Saturday, 24 April 2021 13:30

በ350 ሚ ዶላር ድሬደዋ ውስጥ የሲሚንቶና የብረት ፋብሪካ ሊገነባ ነው

Written by  ናፍቆት ዩሴፍ
Rate this item
(0 votes)

    አፋርና ሱማሌን የወረረው መጤ አረም የድንጋይ ከሰልን ሊተካ ነው
                     
            በኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ የቢዝነስ ስራ ታሪክ ባለው ኢስት አፍሪካ ሆልዲንግ እና በቻይናው ዌስት ኢንተርናሽና ሆልዲንግ ኩባንያ በ350 ሚ. ዶላር በድሬደዋ ግዙፍ የሲሚንቶና የብረታ ብረት ፋብሪካ ሊገነባ ነው።
ባለፈው እሁድ ሚያዚያ 10 ቀን 2013 ዓ.ም በድሬድዋ ኢንዱስትሪ ፓርክ አቅራቢያ የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠለት ይሄው ግዙፍ ፋብሪካ፤ በ103 ሄክታር መሬት ላይ የሚያርፍ ሲሆን በቀን 5 ሺህ ቶን  ሲሚንቶና በዓመት 300 ሺህ ቶን ብረታ ብረት የማምረት አቅም እንዳለውም ተገልጿል።
የካቲት 25 ቀን 2013 ዓ.ም በሰሜን ሸዋ እንሳሮ ወረዳ፣ ለሚ ከተማ  በ2.2 ቢ.ዶላር ሊገነባ በክብርት የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት ወ/ሮ ሳህለወርቅ ዘውዴ የመሰረት ድንጋይ የተጣለለት የለሚ ሲሚንቶ ኢንዱስትሪያል ኮምፕሌክስ መንትያ የሆነው ይሄው ድሬደዋ ሲሚንቶና ብረታ-ብረት ፋብሪካ የሚያመርታቸው ምርቶች ለውጭ ገበያ እንደሚቀርቡና የውጭ ምንዛሬን ለሀገር እንደሚያመጡ የተገለፀ ሲሆን የለሚው ፋብሪካ ምርቶች ለሀገር ውስጥ ገበያ ያቀርባሉ ተብሏል። የኢስት አፍሪካ ሆልዲንግ ማዕድንና ኢነርጂ ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስኪጅ አቶ ገዛኸኝ ሀምዛ በስነ-ስርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ ኢትዮጵያ ለሀይል አቅርቦት ግብአትነት የሚውለውን የድንጋይ ከሰል ከውጪ ለማስገባት በዓመት 200 ሚ. ዶላር እንደምታወጣና ወደ አየር ከሚለቀቀው የካርቦን ልቀት 60 በመቶው ከዚሁ ከድንጋይ ከሰል እንደሚወጣ አስታውሰው፤ ኢስት አፍሪካ ሆልዲንግ ይህንን ግምት ውስጥ ያስገባና 6 ዓመታትን የፈጀ ጥናትና ምርምር ማድረጉን ገልፀው ነበር።
ጥናትና ምርምሩ ዋና ትኩረቱን ያደረገው የአፋርና የሶማሌን 2.2 ሚ ሄክታር መሬት ወርሮ በመያዝ የአረርብቶ አደሩንና የከፊል አርብቶ አደሩን የግጦሽና የእርሻ መሬት አጥፍቶ ቀውስ እያስከተለ ያለውን “ፎሮስፒስ ጆሪፍሎራ” የተሰኘ መጤ አረም፣ የድንጋይ ከሰልን በመተካት የሃይል አማራጭ በሚሆንበት መንገድ ላይ እንደሆነም አቶ ገዛኸኝ ተናግረዋል።
ይህንኑ መጤ አረም  በሀይል አማራጭነት ለመጠቀም የሚቻልበት ሁኔታ ላይ ውጤታማ ስራ ለመስራት ኢስት አፍሪካ ሆልዲንግ ባለሙያዎቹን ወደ ኩባ ፣ ናሚቢያ፣ ኦስትሪያና ሌሎች አገራት በመላክ ሲያስጠና መቆየቱን አስታውቀው  ድሬድዋ በሚገኘው የቀድሞው ናሽናል ሲሚንቶ ፋብሪካ ውስጥ የሙከራ ስራ ለመስራት አረሙን የማጨጃና የመፍጫ ማሽነሪ ከውጪ ለማስገባት 170 ሚ. ብር መመደቡንም አቶ ገዛኸኝ ጨምረው ገልጸዋል።
ግንባታው “ሲኖማ” በተሰኘና ከ500 በላይ የሲሚንቶ ፋብሪካዎችን በተለያዩ ዓለማት በመገንባት በሚታወቀው ኩባንያ እንደሚከናወንና በታቀደለት ጊዜ እንደሚጠናቀቅ የተነገረለት ፋብሪካው ስራ ሲጀምር ለ2 ሺህ ቀጥተኛና ለ10 ሺህ ቀጥተኛ ያልሆኑ ዜጎች የስራ እድል ይፈጥራል ተብሏል።
በመሰረት ድንጋይ የማስቀመጥ ስነ-ስርዓቱ ላይ የፌዴሬሽን ምክር ቤት  አፈ-ጉባኤ አቶ አደም ፋራህ፣ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል፣ የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሙስጠፌ መሃመድ፣ የኦሮሚያ ክልል ም/ፕሬዚዳንት አቶ አዲሱ አረጋ፣ የኢስት አፍሪካ ሆልዲንግ የአማካሪ ቦርድ አባል አምባሳደር ማህሙድ ድሪር፣ የድሬድዋ ከተማ ም/ከንቲባ አቶ አህመድ መሃመድ ቡህ፣ የፑንትላንድ፣ የጅቡቲ፣ ሶማሌላንድና የዋናው ሶማሊያ ተወካዮች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች ተገኝተዋል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ አደም ፋራህ ባደረጉት ንግግር፤ የኢስት አፍሪካ ሆልዲንግ ኩባንያ ባለቤትና ዋና ስራ አስፈጻሚ ብዙአየሁ እንዳለን (ዶ/ር) ለረጅም ጊዜ እንደሚያውቋቸው ገልጸው፤ በሀገር ግንባታ በስራ እድል ፈጠራ፣ ማህበራዊ ሃላፊትን በመወጣትና በሁለንተናዊ የሀገር ኢኮኖሚ እድገት እያደረጉ ስላሉት አበርክቶ አመስግነዋቸዋል። ይህ አዲስ ፋብሪካ ሲገነባም ለአየር ንብረትና ለማህበረሰቡ እንዲስማማ ተደርጎ እንዲሰራ አደራ  ብለዋል። የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል በበኩላቸው በለሚ ከተማም ሆነ በድሬደዋ በኢስት አፍሪካ ሆልዲንግ ኩባንያ እየተገነቡ ያሉት የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ከሰሀራ በታች ካሉ ሀገራት በጣም ያነሰ መጠን ያለውን የኢትዮጵያ የነፍስ ወከፍ የሲሚንቶ ፍላጎት በማሳደግ በኩል ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖራቸው ገልፀው፣ እኛም ከ60 ዓመት በላይ ያገለገለውን ህግ ከመቀየር ጀምሮ ለኢንቨስተሮች ምቹ ሁኔታዎችን እየፈጠርን በመሆኑ አስፋጊውን እገዛ እናደርጋለን ሲሉ ቃል ገብተዋል።
የድሬደዋ ከተማ ም/ከንቲባ አክለውም አቶ አህመድ መሃመድ ቡህ ባደረጉት ንግግር፤ ኢስት አፍሪካ ሆልዲንግ ከረጅም ዓመታት በፊት ናሽናል ሲሚንቶ ፋብሪካን በድሬደዋ በመገንባት በኢትዮጵያ የግንባታ ስራ ላይ ያሳረፈውን አሻራና ለ1 ሺህ 500 ሰዎች ከፈጠረው የስራ እድል በተጨማሪ ከተማ አስተዳደሩ በሚያደርጋቸው በርካታ የልማት ጥሪዎች ምላሽ በመስጠት የሚቀድመው እንደሌለም ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።
ም/ከንቲባው ለማህበረሰቡ መብራት በማስገባት፣ የውሃ ጉድጓድ በመቆፈር፣ በኮቪድ ጊዜ ተዘግተው የነበሩ ት/ቤቶች ማሟላት ያለባቸውን አሟልተው ወደ መማር ማስተማሩ እንዲገቡ በማገዝ፣ በኮቪድ ምክንያት ለከፍተኛ ችግር ለተጋለጡ ከ700 በላይ ቤተሰቦች ድጋፍ በማድረግ ለድሬደዋ ስታዲም ግንባታና ለበርካታ ማህበራዊ ጥሪዎች የለገሱትን ገንዘብና የሰጡትን ምላሽ አድንቀው፣ ቀደምት በሆኑት ድሬደዋ ጨርቃ ጨርቅ፣ ድሬደዋ የምግብ ፋብሪካ ፣ የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር መስመር  ማዕከልነትና በሌሎችም ፋብሪካዎቿ በምትታወቀው የበርሃዋ ገነትና የፍቅር ከተማ ድሬደዋ ዳግም ይህን ፋሪካ ለመገንባ  በመፍቀዳቸው ዶ/ር ብዙአየሁ እንዳለን አመስግነዋል። ከተማ አስተዳደሩ የትኛውንም ዓይነት ትብብር ለማድረግ እንደሚተጋም ቃል ገብተዋል።
ድሬደዋ የሲሚንቶና የብረታ ብረት ፋብሪካ ተገንብቶ ወደ ስራ ሲገባ በአካባቢ ጥበቃ፣ በአካባቢ ላሉ ማህበረሰቦች መሰረተ ልማት በመገንባትና በበርካታ ስራዎች ማህበራዊ ሃላፊነቱን ይወጣል ተብሏል።
የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሙስጠፌ መሃመድ በበኩላቸው፤  የኩባንያው ባለቤት ብዙአየሁ እንዳለ (ዶ/ር)፤ ለሀገር ልማት እየሰሩ ያሉትን ስራ አድንቀው፣ አሁን ላይ ኢትዮጵያ የሚያስፈልጓት እንደነ ዶ/ር ብዙአየሁ እንዳለ አይነት ለልማት የሚተጉ ዜጎች ናቸው ሲሉም ተናግረዋል።
የኩባንያው ዋና ስራ አስፈጻሚ ብዙአየሁ እንዳለ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ “ንፁህ ያልሆነ ገንዘብ ወደ ቤት ይዘህ አትምጣ ያጠፋሃል” የሚለውን የአባታቸውን ምክር ተግባር ላይ በማዋል ሲሰሩ መኖራቸውንና ለልጆቻቸውም ይህን መርህ እያስተማሩ እዚህ  መድረሳቸውን ገልፀው አሁን ላሉበት እንዲበቁ የረዷቸውን በሙሉ በተለይም ከበፊት ጀምሮ እንደ ልጁ የተቀበላቸውን የድሬደዋን ህዝብ አመስግነው የፋብሪካው በድሬደዋ መገንባት ለህዝቡ ሲያንሰው ነው ብለዋል።

Read 1606 times