Print this page
Sunday, 25 April 2021 00:00

በሰሜን ሸዋ ዞን የተፈጸመው ጥቃትና ያስከተለው ጥፋት

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(0 votes)

 • አጣዬና ኤፍራታ ግድም ወረዳዎች ሙሉ በሙሉ ወድመዋል
        • የአካባቢው ፀጥታ በኮማንድ ፖስት እየተመራ ቢሆንም አሁንም የፀጥታ ስጋት አለ
        • ከ250 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች አስቸኳይ የምግብ እርዳታ ይፈልጋሉ
        • በሺዎች የሚቆጠሩ የአካባቢው ነዋሪዎች ሞትን ሸሽተው በጫካ ውስጥ ተጠልለዋል
                     
            ካለፈው መጋቢት ወር አጋማሽ ጀምሮ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ውስጥ በሚገኙ ወረዳዎች ላይ በተፈጸመ ጥቃት የበርካታ ሰዎች ህይወት ጠፍቷል - ከፍተኛ መጠን ያለው ንብረትም ወድሟል። በጥቃቱ ህይወታቸው ያለፈ ወገኖችን ቁጥር እስካሁን በውል ለመረዳት አለመቻሉንና የሟቾቹን ቁጥር ለማወቅ ጥረት እየተደረገ እንደሆነም ተነግሯል። በአሁኑ ወቅት አካባቢው በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስር ሆኖ በኮማንድ ፖስት የሚመራ ቢሆንም፣ ህብረተሰቡ አሁንም በከፍተኛ የደህንነት ስጋት ውስጥ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል።
የሰሜን ሸዋ ዞን የፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አበራ መኮንን ለአዲስ አድማስ እንደተናገሩት፤ በዞኑ የደረሰውን ጥፋትና በጥቃቱ ህይወታቸውን ያጡ ወገኖቻችንን ቁጥር ለማወቅ እየተሰራ ሲሆን እጅግ በርካታ ወገኖች በጥቃቱ ህይወታቸወን አጥተዋል። አካባቢው በአሁኑ ወቅት በኮማንድ ፖስት የሚመራ መሆኑን ያመለከቱት የጸጥታ ቢሮ ኃላፊው፤ በጥቃቱ የሞቱና ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች የመለየቱ ስራ ሲጠናቀቅ መረጃው በኮማንድ ፖስቱ በኩል ይገለጻል ብለዋል። በጥቃቱ ከ253 ሺ በላይ ነዋሪዎች ከቀያቸው መፈናቀላቸውን የጠቆሙት አቶ አበራ፤ እነዚህ ተፈናቃይ ወገኖች በደብረ ብርሃን፣ ደብረሲና፣ መሀል ሜዳና አንጾኪያ መኮይ ውስጥ በሚገኙ ት/ቤቶችና የእምነት ቦታዎች ወስጥ ተጠልለው እንደሚገኙና በሺዎች የሚቆጠሩትም አሁንም ድረስ በጫካ ውስጥ ተሸሽገው እንዳሉ ተናግረዋል።
የሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳዳሪው አቶ ታደሰ ገ/ጻዲቅ በተለይ ለአዲስ አድማስ እንደተናገሩት የደረሰው ጥቃት ድንገተኛና  እጅግ ዘመናዊ በሆነ መሳሪያና በተደራጀ ሃይል የታገዘ በመሆኑ የደረሰው ጥፋት የከፋ ሆኗል ብለዋል። በጥቃቱ ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች የመለየቱና በአካባቢው ዳግም ተመሳሳይ  ጉዳት እንዳይደርስ የመከላከሉ ስራ እየተሰራ መሆኑንም አስተዳዳሪው ገልፀዋል። የመከላከያ ኃይል ወደ ስፍራው ከመግባቱና አካባቢው በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስር ሆኖ በኮማድ ፖስት መተዳደር መጀመሩን ተከትሎ፤ በአሁኑ ወቅት አንጻራዊ ሰላም እንደሚታይም ተናግረዋል።
የሰሜን ሸዋ ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽ/ቤት ሃላፊው አቶ ወርቃለማሁ ኮስትሬ በበኩላቸው፤ በጥቃቱ ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉት ከ253 ሺ በላይ ወገኖች አስቸኳይ የምግብ እርዳታ እንደሚሹ ጠቁመው  የአካባቢው ማህበረሰብ  ተፈናቃይ ወገኖቹን ለመርዳት እያሳየ ያለውን ከፍተኛ ርብርብ ሊደነቅ የሚገባው ነው ብለዋል። ዞኑ በአብዛኛው ከፍተኛ ጉዳት የዴረሰበት መሆኑን ያመለከቱት አቶ ወርቃለማሁ፤ በተለይም አጣዬና ኤፍራታ ግድም ወዳዎች በጥቃቱ ሙሉ በሙሉ ወድመዋል ብለዋል። በነዚህ ወረዳዎች ይኖሩ የነበሩ ወገኖችን የአካባቢው ሰላም ተረጋግጦ ወደ ቀያቸው ተመለሱ ባል እንኳን የሚገቡበት ቤት የላቸውም ብለዋል። እነዚህን ወገኖች ወደ ቀያቸው የመመለሱ ተግባር በመንግስት ብቻ የሚቻል ባለመሆኑ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ይድረስልን  ሲሉ ጥሪያቸያውን አሰምተዋል።
ኤፍራታና ግድም ወረዳ ሞላሌ ቀበሌ ውስጥ ይኖሩ የነበሩት አቶ ቢሆነኝ ካሳ ከቀናት በፊት አቅራቢያቸው ከምትገኘው ነጌሳ ቀበሌ ውስጥ በሚኖሩ ወገኖች ላይ የደረሰው ጥቃትና የተፈጸመው ስቅጣጭ ወንጀል እንቅልፍ ነስቷቸው መሰንበቱን ይናገራሉ። “ሰው ወልዶ ከብዶ ካረጀበት፣ ክፉ ደጉን ካየበት ቀዬ ድረሰ መጥተው፣ እንዲህ አይነት ውርጅብኝ የሚያወርዱበት ምን አይነት ፍጡራን ናቸው” ሲሉ በሃዘን ስሜት ይጠይቃሉ። ከነጌሳ ቀበሌ ተፈናቅለው  ወደ ቀዬአቸው ለመጡ ወገኖቻቸው ቤት ያፈራውን እያቃመሱና ከመኝታቸው እያስተኙ ነው የሰነበቱት። ሚያዚያ 11/2013 ዓ.ም ዳግም ወደ አካባቢው የዘመተው ታጣቂ ቡድን ከሞት ሽሽት የተጠለሉበትን ሞላሌ ቀበሌ በየጥይት ዝናብ ያዘንብበት ጀመረ።
የቻለ እግሩ ወደመራው ሽሽቱን ተያያዘው የደከመ የጥይት እራት ሆኖ አካባቢው በሬሳና በሚቃጠሉ ቤቶች ሽታ ተሞላ። አቶ ቢሆነኝ ይህንን ወቅት የሚያስታውሱት እጅግ በከፋ ሃዘንና ቁጭት ነው። በቤታቸው ተጠልለው ከነበሩት ሰባት የጎረቤት ቀበሌ ስደተኞች አምስቱና ባለቤታቸው በጥቃቱ ህይወታቸውን አጥተዋል።
ሁለት ልጆቻቸው የት እንደሉ አሁንም አያውቁም። እሳቸው ግን ራሳቸውን መንዝ ወረዳ ውስጥ ማግኘታቸውንና ምን እንደተፈጠረ በምን አይነት ሁኔታ ውስጥ እንዳለፉ እንደማያስታውሱ ይናገራሉ። ባለቤታቸው ሲወድቁ ማየታቸውን ግን እንደሚያስታውሱ ይገልጻሉ።
በአሁኑ ወቅት መንዝ ወረዳ ውስጥ በሚገኝ መጠለያ ውስጥ የሚገኙት አቶ ቢሆነኝ፣ በአካባቢው ማህበረሰብ በሚደረግላቸው ድጋፍና እንክብካቤ ራሳቸውን በህይወት ማቆየት መቻላቸውን ነው የሚናገሩት።
በአካባቢው ጥቃት ሲፈጽሙ የነበሩት  የተደራጁ፣ ዘመናዊ መሳሪያን የታጠቁ፣ ለሰው ልጅ ፍጹም ሃዘኔታ የሌላቸው አረመኔዎች ነበሩ ያሉት በሰሜን ሸዋ ዞን ውስጥ በምትገኘው ቀወት ወረዳ ኩሪበር ቀበሌ ውስጥ ነዋሪ የነበሩትና በጥቃቱ ሁለት ልጆቻቸውንና ታናሽ ወንድማቸውን እንዳጡ የሚገልጹት አቶ ተስፋሁን ተመስገን፤ ጥቃት የተፈጸመው ባለፈው አርብ እንደነበርና በጥቃቱም በርካታ ሰዎች መሞታቸው ተናግረዋል። እሳቸው በሚኖሩበት ቀበሌ ሰዎች ቢገደሉም ቤቶች ግን አልተቃጠሉም ብለዋል። ከኦሮሞ ብሔር አስተዳደር ጋር ተጎራብቶ በሚገኘው በዚህ ቀበሌ ውስጥ ጥቃቱ በሚፈጸምበት ወቅት ነዋሪዎቹን ለማዳን ከፍተኛ ጥረት ያደርጉ የነበሩ የኦሮሞ ብሔር ተወላጆች እንደነበሩም አስተውለዋል። ከጥቃቱ መፈጸም በኋላ ከሚኖሩባቸው ወረዳዎች ሸሽተው በርካታ የቀበሌው ነዋሪዎች አሁንም ድረስ እዚያ እንደሚገኙ ጠቁመው በአቅራቢያ በሚገኙ ጫካዎች ውስጥም በርካታ ቁጥር ያላቸው የአካባቢዋ ነዋሪዎች ተደብቀው እንደሚገኙ ተናግረዋል።
በዞኑ የተፈጸመው ጥቃት ክልሉን አስፍቶ ወደ ሸዋ ሮቢትም የተዛመተ ሲሆን ባለፈው ቅዳሜ የሸዋ ሮቢቷ  ዙጢ ቀበሌ የጥቃቱ ሰለባ ሆናለች።
በአካባቢው በነበረው የጸጥታ ስጋት በርካታ የሸዋ ሮቢት ከተማ ነዋሪዎች ቤታቸውን ጥለው ወደ አቅራቢያ ወረዳዎች የሸሹ ሲሆን ጥቃት ፈጻሚዎቹ ዙጢ ቀበሌ ውስጥ ባገኟቸው ሰዎች ላይ ጥቃቱን ፈጽመው  አካባቢውን ጥለው ሄደዋል። የመከላከያ ኃይል እሁድ ምሽቱን ወደ ስፋራው በመድረሱ ጥቃት ፈጻሚዎቹ ወደ ሸዋ ሮቢት ሌሎች አካባቢዎች ሊያደርጉት የነበረውን እንቅስቃሴ አቋርጠው መሄዳቸውን ከአካባቢው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ሚዚያ 10 ቀን 2013 ዓ.ም ምሽት ላይ የመከላከያ ሰራዊት ወደ ሰሜን ሸዋ ዞን ያቀና ሲሆን ከደብረሲና ጀምሮ እስከ ደቡብ ወሎ ዞን ኮምቦልቻ ከተማ ድረስ ያለውን አካባቢ በዕዝ ማእከል (በኮማንድ ፖስት) ውስጥ እንዲሆኑ ተደርጓል። በእነዚህ አካባቢዎች በ20 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ መሳሪያ ይዞ መንቀሳቀስ እንደማይቻል የሚደነግግ አዋጅ ወጥቶ ተግባራዊ ተደርጓል።
የአካባቢው ባለስልጣናት ከመኖሪያ ቤታቸው የተፈናቀሉ ወገኖችን ለመርዳትና ወደ መኖሪያቸው ለመመለስ ጥረት የተደረገ ነው ቢሉም፤ ከመኖሪያቸው ተፈናቃዮች ግን ሁኔታው እጅግ የተለየ መሆኑን  የአካባቢው ማህበረሰብ በሚያደርግላቸው  ድጋፍ ህይወታቸው መቆየቱን ፣ እጅግ በከፋ ረሃብ፣ እርዛትና ስቃይ ውስጥ እንዳሉ ይናገራሉ። እኛ የተፈናቀልነው ከቆላማውና ሞቃት ከሆነው አካባቢ ሆኖ አሁን የደብረ ብርሃን ብርድን መቋቋም አቅቶን ልጆቻችን ለከፋ በሽታ እየተዳረጉብን ነው ያሉት ከአንጾኪያ ወረዳ የተፈናቀሉት አቶ ስዩም ታደለ፤ “ሁሉም ወገን ይድረስልን፤ ከጥይት ሞት ሸሽተን በረሃብና በእርዛት ልንሞት ነው ብለዋል።
ተፈናቃዮችን የመርዳቱና መልሶ የማቋቋሙ ስራ የሁሉንም ዜጋ እርብርብ የሚጠይቅ ተግባር መሆኑን  የዞኑ አደጋ መከላከልና  ምግብ ዋስትና ጽ/ቤት ሃላፊ ተናግረዋል።

Read 3017 times