Saturday, 03 April 2021 00:00

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(1 Vote)

 "ነግ በኔ" ብሎ የማይጠረጥር  እሱ ሁለቴ ይሞታል; ይላሉ አባቶች።
ወዳጄ፡- ምክንያት ስላለኝ አንድ መጥፎ ቀልድ እነግርሃለሁ።… እንደ ዋልድባው ዘፈን ቁጠርልኝ።…
ወጣቱ አዲስ የተቀጠረ መርከበኛ ነው። ጥቂት ወራት ባህር ላይ ካሳለፈ በኋላ ወደ መርከቡ ካፒቴን በመሄድ ሲፈራና ሲቸር፡-
“እዚህ ሁሉም ነገር ጥሩ ነው።… ግን…”
“ግን ምን? ችግር አለ?”
“ሴት የለም”
“እም…” ካፒቴኑ ትንሽ አሰበና፤ መርከበኛውን እየመራ ወደ አንድ ትንሽ ክፍል አስገባው።
“ያንን በርሜል ታያለህ?”
“አዎ”
“መዝናናት ስትፈልግ ጣትህን በቀዳዳው በኩል ትሰዳለህ። ውስጥ ያለው ሰይጣን አስደስቶ ይሸኝሃል” አለው። እንደተባለውም መርከበኛው መዝናናት ሲፈልግ ወደ ተዓምረኛው በርሜል እየሄደ የልቡ ይደርስለታል። አንድ ቀን ግን የፈለገው ሊሆን አልቻለም። በርሜሉ ውስጥ ሰይጣኑ አልነበረም። ወደ ካፒቴኑ ሂዶ ያጋጠመውን ነገረው፡፡ አለቃውም የስም ዝርዝር አውጥቶ ተመለከተና የሆነ ነገር አለው።
በዚህን ጊዜ ወጣቱ ባህረኛ ራሱን ስቶ ወደቀ።… ምን ቢለው ይሆን?... መጨረሻ ላይ እናየዋለን።
*   *   *
አንዳንድ ሰዎች ስለ ሌላው ሰው ባህሪ ለመረዳት አዘውትሮ የሚያዳምጣቸውን ሙዚቃዎች ማወቅ በቂ ነው ይላሉ።… “ጓደኞችህን ንገረኝና ማንነትህ እነግርሃለሁ”… እንደሚሉት። በበኩሌ፤ “ሙዚቃ” ስል ይህ በዓዋጅ የተጫነብን የሚመስለውን ፉከራና ቀረርቶ ሳይሆን የፈጠራ ውጤት የሆነውን፣ ነፍሳችንን ከውስጣችን የመስረቅ ዓቅም ያለውን ጥበብ ነው። ይህን ስል አሁን በአገራችን ሙዚቃ ውስጥ ቦግ ድርግም የሚሉ፣ ከሰለጠነው ዓለም የሚፎካከሩ፣ በባህላዊም ሆነ በዘመናዊ መሳሪያዎች የተቀናበሩ ውብ የጥበብ ስራዎች የሉም ማለቴ አይደለም። ጥቂትም እንኳ ቢሆኑ እነሱን አለማበረታታት ስህተት እንደሆነም ይሰማኛል።
ወዳጄ፡- ብዙ ሊቃውንት የእያንዳንዱ ሰው የህይወት ማዕዘን የሚሞረድበት መንገድ ወይም የሽክርክሪቱ ቃና የሚቃኘው… ማለትም፡- ሃዘንና ደስታው፣ ትዝታና ተስፋው በዕለት ተዕለት ኑሮው ላይ አሻራውን እንዳሳረፈ ወይም በጎም ሆነ ክፉ ጥላውን እንደጣለ የምናውቅበት ወይም የምናይበት የህሊና መስተዋት ጥበብ እንደሆነ ይናገራሉ።… ከጥበብ ደግሞ ሙዚቃ!...”Life without music is a mere malady…; (ህይወት ያለ ሙዚቃ ህመም ነው፤ እንደ ማለት!!)
አጋጣሚ ሆኖ ከወዳጄ ዘኔ ጋር ባለፈው ሰኞ ተገናኝተን፣ ሁሌም እንደምናደርገው፣ የልብ ሙዚቃዎቻችንን እናዳምጥ ነበር። ጀምስ ብራውንና ሉቺያኖ ፓቫሮቲ፣ ናት ኪንግ ኮልና ጂም ሪቭስ፣ ኒና ስምዖንና ቢሊ ሆሊዴይ፣ ፍራንክ ሲናትራና ሉዊስ አርምስትሮንግ -- ከብዙ ጥቂቶች ናቸው። እና ጨዋታን ጨዋታ ያነሳዋል ሆነና…
“ተሜ፤ አሊ ታንጎ መሞቱን ሰምተሃል?” ሲል ጠየቀኝ
“ኧረ አልሰማሁም”
“ልጅ እያለህ አንደምታውቀው ነግረኸኝ ነበር”
"እውነት ነው"
“ሰውየውኮ እንደነ ጋሼ አምሃ በኢትዮጵያ ሙዚቃ ኢንዱስትሪ ታሪክ ውስጥ የራሱን አስተዋፅኦ ያደረገ ነው”
“እርግጥ ነው!”
“ታዲያ ነፍስ ይማር ማንን ገደለ?” አለኝ።
ዕውነቱን ነው።… ነፍስ ይማር ጋሽ አሊ!
ወዳጄ፡- የለውጥ ህግ ከሚመራባቸው መሰረታዊ የፍልስፍና መርሆች አንዱ (cause & effect) የምንለው የአስተሳሰብ ብርሃን ይመስለኛል፡፡ ማንኛውም ሰውም ሆነ ነገር ለማንነቱ ወይ ራሱን ሆኖ ለተገኘበት  (beng and becoming) ጉዳይ ሰበብ የፈጠሩለት ውጫዊና ውስጣዊ ምክንያቶች መኖራቸው እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የግለሰቦች የአእምሮ ብቃትም የሚጫወተው ጉልህ ሚና ከፍተኛ ነው። ነብያቶቻችን፣ ደራሲዎቻችን፣ ሳይንቲስቶቻችን፣ መሪዎቻችንም ሆኑ ሰማዕቶቻችችን ግለሰቦች ናቸው። አሊ ታንጎም እንደ ሌሎቹ ሁሉ እስከ እነ እዕንከኑ ለሙዚቃው ኢንዱስትሪ ያበረከተው አስተዋጽኦ ቀላል አይደለም፤ ዝርዝሩን በትክክል ባላውቅም፣ የብዙ ዘፋኞችን የሙዚቃ አልበም በማሳተም፣ ቢያንስ ለዝና አብቅቷቸዋል።… ነፍስ ይማር ጋሽ ዓሊ!
ዓሊ ታንጎን ከአንድም ሁለት ጊዜ በቅርብ ርቀት አግኝቼዋለሁ። የመጀመሪያው በአስራ ዘጠኝ ሰባዎቹ መጀመሪያ አካባቢ፣ የአስራ ሁለተኛ ክፍል ሮርጅድ ትራንስክርፒት ለልጅህ አሰርተሃል ተብሎ ተከሶ፣ ለጥቂት ወራት ማዕከላዊ እስር ቤት በቆየበት ጊዜ ነው። ሁለተኛው በ1987 ዓ.ም የቤተሰቦቹ ንብረት የነበረውን የቡና ወፍጮ አስመልሶ፣ የቡና ንግድ በጀመረበት ወቅት ነበር። አሊ ጅማ ከተማ ውስጥ ሲኖር የነበረው ቀደም ሲል የቀኝ አዝማች ተካ ኤጋኖ ንብረት በነበረውና ከለውጡ በፊት ´ደርጊቱ ሆቴል´ ተብሎ በሚጠራው፣ በጊዜው ቁጥር አንድ በሚባል ሆቴል ነበር። እኔና ጓደኞቼም በዚሁ ሆቴል ደንበኞች በመሆናችን አብዛኛዎቹን ምሽቶች የምናሳልፈው እዛ ነው። … እና ጋሽ ዓሊ ባለበት። በነገራችን ላይ ዓሊ ታንጎ ከሙዚቃ ስራው ባለፈ በግሉ ከፍተኛ የሙዚቃ ዕውቀት ነበረው። የተለያዩ አገራት አርቲስቶች የተጫወቷቸው ምርጥ ክላሲካል ሙዚቃዎችን የያዙ የግል ካሴቶቹን፣ ለሆቴሉ ሰዎች እየሰጠ አስደምጦናል። አሪፍ ሙዚቃ ማዳመጥና ማንበብ ያኔ የነቁ ወጣቶች ባህል ነበር።
ጅማ ፣ ጊቤና (የቀድሞው ስሙ ግዮን) ጎጀብ (የቀድሞው ስሙ ቪቺሊሎ) የተባሉት ሶስቱ ትላልቅ ሆቴሎች ከወትሮው በተለየ መልክ በሁሉም የሙስሊምና የክርስቲያን በዓላት ዋዜማዎች፣ የዳንስ ምሽት በማዘጋጀት የመግቢያ ቲኬቶችን በነጠላ አስር፣ በጥንድ አስራ አምስት ብር በመሸጥ ይወዳደራሉ። ጅማ (ደጊቱ) ሆቴል ከሚሰጠው አገልግሎት በተጨማሪ ዘወትር ሃሙስ ምሽት Candle party እና Barbacue ያዘጋጃል። ሆቴሉ ሙዚቃ አክባሪ ደምበኞቹን አንዴ በጃዝ፣ አንዴ በብሉዝ፣ አንዴ በሮክ እንዲሁም በሶልና አር ኤንድ ቢ ስልቶች ሲወዘውዛቸው፣ ከውቧ ከተማ አናት ላይ ሆና የምትስቀው ጨረቃም አብራ ሽር ብትን የምትል ትመስል ነበር።
ወዳጄ፡-  ሙዚቃ ስሜትን በከፍተኛ ደረጃ የማነቃቃት ሃይል አለው፤ መንፈስ ነው። ባለፈው ዓመት ኮሮና ቫይረስ በፈጠረው ቀውስ፣ የሚይዘውና የሚጨብጠው ጠፍቶት ሲያጣጥር የነበረው የዓለማችን ህዝብ፣ ወደ ቀልቡ እንዲመለስ ያደረገው ሙዚቃ ነው። ውዱ አርቲስት አንድርያ ቮቼሊ፤ “Amazing race” የተሰኘውን ድንቅ ሙዚቃ ብቻውን ቫቲካን በሚገኘው የታላቁ ጴጥሮስ ካቴድራል ሲጫወት ህዝቦች በያሉበት ሆነው በእንባ ተራጭተዋል። እኛም ዓሊ ታንጎን በያለንበት ሆነን ስንሰናበት፣ ቢያንስ የሃመልማልን ውብ እንጉርጉሮዎች እያሰብን ነው።… ነፍስ ይማር ጋሽ ዓሊ!!
ወደ ጀመርነው ጨዋታ ስንመለስ፡- ካፒቴኑ ዝርዝሩን ከተመለከተ በኋላ ለወጣቱ  የነገረው፤  “የዛሬው ተረኛ ሰይጣን አንተ ነህ!” በማለት ነበር።
ሠላም!


Read 1411 times