Saturday, 24 April 2021 14:08

የዝምታው ጩኸት

Written by  አፀደ ኪዳኔ (ቶማስ)
Rate this item
(9 votes)

   ከመውደዱ ጫካ ውስጥ የጠፋሁ፣ ከፍቅሩ ግርጌ ላይ እንደ ሳር ድንገት በቅዬ በዝምታው ንዳድ የወየብኩ፣ በቸልታው ውስጥ የምደርቅ ብኩን ነኝ። ከጉዳዩ እንደማይጥፈኝ አውቃለሁ።  በዝምታ እባጭ ተኮፍሶ፣ እንደ ተራ ነገር ያየኛል። እስሩ አስቀምጦኝ የማይረባ ተልካሻ መፅሐፍ ለመቶኛ ጊዜ ያነባል። እውነቱን በጊዜ ውስጥ ሲፈልግ ጭራሽ ይረሳኛል። ጭራሽ በዝምታው ይቀብረኛል። ይኼኔ ነቁጥ የእንባ ኳስ ጉንጬ ላይ መፍሰስ ይጀምራል።
ለምን ቸል ይለኛል? (ቸል መባል ለሴት ልጅ መርዝ እንደሆነ አያውቅም)  ለምን ፍቅሬን አይረዳም (በወደዱት አለመፈቀር ህመም እንደሆነ አላየም? ሽሽቱስ የቱ ጋ ይቆማል? በእሱስ መቃጠሌ የሚያበቃው የቱ ጋ ነው?) የተገናኘንበትን  ዕለት እረግማለሁ። ከእሱ ያሰናሰለኝን ፍቅር እጠላለሁ።  ዓለምን እንቃለሁ።
ሲወጣ -  ጥቁር ጃኬቱን ደርቦ፣ ጥቁር ኮፍያ አድርጎ ከዚያ የጠጅ ቤት ጓሮ ቅዝዝ ብሎ ይገባል። እንደገባ በዝምታ ይቀመጣል። አሳላፊው ፈጠን ብሎ መጥቶ ጠጁን ይቀዳና -- ያመጣለታል፤ ከዚያ ትኩስ ድንች። ሹካውን እየሰካ ይተክዛል። ያን ትኩስ ድንች ሰፊ አፉ ውስጥ እያላመጠ፣ ስለዚያች ትታው ስለሄደች እንስት ያስባል።  ግራጫ ዝምታው፣ የሚልገው የጉንጩ ሪዝ፣ አይኑን ከሚተክልበት አግድም ወንበር ላይ  የተቀባው አረንጓዴ ቀለም  ሁሉ ዝምታን የሚናገሩ፣ ዝምታን የሚያወሱ፣ ዝምታን የሚሰብኩ ይመስላሉ።  ሃገሩ የሚያወራው በፊት ጥላው ስለሄደች እንስት ነው። እኔም አንዳንዴ እዛ ጠጅ ቤት ትክዝ ብሎ ሳየው እሷን የሚያስብ፣ እሷን የሚያልም ይመስለኛል። ይመስለኛል ሳይሆን በእርግጠኝነት እሷን ነው የሚያስበው። ሳላውቃት  እጠላታለሁ። እንዲህ አፍዛ አደንዝዛ ያስቀረችው እሷ መሆኗን ሳውቅ፣ አንቀሽ ግደያት አንቀሽ ግደያት የሚል ስሜት ይፈታተነኛል።  አንድ ዕለት ስለዚች እንስት ብጠይቀው ሩቅ እያማተረ፣  ሪዙን እየላገ፣ እንዲህ አለኝ፡-
«ወሰዷት። ነፋስ ክንፍ  ላይ ተቀምጣ፣ ከዚያ ህይወት ካበቃበት የመለየት መጨረሻ ሄደች። እውነትን ሰምታ በዋሾነት የፈረጀችው፣ ዓይኗ ክዳ የልቧን ትርክት ወደ  ሰማችው ሃገር ሄደች። ዓይኗን ዓይኔ ላይ ጥላ፣ አፍታ ቆይታ ከንፈሬን በከንፈሯ ነክታ ሄደች። ሻንጣዋ እየጎተተች፣ ሰላም መግባቷን የተመኘኹላት ቃል ጀርባዋን ጨርፎ እግሯ ስር ሲንከባለል፣ ዝቅ ብላ አይታው--- ወደ እዚያኛው ህይወት ሄደች።»
«አልገባኝም» አልኩት
«ማለቴ ሌላ ወድዳ ነው»
አሁንም ሩቅ እያማተረ «ይላሉ» አለኝ፤ እሱ እንዳላመነበት ሁሉ።
ታዲያ ለእኔ ግድ እንደሌለው እያወቅሁ እሱን መከተሌ አይገርምም? ያቺን አዚማም ሙጥኝ እንዳለ ስሩ ስዳክር አያናድድም? ሁሉም ሰው ለፍቅር ቦታ ሊኖረው ይገባል። ሁሉም ምን እንደሚፈልግ ማወቅ አለበት። ምን እንደጎደለኝ አስባለሁ። እርቃኔን መስታወት ፊት ቆሜ ጠይም ጭኔን አያለሁ። እንደ ጦር የተሰበቁ ጡቶቼን እያሸሁ ውበት ያንሳቸው ይሆን እያልኩ አስባለሁ። ቀይ ከንፈሬን፣ ትልልቅ አይኖቼን ደጋግሜ አያለሁ።
እንዳሰበው የተሳካለት ማን ነው? በወደደው የተፈቀረ እድለኛስ ማን ይሆን? ህልም በሚመስል የጨለማ አናት ላይ ቆሜ፣ ይኼን ሰው እከተላለሁ። ይህም ሰው አሸብር ይባላል። እንደ ስሙ በዝምታ አለም የሚያሸብር፣ የወደደውን የሚያሸብር፣ ቤተሰቡን የሚያሸብር ነው። ነገረ ስራው ሁሉ ይደንቃል። ቀኝ ስትሉት ግራ፣ ግራ ስትሉት ቀኝ ነው። ታዲያ ከዚያ ጠጅ ቤት ወጥቶ እቤቴ ድረስ አንኳኩቶ ይመጣል።
ስስ ፈገግታ አይኔ ላይ ጥሎ፣ ሰላም መሆኔን ይጠይቃል። እኔም ቶሎ ወደ ጓዳ ገብቼ ቤት ያፈራውን አቀርብለታለሁ። የሚበላውን እየበላ፣ ወይም የሚጠጣውን እየጠጣ ደግሞ ሰላም መሆኔን ይጠይቀኛል። ደግሞ መጠየቁ እያስገረመኝ፣ ይኼን ጠጅ መተው እንዳለበት፣ ውስጡም እየተጎዳ እንደሆነ እመክረዋለሁ። አሁንም ስስ ፈገግታ አይኔ ላይ ጥሎ ዝም ይላል። ዝምታው ያበግነኛል። አጠገቡ ቁጭ ብዬ አፍጥጬ አየውና፣ ዘልዬ ከንፈሩ ላይ ከንፈሬን አሰፍራለሁ። ታዲያ ወንድነቱ ቶሎ ይሞቃል። በዚያ ጠንካራ መዳፉ ጡቶቼን ያሻቸዋል። ተያይዘን አልጋው ላይ እንወጣለን። አንዳንዴ ይሄን ብቻ ፈልጎ እኔ ጋ የሚመጣ ይመስለኛል። ለምን እንደማያወራ ስጠይቀው፣ አመሌ ነው ይለኛል። #አመልህ አስከፍቶኛል፤ እባክህ ቀይርልኝ; እለዋለሁ። ሳቅ ይልና ዝም ይላል። አሁንም እናደዳለሁ።
እንግዲህ  ፍቅር የያዘኝ ከዚህ ሰው ነው። እንደ አራስ ልጅ እሳሳለታለሁ። እንደ ህፃን እቅፌ ውስጥ ከትቼ ጡቴን ባጠባው ደስ ይለኛል። ጀርባዬ ላይ ታቅፌው እሹሩሩ እያልኩ ባስተኛው  በምን እድሌ። አሸብር አንዳንዴ ያለ እድሜ የገረጀፈ ሽማግሌ፣ አንዳንዴም ያለ እድሜው ህፃን የሆነ ይመስላል። ሁለት ተቃራኒ ማንነቶች ይዞ ዓለም ላይ ያለ ተፃራሪ ነገር የተዛነቀበት ምስኪን ፍጥረት ነው። ሁሌ ለምን ጥቁር ኮፍያና ጥቁር ጃኬት እንደሚያደርግ እጠይቀዋለሁ።
«ለምን እንደ ሃዘንተኛ ጥቁር ነገር ታበዛለህ?»
«ዓለም  የሃዘኖች ሙዳይ ናት። ደስታዬ እኮ በግልፅ የሚታይ ሃዘኔ ነው» ይለኛል።
«ደግሞ ይኼ ምን ማለት ነው?»
«ደስተኛ በመሆኔ ነው ሃዘንተኛ የሆንኩት። ማለቴ ጥቁር ቀለም የነጭ ቀለም ግልባጭ ነው»
«እኔ ምንህም አልገባኝም!»
«እርሺው!»
 አሁን የተናገረው ምኑ ይገባል?  እንዲህ ሲያቃጥለኝ ያድራል። ሁሌም ከጥቂት ነገር በስተቀር ብዙ ነገር አያወራም። እኔም በዝምታው የፍቅር መልኬ ወይቦ ስጠወልግ ይታወቀኛል።
አንድ ሰሞን ጠፋብኝ። እዚያ የሚያዘወትረው ጠጅ ቤት ሄጄ ብጠይቅ ከመጣ ሳምንት እንዳለፈው ነገሩኝ። የሆነው ነገር እንዳለ ብዬ ቤቱ ሄድኩ። የአጥሩን በር አልፌ ቤቱን ማንኳኳት ጀመርኩ። ትንሽ ዘግይቶ በሩን ከፈተው። የታመቃ አየር አፍንጫዬን አፈነኝ። ፀጉሩ ተንጨብርሯል። አዳፋ ነጭ ቲሸርት ለብሶ፣ በዚያ ብጫ ጥርሱ ፈገግ አለ። ግቢም አላለኝም። በፈገግታው ውስጥ የሆነ ደስ የማይል ነገር አየሁ።  ለምን እንደጠፋ ጠየኩት። ትንሽ ለራሱ ጊዜ መስጠት እንዳለበት ቀባጠረ።  አፈር አለና እንድገባ ጠየቀኝ። ስገባ አልጋው ተዘበራርቋል።  አንድ ፎጣ ወንበሩ ላይ ተቀምጧል። ጠረጴዛው ላይ ብዙ መፅሐፎች ወደ ላይ ተደርድረዋል። ቤቱ ለቀናት እንዳልፀዳ ያስታውቃል። በዚያ ላይ  ትንሽ ፉካ ቢኖረውም አልተከፈተም፣ ቤቱ ታፍኗል። ፎጣውን አልጋው ላይ አስቀምጬ ወንበሩ ላይ ቁጭ አልኩ። አይን አይኔን ማየት ጀመረ። አልጋው ደርዝ ላይ ተቀመጠ።
«ስትጠፋ እኮ አስጨነቅኸኝ»
«አንዳንዴ እንዲህ ያደርገኛል። ሁሉም ነገር ይሰለቸኛል። ፍፁም ከሰርካዊ ኑረቴ በተቃራኒው እሆናለሁ። ለምን እንደምኖር አላውቅም። አንዳንድ ነገሮች በጣም ይሰለቻሉ። የምለው ይገባሻል?»
ጭንቅላቴን በአዎንታ ነቀነቅኩ፣ ንግግሩን እንዲቀጥል ዝም አልኩ።
«መኖር ዳገት የሆነብኝ ሰው ነኝ። እውነቱን ንገረኝ ካልሽኝ  ሁሉም ነገር ታክቶኛል። ሁሉም ነገር ሰልችቶኛል። እንጀራ ቆርሶ መብላት ሰልችቶኛል። ድንገት እያዞረ የሚጥለኝ በሽታ ሳይቀር ሰልችቶኛል።  እግዜር ሽርኬ ይመስለኝ ነበር። አሁን አሁን ሳየው ግን ደመኛዬ መስሎ ይታየኛል። ብቻዬን ተጥያለሁ። የሚፈልገኝ ሰው የለም። መዓልት በእኔ ጨልሟል። ህይወት ሁሌም የምትግተኝ እንደ ዝሆን ሃሞት መራራዋን ነው» ዓይኖቹ በጣም ቀልተው ፈጠጡ። የሚናገረው ከመጠን በላይ ስሜታዊ ሆኖ ነው።
«ስለዚህ» አለ፤ «ስለዚህ እራሴን ማዳመጥ አለብኝ። ወጥቼ ስራ መስራት አለብኝ። አዎ! የቀን ስራም ቢሆን መስራት አለብኝ። እድሜዬን ሙሉ የቤተሰብ ተጧሪ ሆኜ መኖር አልፈልግም!  አየሽ ፣ አባትሽ በእርጅና ጊዜው  ደክሞ ያመጣውን እንጀራ አልጋ ላይ ተኝቶ መብላት በጣም ከባድ ነው። እራስሽን እንድትጠዪ ያደርግሻል። እንደኔ መለወጥ የማትችይውን ነገር ለመለወጥ ስትሞክሪ ከራስሽ ጋር ትጣያለሽ»
«ስራማ መስራት እንዳለብህ ብዙ ጊዜ ነግሬሃለሁ።»
«አዎ! አዎ! ነግረሺኛል። ግን አልቻልኩም። ወጥቼ መስራት አልሆነልኝም። ምክንያቱም የለመድኩት ተኝቶ መብላት ነው። ይህም መራራ እንጀራ እንደሆነ የሚያውቀው ያውቀዋል። ቀን ተቀን ተመሳሳይ ህይወት አይሰለችም?  ግብ የሌለው ኑሮ አይታክትም!? ፍቅር አልቦ ልብ’ስ እንደ የመቃብር ዲንጋይ አይከብድም? አንቺን እንኳን ስንቴ አስቀየምኩሽ»
እንደ ዛሬ ብዙ ሲያወራ ሰምቼው አላውቅም።  እንደ እሳት ላንቃ የሚቅለበለብ አንደበት እንዳለው ፈፅሞ አላውቅም ነበር። ምን እንደምለው ጠፋኝ። ዝም ብዬ ላደምጠውም አሰብኩ። ወይም እንዲናገር የአንደበቱ እሳት ላይ  ጋዝ ማርከፍከፍ አማረኝ።
«እኔ የማውቀህ ነበር የሚመስለኝ” አልኩት።
«በፍፁም! ወድጄ አይደለም። ከመሄድ ጋር ቢሄድ ነው ልቤ።  በማጣት ወላፈን ዘወትር  ብነድ፣ የማደርገው ቢጠፋኝ ነው። ብዙ ጊዜ ልወድሽ ሞክሬያለሁ። ግን አንድ ነገር አንቆ እንደያዘኝ አልሆን አለኝ። ከሄደ ሰው ምን ቀረው ልቤ። ያጣውን ዝንተ ዓለም ለምን ያመነዥጋል?  ከጠላው ሰው ምን አለው?»
«አሁን የሚያስፈልግህ መረጋጋት ነው» አልኩት፣ ምንም እንደምለው ጨንቆኝ።
«መረጋጋት አልችልም። ዝምታዬ በጩኸት የታጀበ ነው። ደንቁሬያለሁ። አለም ላይ ፊቴን አዙሬ የት የምደርስ ይመስልሻል? ከዚያ ጠጅ ቤት አልፋለሁ? በፍፁም! እዚያ አምቡላ ስር እንደ ዶሮ ከመንደፋደፍ አላልፍም። አሁን ግን በጣም በጣም ሰልችቶኛል። ሁሉም ነገር ታክቶኛል።»
«ካልተረጋጋህ ምንም ማድረግ አትችልም አሸብር። ወደድክም ጠላህም አማራጭህ አንድ ነው። ተረጋግተህ አስበህ እራስህን መለወጥ። ወጥተህ መስራት። መርሳት ያለብህም ነገር ካለ መርሳት ግዴታህ ይሆናል።
«ሃሃሃሃሃሃሃሃሃሃ.... መርጦ መርሳት፣ መርጦ ማስታወስ ቢቻልማ እንዴት ጥሩ ነበር። አፍሽ ላይ እንደምትናገሪው ሁሉም ነገር ቀላል አይደለም።»
ከዚህ በላይ ላወራ አልቻልኩም። እራሱን እንዲያረጋጋ ነግሬው ተነስቼ ወጣሁ።  ቤቴ ሆኜም ግን የማስበውም የማልመውም ስለ እሱ ነበር። ምን ባደርገው እንደሚስተካከል አስባለሁ። አይኑ ላይ የማነበው ነገር ደስ አላለኝም። አንዳች መጥፎ ነገር ታይቶኛል። ነገር ግን ያ መጥፎ ነገር ምን እንደሆነ ማወቅ አልቻልኩም። አሸብር ለካ በዝምታ ውስጥ ሲሸበር ነበር። ለካ ዝምታው የማይሰማ  ጩኸት ነው።  ለካ እሱነቱን ገና አልተቀበለም። ከእራሱ ጋር ተጣልቷል። ከራሱ ጋር ተፋትቷል። ለካ አሸብር ገና ያላደገ ህፃን ነው። መንፈሱ ግን እንደ ድኩም ሽማግሌ ነው። በጣም በጣም አዘንኩለት።
በዚህ ሁኔታ ሁለት ቀናቶች  አለፉ። አሸብር አሁንም አልመጣም። ውስጤን አንዳች መጥፎ ስሜት ሰቀዘኝ። ድንገት ካለ ብዬ የሚያዘወትርበት ጠጅ ቤት ሄድኩኝ።  እዛም ደርሶ እንደማያውቅ  ሰማሁ። ቤቱ መሄድ ቅፍፍ አለኝ። ድባቴውን እንደ ብርድልብስ  ተጠቅሎ የሚናቸፍ አውሬ እንዳይሆን ሰጋሁ።
የአጥሩን በር እየከፈቱ የሚወጡ ሰዎች አየሁ። ነጠላ አዘቅዝቀው፣ ካፖርት ደርበው ከግቢው እየተግተለተሉ ይወጣሉ። ሁናቴው ስላሰጋኝ ምን እንደተፈጠረ መጠየቅ ፈለግሁኝ። አንድ እናት ሲወጡ አይን ላይን ተያየን።
«ምን ተፈጥሮ ነው፣ እናቴ?» አልኳቸው፣ ፈራ ተባ እያልኩ።
«ውይ ልጅ! አሸብር...» ቃሉን አንጠልጥለው ተዉት።
«አሸብር ምን?»
«ታንቆ ሞተ»


Read 2021 times