Print this page
Wednesday, 28 April 2021 00:00

አሜሪካ - የግል ጠመንጃና የሽጉጥ ውቅያኖስ።

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(0 votes)

     • አሜሪካ የህዝብ ብዛት፡ 340 ሚሊዮን።
      • የግል ጠመንጃና ሽጉጥ ብዛት፡ 400 ሚሊዮን።
      • ለእያንዳንዱ ቤተሰብ፣ በአማካይ፡ 3 ጠመንጃ ወይም ሽጉጥ።
      • በየአመቱ ለአሜሪካ ገበያ የሚቀርብ ሕጋዊ የመሳሪያ ብዛት፡ 9 ሚሊዮን (4.5 ሚሊዮን ጠመንጃ፣ 4.5 ሚሊዮን ሽጉጥ)።
      • የነፃነትና የመብት ምንነት፣ በጠመንጃና በሽጉጥ መነፅር ማየት፡፡
                  
            ከትልልቅ “ሱፐርማርኬቶች”፣ ከመሳሪያ መደብሮች፣ አልያም ከ”ባዛር”፣ አማርጠው ይገዛሉ - ሽጉጥና ጠመንጃ። የራሳቸውን ሽጉጥ የሚሰሩም አሉ - በ3ዲ ፕሪንተር ጭምር። አብዛኛው አሜሪካዊ ግን፣ ሸማች ነው። 21 ዓመት የሞላው፣ ወንጀል ያልፈፀመ፣ በአእምሮ ህመም ያልተጎዳ ማንኛውም ዜጋ፣ ያለ ብዙ ውጣውረድ፣ መሳሪያ መግዛት ይችላል።
የመሳሪያ ባለቤት ለመሆን፣ የመንግስት ፈቃድ አያስፈልግም። መብት ነውና። ይሄ፣ አንድ ነገር ነው።
መሳሪያ ይዞ መንቀሳቀስ ግን፣ ሌላ ነገር ነው።
እሷ፣ ሽጉጥዋን በቦርሳዋ ሸክፋ ወይም ከወገቧ ታጥቃ፣.... እሱ፣ ጠመንጃውን አነግቶ ወይም ትከሻው ላይ አገልድሞ መንቀሳቀስ፣... ይሄ፣ አሜሪካ ውስጥ ሁሌም ያወዛግባል።
የግል መሳሪያ መታጠቅ፣ በአገረ አሜሪካ፣ በፌደራልና በየክልሉ፣ የብዙ ህጎች ሰበብ እየሆነ፣ በድጋፍና በተቃውሞ ብዙዎችን ያንጫጫል። አንዳንዶቹማ፣ እንደ መስከር እንደ መቃዠት ያደርጋቸዋል።
“መንግስት፣ ትጥቃችንን አስፈትቶ አምባገነን ለመሆን አሲሯል” በሚል እምነት፣ ለክፉ ቀን የሚዘጋጁ፣ ዋሻ የሚምሱ፣ ምድር ቤት የሚገነቡ ጠርጣራ ሰዎች፣ ጥቂት አይደሉም። “መንግስት፣ አሜሪካን አፍርሶ፣ ለዓለማቀፋዊ አገዛዝ (ለዩኤን አገዛዝ) አሳልፎ ሊሰጠን ነው” በማለትም የዓመጽ ጭስ ያስነጥሳሉ።
የዚህ ተቃራኒዎች ደግሞ አሉ። “አገሬው ሁሉ ታጥቆ፣ ጓዳውና አደባባዩ ሁሉ በጠመንጃና በሽጉጥ ተጥለቅልቋል። ከዛሬ ነገ፣ ህዝቡ ይተላለቃል” በሚል እምነት፣ ከወዲሁ ሙሾ ያወርዳሉ። የምፅአትና የመዓት ንግርትን በእሪታ ያውጃሉ።
በፍሎሪዳ ግዛት፣ “አዲስ የህግ ማሻሻያ” የተረቀቀ ጊዜ፣ ምን ያህል ጫጫታ እንደተፈጠረ መጥቀስ ይቻላል። አምና በ2020 የታተመው፣ “Guns and Control” የተሰኘው መፅሐፍ ታሪኩን ያጋራናል። “መሳሪያ ይዘው መንቀሳቀስ የሚፈልጉ ዜጎች፣ የፈቃድ ወረቀት የማግኘት መብት አላቸው” የሚል ነው - በጊዜው አወዛጋቢ የነበረው የፍሎሪዳ ህግ። ብዙ ተወግዟል። “አዳሜ ጠመንጃና ሽጉጥ ሲታጠቅ፣ የፍሎሪዳ ከተሞች ጉዳቸው ይፈላል። በተኩስ እሩምታ ይናወጣሉ፤ በደም ጎርፍ ይጥለቀለቃሉ” ብለው እሪታቸውን አሰምተዋል - ተቃዋሚዎች።
ፍሎሪዳ፣ በጎብኚዎች ጎርፍ ነው የምትታውቀው። የምን የደም ጎርፍ? ምን ያወራሉ? የህጉ ተቃዋሚዎች ግን፣ ለጥያቄና መልስ የሚሆን ጊዜ አልነበራቸውም። እልፍ አእላፍ በራሪ ወረቀቶችን አትመው በየቦታው ለአላፊ አግዳሚው ለመስጠት ዘመቱ። የአውሮፕላን ማረፊያ ላይ፣ ጎብኚዎች ከየአካባቢው፣ ከባህር ማዶም ሲመጡ፣ ገና እግራቸው ፍሎሪዳን ሲረግጥ፣ አስደንጋጭ በራሪ ወረቀት ይጠብቃቻዋል።
“ከዘንድሮ በኋላ፣ ወደ ፍሎሪዳ እንዳትመጡ። ለከርሞ፣ ሁሉም ታጥቆ መታኮስና መተላለቅ ይጀምራል። ለምታውቁት ሰው ሁሉ ምከሩ። ለዘመድ ለወዳጅ ሁሉ አስጠንቅቁ። ወደ ፍሎሪዳ ዝር እንዳይሉ ንገሯቸው።”
ጎብኚዎችን በሚያስደነብር አስፈሪ በራሪ ወረቀቶች አማካኝነት የተቋውሞ ዘመቻ ቢካሄድበትም፣ የፍሎሪዳው ህግ ተግባራዊ መሆኑ አልቀረም። ደግነቱ፣ የተፈራው “የከተማ ጦርነት”፣ በፍሎሪዳ አልተከሰተም።
በተቃራኒው፤ ከአመት ዓመት የወንጀል ድርጊቶች ቁጥር ሲቀንስ ታየ። እንዴት ይቀንሳል? አንዳንድ ሰዎችን አስገርሟል። ህጉን ለሚደግፉ ሰዎች ግን፣ ነገሩ አሰገራሚ ጉዳይ አልሆነባቸውም። ከመነሻው፣ ህጉ የተዘጋጀው፣ የወንጅል ድርጊቶችን ለመቀነስ ይረዳል በሚል ነውና።
የአሜሪካና የሽጉጥ ፍቅር እንደገና ታደሰ።
የፍሎሪዳ ሙከራ ከታየ በኋላ፣ የመሳሪያ ትጥቅና የአሜሪካ ታሪክ ተቀየረ። አሜሪካና ጠመንጃ፣ አሜሪካውያንና ሽጉጥ፤ ከድሮውም በላይ የተዛመዱበት፣ “አንለያይም” ተባብለው የተጋቡት ዘመን ተፈጠረ።
ከፍሎሪዳ በፊት፤ በ10 ትናንሽ ክልሎች ውስጥ ብቻ ነበር የመሳሪያ ትጥቅ የሚፈቀደው። ከዚያስ ወዲህስ? ወደ 42 ክልሎች ተስፋፍቷል። ግን አይነቱ በየክልሉ ይለያያል። ዋሺንግተን ዲሲን ሳይጨምር፣ የአሜሪካ ግዛቶች ወይም ክልሎች 51 አይደሉ? እና ስንቶቹ ፈቀዱ? ስንቶቹስ ከለከሉ? ፈቃድ ከመስጠት የታቀቡ መኖራቸውስ?
“ፈቃድ እሰጣለሁ”፤ “ፈቃድ መስጠት እችላለሁ”።
በደፈናው፣ “የግል መሳሪያ ይዞ መንቀሳቀስ ክልክል ነው” ብሎ ያወጀ ክልል የለም። ነገር ግን መንግስት፣ “ፈቃድ መስጠት ይችላል” የሚል ህግ፣ እንደክልከላ ነው የሚቆጠረው። ለምን? ሽጉጥ ገዝተህ ቤት ውስጥ ማስቀመጥ፣ መብት ቢሆንም፣ ሽጉጥ ይዞ መንቀሳቀስ ግን... በመንግስት ፈቃድና ችሮታ ብቻ ይሆናል ማለት ነው። የክልሉ አስተዳደር፣ “ከፈለገ ፈቃድ ሊሰጥ ይችላል” እንደ ማለት ነው። ካልፈለገ ደግሞ መከላከል ይችላል። እንዲህ አይነት ህግ፣ በአገረ አሜሪካ እንደ ክልከላ ይቆጠራል። የዘጠኝ ክልሎች ህግ፣ ከዚህ የክልከላ ጎራ ይመደባል። የመሳሪያ ባለቤትነት መብትን ቢያከብሩም፣ ታጥቆ የመንቀሳቀስ መብትን ይገድባሉ። ይከላከላሉ።
የአብዛኛዎቹ ክልሎች ህግ ግን፣ ከዚህ ይለያል። “ፈቃድ መስጠት እችላለሁ” አይሉም። “ፈቃድ እሰጣለሁ” የሚል ህግ ያወጡ ናቸው - 27 የአሜሪካ ግዛቶች።
“ፈቃድ እሰጣለሁ” የሚል ህግ፣ “ፈቃድ መስጠት እችላለሁ፤ ስልጣን አለኝ” እንደማለት አይደለም። ከስልጣን ጋር፣ “ፈቃድ የመስጠት ሃላፊነት ወይም ግዴታ አለብኝ” የሚል ትርጉም አለው። ፈቃድ አልሰጥም ብሎ መከልከል አይችልም ማለት ነው።
ታዲያ አትርሱ። መሳሪያ ለመግዛት የመንግስት ፈቃድ አያስፈልግም። የእድሜና የአእምሮ ጤንነት መመዘኛዎችን ያሟላ፣ እንዲሁም ከወንጀል ጋር ያልተነካካ ሰው፣ ሽጉጥ ለመግዛት ፍቃድ ማውጣት አያስፈልገውም። ታጥቆ ለመንቀሳቀስ ግን፣ ተጨማሪ መመዘኛዎችን ማሟላትና ፈቃድ ማውጣት የግድ ነው። ከመንጃ ፈቃድ ጋር ይመሳሰላል። አጭር የእውቀትና የልምድ ስልጠና መውሰድ አለብህ ይሉሃል። ከቀበቶ ጋር ማቆራኛ ወይም ማንገቻ ያለው የመሳሪያ ማቀፊያ፣ አልያም መያዣ ቦርሳ ሊኖርህ ይገባል የሚሉ ህጎችም አሉ።
ያም ሆኖ ይህ፣ መመዘኛዎችን የሚያሟሉ ዜጎች ሁሉ፣ መሳሪያ መታጠቅ ሲፈልጉ፣ የመንግስት አስተዳደር ፈቃድ መስጠት ግዴታው ነው - በ27 የአሜሪካ ግዛቶች። በሌሎች ግዛቶችስ?
መብት ከተከበረ፣ “ከልካይ የለውም”፤ “ፈቃጅ አያሻውም”።
“Guns and Control” የተሰኘው መፅሐፍ እንደሚገልፀው፣ በአገረ አሜሪካ፣...
9 ግዛቶች፣ የመሳሪያ ባለቤትነት መብትን ያከብራሉ እንጂ፣ መሳሪያ መታጠቅን “መፍቀድ ይችላሉ”፣ ማለትም፣ “መከልከል ይችላሉ”።
27 ግዛቶች፣ የመሳሪያ ባለቤትነት መብትን ብቻ ሳይሆን፣ መሳሪያ የመታጠቅ መብትንም ያከብራሉ (በእርግጥ፣ የፈቃድ ወረቀት ያስፈልጋል ይላሉ)።
ቀሪዎቹ 15 ግዛቶች፣ “ከልካይም ፈቃጅም” አይደሉም። ነገሩ እንዲህ ነው።
የመሳሪያ ባለቤትነት፣ እንዲሁም መሳሪያ ታጥቆ መንቀሳቀስ፣ የእያንዳንዱ ዜጋ መብቶች ናቸው ከሚል ሃሳብ ይነሳሉ። መብቶች ደግሞ፣ በተፈጥሯቸው፣ ሊከለከሉ የማይገባቸው፣ ፈቃጅም የማያስፈልጋቸው መብቶች ናቸው የሚል ነው፣ የ15 ግዛቶች የህግ ቅኝት።
የመኖሪያ ቦታ መቀየር፣ ስራ መቀጠር፣ ጋብቻ መፈፀም፣ የእያንዳንዱ ሰው መብት አይደል? ከልካይ የለውም፤ ፈቃጅም አያስፈልገውም። የመሳሪያ ባለቤትነትና መሳሪያ ይዞ መንቀሳቀስም፣ ፈቃጅ አያሻውም እንደማለት ነው።
መብትና ነፃነት፣ ከጠመንጃና ከሽጉጥም ምን አገናኛቸው?
“ሌሎች መብቶችን ሁሉ የሚያካትት መብት” ተብሎ በቀዳሚነት መጠቀስ የሚገባው፣ የህልውና መብት ነው። the right to life ይሉታል። ማንም ሃይል ወይም ማንም ሰው፣ በማንም ሰው ህይወት ላይ ጥቃት መሰንዘር ወይም ጉዳት ማድረስ አይገባውም። የግል ማንነትና የግል ሃላፊነት ላይ የተመሰረተ ነው - በሕይወት የመኖር መብት።
በእርግጥ፣ ከህልውና መብት ጋር፤ እያንዳንዱ ሰው፣ ህልውናውን ለማለምለም፣ በሃሳብና በተግባር የመጣር የግል ሃላፊነት ይኖረዋል። ከዚህ ጎን ለጎን፣ የማሰብ አእምሯዊ አቅሙንና የመስራት አካላዊ ጉልበቱን የመጠበቅ ነፃነት ይኖረዋል - the right to liberty እንዲል መፅሐፉ።
ታዲያ፣ አስቦ የመስራት ነፃነት፣ ለብቻው በቂ አይደለም። የስራ ፍሬውን፣ የጥረት ውጤቱን የማስከበር መብት ከሌለው፣ ምኑን ኖረው? ባርነትና ልፋት ብቻ ይሆናል። የንብረት ባለቤት መብት፣ ዋና የኑሮ ዋስትና ነው - the right to property ይሉታል አንዳንዶቹ። ሌሎች ደግሞ መንፈሳዊ (ወይም አእምሯዊ) ባህሪይንም በመጨመር፣ መነሻውንና አላማውን በማካተት፣ the right to the pursuit of happiness ብለው ይሰይሙታል።
በዚህ መንገድ፣ “የስልጡን ፖለቲካ መሰረታዊ መርሆች”ን የሚያብራራልን የአሜሪካ የነፃነት መግለጫ፣ ተጨማሪ ቁምነገር ይነግረናል። በጥቅሉ፣ የመንግስት አስፈላጊነት፣ እነዚህን መብቶች ለማስከበር ነው ይለናል። ግድያንና ጥቃትን፣ አፈናንና ሁከትን፣ ስርቆትንና ዝርፊያን ለመከላከል፣ አጥፊዎችን ደግሞ በአፀፋ ለመቅጣት ያገለግላል - መንግስት።
“የመንግስት ስራ፣ የእያንዳንዱን ሰው መብት ማስከበር ነው” ከሚለው መርህ ጋር፤ ተጓዳኝ ነጥቦች አሉ።
አንደኛው ነጥብ፣ የእያንዳንዱን ሰው መብት ማስከበር የሚገባው መንግስት፣ በቅድሚያ እሱ ራሱ፣ መብት አክባሪ መሆን ይኖርበታል።
ሁለተኛው ቁም ነገርስ?
አዎ፣ መብትን የማስከበር (ወንጀልን የመከላከልና በአፀፋ የመቀጣት) ሃላፊነት፣ የመንግስት ሃላፊነት ነው - የፖሊስና ፍርድ ቤት። ለዚህም፤ እውነተኛ መረጃንና አስተማማኝ ማስረጃን አጥርቶ ለማወቅ የሚያስችል ሕጋዊ ስርዓት ያስፈልጋል። ጥፋተኛን በማያሻማ መንገድ ለማረጋገጥ የሚያስችል ጠንቃቃ ህጋዊ አሰራርንም ማሟላት ይገባል።
እያንዳንዱ ሰው፣ ጥቃት ተሰነዘረብኝ፤ በደል ደረሰብኝ፣ ግፍ ተፈፀመብኝ ብሎ ባሰበ ቁጥር፣ በዘፈቀደ “መሰለኝ፣ አሰኘኝ” በሚል ስሜት እርምጃ መውሰድ የለበትም። እውነትን በማስረጃ የሚረጋገጥ፣ ጥፋተኛን ለይቶ የሚበይን፣ ተገቢውን የአፀፋ ቅጣት የሚወስን ግልፅ ህጋዊ አሰራርን መከተል ይገባዋል። መንግስት ይህንን ካልሰራ ምን ያደርጋል?
እንዲህም ሆኖ፣ እያንዳንዱ ሰው፣ እጁን አጣጥፎ ፖሊስን መጠበቅ አለበት ማለት አይደለም። አጣዳፊና ደራሽ ጥቃቶችን፣ በራሱ አቅም የመከላከል፣ አፀፋውን የመመለስ መብት አለው። እያንዳንዱ ሰው፣ ለግቢው የግንብ አጥር መገንባት፣ የቤቱን በር መቆለፍ፣ ሰፈር መንደሩን በተራ መጠበቅ ወይም ዘበኛ መቅጠር ይችላል - መብቱ ነው። ይህም ብቻ አይደለም። ዝርፊያን፣ ድብደባን፣ ወይም የግድያ ጥቃትን የመመከት መብት አለው - እያንዳንዱ ሰው።
እዚህ ላይ ነው፤ የጠመንጃና የሽጉጥ ጉዳይ፣ ገናና የመብት ጉዳይ ሆኖ የሚመጣው።
በአሜሪካ ህገመንግስትም፣ መንግስት፣ “መሳሪያ የመያዝ መብትን” የመገድብ ስልጣን እንደሌለው ይገለፃል። ነገር ግን፣ በህገመንግስት ስለተፃፈ ከውዝግብ አምልጧል ማለት አይደለም። አከራካሪ መሆኑ አልቀረም። ትርጉሙና ልኩ፣ የፖለቲከኞች መነታረኪያ ብቻ ሳይሆን፣ የፍርድ ቤት መሟገቻም ነው። የግል ጠመንጃና የሽጉጥ ቁጥር ግን ከዓመት ዓመት እየጨመረ ቀጥሏል።


Read 4792 times