Print this page
Tuesday, 27 April 2021 00:00

መከራና ፈተና ያልበገረው ስደተኛ ሼፍ

Written by  ናፍቆት ዩሴፍ
Rate this item
(0 votes)

 ተወልዶ ያደገው እዚሁ አዲስ አበባ የካ ሚካኤል አካባቢ ነው፡፡ በሰው ልጅ አቅም ሊታለፍ ቀርቶ ሊታሰብ የሚከብድ ብዙ መከራዎችን በትግል አሸንፏል፡፡ ምግብ ሳይበላ ለቀናት ውሎ አድሯል፣ ጎኑን ማሳረፊያ መኝታ አጥቶ ብዙ ተንከራትቷል፤ ልብስና ጫማ ለእሱ ቅንጦት ነበሩ፡፡ ከጉልበት ሰራተኛነት እስከ ሰው ቤት ሰራተኛነት ያልሰራው ሥራ የለም። በስደት ጀርመን ገብቶ ብዙ ውጣ ውረዶችን አሳልፏል፡፡ በአጠቃላይ ከህይወት ጋር ግብግብ ገጥሞ ነው የኖረው ግን የቱንም ያህል መከራና ፈተና አልበገረውም።
ከልጅነት እስከ ዕውቀት የተጋፈጠውን መከራና ፈተና ለስኬት ያበቃውን ምስጢር የሚያስቃኝ “ስደተኛው ሼፍ” የተሰኘ መፅሐፍም ለንባብ አብቅቷል። ሼፍ አንተነህ ድፋባቸው፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ ከሼፍ አንተነህ ጋር ቀጣዩን አስደማሚ ቃለ ምልልስ አድርጋለች፡፡ እነሆ፡-

       • “እኔ ያጣሁት የሚበላና የሚለበስ ብቻ ሳይሆን ፍቅርም ነው”
       • መከራውንና ውጣ ውረዱን ያለፍኩበት መሳሪያ ትዕግስት ነው
       • አሁን ብቸገር የማላውቀው ዓለም ውስጥ አይደለም የምገባው


                 ከጀርመን ወደ ሀገር ቤት፣ከአገር ቤት ወደ ጀርመን መለስ ቀለስ እያልክ ነው፡፡ ለስራ ነው ለእረፍት?
ለሁለቱም ማለት ይቻላል፡፡ አንዳንዴ አገሬ ላይ ለመስራት የምፈልጋቸውን ስራዎች ለማጥናትም እግረ መንገዴንም ለማረፍ ነው ወጣ ገባ የምለው፡፡
ከልጅነትህ ጀምሮ በርካታ ተስፋ አስቆራጭ የሆኑና የሚያልፉ የማይመስሉ ፈተናዎችን ተጋፍጠሀል፡፡ በዚህ ሁሉ መከራ ውስጥ ተስፋ እንዳትቆርጥ ያገዘህ ምንድን ነው?
እውነት ለመናገር እኔ ያሳለፍኩት ችግር ሲወራና ሲፃፍ ቀላል ይመስላል እንጂ ስኖረው በእጅጉ ከባድና አሰቃቂ ነበር። እንዳልሽው የሚያልፉ የማይመስሉ መከራዎች ነበሩ፡፡ ነገር ግን ያንን ጨለማ ያሸነፍኩበት ምክንያት እግዚአብሔር ያንን የሚሸከም ትከሻና የምታገስበት ፀጋ ሰጥቶኝ ነው ብዬ አምናለሁ። ችግሮቹም ያለፉት በእግዚአብሔር ነው፡፡ ያ ሁሉ እንዲያልፍ፣ የኔ ሕይወት ሰው እንዲያስተምር ያደረገውም ለበጎ ነው፡፡ ባያልፍ ኖሮ ዛሬ አያስተምርም ነበር፡፡ ስለዚህ ፀጋም አለ፡፡ በሌላ በኩል እኔ ሁሌ የማየው ነገን ነበር፡፡ ግልምጫውም፣ ንቀቱም፣ ረሀቡም፣ እርዛቱም ሆነ ሌሎች ችግሮች በህይወቴ ሲያልፉ ጥለውት የሚያልፉት ነገር አለ፡፡ አንዳንዱን ጠባሳ ጥሎ ሲያልፍ፣ አንዳንዱ ጠባሳ ሳይጥል እንዲሁ ተጋግጬ የማልፍበት ሁኔታ ነበር፡፡
ዋናው መከራውን ያለፍኩበት መሳሪያ ትዕግስት ነው፡፡ በጣም እታገስ ነበር፡፡ ስመታ እንዳልተመታ፣ ስናቅ እንዳልተናቅሁ እየቆጠርኩና ነገሮችን ለመርሳት እየሞከርኩ ነው ያሳለፍኩት፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰው የምጠጣው ውሃ ውስጥ መርዝ ሲጨምር ባየው ምንም እንዳልተፈጠረ አድርጌ የመርሳትና ወደፊት የመቀጠል አቅም ነበረኝ፡፡ እንዲህ አይነት ትዕግስት ነው ያንን ሁሉ ችግር እንዳልፍ ያደረገኝ፡፡
ከልጅነትህ ጀምሮ ምግብም፣ልብስም የቤተሰብ ፍቅርም ሳታገኝ ተጎድተህ ነው ያደግኸው፡፡ አሁን ከዚያ ፍፁም ተቃራኒ በሆነ የህይወት መስመር ውስጥ ነው የምትገኘው፡፡ ለአንተ ማጣትና ማግኘት እንዴት ይገለፃል?
እንግዲህ ማግኘትና ማጣት በዓለም ላይ ያሉ ነገሮች ናቸው፡፡ በነዚህ ሁለት ተቃራኒ መስመሮች ሰዎች ያልፋሉ፡፡ ነገር ግን አጥቶ ከማግኘት፣ አግኝቶ ማጣትን ለማንም አያድርስ ነው የምለው፡፡ አጥቶ ማግኘት ግን ጥሩ ነው፤ እርካታን ደስታን ይሰጣል፡፡ ያረጋጋልም፡፡ እኔ አሁን ላይ የተረጋጋ ህይወት ነው ያለኝ፡፡ ችግርን በደንብ ስለማውቀው አልፈራውም። ችግርን ከሀ እስከ ፐ ስለማውቀው አሁን ብቸገር፣ የማላውቀው ዓለም ውስጥ አይደለም የምገባው፡፡ አሁን አይ በለውና የሆነ ችግር ውስጥ ብገባ፣ እንደገና እንደምነሳ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ስለዚህ ማጣት አያስፈራኝም፤ አያስደነግጠኝምም፡፡ አሁን ላይ ስለማልፈራው እሱም ቶሎ ቶሎ አያገኘኝም፡፡ ይሄ ማለት አይቸግረኝም ማለት ሳይሆን የድሮውን ያህል አይደቁሰኝም፡፡ አይርበኝም፤ የምለብሰው አላጣም፤ ጫማም አልቸገርም፡፡ ያኔ የሚቀመስ ዳቦ እንኳን ይታጣል፡፡ ሌላው ቀርቶ ውሃ ተጠምቼ ወዲያው ውሃ የሚያጠጣኝ ላላገኝ እችል ነበር፤ ያ ሁሉ ታልፏል፡፡ አሁን እነዚያ ነገሮች ስጋት አይሆኑብኝም፡፡ አንዳንዴ እኮ አንድ ቤተሰብ በጣም ችግረኛ ቢሆንም፣ የእናት አባት  ፍቅር አግኝተው ተደጋግፈው ይኖራሉ፡፡ እኔ ያጣሁት የሚበላና የሚለበስ ብቻ ሳይሆን የቤተሰብ ፍቅርም ነበር፡፡  እኔ መወደድ መዳሰስ፣መታቀፍ በአጠቃላይ ለሰው ልጅ ከምግብ በላይ አስፈላጊ የሆኑት ነገሮችን  ነው የተነፈግሁት፡፡
እናትህ ከቤት ከማባረር ጀምሮ ብዙ ነገር እንዳደረጉህ ፅፈሀል። በተለይ አንድ ጊዜ የወንድምህ ቤተሰቦች ቤት ሰርግ ተደግሶ፣ ሁለታችሁም ሰርግ ቤት ከሄዳችሁ በኋላ በር ላይ እናትህና ወንድምህ ጥለውህ ገብተው፣ ከጎዳና ልጆች ጋር ተቀላቅለህ ምግብ የበላህበት አጋጣሚን አስታውሰሃል። እስካሁን እናትህን ተቀይመሃቸዋል ማለት ነው?
እናቴ ለኔ በጣም ታሳዝነኛለች፤ ምክንያቱም የራሷ ተፅዕኖ አለባት፡፡ ያንን ያደረገችበት ምክንያት ክፉ ስለሆነች አልነበረም፤ እሷን የገጠሟት ሰዎች ህይወቷ በምሬት እንዲሞላ ያደረጉ ስለነበሩ ነው። በልጅነቷ ብዙ ወንዶች አግብታለች፤ በጣም ቆንጆ፣ አስተዋይ ብትማር ትልቅ ቦታ ልትደርስ የምትችል ሴት ነበረች። ጥሩ  ወንዶች ስላልገጠሟት የተማረረ ህይወት ነው ያሳለፈችው። የዛ የተማረረ ህይወት ውጤት ነኝ እኔ፡፡ ስለዚህ እናቴ በህይወቷ ስትማረር፣ እኔን በመሳደብ በመርገምና በመደብደብ ነበር ምሬቷን የምታንፀባርቀው፡፡ ለምሳሌ የእኔ አባት ጥሏት ነው የሄደው፡፡ ያንን ንዴት በኔ ላይ ነው የምትወጣው፡፡ ምንም ባደርግላት፣ ምንም ብሰራላት አትደሰትም። እንደውም አንዳንዴ “አንተ የዛ አረመኔ ልጅ!” ትለኝ ነበር፡፡ ስለዚህ እንደዛ ያደረጋት በህይወቷ  የገጠሟት ሰዎች እንጂ እናቴ በተፈጥሮዋ ክፉ ሆና  አይደለም፡፡ የሰርግ ቤቱ ጉዳይ እንዳልሽው ለምን ከአዕምሮዬ አልጠፋም እንዳለኝ አላውቅም፡፡ በህይወቴ ከተከፋሁባቸውና ካዘንኩባቸው ቀናት አንዱ ነው፡፡
እየተማርክ የቀን ስራ ትሰራ ነበር፡፡ በሀያት የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ፣ የጉልበት ሥራ እየሰራህ ፈጣሪ እንጀራ እንዲያበላህ ስለጸለይክበት ቀን እስቲ ንገረኝ...?
በህይወቴ ከማስታውሳቸውና ከህሊናዬ ከማይጠፉ ነገሮች አንዱ ነው - ያ ቀን።  በህይወቴ መንፈሳዊ ህይወትና እምነት የያዝኩባት ቀን ሆና ተመዝግባለች። ያኔ እድሜዬም መንፈሳዊ ህይወቴም ያልጠነከረበት ወቅት ነበር። ረሃብ ውስጥ ነበርኩ። ላለፉት ሁለትና ሶስት ቀናት ምግብ አልበላሁም። ነገር ግን ከባድ ስራ ይጠብቀኛል። ብረት ነው የምሸከመው። የዛን ቀን ከሰዓት ብረት አወርድ ነበር። እናም በጣም እርቦኝ እንዳነበብሽው፣ ኪሴ ውስጥ 35 ሳንቲም ብቻ ነው የነበረችኝ። ያን ጊዜ ከሀያት መገናኛ የአውቶብስ መሳፈሪያ 25 ሳንቲም ነበር፡፡ እናም ለዛ ብዬ ነው ሳንቲሟን ያስቀመጥኳት። አርማታ ስሸከም ውዬ ምግብ ሳልበላ በእግሬ ከሀያት መገናኛ መምጣት አልችልም። ረሃቡ የአንድ ቀን ቢሆን ጥሩ ነበር። ግን አይደለም፡፡ በእግር ለመሄድ ዕድል የሚሰጥ አቅም አልነበረኝም። በዛ በምሳ ሰዓት ሁሉም የቋጠረውን ምሳ ዕቃ እየፈታ ለመብላት ይተራመሳል። ያኔ በሀያት የሚሰራው ወደ 10 ሺህ ገደማ የሚሆን ሰው ነው። እኔ ምንም የለኝም። ስለዚህ 35 ሳንቲሟን አውጥቼ ከገበሬዎች ላይ ቆሎ ገዝቼ እየቆረጠምኩ “አምላኬ እባክህ እንጀራ አብላኝ” ብዬ ጸለይኩኝ። ቆሎውን እየበላሁ በዚያ ቅጽበት አንድ የማላውቀው ሰው ከኋላዬ መጥቶ “ሰላም ነህ” አለኝ።
ሰውየው ምንድን ነው? ማለቴ አሰሪ ነው ወይስ?
ኧረ አሰሪ አይደለም። ሽርጥ የለበሰ እንደኔው በቀን 6 ብር እየተከፈለው የሚሰራ የቀን ሰራተኛ ነው። እኔም የ6 ብር ደሞዝተኛ ነኝ በቀን። ያኔ በቀን 6 ብር ነው የሚከፈለው - ሰራተኛ ቀይ ወጥ በ3 ብር መብላት አይችልም። ያኔ ቀይ ወጥ 3 ብር ነበር።
ከዚያስ ምን አለህ?
ይህ ሰው “ምሳ እንብላ” አለኝ፡፡ “አይ እኔ ልበላ ነው፤ አመሰግናለሁ” አልኩት። እኔ ልበላ ነው ያልኩት፣ ያንን በኪሴ የያዝኩትን ከገበሬዎች የገዛሁትን ቆሎ ነው፡፡ “ኧረ ግዴለም ና እንብላ” ብሎ ይዞኝ ሄደ። ቆርቆሮ ቤቶች ውስጥ ካቦዎች አሰሪዎችና ከ10 ብር በላይ ደሞዝ ያላቸው የሚበሉበት ነው። እኛ ሳጠራ ቤቶች ውስጥ ነበር የምንበላው - ቂጣ በሚጥሚጣና ሽልጦ።  እኔ ያኔ ያጣሁት ቂጣና ሽልጦ ነበር። ይህ ሰው ይዞኝ ሄደና ገባን። “አንድ ቀይ ወጥ” ብሎ አዘዘ። እኔ ለሁለት ልንበላ ነበር የመሰለኝ። ለኔ አዘዘና እሱ ወደ ጓዳ ገብቶ ከጓደኞቹ ጋ ማውራት ጀመረ። ለኔ ቀይ ወጥ መሃሉ ላይ ቅልጥም ያለው መጣልኝ፡፡  “ምሳው ቀርቧል ና  እንብላ” አልኩት። “ኧረ ፍሬንድ ላንቺ ነው ያዘዝኩት፤ እኔ ምሳ እቃ ይዤ መጥቼ ነበር በልቻለሁ” አለኝና እንድበላ ገፋፋኝ። በጣም ገረመኝ። እንጀራ ከበላሁ በጣም ቆይቼ ነበር፤ በተለይ ስጋማ  ካየሁትም በጣም ቆይቷል። ያንን ምሳ እየበላሁ እንባ ተናነቀኝ። በዚያች አጭር ጊዜ ፈጣሪዬ ፀሎቴን ሰምቶ የማላውቀውን ሰው ልኮ እንደዛ እንጀራ እንድበላ አደረገኝ። ያውም በቀይ ወጥ፣ ያውም ቅልጥም ያለው እንጀራ በዚያ ምድረበዳ አበላኝ፡፡ በእግዚአብሔር ላይ ያለኝ እምነት ከዚያን ጊዜ ጀምሮ መጠንከር ጀመረ። “ሁሌ አምንሃለሁ” ብዬ ወደ ሰማይ አንጋጥጬ እግዚአብሔርን አመሰገንኩኝ።
በሳምንቱ እዛው ግቢ ብሎኬት ፋብሪካ ውስጥ 1 ብር ደሞዝ ጭማሪ ተደርጎ በሰባት ብር ተቀጠርኩ። ምግብም እንደሌላው በዱቤ መብላት ጀመርኩኝ። የምግብ ችግሬ እዛው እየተቀረፈ ፀሎቴም እየሰራ መጣ።
አንዴ በሌሊት ከቤትህ ወጥተህ በጅብ ልትበላ ነበር ግን ለምንድን ነው በሌሊት የወጣኸው?
የማልረሳቸው አስጨናቂ ጊዜያት በአንባቢ አዕምሮ ውስጥ እንደሚቀር አንቺ ማሳያ ነሽ። የእግዚአብሔርን ተዓምር ካየሁበት ዕለት አንዱ ይሄ ቀን ነው። ሜክሲኮ አካባቢ ኬክ ቤት ረዳትነት በስንት ፍለጋ ተገኝቶልኝ መስራት ጀምሬ ነበር። ሳንቲም ያለኝ ጊዜ 11 ሰዓት እነቃና በትራንስፖርት እሄዳለሁ። በዚያን ቀን ግን ሳንቲም ስላልነበረኝና በእገሬ ስለምሄድ ተኝቼ እንዳይረፍድብኝ ስነቃ ስተኛ ቆይቼ የሆነ ሰዓት ላይ ብንን ስል የረፈደብኝ  መስሎኝ ነው ውጥት ብዬ መሄድ የጀመርኩት። እኔ 20 ጉዳይ ለ11 መስሎኝ፣ 20 ጉዳይ ለ10 ነው የወጣሁት፡፡ አስቢው…. ዘጠኝ ሰዓት ከምናምን ማለት ነው። እርግጥ ስወጣ ጨለማው ከብዶኛል። ያልለመድኩት አይነት ድቅድቅ ጨለማ ነው። ትንሽ እንደሄድኩ የየካ ጫካ ያስፈራል፤ ብዙ የጅብ ድምጽ ይሰማኛል። ሲጮሁ ራቅ ብሎ ያው የሰፈራችን ኳስ ሜዳ አካባቢ ሆነው ነበር የመሰለኝ። ነገር ግን ጉዞዬን ስቀጥል፣ በኔና በጅቦቹ መሃል ከ15 -20 ሜትር በሚሆን ርቀት ላይ አየኋቸው መሃላቸው ገባሁ። ወደ ኋላ ብመለስ ከተከተሉኝ ማምለጫ የለኝም። ያለኝ አማራጭ መቆም ብቻ ነበር። ብዙ ናቸው፤ አይናቸው ያበራል። አንዱ ግን እየቀረበኝ መጣ፤ ሊተናኮለኝ እንደሆነ ገባኝ፤ ድንጋይ ለማንሳት መሬቱ አይታየኝም። ግን ዝም ብዬ ጎንበስ ብዬ ድንጋይ እንደ ማንሳት ስል ሽሽት ይላል። ከዛ ደሞ ይቀርበኛል። በቃ ጭንቅ ውስጥ ገባሁ። በቃ ተበላሁ ብዬ ተስፋ ቆርጬ ነበር። “ፈጣሪዬ አውጣኝ፤ ተዓምር ስራ” ብዬ ጸለይኩኝ። እንደምንም መሬት ዳስሼ ሁለት ድንጋይ አነሳሁ። በዚያ ድንጋይ ሆዱን መታሁትና ጮኸ። በአንዱ ድንጋይ የአንድ ቤት ቆርቆሮ አጥር በሃይል ስመታ ሁሉም ገለል አሉልኝና  በዚያች ቅጽበት አንድ መንገደኛ አግኝቼ ወደ ዋናው አስፓልት ወጣሁ። ያንን ጊዜ  ባልተመቻቸ ሁኔታም ውስጥ ቢሆን እንድኖር አንድ ተጨማሪ እድል እንደተሰጠኝ ነው ያሰብኩትና እግዚአብሔርን ያመሰገንኩት።
በእኛ አገር ባህልም እንበለው ስነ-ልቦና፣ ወግም  እንበለው ልማድ… ወንደ ልጅ የፈለገ ቢቸገር በቤት ሰራተኝነት አይቀጠርም፡፡ አንተ ያን አድርገኸዋል…
በዚያ ሰዓት ባህል ወግ…. የሚሉትን ነገር ማሰብ ለእኔ ቅንጦት ነበር። እኔ የማስበው ከሌብነት ውጪ ማንኛውንም ስራ ሰርቼ ራሴን ለማሸነፍ ነው። በወቅቱ መማር እፈልጋለሁ። መቀየር እፈልጋለሁ። ስለዚህ ስራ ሳልንቅ መስራትና መለወጥ  ነበረብኝ።  የቤት ሰራተኝነት አይደለም ምንም ቢሆን ለመስራት ቆርጫለሁ።  ለምን? መማር አለብኝ፡፡ ለምን? በበቂ ሁኔታ መናቅን፣ መገፋትን፣ መራብን፣ ብቸኝነትን አይቻለሁ። ከዚህ ሁሉ ለመውጣት መማር መቀየር አለብኝ።
በእርግጥ የቀጠሩኝ ባልና ሚስቶች የማላውቃቸው ሰዎች አይደሉም፡፡ መርዳትና ማስተማር ይችሉ ነበር፤ ግን ያንን አላደረጉም። በፊት በመንፈሳዊ ህይወት አብረን እናገለግል የነበርን ሰዎች ነን። ነገር ግን እግዚአብሔር በዚያ እንዳልፍ ፈልጎም እንደሆነ አላውቅም። ያ ሆነ። ሰውየው ከውጪ መጥቶ አገኘኝ፤ ሚስቱ የውጪ ዜጋ ናት። “አንተነህ በጣም ጎበዝ! እየተማርክ እንደሆነ ሰማሁ በርታ”! አለኝ። “አዎ እየተማርኩም እየሰራሁም ነበረ፤ ግን ት/ቤቱ 40 ብር ክፍያ ጨምሮብን  ያንን መክፈል የሚያስችል ደሞዝ ስላልሆነ ያንን ስራ አቁሜ ሌላ እየፈለግሁ ነው” አልኩት። “አይ ችግር የለም፤ የቤት ሰራተኝነት  ስሜት ካልተሰማህ ለምን አትሰራም” አለኝ። እኔ ደሞ በፊት የምናገለግልበት የውጪ ድርጅት ውስጥ በተላላኪነትም ቢሆን እንደሚያስቀጥረኝ ጠብቄ ነበር። ሲኤምሲ አፓርትመንቶች ውስጥ ቀጠረኝና ሄድኩኝ፡፡ ፡፡አሜሪካዊቷ ሚስቱም በፊት በጣም የምታውቀኝ የምንከባበር ነበርን። አሁን እንደማያውቁኝ ሆኑ። እሺ ብዬ ገባሁ፤ ሚስቱ ኪችን ውስጥ ብዙ የሚታጠብ እቃ ነበር፤ አሳየችኝ። ቤት እንዴት እንደሚጸዳ፣ ምግብ እንዴት እንደሚሰራ ሱቅ እቃ መገዛዛት፣ ሽንት ቤትና የሚታጠብበትን ኬሚካል ሁሉ አሳየችኝ። የህጻናት ልብስ አስተጣጠብና ሌላ ሌላውንም አሳየችኝ ብቻ ሁሉንም ስራ ብዬ ተቀበልኩኝ። ማንኛዋም የቤት ሰራተኛ የምትሰራውን ሁሉ እሰራለሁ። ብዙ እንግዳ ይበዛል፤ ምግብ ቶሎ ቶሎ እሰራለሁ። ብቻ ምን አለፋሽ… ስራዬ ብዬ ስለያዝኩት  ምንም አልመሰለኝም።
ስንት ብር ነበር ደሞዝህ? ምን ያህል ጊዜስ ሰራህ?
ትምህርቴን ለመጨረስ የቀረኝ አራት ወራት ብቻ ነበር። እነሱ የሚኖሩት ሲኤምሲ ነው፤ እኔ የምማረው ፒያሳ ኤልኤም ኢንተርናሽናል የሆቴልና ቱሪዝም ኮሌጅ ነው። 260 ብር ይከፍሉኛል፤ 220 ብር ለት/ቤት እከፍላለሁ፤ አርባ ብር ትተርፈኛለች። ያቺ አርባ ብር አትበቃኝም። አንድ ሰው ዝም ብሎ በየወሩ 50 ብር ስለሚረዳኝ እያብቃቃሁ ነው  የምኖረው…ለትራንስፖርትም ለምንም። አየሽ  እነዚህ ሰዎች ቤት በተመላላሽነት ነበር የምሰራው፤፡
አንተ ምግብ እየራበህና እየናፈቀህ ነው ያደግኸው፡፡ ግን ደግሞ የምግብ ዝግጅት ሙያ ሰልጥነህ ሼፍ ሆነሀል… እንዴት ፍላጎቱ አደረብህ?
እውነት ነው፤ ብዙ ሰው ወደ ምግብ ባለሙያነት የሚገባው ከቅንጦት ሊሆን ይችላል። የኔ እንደዛ አይደለም። የማትሪክ ውጤት ስላልመጣልኝ ከአንድ ጓደኛዬ ጋር ዶሮ ለማርባት ሞክረን ነበር። ከጫካ እንጨት ቆርጠን ዶሮ ቤት ሰራን፤ ዶሮዎች ገዝተን ስራ ጀመርን። 30 ዶሮዎች ነበሩ፤ አነር በላብን፤ ከአነር የተረፉትንም በሽታ ገብቶ ጨረሳቸው። በዚህ ስራ ብዙ ተስፋ ነበረን። ይሄ ተስፋ በዚህ ተሟጠጠ። እኔ ከዛ በፊት የቀን ስራ ነው ሰርቼ የማውቀው፤ ትምህርቴን ለመማርም ወተት ተሸክሜ እያመላለስኩ በወር 20 ብር ይከፈለኝ ነበር። 16 ብር ለ8ኛ ክፍል የግል ት/ቤት እከፍል ነበር። ብቻ ስራ ስፈልግ የማውቃቸው መንፈሳዊ ሰዎች ፈልገው፣ እዛ ሌሊት ወጥቼ ስሄድ ጅብ ልበላበት የነበረው ኬክ ቤት አስገቡኝ፤ ረዳት ኬክ ጋጋሪ ሆንኩኝ። በወር 130 ብር ደሞዝ።  ከሰኞ እስከ ሰኞ እሰራለሁ። ጠዋት ገብቼ ቀን 10 ሰዓት እወጣ ነበር። ለኔ ዳቦ ማግኘት ቀላል አልነበረም።
እየሰራሁ ሙያ ለመልመድ ስጣጣር ዋና ኬክ ጋጋሪው ፈቃደኛ አልነበረም። ይከለክለኝ ነበር፡፡ ሙያውን እንድለምድ አልፈለገም እኔም ለምን ተምሬ ሙያተኛ አልሆንም ብዬ ነው ኤልኤም ኢንተርናሽናል የገባሁት። በኋላ የቀለም ትምህርቱ አልቆ ወደ ተግባር ስንገባ የግብአት መግዣ ስለሚያስፈልግ 40 ብር ጭማሪ ተደርጎ፣ 130 ብሩ ስላልበቃኝ ትቼ ስራ ስፈልግ ነው እነዛ ባልና ሚስቶች በ260 ብር የቀጠሩኝ፤ የቤት ሰራተኛ የሆንኩት፡፡ በዚህ ምክንያት ነው፤ የተማርኩትም  ሼፍም የሆንኩትም።
መከራና ፈተናው አውሮፓም ሄደህ አልቀረልህም በሼፍነት ስትሰራ የምታውቀው ሰው ስፔን ለእረፍት ጋብዞህ የሄድክበትና ወደ ጀርመን የተሰደድክበት ሂደት  እጅግ ከማይረሱ አሳዛኝ ታሪኮችህ ተጠቃሽ ነው። አሁን ላይ ስታስበው ምን ይሰማሃል?
አሁን ላይ ሳስበው ያን ሁሉ እንዴት አድርጌ፣ በምን አቅሜ ቻልኩት እላለሁ። በጀርመን ከአንዱ ስደተኛ ካምፕ ወደ ሌላው የተንገላታሁበት፣ የእናቴን ሞት በፌስቡክ የሰማሁበት፣ በዛን ጊዜ አንድ ስደተኛ ጥገኝነት መጠየቅ የሚችለው ከአገሩ ወጥቶ መጀመሪያ እግሩ የረገጠበት ስለሆነ ወደ ስፔይን ይመለስ ስባል በጣም ብዙ መከራ ተደራርቦብኛል፡፡ እዚህ አገር ቤትም´ኮ በተለይ ሼፍ ሆኜ ለመስራት ስገባ ያጋጠመኝ ዋና ሼፍ ንቀቱ፣ በአባቴ ስም በብሔሬ ያላግጥ የነበረበት ሁኔታ… አንዱን ምግብ ጥሩ አድርጌ ስሰራ ወደ እቃ አጣቢነት፣ ከዚያ ወደ ኬክ፣ ከዚያ ወደ አንዱ እያንከለከለ ያደረሰብኝ በደል በእጅጉ አይረሳኝም። አፍሪካ ህብረት ለትልልቅ ዴሊጌቶች ዲፕሎማቶች ዋና ሼፍ ሆኜ ስሰራ “ረዳት ይመጣልሃል፣ ስራ በዝቷል” ተብሎ  ተብሎ ማን ቢመጣ ጥሩ ነው ያ ያንገላታኝ የነበረ ሼፍ፡፡ ከእርሱ ጋር ነው የምትሰራው ተባልኩ ግን እሱም ዳግመኛ ወደ አፍሪካ ህብረት ድርስ አላለም። በዚህ መልኩ እጅግ ብዙ አሰቃቂ ነገሮችን አልፌ አሁን እዚህ ደርሼያለሁ። ተይው የአውሮፓውን እዚህ አገር ቤትም ነው የምልሽ።
በእርግጥ በአሁኑ ሰዓት ጀርመን ኑረንበርግ ውስጥ እጅግ ቅንጡ በሆነና በባለ 5 ኮከብ “ዓለም አቀፍ ሆቴል” ውስጥ ነው የምትሰራው?
አዎ እዛ ነው የምሰራው።
 አንዳንድ ሰው በእንደዚህ አይነት መከራ አልፎ ጥሩ ደረጃ ላይ ሲደርስ ያለፈ ታሪኩን ለማውራት ያፍራል፡፡ አንተ ሌላው ከኔ ይማር ብለህ ታሪክህን በግልጽ በመጽሐፍ ለአንባቢ አቅርበሃል፡፡ እንዴት ደፈርክ?
ሁሌም ራስን ሆኖ…. ማንነትን ተቀብሎ በመኖር መርህ አምናለሁ። እኔ ያለፈውም  አሁን ያለሁበትም ህይወቴ የኔ ታሪክ ነው። በስርቆትና በወንጀል አልተሳተፍኩም፡፡ እንደዚያ እየራበኝ ስርቆት አስቤ አላውቅም፤ ግን ዝቅ ብዬ ሰርቻለሁ። ብዙ ሰው ከእኔ እንዲማር  ነው  የጻፍኩት ፤ደግሞ ያስተምራል ብዬ አምናለሁ። መጽሐፉ ሲታተም ገንዘብ ለማግኘት አይደለም። አሁን ወደ ጀርመንኛ እየተተረጎመ ነው። እናም ራሴን ሆኜ መኖሬ ነው የሚስደስተኝ። ስለዚህ በህይወቴ የማፍርበት የምሸማቀቅበት ነገር የለም።
በመጨረሻ የምትለው አለ?
በዛ በችግሬ ወቅት ከጎኔ የቆሙ በርካቶች ናቸው። በጀርመንም ብዙ ያገዙኝ ጀርመናዊያን አሉ፣ አገር ቤትም እንደዛው ስም ባልጠቅስም ለሁሉም ምስጋናዬ ይድረሳቸው፡፡ ሁሉንም አመሰግናለሁ። መፅሐፉን ቅርጽ በማስያዝ በኩል ደራሲ  ኃይለመለኮት መዋዕልና ጋዜጠኛ ብርሃኑ ሰሙን አመሰግናለሁ። በርካቶች የማመሰግናቸው ሰዎች አሉ።
በመጨረሻም “ስደተኛው ሼፍ” የተሰኘው መፅሐፌ ሃቀኛ ያልተበረዘ፣ የውሸት ታሪክ የሌለበት፣ እውነተኛ ፅናትና የትግል ማሳያና ማሸነፊያ መንገድ ስለሆነ፣ ሰዎች አንብበው እንዲማሩበት እጋብዛለሁ።


Read 2667 times