Saturday, 17 April 2021 12:43

ከ37 በላይ ስደተኛ ኦሎምፒያኖች በኦሎምፒክ ባንዲራ ይሰለፋሉ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(1 Vote)

    በቶኪዮ 2020 ኦሎምፒክና ፓራሊምፒክስ ላይ ለሚሳተፈው የስደተኞች ኦሎምፒክ ቡድን የትውውቅ ስራዎች ቀጥለዋል፡፡ የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ተቋም ከፍተኛ ኮሚሽነር   በለቀቁት የማስታወቂያ ቪድዮ ስፖርት የዓለም ሰላምን እንደሚያመጣና ለስደተኞችም የሚሆን ነው ብለዋል፡፡ ስደተኞች የኦሎምፒክ ባንዲራን በማንገብ ተሳትፎ ማድረጋቸው ለዓለም ህዝብ መቻቻል፣ አብሮነት እና ሰላምን ያስተምራል፤ ይህም የኦሎምፒክ አጠቃላይ ዓላማን ያንፀባርቃል ተብሏል፡፡
ስደተኛ ኦሎምፒያኖች ኦሎምፒክ ላይ ለመጀመርያ ጊዜ የተሰለፉት በ31ኛው ኦሎምፒያድ 2016 እኤአ ሪዮ ዲጄኔሮ ላይ ነው፡፡ ዓለምአቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ ይህን ተግባራዊ ሲያደርግ በሰው ልጆች ላይ እየበዛ በመጣው ስደትና መፈናቀል  የግንዛቤ ለውጥ ለመፍጠር ነው፡፡ ‹‹ይህ በዓለም ላይ ላሉት ሁሉም ተፈናቃዮች ልዩ  የተስፋ ምልክት ይሆናል፣ ስደትን በዓለም ዙርያ ያመጣውን ቀውስ  ዓለም በደንብ ያውቃል። ስደተኞች እንደእኛው ሰብዓዊ ፍጡራን መሆናቸውን ለዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ያንፀባርቃል›› ብለው የተናገሩት የዓለም አቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዝዳንት ቶማስ ባች ናቸው፡፡
የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ተቋም እንዳመለከተው በቶኪቶ 2020 ላይ ለመሳተፍ ከ60 በላይ ስደተኛ ኦሎምፒያኖችና ፓራኦሎምፒያኖች በተለያዩ አገራት ዝግጅታቸውን እየሰሩ ናቸው። ዓለም አቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ የኦሎምፒክ ስደተኞች ፋውንዴሽን መስርቶ የአራት ዓመታት እቅድ በማውጣት እየተንቀሳቀሰ ሲሆን እስከ 2024 እኤአ ከ1 ሚሊዮን በላይ ስደተኞችን ለመርዳት እና በኦሎምፒክ መርህ ውስጥ ለማሳለፍ ነው፡፡ በፋውንዴሽኑ አማካኝነት ስደተኞች ከኦሎምፒክ ስፖርቶች ጋር እየተቀራረቡ ናቸው። ከሪዮ ኦሎምፒክ በኋላ በ6 አገራት የሚገኙ 200ሺ ስደተኞችን በኦሎምፒክ መርህ ማስተሳሰር ተችሏል፡፡ የስደተኞች ኦሊምፒክ ቡድኑ በቶኪዮ 2020 መክፈቻ ሥነ ሥርዓት ላይ በቀድሞዋ ኦሎምፒያን ቴግላ ላውሩፕ የሚመራው ቡድን የኦሊምፒክ ሰንደቅ ዓላማ በማንገብ በሁለተኛ ደረጃ ከግሪክ ቀጥሎ በሰልፍ ትርኢቱ ይሳተፋል፡፡  ቡድኑ በኦሎምፒኩ በሚሰልፍባቸው  ውድድሮች፤ መድረኮችና የሜዳልያ ሥነ ሥርዓቶችን የኦሎምፒክ ሰንደቅ ዓላማ የሚውለበለብና የኦሎምፒክ መዝሙር የሚጫወት ሲሆን እንደሌሎች 206 ብሄራዊ  ኦሎምፒክ ኮሚቴዎች በኦሎምፒክ መንደር የሚስተናገድ ይሆናል፡፡
‹‹ ከስደተኞች መካከል ታላላቅ የወደፊቱ የዓለም መሪዎች እና  ለውጥ ፈጣሪዎች ይገኛሉ ፡፡ ስፖርትን በመላው ዓለም ለሚሰደዱ ወጣት ትውልዶች ማድረስ ትልቅና በክብር የምቀበለው ሃላፊነት ነው፡፡›› በማለት የተናገረው የቀድሞ ኦሎምፒያን ምርጥ የረጅም ርቀት ሯጭ  ፖል ቴርጋት ነው። የኬንያ ብሄራዊ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዝዳንት የሆነው ፖል ቴርጋት የዓለም አቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ አባል ሲሆን  በኦሎምፒክ የስደተኞች ፋውንዴሽን ላይ በአባልነት እንዲሰራ ተሹሟል። ኬንያ ከኦሎምፒክ የስደተኞች ቡድን ጋር ከሰሩ አገራት  አንዷ ስትሆን በIOC ነፃ የኦሎምፒክ ተሳትፎ ያገኙ 18 ስደተኛ ኦሎምፒያኖች ለልዩ ስልጠና አስተናግዳለች፡፡  በዓለም አቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ነፃ የኦሎምፒክ ተሳትፎ እድል ያገኙ ከ55 በላይ ስደተኛ ኦሎምፒያኖች ከ13  አገራት ተመልምለዋል፡፡ የኦሎምፒክ ስደተኞች ፋውንዴሽን በአምስቱም አህጉራት ከሚገኙ   21 ብሄራዊ ኦሎምፒክ ኮሚቴዎች ጋር እየሰራ ሲሆን ስደተኛ ኦሎምፒያኖችን የሚያስተናግዱት አገራት አውስትራሊያ ፤ኦስትሪያ፤ ቤልጅዬም፤ ብራዚል፤ ካናዳ፤ ክሮሽያ፤ ግብፅ፤ ፈረንሳይ፤ ጀርመን፤ እስራኤል፤ ጆርዳን፤ ኬንያ፤ ሉክሰምበርግ፤ ፖርቱጋል፤ ሆላንድ፤ ኒውዝላንድ፤ ትርኒዳንድ ኤንድ ቶቤጎ፤ ቱርክ፤ ስዊድን፤ ስዊዘርላንድ እና ዩናይትድ ኪንግደም ናቸው፡፡ ከአፍሪካና ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች ከ1 ሚሊዮን በላይ ስደተኞችን ተቀብላ የምታስተናግደው ኢትዮጵያ በዚሁ የኦሎምፒክ እንቅስቃሴ አለመሳተፏ ከፍተኛ ድክመት ነው። በውዝግብ የተጠመደው ኦሎምፒክ ኮሚቴ በተመሳሳይ ዓለም አቀፍ ተግባራት የሚሳተፍበት ቁመናና ትኩረት እንደሌለውም ያመለክታል፡፡
በ31ኛው ኦሎምፒያድ ሪዮ ዲጄኔሮ በተሳተፈው የስደተኞች ኦሎምፒክ ቡድን በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ሲሳተፍ 10 ስደተኛ አሎምፒያኖች በሶስት የኦሎምፒክ ውድድሮች  በአትሌቲክስ፤ ጁዶ እና ውሃ ዋና የመሰለፍ እድል አግኝተዋል፡፡ ዓለም አቀፉ ኦሎምፒክ ከሚቴ ባለፉት 4 ዓመታት ከ2 ሚሊዮን ዶላር በላይ ኢንቨስት አድርጎ ለቶኪዮ 2020  ያቀደው  37 ስደተኛ አሎምፒያኖችን ለማሳተፍ ሲሆን ዝርዝሩ ጁን 20 ከሚከበረው የዓለም ስደተኞች ቀን ተያይዞ በይፋ ይገለጻል።  በ32ኛው ቶኪዮ ላይ የስደተኞች ኦሎምፒክ ቡድን በ12 የኦሎምፒክ ስፖርቶች በአትሌቲከስ፤ ውሃ ዋና፤ ባድሜንተን፤ ቦክስ፤ ሻሞላ፤ ብስክሌት፤ ጁዶ፤ ካራቴ፤ ቴክዋንዶ፤ ኢላማ ተኩስ፤ ክብደት ማንሳትና ነፃ ትግል ላይ  እንደሚሳተፉ ይጠበቃል።
ዓለም አቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ለኦሎምፒክ ተሳትፎ በሚያዘጋጀው ነፃ እድል ከ32ኛው ኦሎምፒያድ በፊት ከ171 በላይ ብሄራዊ ኦሎምፒክ ኮሚቴዎች ተጠቃሚ ሲሆኑ፤ በ21 የኦሎምፒክ ስፖርቶች ለሚወዳደሩ ከ1280 በላይ ኦሎምፒያኖች ስኮላርሺፖቹ ተሰጥተዋል። በዓለም አቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ነፃ እድል 657 ኦሎምፒያኖች ታላቁን ዩስፖርት መድረክ ተሳትፈው 72 የኦሎምፒክ ሜዳልያዎችን ተቀዳጅተዋል፡፡Read 10655 times Last modified on Saturday, 17 April 2021 13:01