Print this page
Saturday, 17 April 2021 11:57

"የሁለቱ መደመሮች" መጽሐፍት ዳሰሳ

Written by  አንዳርጋቸው ጽጌ
Rate this item
(1 Vote)


(ክፍል - 2)


                 የይዘት ዳሰሳ
የይዘት ዳሰሳውን መልክ ለማስያዝ እንዲሁም የአንባቢንም ስራ ለማቅለል የእነዚህን ሁለት መጽሐፍት ዳሰሳ በአንድ መሰረታዊ ቁም ነገር ዙሪያ ማድረግ ተገቢ ነው። እንዴት ሁለት መጽሐፍት በአንድ መሰረታዊ ቁም ነገር ዙሪያ ማድረግ ይቻላል ለምትሉ፤ መልሴ እነሆ።
እነዚህ ሁለት መጽሐፍት ከርእሳቸው ተመሳሳይነት ባሻገር “መደመር” የሚለውን ቃል ወሳኝ ቃል በማድረግ በርካታ ጉዳዮች የሚተነተኑባቸው ችግሮች የሚፈተሹባቸው፣ መፍትሄዎች የሚጠቆሙባቸው ሆነዋል። “የመደመር መንገድ” ያስፈለገበት ምክንያት “መደመር” በሚለው መጽሐፍ ውስጥ ስለ መደመር የቀረቡትን እይታዎች የበለጠ በተለያዩ ንድፈ ሃሳባዊ ባልሆኑ የስነጽሁፍ አግባቦች በሚቀርቡ የተለያዩ ትረካዎች ማበልጸግ ይቻላል በሚል እምነት ነው። ዐቢይ ይህን በቀጥታ አላለም። ቢሆንም የኔ ድምዳሜ ትክክል ለመሆኑ ማስረጃው “የመደመር መንገድ” እንደ “መደመር” መግቢያ ወይም መቅድም የሌለው መጽሐፍ መሆኑ ነው። ይህ ማለት “የመደመር መንገድ” ራሱን “የመደመር” ቅጥያ አድርጎ ስላየው ሌላ መቅድም አላስፈለገውም ማለት ነው።
ስለዚህም ዶ/ር ዐቢይ “መደመር” የሚለውን መጽሐፉን ለምን እንደጻፈው በግልጽ ያስቀመጠው ወይም ያስቀመጣቸው አላማዎች ለ”የመደመር መንገድ”ም የሚሰሩ አላማዎች ናቸው። እነዚህ አላማዎች ምንድን ናቸው? አላማውን ወይም አላማዎቹን  አሳክቷል ወይ?
የተለያዩ ጸሃፍት የተለያዩ ግቦች አንግበው በመነሳት መጽሐፍት ይጽፋሉ። ለዚህ ግብ የሚያዋጣውን የአጻጻፍ ስልት ወይም አይነት ይመርጣሉ። ትልቁ ጥያቄ ጸሃፍቱ በቅርጽና በይዘት በግልጽ ወይም በውስጠ ታዋቂነት ያስቀመጧቸውን ግቦች በመምታት ተሳክቶላቸዋል ወይ ነው። የሁለቱን መደመሮች ጥንካሬና ድክመት ለመፈትሽ የወሰንኩት ከዚህ ቅኝት አኳያ ነው።
በቅርጽ ወይም አቀራረብ የሚለውን ጉዳይ ከይዘት ውጭ በሚለው ርእስ ስር ቀደም ብለን አይተነዋል።  ዐቢይ በዚህ ረገድ በሚገባ ተሳክቶለታል። የሚቀረን የይዘት ዳሰሳው ነው። ከባዱ ክፍልም ይህ ነው።
በቅድሚያ “መደመር” ን በተመለከተ
የ”መደመር” መጽሐፍን ስኬት ለመለካት የምንጀመረው ዐቢይ ይህን መጽሐፍ ለመጻፍ ባነሳሱት ምክንያቶችና ለማሳካት ባሰባቸው ግቦች ላይ በመመስረት ነው። ወደ እዚህ ቁምነገር በዝርዝር ከመግባታችን በፊት በይዘት ደረጃ መጽሐፉ ያነሳቸውን ሌሎች ቁምነገሮች ለአንባቢ ገልጾ ማለፍ ፍትሃዊ ይመስለኛል።
መጽሐፉ በሚያስገርም መልኩ የተነጣጠሉ ነገር ግን እርስ በርሳቸው የተጎናጎኑ ጉዳዮችን ያነሳል። የመጽሐፉ አደረጃጀትም ይህንኑ በተያያዥነትና በተናጠል የሚቀርቡ ጉዳዮችን አስመልክቶ የተደራጀ ነው። መሰረታዊ ክፍሎቹ 4 ሲሆኑ እነዚህ ክፍሎች ደግሞ በ16 ምእራፎች ተከፍለዋል።
ከላይ በገለጽኩት ምክንያት እያንዳንዱን ምእራፍ የሚመለከት ዳሰሳ ማቅረብ አያስፈልግም። ምእራፎቹ በሙሉ “መደመርን” የበለጠ ለማበልጸግና ለማብራራት የቀረቡ ስለሆኑ ዳሰሳው ትኩረቱ ራሱ መደመር ላይ ቢሆን ተገቢ ይሆናል። ይህን ብዬም አንባቢ እያንዳንዱን ምእራፍ በጥንቃቄ ቢያነብ ብዙ እውቀት እንደሚገበይ ለመጠቆም እወዳለሁ። ጥቆማዬን ለማጠናከር ወደ ዋናው የዳሰሳዬ እምብርት ከመሸጋገሬ በፊት የመጽሐፉን 4 ክፍሎች በወፍ በረራ መልኩ ወደ መቃኘት እሸጋገራለሁ።
ክፍል 1 የመደመር እሳቤ መነሻ ሃሳቦች
ከመጽሐፉ አራት ክፍሎች፣ የመጀመሪያው ክፍል “መደመር” የሚለውን ነገር ዶ/ር ዐቢይ ለማብራራት የተጠቀመበት ክፍል ነው። “ነገር” ያልኩት ሌላ ቃል በመጠቀም ለ”መደመር” ያልሆነውን ትርጉም ላለመስጠት ጥንቃቄ ለማድረግ ነው። ወደፊት እንደምናየው መደመር ብዙ ትርጉም አለውና። የመጀመሪያው ክፍል የመጽሐፉን ቁልፍ ወይም ገዢ ቃል በማብራራት፣ ስርወ መሰረቱን በመግለጽ እንደ ጽንሰ ቃል “መደመር” ያደገባቸውን የተለያዩ ሁኔታዎች ሂደቶችና ደረጃዎች ለመግለጽ በስራ ላይ የዋለው ክፍል ነው።
የመጽሐፉን ቁልፍ ቃል መግለጽ ቀዳሚ ተግባር አድርጎ ዐቢይ መውሰዱ ሌሎችን ክፍሎችና ምእራፎች በቀላሉ ለመከታተል የሚጠቅም በመሆኑ ትክክለኛ አካሄድ ነው። በአንዳንድ የፍልስፍና አስተምርሆዎች በቃላት ትርጉምና አጠቃቀም ላይ ግልጽነትና ስምምነት እንዲኖር ማድረግ የፍልስፍና ተዋስኦ መሰረት ተደርጎ ስለሚወሰድ ዐቢይ መደመርን በመግለጽ መጀመሩ፣ ቃሉ ፍልስፍናዊ ትርጉም እንደተሰጠው አመላካች ነው። ትልቁ ጥያቄ፣ በዚህ ክፍል መደመር ምን እንደሆነ ዶ/ር ዐቢይ  ማሳየት ችሏል ወይ?
ይህን ገዥ ቃል በሚቀጥሉት የመጽሐፉ ክፍሎች በተደጋጋሚ ስራ ላይ ውሎ እናገኘዋለን። “መደመር” በመደመር ቅኝት ይታያሉ የተባሉ ጉዳዮችን ማሳያ ሆኖ እናገኘዋለን ወይ? በተለይ “መደመር” ጸሃፊው እንደተመኘው፣ እንደ ህዝብ እና እንደ ሃገር ከገባንበት አደገኛ ቅርቃር ሊያወጣን የሚችል አዲስ የአተያይ ግኝት ሆኖ ማየት ችለናል ወይ?
የደራሲውም ትልቅ ትኩረት “መደመርን” ለችግሮቻችን ፈውስ እንደ ተአምራዊ ኪኒን (Magic Bullet) የማቅረብ በመሆኑ የመጽሐፉ ጥንካሬ ወይም ድክመት ዋናው መለኪያ ከዚህ ቃል ጋር የተያያዘ ሆኗል። አብይ በ“የመደመር መንገድ” ገጽ 62 ላይ “መደመር ሃገራዊ ተአምር መስራት ይችላል” ይለናል። አንባቢዎችም ሳንወድ በግድ የመጽሐፉን ዳሰሳ ዋና ትኩረት እዚህ ጉዳይ ላይ እንድናደርግ አስገድዶናል፡፡
የ“መደመር” ክፍል 2 የሃገራችን የፖለቲካ ስብራትና የጥገና አማራጮችና
ክፍል 3 የሃገራችን የኢኮኖሚ ስርአት ስብራትና የጥገና አማራጮች፤
ከአራቱ የመጽሐፉ ክፍሎች ሁለቱ ክፍሎች የሃገራችንን የፖለቲካና የኢኮኖሚ ስብራቶች የሚመረምሩ ናቸው። እነዚህ ሁለት ክፍሎች በተለይ የኢትዮጵያ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ስብራቶች የቀረቡባቸውና መፍትሄ የተጠቆሙባቸው ዝርዝር ጉዳዮችን አካተዋል። የፖለቲካ ችግሮቻችን አጥጋቢ በሚባል ደረጃ ቀርበዋል። የኢኮኖሚ ችግሮቻችንም እንደዚሁ። መፍትሄዎቻቸውም በመጽሐፉ ማዕቀፍ ውስጥ ሲታዩ በዝርዝር ቀርበዋል። እነዚህ ሁለት ክፍሎች ውስጥ በቀረቡ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ጉዳዮች ዙሪያ የተለያዩ ሙያተኞች የራሳቸውን አስተያየቶች መስጠት የሚችሉባቸው በርካታ ነጥቦች አሉ።
የታሪክ ሰዎች ከታሪክ አኳያ፣ የፖለቲካ ሰዎች ከፖለቲካ አኳያ፣ የመንግስት አስተዳደር ባለሙያዎች ከመንግስት አስተዳደር አኳያ፣ የሌሎችም የእውቀት ዘርፎች ባለሙያዎችም በየሙያው ዘርፍ በተነሱ ጉዳዮች ዙሪያ ብዙ ማለት ይችላሉ። ኢኮኖሚስቶች፣ ከተለያዩ የኢኮኖሚ ንድፈ ሃሳቦች አንስቶ፣ በዝርዝር የኢኮኖሚ መስኮች፣ ግብርናን፤ ንግድን፣ ፋይናንስን፣ ኢንዱስትሪ፣ ቴክኖሎጂና ወዘተ በመሰሉ ጉዳዮች ላይ ዐቢይ ባቀረባቸው ምልከታዎች ላይ በበጎም ይሁን በአሉታዊ መንገድ በርካታ አስተያየቶችን መስጠት ይችላሉ።
መደመርና የውጭ ግንኙነት
አራተኛው ክፍል ዶ/ር ዐቢይ የፖለቲካ ተንታኝ ብቻ ሳይሆን የሃገርና የፖለቲካ መሪ ጭምር በመሆኑ የገባ የሚመስል ነገር አለው። ይህ የመጨረሻ ክፍል የሚጠቁመው ነገር ዶ/ር ዐቢይ መጽሐፉን ሲጽፍ የብልጽግና ፓርቲን በአንድ አይኑ እያየ እንደሆነ ነው። እንደውም ከዚህ የመጽሐፉ የመጨረሻ ክፍል ተነስተን ወደ ኋላ መጽሐፉን ስንቃኝ “መደመር” በአንድ በኩል እንደ አንድ አዲስ የፖለቲካ ፍልስፍና፣  በሌላ በኩል እንደ አንድ የፖለቲካ ድርጅት የፖሊሲ አቅጣጫዎች መጠቆሚያነት ታስቦ የተጻፈ ሆኖ እናገኘዋለን። የብልጽግና ፓርቲ መሪዎችንና አባላትን የማስተማሪያ መጽሐፍ እንዲሆንም ጭምር ታስቦ የተዘጋጀ ቢሆን አይገርምም።
ብልጽግና ከኢህአዴግ በአደረጃጀት ብቻ ሳይሆን፣ በርእዮተ አለም ደረጃ ከአብዮታዊ ዴሞክራሲ ጋር ተፋትቼያለሁ እስካለ ድረስ አብዮታዊ ዴሞክራሲን በምን እንደተካው መግለጽ አለበት። የዐቢይ ድካም ይህንን ጉዳይ ግምት ውስጥ ያስገባ ይመስላል። ቀደም ብለን እንዳየነው “የመደመር መንገድ” የሚለው ሁለተኛው መጽሐፍ የመጨረሻው ክፍል ያለቦታው የገባ ከሚመስል ከብልጽግና ፓርቲ ጋር በቀጥታ በተገናኘ ጽሁፍ መዘጋቱ ዐቢይ በአንድ አይኑ ብልጽግናን እያሰበ መጽሐፎቹን ጽፏቸዋል ለሚለው ግምቴ ተጨማሪ ማስረጃ ይሆናል የሚል እምነት አለኝ።
ከዚህ በላይ የጻፍኳቸውን ጥቂት መስመሮች ለመጻፍ ለምን እንደፈለግሁ ልግለጽ።
የወጭ ጉዳይ ችግራችን እንደ ፖለቲካና ኢኮኖሚ ችግሮቻችን የሃገሪቱንና የህዝቧን ህይወት በሁለንተናዊ መልኩ የሚነካ ችግር ነው የሚል እምነት የለኝም። ይህን ስል “ኢትዮጵያ በጣም ስሱ በሆነ ጂኦ ፖለቲካዊ አካባቢ የምትገኝ፣ ከሌሎች የቅርብና የሩቅ ሃገሮች ጋር የሚኖራትን ግንኙነቶች በጥንቃቄና በተጠና ፖሊሲ አማካይነት መምራት የለባትም እያልኩ” አይደለም። “ኢትዮጵያ ከውጭ መንግስታት ጋር የሚኖራት ግንኙነት በዋነኛነት የሚወሰነው በሃገራችን ውስጥ በሚኖረን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጥንካሬና ወይም ድክመት ላይ ነው” ለማለት ነው። የውስጥ ችግር የሌለባት ኢትዮጵያ በውጭ ጉዳይ የሚገጥማት ችግር አሳሳቢ አይሆንም። ሌላው ምክንያቴ፣ በሌሎቹ ሁለት ክፍሎች የመደመር ሃሳብ በቁልፍ ማብራሪያነት በቀረበበት ደረጃ ለውጭ ጉዳይ እምብዛም አስፈላጊ ሆኖ አለመታየቱ ነው። የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አቅጣጫ ከመደመር እሳቤ አኳያ እንዲታይ የሚያመላክት ነገር ቢኖርም፣ “መደመርን” ከሚገባው በላይ ለመለጠጥ የተደረገ ጥረት የሚመስል ነገር አለው።
የተቀመጠው የውጭ ጉዳይ የፖሊሲ አቅጣጫ ያለ መደመር እሳቤ፣ በተለመዱት የመልካም ጉርብትና፣ የትብብር፣ የጋራ ደህንነትና ጥቅም ማስጠበቅ ወዘተ በሚሉ እሳቤዎች መቅረብ ይችል ነበር የሚል እምነት አለኝ። እነዚህ እሳቤዎች ከመደመር በፊት የነበሩ ስለሆነ ያለ መደመርም ለውጭ ጉዳይ ፖሊሲ መቅረጫነት ሊያገለግሉ ይችሉ ነበር።
አንድ ሃገር በደንብ የታሰበበት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ እንዲኖረው ማድረግ የግድ ነው። በዚህ ክፍል የውጭ ጉዳይን በተመለከተ በዶ/ር ዐቢይ የቀረቡት ምልከታዎች በንድፈ ሃሳብ ብቃትና በተግባራዊ መስኩም አንባቢን የሚያስታጥቁት በርካታ ጥሩ ሃሳቦች አሉት። በዚህ ከፍል ውስጥ በተነሱት ጉዳዮች ላይም የአለም አቀፍ ግንኙነት ሙያተኞች “መደመር እና የውጭ ግንኙነት”ን በተመለከተ  መደመር የሚለውን ቃል ወደ ጎን አስቀምጠው ቢያነቡት የሚስማሙባቸውና የማይስማሙባቸው ነጥቦች እንደሚኖሩ መገመት ይቻላል።
ያም ሆኖ ዐቢይ ስፋት ያለውን ወቅታዊ አለም አቀፍ ሁኔታ በትንሽ ገጾች በአግባቡ ጨምቆ “ኢትዮጵያ በዚህ አለም አቀፋዊ ሁኔታ ውስጥ የውጭ ግንኙነቷ ምን ሊሆን ይገባዋል” ለሚለው ጥያቄ የሰጠው ምላሽ፣ ለሃገሪቱ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ስብራቶች መጠገኛነት ከሰጣቸው ምላሾች ጋር ተደምሮ ጸሃፊው የዋዛ ፖለቲከኛ እንዳልሆነ የሚያሳይ ነው።
እውነቱን እንነጋገር ከተባለ የመደመር መጽሐፎች ዐቢይ ሊያላብሳቸው የፈለገው የፍልስፍና ገጽታ ቀርቶባቸው በንጹህ የፖለቲካ ጽሁፍነት ከተመዘኑ እስከ ዛሬ ድረስ በሃገሪቱ ታዋቂ የፖለቲካ መሪዎች ከተጻፉት የፖለቲካ መጻህፍት የላቁ ናቸው። ችግሩ ዐቢይ የፖለቲካ ብቻ ሳይሆን የፖለቲካ ፍልስፍና መጽሐፎች አድርጎ ስላቀረባቸው ከዚያ አኳያ ሲዳሰሱ ውስኑነት የሚታይባቸው መጽሐፍት መሆናቸው ነው። እኔም የምሸጋገረው ወደዚሁ ዳሰሳ ነው።
“መደመር”  በሁለቱ መጽሃፎች ትልቅ ክብደት የተሰጠው ቃል!
የዐቢይን ሁለቱን የመደመር መጽሐፎች ለመዳሰስ የሚነሳ ማንም የምር ሃያሲ “መደመር” የሚለው ቃል በመጽሐፉ ውስጥ የተሰጠውን ማእከላዊ ቦታ ሳያጤንና አስተያየቱን ሳይሰነዝር ማለፍ አይችልም። የመጽሐፎቹ ዋልታና ማገር “መደመር” ነው። የመጽሐፎቹ መሰረታዊ ጥንካሬ ወይም ድክመት የሚለካ ከሆነ  “መደመር”ን በተመለከተ ከሚኖረው ጥንካሬና ድክመት  ነው። ስለ መጽሐፉ ከላይ ያቀረብኳቸው እጅግ ብዙ ጠንካራ ጎኖች እንዳሉ ሆኖም፣ ዶ/ር ዐቢይ ይህን ቃል ማእከላዊና ተአምራዊ ትርጉም የሰጠው በመሆኑ በዋንኛነት መጽሐፉን እንድንመዝንለት የፈለገው ከዚህ ቃል ጋር በተያያዘ ነገሮችን ያየበትን የእይታ ትክክለኛነትና አጥጋቢነት ነው።
የ”መደመር” ሃሳብ መነሻ
ዐቢይ መደመርን ተራ ከሆነ የመደራረብ፣ የማከል፣ የመጨመር ቃል ወደ ላቀ ጽንሰ ቃል (concept) አሳድጎ እንዲያይ ያደረጉትን ነጥቦች  በ”መደመር” መቅድም ይዘረዝራቸዋል።
ጸሃፊው በልጅነት እድሜ ተፈጥሮን በተመለከተ የነበረ የደመነፍስ ግንዛቤ፣ የማህበረሰብ ባህሎችን ማጤን፣ ከስራ አለም ከተገኘ ልምድና ተመክሮ፣ የሃገራችንን የረጅም ዘመን ታሪክ ከማጥናት፣ የሰውን ልጅ ስነልቦናዊ ስሪቶች ከመመርመር፣ የሰውን ልጅ ተፈጥሮና የራሱ የጸሃፊው የግል ህይወት ላይ ከተደረጉ ማሰላስሎች በመነሳት ከተገኘ እውቀት መደመርን ከተራ ቃል ወደ ላቀ ጽንሰ ቃል አሳድጎ እንዲያየው እንዳደረገው ገልጾልናል። የሁለቱም መጽሐፎች የመጀመሪያዎቹ ገጾች የሚያተኩሩት በዐቢይ ውስጥ “የመደመር ሃሳብ” እንዲያድግ ባደረጉ ኩነቶች ላይ ነው።  ይህ መንደርደሪያ ግልጽና የማያሻማ ነው።
መደመር ምንድን ነው?
ከዚህ በላይ ከቀረበው መንደርደሪያ አንባቢ የሚጠብቀው በመግቢያው ከተዘረዘሩት ተመክሮዎች ማሰላሰሎችና ወዘተ በመነሳት ለመደመር የተሰጠ የማያሻማ አገላለጽና የቃሉ አጠቃቀም ነው። የመጽሐፉ  አጠቃላይ ጥንካሬ ሸብረክ ማለት የሚጀምረው እዚህ ላይ ነው። ከ”መደመር” ገጽ V ጀምሮ የመደመር ትርጉም ወደ አንድ መሰባስቡን ትቶ መሰነጣጠቅ ይጀምራል።  መደመር አስተሳሰብ (way of thinking) ፍልስፍና፣ እሳቤ፣ ርእዮተ አለም፣ አተያይ (perspective)፣ መርህ፣ እሴት፣ ተራ መተባበር፣ አንድነት፣ መከማቸት፣ መሰብሰብ፣ የበጎ ባህርይ መገለጫ፣ ብያኔ፣ የላቀ ድምር (synergy) የሚሉ የተለያዩ ትርጉሞች እየተላበሰ እስከ መጽሐፉ መጨረሻ ይቀጥላል።
በመደመር ፍልስፍና በመደመር እሳቤ፣ በመደመር መርህ፣ በመደመር ብያኔ ወዘተ የሚሉ አገላለጾች በሁሉምና በሁለቱም  የመጽሐፉ ገጾች በተደጋጋሚ ይገኛሉ። በመሆኑም ለማስረጃነት ገጽ መጥቀሱ አስፈላጊ አይደለም። አንዱ የ”መደመር” ድክመት ለመደመር አንድ ጠንካራ ግልጽ የሆነ ትርጉም ሰጥቶ ከመጽሐፉ መጀመሪያ እስከ መጨረሻ ይህ አጠቃቀም በስራ ላይ መዋል አለመቻሉ ነው። ይህ ባለመሆኑ መደመር ዶ/ር ዐቢይ እንደተመኘው በራሱ መቆም የቻለ የፖለቲካ ፍልስፍና ሊሆን አልቻለም።
መደመር ግልጽ የሆነ የፍልስፍና ትርጉምና አጠቃቀም ያለው ቃል ቢሆን ኖሮ መጽሐፉ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ የሚያነሳቸውን ጉዳዮች በዚህ ፍልስፍና እይታ እየተመለከተ የሚቀጥል መሆን ይችል ነበር። (ይህ የመጀመሪያው መጽሐፍ ድክመት ወደ ሁለተኛው መጽሐፍ በቀጥታ ተዛውሯል። ሁለተኛው መጽሐፍ የወረሰው የመደመር ትርጉም ከአንደኛው የመጣ በመሆኑ።)
ለፍልስፍና ጽሁፍ ስኬት አንዱ ቁልፍ መለኪያ፣ የጽንሰ ቃል ወይም የጽንሰ ሃሳብ አጠቃቀም ቀጣይነትና ወጥነት ያለው ትርጉም ማላበስ ነው። ዐቢይ ይህን ማድረግ ችሎ ቢሆን መደመር ራሱን የቻለ የአስተሳሰብ መሰባሰቢያ (school of thought) ይሆን ነበር። ጥሩ የአስተሳሰብ መሰባሰቢያ ከሆነ ደግሞ አድማሳዊ ጉልበት ስለሚኖረው እንደ ፖለቲካ ፍልስፍና በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ከኢትዮጵያ ውጭም በአስተሳሰብ ማሰባሰቢያነቱ ለአፍሪካም ፋይዳው የጎላ የፖለቲካ ፍልስፍና ይሆን ነበር።  ይህ አልሆነም።
በዚህ የተነሳ ዶ/ር ዐቢይ በፈላስፋ እይታ የጀመረው ጽሁፍ በሂደት፣ በአንድ የፖለቲካ መሪ፣ በአንድ ቴክኖክራት፣ በዩኒቨርስቲ መምህር፣ በሰባኪ፣ በስነምግባር አስተማሪ፣ በአነቃቂ ተናጋሪ፣ እንደሚዘጋጁ የተለያዩ ጽሁፎች የተለያዩ ገጽታዎች ያለው ሆኗል። ዶ/ር ዐቢይ (መደመር ገጽ V ላይ) እንደነገረን፤ ብዙዎቹ ጽሁፎች በዚህ አይነቱ መንገድ ተዘጋጅተው የነበሩ የማሰልጠኛና የማስተማሪያ ጽሁፎች መሆናቸው ለትዝብቴ ትክክለኛለት ተጨማሪ ማረጋገጫ ነው።
የ“መደመር” ፋይዳ፤
በመጀመሪያው መጽሐፍ፣ በፖለቲካ ጉዳይ ላይ የቀረበው ጽሁፍ መደመር የሚለው ቃል ሳይገባበት በአንድ የበሰለ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር፣ ወይም ብቁ ፖለቲከኛ ሊቀርብ ከሚችለው ልዩነት የሌለው ሆኗል። በተመሳሳይም በኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ የተጻፈው ጽሁፍ በአንድ ብቁ የፖለቲካ ኢኮኖሚስት ወይም ቴክኖክራት ሊጻፍ የሚችል ሆኗል።
ዶ/ር ዐቢይ በፖለቲካ እንደ ሃገርና ህዝብ የገባንባቸውን ችግሮች በደንብ ዘርዝሯቸዋል። በመፍትሄነት ያስቀመጣቸው ነጥቦች በርካታ ናቸው። ርእዮተ አለም ይሁን ቀኖና ከውጭ ቃርመን በማምጣት ከዚህ ቀደም በታሪካችን የሰራነውን ስህተት ደግመን እንዳንሰራ ያስጠነቅቀናል። መፍትሄዎቹ በሚገባ ከሃገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ጋር የተገናዘቡ፣ ፖሊሲዎቹ በጥናትና ምርምር የተደገፉ በጥልቀት የታሰበባቸው ሊሆኑ እንደሚገባ፣ መዋቅራዊና ተቋማዊ ማሻሻያዎችና ግንባታዎች እንደምንሻ፣ በነዚህ መዋቅሮች ውስጥ ለመስራት የሚመጥኑ በቂ እውቀትና ክህሎት ያላቸው ሰራተኞች እንደሚያስፈልጉ፣ እነዚህ ሰራተኞች ሊኖራቸው የሚገባው የስነምግባር የሞራል ባህርያት  ምን እንደሆኑ ይዘረዝራል።
የኢኮኖሚውና የማህበራዊ ችግሮቻችንም በሚገባ ተዳስሰዋል። እዚህ ላይም ቢሆን ለችግሮች ብዙ አይነት መድሃኒቶች ተጠቁመዋል። መፍትሄዎቹ እንደ ፖለቲካው፣ ሃገራዊ ቅኝት ያለው መፍትሄ መሻት፣ የተቋም ግንባታ የመዋቅር ለውጥ ወይም ማሻሻያ፣ የግለሰቦች የእውቀት የክህሎትና የሞራል ግንባታ የሚጠይቅ መሆኑ ተዘርዝሯል። በቀረቡት ችግሮችና በተሰነዘሩት መፍትሄዎች ብዙዎቻችን ልዩነት የሚኖረን አይመስለኝም።
እነዚህ መፍትሄዎች መሃል “መደመርን” የምናገኘው፣ ተቋማዊና መዋቅራዊ መስተጋብር የሚያስፈልጋቸው ነገሮች፣ እርስ በርሳቸው ተቀናጅተው ተሰናስነው በመስራት ስለሚያስገኘው ጠቀሜታ ዶ/ር ዐቢይ ከሚሰጠው አስተያያት ጋር ተያይዞ ነው። በግለሰቦችና በቡድኖች መሃከል የሚደረግ መስተጋብር ጥላቻን ትቶ በፍቅር፣ መጠላለፍን ትቶ በትብብር፣ መከፋፋልን ትቶ በአንድነት ላይ ከሆነ ሃገራችንንና  ማህበረሰባችንን ወደ ከፍታ ማሻገር እንደምንችል በመዘርዝር ነው። ይህ የመደመር ትርጉም በ “የመደመር መንገድ” በሚለው መጽሐፍ በስፋት ስራ ላይ የዋለ ነው። ይህን የመደመር ምልከታም አለመቀበል አይቻልም።
ይሁንና በሁለቱም መጽሐፎች ውስጥ መደመር በስፋት በስራ ላይ የዋለበት አተያይ በባህላችን ከምናውቃቸው፣ “ድር ቢያብር አንበሳ ያስር፣ ከአንድ ብርቱ ሁለት መድሃኒቱ፣ አንድ አይነድ አንድ አይፈርድ፣ አንድ በሬ ስቦ አንድ ሰው አስቦ፣ ጥርስና ከንፈር ሲደጋገፍ ያምር፣ ሃምሳ ሎሚ ለአንድ ሰው ሸክሙ ለሃምሳ ሰው ጌጡና ወዘተ ከመሳሰሉ” ተባብሮ በመስራት፣ በመታገል፣ በመምከር፣ በማሰላስል፣ በማጌጥ ስለሚገኘው ማህበራዊ ጠቀሜታ በባህላችን ከምናውቀው እውቀት በላይ የተሻገረ አዲስ ነገር የለበትም። እንዲህ አይነት የባህል ሃብት እንዳለን ለረሳነው በማስታወሻነት የሚኖረውን ፋይዳ ግን አሳንሼ አላየሁትም።
በሌሎች ገጾች (መደመር ገጽ 36) የመደመር ሃሳብ እያፈረሱ እያወደሙ ከዜሮ አለመጀመር ጋር ይያያዛል። እዚህ መደመር ተራ ድምር ሆኖ ነው የቀረበው። በነበረው ላይ መደመር ከተደመሩት ነገሮች በላይ የላቀ የመደመር ውጤት የሚያመጣ ስላልሆነ መደመሩ ከተራ ክምችት ማሳደግ የዘለለ አይደለም።
በተበታተነ መንገድ ወደ አንድ ግብ ከመሮጥ በጋራ ወደ አንድ ግብ መሮጥ ያለውን ጠቀሜታ ዐቢይ በሚያስረዳባቸው ቦታዎች መደመር፣ ከተራ ድምር በላይ የላቀ ውጤት የሚያስገኝ ሆኖ ይቀርባል። አንድና  አንድ ሲደመር ሁለት መሆኑ ቀርቶ ከሁለት በላይ የሚያድገበትን እሳቤ የያዘ አገላለጽ ነው።
ይህ አመለካከት ከዚህ በላይ በጠቅስናቸው ባህላዊ አባባሎች የተገለጸ ማህበራዊ ግንዛቤ ነው። አንድ በሬ ብቻውን ከሚያርስ አንድ ሰውም ብቻውን ከሚያስብ ሁለቱም ሁለት ሁለት ወይም ከዛ በላይ መሆናቸው ከተራ ድምራቸው የላቀ ውጤት ማምጣታቸው በሚገባ ግንዛቤ የተያዘበት ተረትና ምሳሌ ነው። መደመር የእንግሊዝኛውን synergy (ከተራ ድምር በላይ) የሚል ትርጉም ያገኘበት ምሳሌ ነው።
“አንድን ወይፈን ወይንም አንድ አሮጌ በሬ ለብቻቸው እየጠመዱ ከማረስ፣ ገበሬው ወይፈኑን ከአሮጌው በሬ ጋር አቀናጅቶ በመጥመድ ስራውን የሚሰራው የሁለቱ ቅንጅት በጉልበት ብቻ ሳይሆን በልምድና በእውቀት ጭምር ከተራ ድምር በላይ የተሻገረ ውጤት እንዳለው ስለሚያውቅ ነው።” ይህ ምሳሌ በዐቢይ ሁለተኛው መጽሐፍ በ“የመደመር መንገድ” ውስጥ ተጠቅሷል (ገጽ 22)፡፡ ይህ የላቀ የመደመር እሳቤ፣ ከተራ ድምር በላይ የሚል ትርጉም ያለው እሳቤ በሁለቱም መጽሐፎች ውስጥ በጥቂት ጉዳዮች ላይ ካልሆነ  በስተቀር በርካታ ጉዳዮችን የሚመለከት ሆኖ አናገኘውም።
ከዚህ ውጭ ለመደመር የተሰጡ ሌሎች ትርጉሞች  በሙሉ ከዚህ በፊት በተለያዩ ሰዎች የተባሉና የተጻፉ፣ በተለያዩ የሃገሪቱ የፖለቲካ ሰዎች፣ ምሁራን፣ የሃይማኖት መሪዎች በተለያዩ አጋጣሚዎች በተደጋጋሚ የተነገሩ ናቸው።
የአቀራረብ፣ የተቆርቋሪነት ስሜት፣ የዝርዝር ልዩነቶች ካልሆነ በስተቀር ሃሳቦቹን በተደጋጋሚ የሰማናቸው ናቸው። በችግሮች ትንተና እና በመፍትሄዎቹ ፍለጋ ላይ ዐቢይ ከብዙዎቹ የበለጠ የላቀና የጠለቀ ጥረት ያደረገ መሆኑን  ሳንዘነጋ።


Read 1499 times Last modified on Saturday, 17 April 2021 12:20