Print this page
Saturday, 24 April 2021 13:12

ነፃነትና የእናት አርበኞች ሚና

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(0 votes)

 ለታሪክ ያለኝ ፍቅርና መቆርቆር ከዛሬ  አርባ ስምንት ዓመት በፊት ጀምሮ የነበረ ቢሆን ኖሮ፤ አባቴ ቀኛዝማች አስረስ ጀምበሬ “ቢቡኝ” ላይ አገሩን ከድቶ ከጦር ሜዳ  ከተመለሰው ከደጃዝማች ገሠሠ በለው ጋር ስለ አደረጉት ጦርነት፤ ከደጃዝማች በላይ ዘለቀና ከደጃዝማች ነጋሽ በዛብህ ጋር ስለነበራቸው ግንኙነት፣ ምን ስለ ሠሩ ሁለቱም ቀሚስ እንደሸለሟቸው፤ አቶ አስረስ የሚባሉ ጓደኛቸው ደብረ ማርቆስ ቅዳሜ ገበያ ላይ ተፀዳድተው፣ ኩሳቸውን ተቀብተው ጣሊያን ካምፕ ገብተው ስለፈፀሙት ጀብዱ  ዘርዝረው እንዲነግሩኝ ባደረግሁ ነበር፡፡
ከንቱ ድካም የሆነ ነገር ባጋጠማቸው ቁጥር “ተነግዷል አለ ኤባ” የሚለውን ንግግራቸውን ሳስታውስ አቶ ኤባ (የቀኛዝማች ከድር ኤባ አባት) የውስጥ አርበኛ ነበሩ? ብዬ እንድጠይቅ ይገፋፋኛል፡፡ ሁሉም ፀፀት ትርፉ ነው፡፡
ይህን ጉዳይ ያነሳሁት የግሌን ማሳሰቢያ ለማቅረብ ነው፡፡ እኔ እስከማውቀው ድረስ አርበኞች አባቶቻችንና እናቶቻችን አምስት ዓመት ሙሉ ነፃነታቸውን  አስጠብቀው ለመቆየት ያደረጉት ትግል፣ በታሪክ ተመዝግቦ የሚገኘው በጎንደር፣በሸዋና፣ በከፊል ጎጃም የተካሄደው ነው፡፡ ለዚህ! “ቀሪን ገረመው የአርበኞች ታሪክ” እና “ጎንደሬ በጋሻው” የተባሉ መፅሐፎችን የፃፉት ቀኛዝማች ታደሰ ዘወልዴንና  ገሪማ ታፈረን ማመስገን ይኖርብናል፡፡
በኢትዮጵያ አርበኞች ያልተነሱበትና ጦርነት ያልተካሄደበት አካባቢ ባይኖርም፣ በታሪክ የተመዘገበው ግን  ጥቂቱ ነው፡፡ በጅማ፣ በአርሲ፣ በሲዳሞ፣ በወለጋ፣በወሎና በሌሎችም አካባቢዎች የተደረገውን ትግል ለትውልድ ማሻገር የሚቻለው ዛሬ በሕይወት ያሉ አርበኞችን፣ የአርበኛ  ልጆችንና ቤተሰቦችን በመጠየቅና ታሪኩን በመመዝገብ ነው፡፡ ለዚያም ቢሆን ያለው ጊዜ ከሁለትና ከሶስት ዓመት የበለጠ አይደለም፤ መፍጠን ይጠይቃል፡፡ ሰዎች በሞት ሊለዩን ይችላሉ፡፡ እንደ እኔ  ላለመቆጨት ሁሉም በአጠገቡ ያሉ አርበኞችን የአርበኛ ልጆችን እየጠየቀ ታሪኩን ቢመዘግብ፣ በመጀመሪያ ሊጠፋ የተቃረበን ታሪክ  በማስቀረት የተጓደለው የታሪክ ምዝገባችን እንዲሟላ ያደርጋል፡፡ ለአገራችን ነፃነት እንዳልደከምን ተረስተን ቀረን ለሚለው ወገንም ታሪኩን በመመዝገብ ባለውለታ መሆን ይቻላል፡፡ ወደተነሳሁበት ልመለስ፡፡
በስም ካልተገለፁት ሶስቱ ሴቶች ታሪክ ልጀምር፡፡ አንደኛዋ ሃዲስ አለማየሁ “ትዝታ” በተባለው  መፅሐፋቸው ታሪኳን የነገሩን ሴት ናት፡፡ ይህች ሴት ከራስ እምሩ ጦር ጋር ተጉዛ ይዘዋት የዘመቱትን ጌታዋን ስታገለግል የቆየች ናት፡፡ እንደ ሌሎቹ ሴቶች ሁሉ ለጦሩ ስንቅ ስታቀብል፣ ቁስለኛ ስታነሳ እንደቆየች ይታመናል፡፡ የራስ እምሩ ጦር ወደ ሀገሩ እየተመለሰ እያለ ጣሊያኖች በቦንብ ይደበድቡታል፡፡ ጦር ሜዳ ላይ የወደቁት ጌታዋ ጠመንጃቸውን ለልጃቸው እንድትሰጥ አደራ ብለዋት ስለነበር  የሣቸውን በቅሎ እየጎተተች ሳለ በቦንብ ተደብድባ ሕይወቷ አለፈ፡፡
ሁለት የትግራይ ሴቶችን ጣሊያኖች ወስደው ይዘዋቸው ያድራሉ፡፡ መደፈራቸው ያንገበገባቸው ሴቶች፣  ሁለቱንም ገድለው መሳሪያቸውን ገፈው ከወገን ጦር ጋር ተቀላቀሉ፡፡ ይህ ዝናቸው በመላው ትግራይ ከመናኘቱም በላይ ለንጉስ ነገስቱ ለአፄ ኃይለ ስላሴ ዜናው ተነግሯቸዋል፡፡ እንደነሱ መሆን የወቅቱ ቀስቃሽ ቋንቋ ነበር፡፡
ንጉሰ ነገስቱ አፄ ኃይለ ስላሴ ህዳር 8 ቀን 1933 ዓ.ም ለአዛዥ ከበደ ተሰማ በጻፉት ደብዳቤ ላይ የወ/ሮ ላቀች ደምሰውን ስም ጠቅሰዋል፡፡ ላቀች ደምሰው ከእነ ደጃዝማች መንገሻ አቦይ እኩል ደብዳቤ የተጻፈላቸው ሰው ናቸው፡፡ ለደጃዝማች አቦይ የተጻፈው ዳብዳቤ ባሉበት በወሎ አካባቢ አርበኛውን የሚያስተባብር ስራ እንዲጀምሩ የሚያዝ ስለሆነ ለወ/ሮ ላቀችም የተላከው ትእዛዝ ተመሳሳይ እንደሚሆን ይገመታል፡፡ የማይታወቅና ጥናት የሚጠይቀው የወ/ሮ ላቀች ደምሰው የት አካባቢ ሰው መሆንና በአርበኝነት ዘመናቸው ምን ምን ስራ እንደሰሩ ነው፡፡ የምታውቋቸው ታሪካቸውን ብትነግሩን መልካም ይሆናል፡፡
የአርበኝነት ተጋድሎአቸውን ዝርዝር ያላገኘሁላቸው ሌላዋ ወ/ሮ ከበደች ስዩም ናቸው፡፡ ከበደች የራስ ስዩም መንገሻ ልጅ ሲሆኑ ባለቤታቸው ደጃዝማች  አስፋው ወሰን ካሳ ነበሩ፡፡  የሰላሌ ህዝብ  የአርበኝነት ትግሉ መሪ አድርጎ የመረጣቸው የራስ ካሳ ልጆች፣ ደጃዝማች አስፋው ወሰን ካሳንና አበራ ካሳን መሆኑን ይታወሳል። ጣሊያኖች አምስት መቶ የሚሆኑ የራስ ካሳን አሽከሮችና ባለሟሎች ይዘው፣ ሁለቱ ወንድማማቾች አበራ ካሳና አስፋው ወሰን ካሳ እጃቸውን ካልሰጡ ድረስ የያዟቸውን ሰዎች እንደሚረሽኗቸው ተናገሩ፡፡ ባለቤታቸው ወ/ሮ ከበደች፣ ራስ መስፍን ስለሺና ሌሎች አርበኞች እጃቸውን እንዳይሰጡ መከሯቸው፡፡ ዘመዶቻቸው የተያዙባቸው ሰዎች በበኩላቸው ደግሞ እጃቸውን ሰጥተው የተያዙ ዘመዶቻቸውን ሕይወት እንዲያተርፉ ታገሉ፡፡ ደጃዝማች አበራና ደጃዝማች አስፋው ወሰን እጃቸውን እንደሰጡ ተገደሉ፡፡ ወ/ሮ ከበደች ከራስ አበበ አረጋይ  ጦር  ጋር በመቀላቀል የአምስት ዓመት አርበኝነታቸውን ቀጠሉ፡፡ “የታሪክ ቅርስና ውርስ ራስ አበበ አረጋይ” የተባለው መጽሐፍ ፀሐፊ አጥናፍ ሰገድ ይልማ፤ ወ/ሮ ከበደች  ከራስ አበበ አረጋይ ዋና ዋና የጦር መሪዎች አንዷ እንደነበሩ ፅፈዋል፡፡
ወ/ሮ ፈትለ ወርቅ ሀይሌ፣ የአርበኛው ሀይሌ ሸንቁጥ ልጅ ናቸው፡፡ የተወለዱት በ1915 ዓ.ም መራቤቴ አውራጃ ኮራ በተባለ ቀበሌ ነው፡፡ በልጅ አርበኛ ጀምረው እስከ 1933  ነፃነት እስከተገኘበት ዓመት ድረስ በአርበኝነት ዘልቀዋል፡፡ ጥቅምት 27 ቀን 1931 ዓ.ም ጀግናው ሀይሌ ሸንቁጥ በውጊያ ላይ በወደቁበት ጊዜ ሬሳቸው እንዳይማረክ አድርገዋል፡፡ ጣሊያኖች አመፀኛ ዋሻን በመርዝ ጋዝ ባጠቁ ጊዜ  በህይወት ከተረፉ ጥቂት ሰዎች አንዷ ወ/ሮ ፈትለ ወርቅ ሲሆኑ ተይዘው ደብረ ሲና ላይ በእስር ቆይተዋል። ከእስራት መፈታት የቻሉት በራስ አበበ አረጋይና በጣሊያኖች መካከል የእርቅ ድርድር በተጀመረ ጊዜ ራስ አበበ የተያዙ ሰዎቼን ይፈቱልኝ በማለት ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት መሆኑ ይጠቀሳል፡፡
አያታቸው ሽብሩ ጤናው የጦር መሳሪያ ተረክበው ማለትም የመሳሪያ  ግምጃ  ቤት ሹም ሆነው ከሸዋ እስከ ተንቤን ዘምተዋል። በማይጨው ጦርነትም ተሳትፈዋል፡፡ የወ/ሮ ልኬለሽ በያን አባት፣ በያን ኢብሳ ሲሆኑ እናታቸው ወ/ሮ ይጎዝጎዙ ሽብሩ ይባላሉ፡፡ ልኬለሽ የተወለዱት በ1902 ዓ.ም በከንባታ አውራጃ ሆሳዕና ከተማ ነው፡፡ ወደ ጦር ሜዳ የዘመቱት ከከምባታው ጦር አዛዥ ከደጃዝማች መሸሻ ወልዴ ጦር ጋር ነው። የራስ ከበደ መንገሻና የደጃዝማች በየነ አባ ሰብስብ ጦር ወደፊት ሲጓዝ እሳቸው ያሉበት ጦር አምባላጌን እንዲጠብቅ ተደረገ። በደጃዝማች ሀይሉ ከበደ የሚመራው የሰቆጣና የላስታ ጦር ያደረገውን ተጋድሎ ልኬለሽ የሚገልፁት “ተንቤን ጫካውም ሜዳውም የእግር መርገጫ አልነበረውም፤ ሬሳ ብቻ ነበር; በማለት ነው፡፡
የአራት ወር ተኩል ሕፃን ልጃቸውን ትተው የዘመቱት ወ/ሮ ልኬለሽ በመስከረም ወር 1930 ዓ.ም ቀኝ አዝማች ቁምቤ የተባለውን ባንዳ ገድለው በማሰር ጠመንጃውን ገፈዋል፡፡ በዚሁ ዓመት ከባለቤታቸው ከአቶ በቀለ ካሳ ጋር በመሆን አንድ የፋሺስት ጦር መኮንን በሩምታ ተኩስ በመግደልና መትረየስ በመማረክ ለራስ አበበ አረጋይ አስረክበዋል፡፡ መስከረም 1931 ዓ.ም ሮቤ ወንዝ አጠገብ ሲዋጉ ባለቤታቸው ውጊያው ላይ በመገደላቸው፣የባለቤታቸውን አንገት ቆርጠው ለመውሰድ የመጡትን ባንዳዎች፣ ከባለቤታቸው ወገብ የነበረውን ቦንብ በመወርወር፣ አራቱንም በመግደል ሬሳው እንዳይማረክና በአግባቡ እንዲቀበሩ አድርገዋል፡፡ ባለቤታቸው ይመሩት የነበረውን አንድ ሻምበል መትረየስ ተኳሽ ጦር  መሪነት በመረከብም በሚገባ አዋግተዋል፡፡
አንድ ጊዜ ሰራዊቱ ከፍተኛ ውጊያ ላይ ተጠምዶ  እያፈገፈገና እየተዋጋ ባለበት ሰዓት ከጦሩ ጋር ሲጓዝ የነበረ ሰንደቅ ዓላማ ተረስቶ ሳይነሳ በመቅረቱ፣ ልኬለሽ  “ባንዲራዬን ትቼማ አልሄድም; በማለት ጫካ ውስጥ ገብተው ሲታኮሱ ሰንብተው፣ ሰንደቅ ዓላማቸውን ይዘው ወደ ጦሩ ተመልሰዋል፡፡
ወ/ሮ ልኬለሽ ውጊያ በማይኖርበት ጊዜ ትጥቃቻውን አስቀምጠው፣ ጥጥ ፈትለው፣ ሸማ አሰርተው ለሰራዊታቸው ያለብሱ የነበሩ መሆናቸውን አዲስ ዘመን ጋዜጣ ጽፎላቸዋል፡፡
ነገሬን የማጠቃልለው በወ/ሮ እጅጋየሁ ያለው ታሪክ ነው፡፡ ወደ ውጊያ የገቡት ከራስ ደስታ ጦር ጋር በመቀላቀል ነው። ወ/ሮ እጅጋየሁ ከባለቤታቸው ከአቶ አስፋው ፈለቃ ጋር በአላባ፣በከንባታ፣ በኩሎ በዋደራ፣በአገረ ማርያም፣በጭላሎና ሌሎችም አካባቢዎች በተደረጉ ውጊያዎች በመሰለፍ ተዋግተዋል፡፡ የራስ ደስታ ጦር በደረሰበት ጥቃት  እየተዳከመ ሲመጣ፣ ጦሩ ወደ ኬኒያ ገብቶ ተመልሶ በመውጣት የደፈጣ ውጊያ እንዲጀምር በተወሰነ ጊዜ ወደ ኬኒያ ገብተዋል፡፡ እንግሊዞች ጦሩ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ  የደፈጣ ውጊያ እንዲጀምር ባለመፍቀዳቸው ባልና ሚስቱ ለ3 ዓመት “ትቤት” በተባለ ቦታ በስደተኝነት እንዲቀመጡ ሆኗል፡፡ የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ተጀምሮ እንግሊዝ የኢትዮጵያ የጦር ጓደኛ በሆነችበት ጊዜ ወደ አገራቸው ከተመለሱ በኋላ ወ/ሮ እጅጋየሁና ባለቤታቸው በሲዳማ አካባቢ የነበረውን የጠላት ጦር በመውጋት መሳተፋቸውን ማውሳት ተገቢ ይሆናል፡፡
አርበኞቻችን እነዚህ ብቻ አይደሉም፡፡  እነ ወ/ሮ ሸዋ ረገድ ገድሌን፣እነ ወ/ሮ ቀለም ወርቅ ጥሩነህን፣እነ ወ/ሮ ሙሉነሽ በፍርዴን ሳንጠቅስ  ማለፍ አንችልም፡፡
እጅግ ከፍ ያለ አክብሮት ለእናት አርበኞቻችን ይሁን!
 ክብር ሁሉ ለሚያዚያ 27 የድል ቀን!  

Read 2071 times