Saturday, 17 April 2021 00:00

ለፊልም ተመልካቾች የተዘጋጀው የምስጋና ዘመቻ ነገ ይጠናቀቃል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

 ከትንሳኤ በዓል በኋላ ዘመቻው እንደ አዲስ ይጀምራል ተብሏል

            ለበርካታ ዓመታት ፊልም በመመልከት የሀገራችን የፊልም ዕድገት ላይ ጉልህ ሚና ያለውን ተመልካች ለማመስገን የተዘጋጀው የአንድ ወር ዘመቻ ነገ ይጠናቀቃል። የኢትዮጵያ ፊልም ፕሮዲዩሰሮች ማህበር ያዘጋጀው ይህ የተመልካች የምስጋና ፕሮግራም፤ በተለያዩ ሲኒማ ቤቶች ፊልም ለመመልከት የመጡትን ዕድለኞች ድንገቴ ሽልማት (ሰርፕራይዝ) በመሸለምና አርቲስቶች ለተመልካቾች በቀጥታ ሽልማት ሲሰጡ የሰነበቱበት አስደሳችና ስኬታማ ወር እንደነበር የማህበሩ ፕሬዚዳት ቢኒያም አለማየሁ ገልጿል።  
በመጀመሪያው ሳምንት በተለይ በዓለም ሲኒማ ፊልም ለማየት የመጡ ዕድለኞች ሽልማት ያገኙ ሲሆን ሽልማቶቹም ለሁለት ሰዎች ከነቤተሰቦቻቸው አርባ ምንጭ ኃይሌ ሪዞርት፣ ለሁለት ዕድለኞችም እንዲሁ ከነቤተሰቦቻቸው በአዳማ ኃይሌ ሪዞርት እንዲዝናኑ ዕድል የሰጠ ሲሆን ለሁለት ሰዎች ደግሞ በአለም ፊትነስ ሴንተር የጂምናዚየም አገልግሎት እንዲያገኙ ተደርጓል ተብሏል።
በሌሎች ሲኒማ ቤቶች የእጅ ሰዓቶች፣ ነፃ የመግቢያ ካርዶችና መሰል ሽልማቶች ለተመልካች የተበረከቱ ሲሆን ይህም ያልተለመደና አዲስ በመሆኑ በተመልካቹና በፊልም ባለሙያው መካከል ያለውን መቀራረብ ይበልጥ እንደሚያሻሽለው ቢኒያም ዓለማየሁ ገልጿል። በነዚህ ሶስት ሳምንታት ከሽልማቶቹ በተጨማሪ “ስለመና” “ከርቤ” እና ከመናድርድር የተሰኙ አዳዲስና የተመረጡ ፊልሞች በተለያዩ ሲኒማ ቤቶች ለእይታ የቀረቡ ሲሆን ነገ በዘመቻው መዝጊያ የአምለሰት ሙጬ “ምናለሽ” ፊልም ለእይታ እንደሚቀርብ ታውቋል። ከትንሳኤ በዓል በኋላም ይኸው ተመልካችን የማመስገን ዘመቻ በአዲስ መልክ እንደሚቀጥል የማህበሩ ፕሬዚዳንት ቢኒያም አለማየሁ ጨምሮ ገልጿል።

Read 828 times