Saturday, 24 April 2021 12:31

መንግስት የሰሜን ሸዋን ጥቃት ቀድሞ መከላከል ያልቻለበትን ምክንያት ለህዝብ እንዲያስረዳ ኢሠመጉ ጠይቋል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

      መንግስት በሰሜን ሸዋ አካባቢዎች የተፈጸመውን ጥቃት ቀድሞ መከላከልና ማስቆም ያልቻለበትን ምክንያት እንዲሁም ስለቀጣይ እርምጃዎቹ ይፋዊ ማብራሪያ እንዲሰጥ የጠየቀው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሠመጉ)፤ የችግሩ አዝማሚያ ሃገር አጥፊ ነው ብሎታል፡፡
“የድርጊቶቹ አፈጻፀምም ሆነ አዝማሚያ አገራችን ላይ የተደቀነውን ትልቅ ችግር አመላካች በመሆኑ የአገራችን ቀጣይ እጣ ፈንታ በእጅጉ አሳሳቢ አድርጎታል” ብሏል ኢሰመጉ::
በተደጋጋሚ የሃገሪቱ የሠብአዊ መብት አያያዝ እንዲሻሻል ሲወተውት መቆየቱን ያስታወሰው ኢሠመጉ፤ ሆኖም ግን በሀገሪቱ ያለው የሠብአዊ መብቶች ሁኔታ ከመሻሻል ይልቅ እየተባባሰና እጅግ አስከፊ ሁኔታ ላይ ደርሶ ሠብአዊ መብቶች ምንም ዋስትና የላቸውም ማለት የሚቻልበት ጊዜ ላይ ደርሰናል፤ ብሏል፡፡
የአጣዬ አካባቢ ሁኔታን በተደጋጋሚ ሲያሳስብ እንደነበር በመጠቆምም፤ ነገር ግን መንግስት ምክረ ሃሳብ ሰምቶ የማስተካከያ እርምጃ ባለመውሰዱ በድጋሚ ችግሮች መፈጠራቸውን አውስቷል፡፡
ከሚያዚያ 6 ቀን 2013 ዓ.ም ከምሽቱ 4 ሰዓት አካባቢ ጀምሮ ባሉት ተከታታይ ቀናት በተፈፀመው በከባድ መሳሪያ የታገዘና ነዋሪዎች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት፣ ሰዎችን ለሞትና መፈናቀል እንዲሁም ንብረትን ለውድመት መዳረጉን ኢሰመጉ በሪፖርቱ አትቷል፡፡
በዚህ ጥቃት በአጣዬ  ዙሪያ ባሉት ማጀቴ፣ በቆሪ ሜዳ፣ በዙጢ፣ በዩሎ ቆላ፣ በሙሉ በርጊቢ፣ ካራ ቆሬ፣ ኔጌሶ፣ ኩሪቱሪ እና ሌሎች አካባቢዎች በተደራጁ ታጣቂ ሃይሎች ጉዳት ደርሷል ብሏል፡፡
በማጀቴ ጥቃቱን ተከትሎ፣ በርካታ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውንና መቁሰላቸውን፣ ነዋሪዎች አካባቢያቸውን ለቀው ወደ ገጠር ቀበሌ መሰደዳቸውንም የኢሰመጉ ሪፖርት ያመለክታል፡፡ በአጣዬ፣ ቆሪ ሜዳ፣ ዙጢ፣ ካራቆሬ፣ የተባሉ ከተሞች ደግሞ ከፍተኛ ውድመት እንደደረሰባቸውና ነዋሪዎቻቸውም መፈናቀላቸውን ጠቁሟል፡፡ በተጨማሪም ከሚያዝያ 7 ቀን 2013 ጀምሮ ከሸ ሮቢት ወደ ደሴ የሚወስደው መንገድ ዝግ በመሆኑ ተጓዦች መቸገራቸውን ኢሰመጉ አመልክቷል፡፡
ኢሰመጉ በጉዳዩ ላይ ጠቅለል ያለ ሪፖርቱን በቅርቡ ይፋ እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በበኩሉ፤ በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ካማሺ ዞን የሴዳል ወረዳን ታጣቂዎች ሙሉ ለሙሉ መቆጣጠራቸውን አስታውቆ፣ መንግስት ለሰላማዊ ሰዎች በአፋጣኝ ይደርስላቸው ዘንድ ጥሪ አቅርቧል፡፡


Read 10452 times