርቶ ተመልካች ቴአትር ላይ ያለው ሚና መታወቅ አለበት፡፡ ለምሳሌ እኔን “የተመልካች ሚና ምንድን ነው?” ብትይኝ ይሄ ነው ብዬ በግልጽ ልነግርሽ አልችልም፤ ምክንያምቱ ገና አልተጠናም፡፡ ይሄ ግን በደንብ መጠናት አለበት፡፡ ተመልካቾች የትኛውም ኪነ-ጥበብ ላይ ተፅዕኖ አላቸው፤ ያንን ተፅዕኖ ማወቅ የግድ አለብን፡፡ እኛ ይሄን ሳናገናዝብ እጃችን ላይ የመጣውን ቴአትር ነው የምንሰራው። ነገር ግር እጃችን ላይ የመጣው ቴአትር ከተመልካች ተሳትፎ ጋር መያያዝ አለበት፡፡ ስለዚህ በቴአትር ሰሪውና በተመልካቹ መካከል ያለውን ድልድይ መዘርጋት ርቀቱን ወይም ክፍተቱን ማጥበብ ያስፈልጋል። የድሮ ድልድይ አልሰራም ፤አዳዲስ ድልድዮችን መፍጠር አለብን፡፡
ከዚህ አውደ ጥናት በኋላ ቀደም ብዬ እንደገለጽኩት፤ ተመልካችን ታሳቢ ያደረጉ ኮርሶች በትምህርት ክፍሉ ይጀመራሉ ብዬ እጠብቃለሁ። ይሄ ኮርስ ከተከፈተ ደግሞ እዛ ኮርስ ላይ ቀስ ብለው የሚበስሉ ሰዎች ይመጣሉ፡፡ እናም ያ የእነሱ እውቀት ወደ እኛም ይሸጋገራል፡፡ እርግጥ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለውጡን ላናየው እንችላለን። ነገር ግን የተመልካች ልማት አስተሳሰብ መስፋፋት አለበት፡፡ በሌላው የቢዝነስ ዘርፍ እኮ ማርኬቲንግ ትልቅ የስራ ክፍል ነው፡፡ ቴአትርም ይህን ይፈልጋል፡፡ በአሁኑ ወቅት አይደለም ቴአትር ሰርግ ደግሰሽ የጥሪ ወረቀትሽን ማሳመር አለብሽ። በጥሪ ወረቀትሽ ብቻ  ሰዎች ላይመጡልሽ ይችላሉ፡፡ ባለ ኮከብ ሆቴል ውስጥ ደግሰሽ ሰዎች ላይመጡልሽ ይችላሉ እቤትሽም ደግሰሽ ቦታው በሰዎች ሊጨናነቅ ይችላል። እንደ አጠራርሽ ነው የሚወሰነው፡፡ የጥሪ ወረቀቱን ተጨንቀሽ ሰርተሸ በአክብሮትና በጊዜ ሰጥተሽዋል ወይ ነው ጉዳዩ። ቴአትር ላይ ሲሆን ደግሞ አስቢው፡፡
የአዲስ አበባ ቴአትር ቤቶች እኮ ታርጌት የሚያደርጉት የአዲስ አበባን ነዋሪ ነው። ይህን የአዲስ አበባ ነዋሪ እንዴት ነው የምንደርሰው? በሳምንት በምናስተላልፋት የ30 ሰከንድና የ1 ደቂቃ ማስታወቂያ ነው? እሷስ ትሰማለች ወይ? ቀድሞ በራሴ ዕድሜ እንደማስታውሰው፣ ዋና የቴሌቪዥን ማስታወቂያ አስነጋሪዎች ቴአትር ቤቶች ናቸው፡፡
አሁን እልፍ ነው ማስታወቂያው። ብዙ ገንዘብ የወጣባቸው ዘመናዊ ማስታወቂያዎች ይለቀቃሉ። በነዚህ መሃል የኛ ማስታወቂያ ውልብ ብላ ነው የምታልፈው፡፡ በእኔ እምነት ጋዜጠኞች ስለ ቴአትሩ የሚሰሩት ፕሮግራም ያግዘን እንደሆን እንጂ የቴሌቪዥን ማስታወቂያ አይሰራም፡፡
በአጠቃላይ የተለመደው መንገድ አያስኬድም፡፡ አዳዲስ መንገዶች መፈለግ አለባቸው፡፡___________________                 “የቴአትር ጥበብ ከመንግስት ጥገኝነት መላቀቅ አለበት”
                            (ረዳት ፕ/ር ወርቁ ሙሉነህ)


          በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የቴአትር ትምህርት ክፍል ሀላፊና መምህር ነኝ። የሥርዓተ ትምህርቱን ክለሳ አውደ ጥናት እንድታደርጉ እንዴት ተመረጣችሁ ላልሺኝ፣ በሁለት ምክንያት ነው የተመረጥነው። አንደኛው ፍላጎቱ ከእኛ ስለመጣ ሲሆን ሁለተኛውና ዋናው ጉዳይ ግን ዩኒቨርስቲያችን እንደ ዩኒቨርስቲም እንደ ሃገርም ቴአትር ላይ በትልቁ ከፍተኛ ሥራዎችን እየሰራንና አስተዋእፆ እያደረግን ስለሆነ ነው፡፡ የዓለም የቴአትር ቀንን ከአንዴም ሁለት ጊዜ በዩኒቨርስቲያችን ትልልቅ የዘርፉ ባለሙያዎች በተገኙበት አክብረናል፡፡ ይህንን አዲስ አድማስም እንደ ሚዲያ ትልልቅ ሽፋኖችን በመስጠት ለታሪክ አስቀምጦታል። ኢትዮጵያ የዓለም የቴአትር ማህበር አባል የሆነችውም በወልቂጤ ዩኒቨርስቲ አማካኝነት አንጋፋው የጥበብ ሰው ጋሽ ደበበ እሸቱ ምስራቅ አፍሪካን ወክሎ በዓለም የቴአትር ማህበር ውስጥ ይሰራ በነበረበት ጊዜ በፈጠረልን ግንኙነት ነው። በነዚህና መሰል ስራዎች ለቴአትር እድገት እያደረግን ባለነው አበርክቶ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴሩ የክለሳ አውደ ጥናቱን እንድናዘጋጅ መረጠን፡፡ ዩኒቨርስቲያችንም ይህን ጉዳይ ስናቀርብለት ፈቃደኛ ሆኖ 15 ቀን ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ነው እንድናዘጋጅ ሁኔታዎችን ያመቻቸልን። በዚህ አጋጣሚ  የዩኒቨርስቲያችን ፕሬዝዳንትና የስራ ባልደረቦቻቸውንን በእጅጉ እናመሰግናለን፡፡
እንግዲህ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ይህን ክለሳ ሰርቶ እንዲያቀርብና ሌሎችም ዩኒቨርስቲዎች በዚህ በተከለሰው ስርዓተ ትምህርት እንዲያስተምሩ ሀላፊነት የሰጠው ለቀዳሚውና የሁሉም ዩኒቨርስቶዎች እናት ለሆነው አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ነበር፡፡ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ይሆናል ይመጥናል ያለውን ሥርዓተ ትምህርት ቀርፆ አቀረበ። ነገር ግን ሌሎች ዩኒቨርስቲዎች ያልተወያዩበት በመሆኑና በተለይ ክፍለ ሀገር ያሉ ዩኒቨርስቲዎችን ነባራዊ ሁኔታ ያላገናዘበ በመሆኑ እንዲሁም አንዳንዶቹ ኮርሶች የክፍለ ሀገር ዩኒቨርስቲዎች ለመስጠት የሚቸገሩባቸው ሆነው በመገኘታቸው አልተስማሙም፡፡
ስለሆነም ይሄ ጥያቄ ለሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ቀርቦ ክለሳ እንዲደረግበት፣ ይህንንም የክለሳ አውደ ጥናት እኛ እንድናዘጋጅ እውቅና ሰጠን፡፡ ስለዚህ መጋቢት 13 እና 14 ቀን 2013 ዓ.ም አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲን ጨምሮ መቀሌ፣ አክሱም፣ ጎንደር፣ ደብረ ታቦር፣ ወሎ፣ ጂማና ሌሎችም ዩኒቨርስቲዎች እንዲሁም አንጋፋዎቹ ብሔራዊና ሀገር ፍቅር ቴአትር ቤቶች ተሳትፈውበት ጥሩና የሁሉንም ዩኒቨርስቲዎች ነባራዊና ተጨባጭ ሁኔታ ባገናዘበ መልኩ ውይይትና ክርክር ተደርጎ ስምምነት ላይ ደርሰናል። ይሔንን ስምምነት ላይ የደረስንበትን የተከለሰ ሥርዓተ ትምህርት ለሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር እንልካለን። የመጨረሻ አስተያየት ተሰጥቶበት ከፀደቀ በኋላ ሁሉም ዩኒቨርስቲዎች ወጥና አንድ አይነት በሆነ የቴአትር ስርዓተ ትምህርት ማስተማር ይጀምራሉ ማለት ነው፡፡
ቴአትር እንደ ሀገር መፋዘዝ ውስጥ ነው ያለው የሚባለው ቴአትር እንዲነቃቃ ብዙ ስራ ይጠይቃል። የመጀመሪያው ነገር የቴአትር ጥበብ ከመንግስት ጥገኝነት መላቀቅና ነፃ መውጣት አለበት። ኪነ-ጥበቡ በኢኮኖሚ ነፃ እስካልሆነ ድረስ በምንፈልገው መንገድ ሳይሆን መንግስት በቀደደልን መንገድ ብቻ ይሆናል የምንሄደው። ይሄ ለአንድ ሀገር ኪነ-ጥበብ መውደቅ ትልቁ ምክንያት ነው፡፡ ጥበብ በባህሪው ነፃነት ይፈልጋል፡፡ አሁን ግን ጥበቡ በመንግስት ጥገኝነት ስር ስለሆነ፣ እኛም ምርጫ ስለሌለን በገበያው ላይ ትልቅ እንከን እየፈጠረ ነው፡፡
የኢትዮጵያ የቴአትር ታሪክ ብለን ማውራት አንችልም። በእኔ እምነት ቴአትር አዲስ አበባ ላይ ነው ታጥሮ ያለው። አዲስ አበባም ከአራት ቴአትር ቤቶች በደንብ እየሰሩ ያሉት ምናልባትም ሁለቱ ቢሆኑ ነው። እነሱም ቢሆን ነፃ ስላልሆኑ በፈለጉት መንገድ መንቀሳቀስ አይችሉም፡፡ ቢያንስ መንግሰት ኪነ-ጥበቡን ነፃ ቢያደርገውና ራሱን የሚችልበት መንገድ ቢፈጠር በፍጥነት ከመፋዘዝ ይወጣል፡፡ በሃሳብ በክንዋኔና በአጠቃላይ ሁኔታ ከፍ ያሉ፣ የተመልካችን ፊት ወደ ጥበብ የሚመልሱ ሥራዎች መስራት ይችላል፡፡ ነፃ እስካልሆነ ድረስ ግን ችግሩ እየተባባሰ ነው የሚሄደው የሚል እምነት ነው ያለኝ።Read 251 times