Sunday, 18 April 2021 18:00

ዘመን ባንክ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ይፋ አደረገ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

 ከንክኪ ነጻ ቪዛና ማስተር ካርዶች በሀገራችን የመጀመሪያዎቹ ናቸው ተብሏል
                             


           እ.ኤ.አ በ2008 ዓ.ም በአንድ ቅርንጫፍ አገልግሎት የመስጠት ፍልስፍና ሥራውን የጀመረው ዘመን ባንክ፤ ከትላንት በስቲያ አመሻሽ ላይ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን አስተዋወቀ። ባንኩ አሁን ያለንበትን አስቸጋሪ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን  ግምት ውስጥ በማስገባት ደንበኞች ከንክኪ ነጻ የሆነ ግብይት እንዲፈጽሙ የሚያስችሉ “Contactless” ቪዛና ማስተር ካርዶችን ያዘጋጀ ሲሆን ደንበኞች እነዚህን ካርዶች ወደ ኤቲኤም ወይም ፖስ ማሽን በማስጠጋት ብቻ ማንነታቸውን እንዲለይ በማድረግና የምስጢር ቁጥር (Pincode) በመጠቀም በፍጥነት አገልግሎት ማግኘት የሚያስችል ቴክኖሎጂ መፈጠሩን የባንኩ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ደረጀ ዘነበ ገልጸዋል።
ይህም በሀገራችን የባንክ ኢንዱስትሪ የመጀመሪያ ሲሆን ጊዜን በመቆጠብና ንክኪን በማስቀረት ፣የደንበኛችን እርካታ እንደሚጨምር ዋና ሥራ አስፈጻሚው ጨምረው ገልጸዋል።
ባንኩ በዕለቱ ያስተዋወቀው ሌላው ቴክኖሎጂ “ዘመን ፕላቲኒየም” የጉዞ ቅድመ ክፍያ ማስተር ካርድ አገልግሎት ሲሆን፤ ይህም አገልግሎት እስካሁን ከሀገራችን ወደ ውጪ ለሚደረጉ ጉዞዎች የሚያስፈልጉ የውጪ ሀገር ገንዘቦችን ደንበኞች በጥሬ ገንዘብ አማካኝነት ሲስተናገዱ መቆየታቸውን የገለጹት አቶ ደረጀ፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ይህን አገልግሎት በፕላስቲክ ካርድ መስጠት እንዲችል ያወጣውን መመሪያ ተከትሎ ዘመን ባንክ በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን በባንኩ የተዘጋጀ “ዘመን ፕላቲኒየም” የጉዞ ቅድመ ክፍያ ማስተር ካርድ በማዘጋጀትና ወደ ውጪ የሚጓዙ እንዲጠቀሙበት በማድረግ ስራውን አጠናቅቆ ለትግበራ በማብቃቱ ኩራት እንደሚሰማው ገልጸዋል።
ይህ የጉዞ ቅድመ ክፍያ ማስተር ካርድ አገልግሎት ደንበኞች ለጉዟቸው የሚያውሉትን ወጪ አስቀድመው መገመት እንዲችሉና በካርዱም ላይ የሚገኘውን የውጪ ምንዛሬ ገንዘብ ይዘው በመጓዝ ክፍያዎችንና አገልግሎቶችን ለማግኘት የሚያስችል ምቹ የካርድ አገልግሎት መሆኑንም ዋና ሥራ አስፈጻሚው ጨምረው ገልጸዋል።
በሌላም በኩል፤ የውጭ ተጓዦች ጥሬ ገንዘብ ከሀገር ወደ ሀገር ሲጓዙ ይደርስ የነበረውን ስጋት ማለትም የገንዘብ መዘረፍ፣ መጥፋትና የጥሬ ገንዘብ አገልግሎት ማጣት ከመሳሰሉት ችግሮች በማላቀቅ ምቾት እንዲሰማቸው የማያግዝ መሆኑም ተገልጿል። የውጭ ምንዛሬ በካርድ ጭምር እንዲሰጥ የወሰነው ብሔራዊ ባንኩም ሊመሰገን ይገባል ብለዋል- አቶ ደረጀ ዘነበ።
ባንኩ ቀደም ሲል የኢንተርኔትና የሞባይል ስልክ ባንኪንግ አገልግሎቶችን በወቅቱ የነበሩ ቴክኖሎጂዎችንም በመጠቀም ለደንበኞቹ በማስተዋወቅና በመተግበር ቀደምት መሆኑን ያስታወሱት ዋና ስራ አስፈጻሚው፤ አሁን ደግሞ ከጊዜውና ከቴክኖሎጂው ጋር በመራመድ ይበልጥ ዘመናዊና ለደንበኞች ተደራሽ ለማድረግ የኢንተርኔትና የሞባይል ባንኪንግ መተግበሪያውን በአዲስ መልክ ማቅረቡንም አቶ ደረጀ ገልጸዋል።
በዚህ አገልግሎት ደንበኞች የእጅ ስልካቸውን በመጠቀም ብቻ የተለያዩ ክፍያዎችን ማለትም የዲኤስ ቲቪ፣ የስልክና የመሳሰሉትን ክፍያዎች በቀላሉ መፈጸም የሚያስችል ሲሆን፣ በተመሳሳይ ሌሎች ክፍያዎችን ለምሳሌ የአውሮፕላን ጉዞ ትኬት፣ ውሃ፣ መብራት፣ ሆስፒታል፣ ት/ቤት፣ ዩኒቨርስቲዎች፣ የኮሌጆችንና ሌሎች ተዛማጅ ክፍዎችን መከወን እንዲቻል ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራበት እንደሚገኝና በቅርቡም ስራው ተጠናቅቆ አገልግሎት ይሰጣሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ሃላፊው ጠቁመዋል። ባንኩ በተለይ ከንክኪ ነፃ ቪዛና ማስተር ካርዶችን እንዲሁም ዘመን ፕላቲኒየም የጉዞ ቅድመ ክፍያ ካርዶችን አገልግሎት ላይ ለማዋል ከማስተር ካርድና “CRZ Limited” ከተባለ የአየር ላንድ ኩባንያ ጋር በመጣመር ሲሆን ለዚህ ሁሉ ስኬት የበቁትን እነዚህን አጋሮቹን፣ የባንኩን የዳይሬክተሮች ቦርድ፣ የባንኩን የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሰራተኞችና አጠቃላይ የባንኩን የማኔጅመንት አባላት አመስግነዋል።
ባንኩ ባለፉት 13 ዓመት በስኬት መዝለቁን የተናገሩት አቶ ደረጀ ዘነበ፤ በአሁን ወቅት 60 ቅርንጫፎችን በመላው አገሪቱ ከፍቶ እየተንቀሳቀሰ ሲሆን በቅርቡ አዲስ ወዳስገነገባው ህንፃ ሲዛወር ቴክኖሎጂውን ይበልጥ በማዘመን ክፍሎችን በማደራጀትና ዓለም አቀፍ ደረጃውን በመጠበቅ የደንበኞቹን እርካታ ለመጨመር ማቀዱን ጠቁመዋል፡፡
 ባንኩ በቴክኖሎጂው ዘርፍ አበይት ስራዎችን ከመስራት ባለፈ መንግስት “የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025” በማለት ላዘጋጀው ሃገራዊ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂ መተግበር የበኩሉን እያደረገ እንደሚገኝም ገልፀዋል።
ቴክኖሎጂው ይፋ ሲደረግ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ ፣ ማስተር ካርድና “PCR2 Limited” ኩባንያዎች ሃላፊዎች፣ የባንኩ ከፍተኛ አመራሮችና ደንበኞች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል።Read 1393 times