Saturday, 17 April 2021 11:29

እናት እና ነእፓ ፓርቲዎች ከሃይማኖታዊ አወቃቀር ነፃ ነን አሉ

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(2 votes)

   ለ6ኛው አገር አቀፍ ምርጫ 573 እጩዎችን ያቀረበው እናት ፓርቲና 472 እጩዎችን  ለፌደራልና ለክልል ምክር ቤቶች ያቀረበው ነፃነትና እኩልነት ፓርቲ (ነእፓ) ከሃይማኖታዊ አወቃቀር ነፃ ሆነው የተቋቋሙ ፓርቲዎች መሆናቸውን ገለፁ፡፡ ፓርቲዎቹ የሃይማኖት ጉዳይ ከድርጅታችን አወቃቀር ጋር አብሮ የሚሄድ ጉዳይ አይደለምም ብለዋል፡፡
 የእናት ፓርቲ ዋና ፀሀፊ አቶ ጌትነት ወርቁ እከአዲስ አድማስ ተጠይቀው ሲመልሱ፤ “በፓርቲው ውስጥ  ሃይማኖተኛ የሆኑ ሰዎች የሉበትም ማለት አይቻልም። ባለፉት ስርዓት ከፈፀማቸው ስህተቶች ቀዳሚው ሃይማኖትን ጥሎ የመነሳት አባዜ ነው፡፡ ያ ምን አይነት ዋጋ እንዳስከፈለን የምናውቀው ጉዳይ ነው፡፡ ነገር ግን ሃይማኖተኞች በፓርቲው ውስጥ አሉበት ማለት የፓርቲው አወቃቀር ሃይማኖታዊ ነው ማለት አይደለም፡፡ የተለያዩ ሃይማኖቶት ተከታዮች የፓርቲያችን አባላት ናቸው” ብለዋል፡፡
“የኛ ጉዳይ ማንም ሰው በፍትህ ፊት እኩል መሆኑ የሚረጋገጥበት ስርዓትን መገንባት ነው፡፡ ይህ በደንብ ሊታወቅ ይገባል” ብለዋል፡፡ የእኛ አገር ፖለቲካ ምክንያት ፈልጎ የሚጠልፍ ፖለቲካ ነው፡፡ ይህ ዘመቻም የዚሁ አባዜ አንዱ አካል ነው፡፡ ፓርቲውና ሃይማኖቱን የሚያገናኘው ምንም ነገር የለም ብለዋል፡፡  
የነፃነትና እኩልነት ፓርቲ (ነአፓ) መስራችና ስራ አስፈፃሚ ወ/ሮ ነቢሃ መሀመድ በበኩላቸው፤ ፓርቲያቸው የአገሪቱ መፃኢ ዕድል አሳስቦት የተቋቋመ ፓርቲ እንጂ ሀይማኖታዊ አደረጃጀትን ለማስፋፋት ታስቦ የተቋቋመ ድርጅት አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡ “ከፊት ያለን ሰዎች ስማችን የአንድ ሃይማኖት መለያ የሆኑ ስሞችን የያዘ በመሆኑ ብቻ  የሃይማኖት ፓርቲ ነው ሊባል አይገባም” ያሉት ወ/ሮ ነቢሃ “ነፃነትና እኩልነት ፓርቲ ሌሎች ሃይማኖቶችን የሚያከብር፣ ማንም ሰው ሊኖረው የሚገባውን የእምነትና የሃይማኖት መብት ከሌላው ፓርቲ በተለየ ሁኔታ  የሚያከብር ፓርቲ ነው” ብለዋል፡፡ ይህ አባባል በአገሪቱ የተለመደው የጭፍን ጥላቻና ጭፍን ድጋፍ አካል እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
ሁለቱም ፓርቲዎች በቀሪዎቹ ጊዜያት ወደ ህብረተሰቡ በስፋት በመድረስ በተለያዩ መንገዶች ፕሮግራማቸውን በማስተዋወቅ ስራ ላይ እንደሚያተኩሩም ገልፀዋል፡፡


Read 11778 times