Saturday, 24 April 2021 12:28

"እውነት ቦት ጫማውን ሳያጠልቅ ውሸት ዓለምን ዞሮ ይጨርሳል"

Written by 
Rate this item
(6 votes)

 ከዕለታት አንድ ቀን ባልና ሚስት ጎጆ የሚወጡበት ቤት ለማግኘት በመሯሯጥ ላይ ሳሉና መንደሩን በመዳሰስ ሲዟዟሩ አንድ ደላላ ያገኛሉ።
ደላላው፡- “ምን ዓይነት ቤት ነው የፈለጋችሁት?” አላቸው።
ሚስትየው፡- “ግቢው ለብቻና ሰፋ ያለ፣  ከጎረቤት የማያገናኝ ፣ መብራትና ውሃ ለብቻው ቢሆን እንመርጣለን” አለች።
ደላላው፡- “ችግር የለውም””፤ ሌላ ጊዜ የምትፈልጉት ነገር አለ ወይ?”
ባልየው፡- “የግንብ አጥር አለ?”
ደላላው፡- “ችግር የለውም፤ አሁኑኑ በአንድ አፍታ ይገኝላችኋል”
ሚስትየው፡- “ግን የብረት በር መሆን አለበት”
ደላላው፡- “ችግር የለም፤ ሞልቷል”
ባልየው፡- “ቀለሙንም እኛ እንደፈለግን የምንለዋውጠው መሆን አለበት”
ሚስት፡- “ከዋናው አስፋልት በጣም የማይገባ ፤ አስፋልት ዳር የሆነ አለ?”
ደላላው፡- “በጣም ብዙ አለ፤ የሱ አይነት”
ባልየው፡- “እሺ ታዲያ መቼ ነው የምታሳየን?”
ደላላው፡- “ዛሬም ይቻላል፤ ነገም ከነገ ወዲያም ካልሆነም በሚቀጥለው ሳምንት፤ አንዱን ቀን”
ሚስት፡-”በቃ ነገ እንየዋ”
ደላላው፡- “ቆይ አንጣደፍ፤ እኔ ሲለቀቅ ልደውልላችሁ”
ሚስት፡- (በንዴት) “እንዴ! ያልተለቀቀ ቤት ነው እንዴ ሞልቷል በሽ ነው የምትለን የነበረው፤ ቀጣፊ!”
ደላላው፡- “እሱማ የስራችን ጸባይ ነው እኮ እመቤቴ”
ሚስት፡- (እንደገናበንዴት) “ምን  የስራችሁ ፀባይ፤ የራሳችሁ ጸባይ ነው እንጂ አስቸጋሪው”
ደላላው፡- “ለማንኛውም አይቶ መፍረድ ነው፤ ግቢውን ስታዩት ትወዱኛላችሁ፤ ነገ እናየዋለን”  በዚሁ ተሰነባበቱ።
በነገታው ወደ ግቢውና ወደ ቤቱ ተያይዘው ሄዱ። ሲታይ ቤቱ ኮርኒሱ የተቦዳደሰ፣ አጥሩ የአረብ ጥርስ ይመስል የወላለቀ ሆኖ ተገኘ።
“ባልየው ምነው የኔ ወንድም፤ ያ ሁሉ ስለ ግቢና ስለ ቤቱ ውበት መቀባጠር ለምን አስፈለገ፤ እኔንስ ባለቤቴንስ ለምን አንገላታኸን? ላንተ ያለውን´ኮ ብትዋሽም ባትዋሽም አታጣውም!?  ምንጊዜም እውነትን ተማመን። የውሸቱ መንገድ ጊዜያዊና የማያደርስህ ነው” ብሎ መክሮ አሰናበተው።
*   *   *
መንገዶች ሁሉ ለመጀመሪያ ጊዜ ብትሄዱ ብትሄዱ ሩቅ ይመስላሉ፤ ከአንድ ጊዜ በላይ ከባድ አይሆኑም። አዲስ ነገር ግራ የሚያጋባን ለዚህ ነው። ምናልባትም ለውጥን የማንረዳውም የምንፈራውም ለዚህ ነው። በዚህ ላይ እድሜና ልማት ካልበሰሉ ጣጣና አባዜያቸው አስጊ ነው። አይጣልም የሚባል ነው።
መንገዳችን ሁሉ አለቀ በስለት
ምን ይበላ ይሆን የተገናኘን ለት
አክርማ እንኳን የለኝ ሰፍቼ አልጨርሰው
እንዴት በያገሩ ጅምር ይተዋል ሰው
ያለውን ድምጻዊ ውብሸትን አለመርሳት ነው። የመጀመሪያው ሰሙ ኢኮኖሚያዊ መንገዳችንን ማቃናት ምን ያህል እንዳልቀናን የሚጠቁም ነው።
ሁለተኛው ስንኝ በየአጋጣሚው እየጀመርን ያልጨረስናቸው ጉዳዮች አያሌ መሆናቸውን የሚጠቁመን ነው። ምን ያልጀመርናቸው ጉዳዮች ነበሩ? ዛሬ ያለነው የለውጥ ኩርባ ላይ ነው። ያላሰብነው፣ ገቢር ወነቢር አልነበረም። ያላቋረጥነው ድልድይ፤ ያልሰበርነውም ድልድይ አልነበረም።
አስረጂ...
ዲሞክራሲ ...
ፍትህ...
እኩልነት...
ጥምር መንግስት...
የተራማጆች ህብረትና ውህደት...
እንደ መግባቢያና የውይይት መድረክ (ፎረም)...
የህዝብ ድርጅት ጊዜያዊ ጽ/ቤት...
የጤናና ትምህርት ቢሮዎች...
የአርበኞች ማህበር...
የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ማህበር...
የኢትዮጵያ ስካውት ማህበር...
የኢትዮጵያ ሴቶች ትግል ድርጅት...
የኢትዮጵያ አብዮታዊ ወጣቶች ድርጅት...
ወክማና ወህክማ...
 እነዚህ ሁሉ የኢትዮጵያን ወጣቶች የቀረጹ ናቸው ቢባል የዋህነት አይሆንም፤ የኢትዮጵያ ኮሌጆች ቅድሚያ ውድድርን አንዘነጋም።
የቀድሞ ቀኃስ የአሁኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ፤ አያሌ ወጣት ምሁራንን ያፈራ፣ የአፍሪካ የተከበረና ለአፍሪካ ሀገሮች ስኮላርሽፕ እስከ መስጠት የደረሰ አንጋፋ ዩንቨርሲቲ የነበረ ነው። ምንም እንኳን ዛሬ ከሐምሌት ጋር፡-
“ያለፈ ጥረታችንን ሳስታምመው ትዝ ሲለኝ
ከሞከርነው ነገር ይልቅ ያልሞከርነው ነው የሚቆጨኝ”
ብንልም ከመሞከር ወደ ኋላ አንልም። ከሁሉም ወሳኙና አንገብጋቢው የእውነትን ፍለጋ ጥረታችንን አለማቋረጣችን ነው። አለበለዚያ ለትውልድ የምንሰጠው ትረካ አይኖረንም። ልጆቻችን የሚረከቡንን ይወቁ! እኛም አውቀን እናሳውቃቸው። ቢደክመንም ቢደክማቸውም እንተጋገዝ። ምክንያቱም እውነቱን ሲያውቁ በየነፍሳቸው የራሳቸውን እድል ይወስናሉና።
ዛሬም በልጆቻችን ላይ እንስራ!

Read 11416 times