Saturday, 17 April 2021 12:37

የኬንያ ዝግጅት ለአፍሪካ ተምሳሌት ይሆናል

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

   • በ14 ኦሎምፒያዶች በድምሩ 103 ሜዳልያዎች በመቀዳጀት (31 የወርቅ፤ 38 የብርና 34 የነሐስ) በአፍሪካ ትልቁን ውጤት ያስመዘገበች ናት
     • ከ100 በላይ ኦሎምፒያኖችን በ6 የተለያዩ ኦሎምፒክ ስፖርቶች ለማሰለፍ እየሰራች ነው፤ 87 ኦሎምፒያኖች አስፈላጊውን ሚናማ አሟልተዋል፡፡
     • 50 ሚሊዮን ኬንያውያን "YouaretheReason" በሚል መርህ ተሳስረዋል


       ባለፉት አራት ኦሎምፒያዶች በከፍተኛ የሜዳልያ ስብስብ   አፍሪካን በማስጠራትና በመምራት የተሳካላት ኬንያ ከ32ኛው ኦሎምፒያድ ጋር በተያያዘ የምታደርገው እንቅስቃሴ የሚያስደንቅ ነው፡፡ የኬንያ መንግስት፤ የስፖርት ምክር ቤት፤ አትሌቲክሱን የሚመራው "አትሌቲክስ ኬንያ"፤ ብሄራዊ ኦሎምፒክ ኮሚቴውና የቀድሞ ኦሎምፒያኖች ተቀናጅተው እየሰሩ በመሆናቸው ለአፍሪካ ተምሳሌት የሚሆን የኦሎምፒክ ንቅናቄ መፍጠር ችለዋል፡፡  ከቶኪዮ 2020 በፊት  በተሳተፈችባቸው 14 ኦሎምፒያዶች በድምሩ 103 ሜዳልያዎች በመቀዳጀት (31 የወርቅ፤ 38 የብርና 34 የነሐስ) ኬንያ በአፍሪካ ትልቁን ውጤት እንዳስመዘገበች የሚታወቅ ሲሆን  ኢትዮጵያ በ13 ኦሎምፒያዶች በመሳተፍ (22 የወርቅ፤ 11 የብርና 21 የነሐስ) 54 የኦሎምፒክ ሜዳልያዎችን በመሰብሰብ  ትከተላለች፡፡
ኬንያ በዝግጅቷ ለቶኪዮው 32ኛው ኦሎምፒያድ ብቻ ሳይሆን ፓሪስ በ2024 እኤአ ለምታስተናግደውን 33ኛው ኦሎምፒያድ ጭምር ሲሆን የኦሎምፒክ ቡድኑን ዝግጅት ሳይንሳዊና የተሟላ በማድረግ፤ አዳዲስ ኦሎምፒያኖች ለማፍራት በመንቀሳቀስ ፤ የኦሎምፒክ ስፖርቶች ለማብዛት በማቀድና በዓለም አቀፍ ግንኙነቶች ላይ ተሰሚነትን በመጨመር ውጤታማ እየሆነችበት ነው፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ዝግጅትና ተሳትፎ እንደልማዱ በውዝግቦች እንደታጀበ ነው፡፡ በኦሎምፒክ ኮሚቴው እና በአትሌቲክስ ፌደሬሽኑ መካከል የተፈጠሩት ውዝግቦች የኦሎምፒክ ቡድኑን ዝግጅት አዳክመውታል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የስፖርት አስተዳደር በውጤት ከምንቀራረባት ጎረቤታችን ኬንያ ጋር በጭራሽ ለማነፃፀር የሚከብድበት ደረጃ ላይ ደርሰናል፡፡  ኢትዮጵያ ውስጥ ለቶኪዮ 2020  በሚደረገው ዝግጅት የተያዙ ብሄራዊ እቅዶች የታሰበላቸውን ግብ አልመቱም፡፡ በስፖርት አፍቃሪው የኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ምንም አይነት የኦሎምፒክ ጉጉቱን ለመፍጠር አዳጋች ሆኗል፡፡ በዓለም አቀፍ ሚዲያዎችም ስለ ኢትዮጵያውያን ኦሎምፒያኖች ያን ያህል ሽፋን እየተሰጠ አይደለም፡፡ በኢትዮጵያ የስፖርት አስተዳደር ላይ ያሉት አመራሮች በዓለም አቀፍ የስፖርት ተቋማት ከመካሰስ  ባለፈ የሚጫወቱት ሚናም የለም፡፡
ከሳምንት በፊት ኬንያ ላይ  በአገሪቱ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ  ኮቪድ 19 በፈጠረው ወቅታዊ ስጋት  የተነሳ የስፖርት እንቅስቃሴዎች በሙሉ እንዲቋረጡ ያዘዙ ቢሆንም መመርያው የኬንያ ኦሎምፒክ ቡድን ለቶኪዮ 2020 በልዩ ሁኔታ የሚያደርገውን ዝግጅት የሚያስተጓጉለው አልሆነም፡፡ ብሄራዊ ኦሎምፒክ ኮሚቴው ባቀረበው ጥያቄ በሁሉም ባለድርሻ አካላት የኦሎምፒክ ቡድኑ ትኩረት በማግኘቱ በኮቪድ 19 ላይ ከመስጋት ይልቅ ለቡድኑ የሚደረጉ ማበረታቻዎችን በማጠናከር የሚሰሩት ተግባራት ተጠናክረዋል፡፡ የኬንያ ኦሎምፒክ ቡድን ላይ 76 ኦሎምፒያኖች ሚኒማቸውን በሟሟላት ዝግጅት ላይ ሲሆኑ፤ በተለይ በራግቢ እና በመረብ ኳስ በሁለቱም ፆታዎች ያሉትን ቡድኖች ያለፈውን 1ወር በከፍተኛ ጥንቃቄ  በተሞላበት የዝግጅት ፕሮግራም ውስጥ ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡ 87 ኦሎምፒያኖች አስፈላጊውን ሚናማ አሟልተው ዝግጅት እያደረጉ ሲሆን በኦሎምፒክ ቡድን ውስጥ ለሚገኙት ሁሉ ከሳምንት በፊት  የኮቪድ 19 ክትባት መሰጠቱንም ለማወቅ ተችሏል፡፡  ከዚሁ ጋር ተያያይዞ የኬንያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ በአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን የኦሎምፒክ ቡድኑ በቶኪዮ 2020 ላይ በሚኖረው ቆይታ ላይ እቅዱን በይፋ በማስተዋወቅ እየሰራ ይገኛል፡፡ 32ኛው ኦሎምፒያድ ከመጀመሩ  14 ቀናት ቀደም ብሎ የኬንያ ቡድን ጃፓን እንደሚገባ የተገለጸ ሲሆን ኦሎምፒያኖችን እስከ ኦሎምፒኩ መክፈቻ ድረስ ኩሩሜ እና ኩሩሾ በተባሉ ደሴቶች በማረፍ የመጨረሻ ዝግጅታቸውን የሚያከናውኑ ይሆናል፡፡
በፖል ቴርጋት የሚመራው የኬንያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ አትሌቲክሱን ከሚመራው አትሌቲክስ ኬንያ አትሌቲክስ ጋር ተጣጥሞ መስራቱን ከአገሪቱ ሚዲያዎቹ የሚወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ በሳምንቱ አጋማሽ ላይ ቶኪዮ 2020  ሊጀመር ልክ 100  ቀናት ሲቀሩት በዋና ከተማዋ ናይሮቢ በሚገኘው ብሄራዊ ሙዚዬም ስፖርቱ በሚመለከታቸው የካቢኔ አባል ለ50 ሚሊዮን ኬንያውያን የኦሎምፒክ ነጋሪት ተጎስሟል፡፡ የኬንያ ብሄራዊ ኦሎምፒክ ኮሚቴ፤ ቲም ኬንያ እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በቶኪዮ 2020 የሚጠቀሙትን የማህበራዊ ሚዲያ መሪ ቃል "YouaretheReason በይፋ አስተዋውቀዋል፡፡ በኦሎምፒክ መድረክ የኬንያ ኦሎምፒያኖች የሰሩትን ታሪክ በአድናቆት ለማስታወስና ቀጣይ ድሎችንም በጋራ ለማድመቅ ታስቦ ነው፡፡ በነገራችን ላይ ኬንያ በቶኪዮ 2020 ላይ ከፍተኛ ጉጉት ማሳደሯን TEAM KENYA በኦፊሴላዊ ድረገጹ የሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ያመለክታሉ። በዘመናዊ መንገድ የተዘጋጀው፤ እና ከሁሉም የሚዲያ አውታሮች ጋር በሚያስተሳስር የመረጃ መረብ የሚንቀሳቀሰው የድጋፍ ቡድኑ መላው አፍሪካን የሚያስተምር ይሆናል። በሚለው ድረገፅ ላይ ስለኬንያ የኦሎምፒክ ቡድን እንቅስቃሴ የተሟሉ መረጃዎች በዜና፤ በፎቶና በቪድዮ ምስሎች፤ በሊንኮች ተደራጅቶ 32ኛውን ኦሎምፒያድ በተሟላ ሁኔታ እየተጠባበቀ ይገኛል፡፡
ኬንያ በቶኪዮ 2020 ላይ ከ100 በላይ ኦሎምፒያኖችን በ6 የተለያዩ ኦሎምፒክ ስፖርቶች ለማሰለፍ እየሰራች ሲሆን 87 ኦሎምፒያኖች አስፈላጊውን ሚኒማ አሟልተዋል፡፡ ብሄራዊ ኦሎምፒክ ኮሚቴው  ባለፈው ሰሞን ከቸኦሎፒክ ቡድኑ ጋር ከአሰልጣኞቹ ባሻገር የሚሰሩ 5 ባለሙያዎችን የሾመች ሲሆን በህክምና፤ በስፖርት ሳይኮሎጂ፤ በአካል ብቃት፤ በስፖርት ሳይንስ እና በአመጋገብ ዙርያ ቡድኑን የሚያገለግሉ ይሆናል፡፡ የኦሎምፒክ መድረኩ በአንድ ዓመት  መራዘሙ በወቅታዊ አቋማቸው በጥሩ ደረጃ ላይ የነበሩትን ኦሎምፒያኖች ዝግጅት ቢያስተጓጉልም በኬንያ ግን ተመችቷቸዋል። ከቶኪዮ 2020 መራዘም ጋር ተያይዞ ቡድኑን በተሻለ ለማዘጋጀት በሌላ በኩል በአስተዳደራዊ እንቅስቃሴዎች ተምሳሌት በሆኑ አቅጣጫዎች ለመስራት ተችሏል፡፡ ለናሙና ያህል የኬንያ ማራቶን ቡድን የሚጠቀስ ሲሆን ዋና አሰልጣኙ ዲቪድ ሌቲንግ ለአትሌቲክስ ዊክሊ እንደተናገሩት ዝግጅታቸው በሁለቱም ፆታዎች የሜዳልያ ሰንጠረዡን ለመቆጣጠር የሚያስችል መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ይህን ሁኔታም ለውርርድ ማቅረብ ይቻላል በማለት ታዋቂ አቋማሪ ድርጅቶችን ያነሳሱት ዋና አሰልጣኙ በተጨማሪ እንደገለፁት የማራቶን ቡድናቸውን የበላይነት የትኛውም አገር ሊቀናቀነው ወይንም ስጋት ሊሆንበት አይችልም፡፡  የኦሎምፒክ ማራቶን በሚካሄድበት ስፍራ ከፍተኛ ሂውሚዲቲ መኖሩ በከፍተኛ ቦታዎች ለሚኖሩ እና ለሚለማመዱ አትሌቶች ፈታኝ ሁኔታዎችን ሊፈጥርባቸው ይችላል፡፡ አትሌቶች ያላቸውን ልምድ ተጠቅመው እና በአየሩ ክብደት ያለውን ጫና ተቋቁመው ስኬታማ ይሆናሉ  ሲሉም ዴቪድ ሌቲንግ ለአትሌቲክስዊክሊ ተናግረዋል፡፡
በአስተዳደር በኩል በኬንያ ኦሎምፒክ እንቅስቃሴ የሚስተዋለው ተመሳሳይ ልበ ሙሉነት ነው፡፡ የኦሎምፒክ ኮሚቴው ከኬንያ መንግስት እና ኬንያታ ዩኒቨርስቲ ጋር በመተባበር ልዩ የስፖርት ሳይንስ ማዕከል ሊያቋቁም እየተንቀሳቀሰ መሆኑን መጥቀስ ይቻላል፡፡ በኪሳራኒ ውስጥ በሚገኘው ሞይ ኢንተርናሽናል የስፖርት ማዕከል ውስጥ የሚገነባው የሳይንስ ተቋሙ ለሁሉም ስፖርቶች በተለይ ለኬንያ ብሄራዊ ቡድኖች አገልግሎት የሚሰጥና በዘመናዊነት  ለአፍሪካ ተምሳሌት ሊሆን የሚችል ነው፡፡ የኬንያን ስፖርተኞች ዓለም አቀፍ ተሳትፎ በከፍተኛ የብቃት ደረጃ ያሳድጋል የተባለውን የሳይንስ ማዕከል የሚያስገነባው ኦሎምፒክ ኮሚቴው እስከ 2024 የፓሪስ ኦሎምፒክ ድረስ በዚህ እንቅስቃሴው የሚቀጥል ይሆናል። ይህ እንቅስቃሴውም  ኬንያ  በኦሎምፒክ መድረክ የምትሳተፍባቸውን የስፖርት አይነቶችና የምታገኛቸውን ሜዳልያዎች ብዛት እንደሚጨምር ታምኖበታል፡፡ በ2016 እኤአ ላይ ሪዮ ዲጄኔሮ ባስተናገደችው 31ኛው ኦሎምፒያድ ላይ ኬንያ 86 ኦሎምፒያኖችን በማሳተፍ 6 የወርቅ 6 የብርና 1 የነሐስ ሜዳልያ በማስመዝገብ ከአፍሪካ ግንባር ቀደሙን ውጤት ማስመዝገቧ ይታወቃል፡፡
ባለፉት 4 ኦሎምፒያዶች የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ተሳትፎ በውዝግቦች መታጀባቸው የተለመደ ይመስላል፡፡ ኢትዮጵያ በኦሎምፒክ መድረክ ካላት ወርቃማ ታሪክ አንፃር በየኦሎምፒክ ዓመቱ የሚፈጠሩ እልህ አስጨራሽ ንትርኮች እና ጥፋቶች የሚያሳፍሩ፤ ኢትዮጵያ በመድረኩ ልታገኝ የምትችለውን የሜዳልያ ስብስብን የሚያዳክሙ ናቸው፡፡  ኢትዮጵያ በኦሎምፒክ መድረክ እንደ ኬንያ ሁሉ ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገቧ ብቻ ሳይሆን በስፖርት አስተዳደሩም ተምሳሌት መሆን እንደሚገባት በአህጉራዊና ዓለም አቀፍ ተቋማት ውሳኔ ሰጭ እና ተሰሚ ሆና መጠቀስ እንዳለባትም ስፖርትን የሚያስተዳድሩት ማወቅ ይኖርባቸዋል፡፡

     በኢትዮጵያ የቶኪዮ 2020 አጠቃላይ ዝግጅቶች ቢያንስ በሚዲያ አውታሮች ላይ እንደኬንያ ለመንቀሳቀስ ለምን አልተቻለም?  የስፖርቱ አስተዳደር በውዝግቦች በመጠመዱ  ይህን ለማሳካት በጭራሽ የሚታሰብ አይደለም፡፡ የኢትዮጵያን ኦሎምፒክ ቡድን የሚያነቃቃ ምንም አይነት ስራ የለም፡፡ በኦፊሴላዊ ድረገፅ ወይንም በማህበራዊ ሚዲያዎች ባለድርሻ አካላቱን የሚያስተሳስር ምንም አይነት እንቅስቃሴ አልተሞከረም፡፡ በኢትዮጵያ የሚዲያ አውታሮች ላይ ስለ ኦሎምፒኩ ከተወራ ስፖርቱን በሚያስተዳድሩ ተቋማት  ያሉት ውዝግቦች  ሽፋን ያገኛሉ፡፡ የስፖርቱ አመራሮችም ሚዲያዎችን ለዚሁ ሁኔታ ብቻ ይፈልጓቸዋል እንጅ  ለኦሎምፒክ ቡድኑ ሞራል በሚሰጥ ሽፋን እንዲሰሩ አነሳስተው አያውቁም፡፡ የውዝግብ አጀንዳዎቻቸው ማራገቢያ አድርገው ይመለከቷቸዋል፡፡ በተለያዩ ዓለም አቀፍ የስፖርት ውድድሮች በአፍሪካ ዋንጫ፤ በዓለም ዋንጫ፤ በአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና፤ በኦሎምፒክና በሌሎችም ከፍተኛ ልምድ ያላቸውን ዜጎች በማስተባበር የኦሎምፒክ ቡድኑን በማነሳሳት በቀላሉ ሊሰራ ይቻል ነበር፡፡  ምንም  እየተሰራ አይደለም፡፡ የስፖርት አስተዳዳሩ ሚዲያውን ከቶኪዮ 2020 ጋር አያይዞ ብሄራዊ መግባባትን በሚፈጥርበት ዘመቻ ሊያንቀሳቀስ ቢችልም አልተጠቀመበትም፤ ቶኪዮ 2020 ልክ መቶ ቀናት ሲቀሩት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን የወርቅ ኢዮቤልዩውን በ50ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከማክበሩ ባሻገር ሌላ ወሬ አልነበረም፡፡ ኢትዮጵያ በኦሎምፒክ መድረክ ትልቁን ውጤት በአትሌቲክስ ከማስመዝገቧ አንፃር ብሄራዊ ኮሚቴው ቢያንስ ይህን ስነስርዓት በማድመቅ እንኳን ከፌደሬሽኑ ጎን መቆም ያስፈልገው ነበር፡፡

Read 780 times