Saturday, 01 May 2021 12:05

በአሜሪካ የምስራቅ አፍሪካ ልዩ ልኡክ ስለ ኢትዮጵያ የሰጡት አስተያየት እያነጋገረ ነው

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

   የትግራይ ቀውስ እልባት ካላገኘ ኢትዮጵያ ከሶርያ የባሰ ችግር ሊገጥማት ይችላል ብለዋል
                                
              በአሜሪካ መንግስት በቅርቡ የምስራቅ አፍሪካ ልዩ ልኡክ ሆነው የተሾሙትና በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ ይመጣሉ የተባሉት ጄፍሪ ፌልትማን፤ ስለ ኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ የሰጡት  አስተያየት እያነጋገረ ነው። ልዑኩ በትግራይ ያለው ቀውስ እልባት ካላገኘ ኢትዮጵያን ከሶርያ የባሰ ችግር ውስጥ ይከተታል ብለዋል።
የአዲሱ  የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር፣ የምስራቅ አፍሪካ ልዩ ልዑክ  ሃላፊው ፌልትማን፤ ግጭቱ ከትግራይ አልፎ ለምስራቅ አፍሪካም የከፋ አደጋ የደቀነ ነው ብለዋል- “ከፎሬን አፌርስ” ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ።
በአሁኑ ወቅት ጦርነቱን ተከትሎ በቀጠናው ከፍተኛ ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶች እየተፈጸሙ መሆኑን የጠቆሙት ሃላፊው፤ የጦር ወንጀል ተፈጽሟል የሚሉ ክሶችም በስፋት እየቀረቡ ነው። ይህም የአለምን ትኩረት ስቧል ብለዋል።
የትግራይን ቀውስ በሶርያ ከተፈፀመውና በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የሃገሪቱን ዜጎች ሃገር አልባ ካደረገው ግጭት ጋር ያመሳሰሉት ኃላፊው፤ በሶሪያ በትንሹ የተጀመረው ጦርነት ነው አገሪቷን ረብ የለሽ ያደረጋት ብለዋል።  “የእርስ በርስ ጦርነቱ የብዙዎችን ህይወት ያጠፋ ሲሆን  በተፈጠረው ክፍተትም አካባቢው የአለማቀፍ አሸባሪዎች መፈልፈያ ሊሆን በቅቷል ያሉት የልዑኩ ሃላፊ፤  በሶሪያ የተከሰተው ሁኔታ በኢትዮጵያ የማይከሰትበት ምክንያት አይኖርም” ብለዋል።
ሶርያ ከጦርነቱ በፊት 22 ሚሊዮን ዜጎች ያሏት፣ በኢኮኖሚ የዳበረችና ፣ የደስተኛ ዜጎቿ ባለቤት እንደነበረች ያስታወሱት ሃላፊው ፤ በትንሹ የበተጀመረው ጦርነት መቋጫ አጥቶ አሁን ዜጎቿ በዓለም ላይ እንደ አሸዋ ተበትነዋል ብለዋል።
ኢትዮጵያም 110 ሚሊዮን ዜጎች እንዳሏት የጠቀሱት ሃላፊው፤ በትግራይ ያለው ቀውስ በጊዜ መቋጫ ሳይበጅለት ወደ ሌሎች አካባቢዎች የመዛመት እድል እንዲያገኝ ከተደረገ በሶሪያ ያጋጠመውን የሚያስንቅ ቀውስ ሊፈጠር እንደሚችል ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ የምትገኝበት ቀጠና ግጭት የበዛበትና የፀና የሰላም መሰረት የሌለው መሆኑን የጠቆሙት ልዑኩ፤ በአሁኑ ወቅት ይሄ ቀጠና በተደራራቢ ቀውሶች ውስጥ የሚገኝ እጅግ አስቸጋሪው የአለማችን ክፍል ነው ብለዋል። ሃገራቸው አሜሪካ ደግሞ በውጭ ገዳይ ፖሊሲዋ ቀጠናውን እንደ ትልቅ ስትራቴጂክ አካባቢ እንደምታየው በመግለጽም፤  ለትግራይ ቀውስ ፈጣን መፍትሄ ማበጀት እንደሚገባ መክረዋል።
በአሁኑ ወቅት ይህን ወሳኝ ቀጠና እየተፈታተኑ ያሉ ውጥረቶችና ግጭቶች ያሏቸውንም ሃላፊው ተንትነዋል። ዋነኛው ቀውስ በትግራይ ያለው ጦርነት መሆኑን፣ ይህም ከኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይነት አልፎ ኤርትራም በወታደሮቿ በቀጥታ ተሳታፊ እንደሆነችበት በመጠቆም ይህም ሁኔታውን አደገኛና ውስብስብ ያደርገዋል ብለዋል።
የኤርትራ ሰራዊት በጦርነቱ ከመሳተፉም ባሻገር በመጠነ ሰፊ  የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ፣ እንዲሁም በሰላማዊ ሰዎች ግድያ የሚወነጀል መሆኑ፣ ቀጣዩን ሁኔታ አስከፊ እንደሚያደርገው ተናግረዋል።
ሌላኛው ኢትዮጵያን ማዕከል አድርጎ የሚገኝ የቀውስ ስጋት ደግሞ የሱዳን አለመረጋጋትና በኢትዮጵያ ድንበር አካባቢም ትንኮሳ መፈጸሟ ነው ይላሉ የልኡኩ- ሃላፊ።  ሁለቱ ሃገሮች ወደ ጦርነት የሚገቡ ከሆነ ደግሞ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በጦርነቱ የሚሳተፉ አካላት ይበዛሉ። ይህም አካባቢውን ጎራ የለየ የጦርነት ማካሄጃ ሊያደርገው ይችላል ብለዋል።
እንደ ሱዳን ሁሉ መንግስታቸው  በቅጡ መሬት ያልረገጠላቸውና፣ ፅኑ መሰረት ያልያዘላቸው ሌሎች አገራት እንዳሉም ይጠቅሳሉ። ደቡብ ሱዳንና ሶማሊያም። እኒህም ተመሳሳይ ስጋት አለባቸው ይላሉ-ሃላፊው።
“ወዲህ ደግሞ የህዳሴ ግድብ ውዝግብ አለ፤ ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ የዚህ ስጋት ዋነኛ ባለ ድርሻ ቢሆኑም፤ ፈተናው የሚጸናው ግን በኢትዮጵያ ላይ ነው” ብለዋል- ሃላፊው በቃለ ምልልሳቸው።
ልኡካቸው ከእነዚህ ሁሉ የቀጠናው ችግሮች ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እንዲሻሻሉ ለማድረግ የሚሰራው የትግራይ ግጭት በሚቆምበት፣ የሱዳንና የኢትዮጵያ የድንበር ውዝግብ በሰላም በሚፈታበት እንዲሁም ከህዳሴው ግድብ ጋር በተያያዘ ያሉ ውጥረቶች በውይይትና ድርድር በሚፈቱበት ሁኔታ ላይ ይሆናል ብለዋል።
ይህን ሂደት ለማስጀመርና ከሃገራቱ መሪዎች ጋር ለመነጋገርም በቅርቡ ወደ ቀጠናው እንደሚያመሩ በቃለ ምልልሳቸው ላይ አውስተዋል።
በተለይ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድና ከኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሣያስ አፈወርቂ ጋር በጉዳዩ ላይ ጠንካራ ውይይት ማድረግ እንደሚሹ ነው ፌልትማን የተናገሩት።
“ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አንድነቷ የተጠበቀ የተዋሃደችና ጠንካራ  ኢትዮጵያን ማየት ይፈልጋሉ የሚል  ግምት አለኝ” ያሉት ሃላፊው “ኢትዮጵያ እንድትፈራርስ አይፈልጉም፤ ውይይታችንም  ይህን ማዕከል ያደረገ ይሆናል” ብለዋል።
የተባበሩት መንግስታት ዲፕሎማት ሳሉ ከኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር ተገናኝተው እንደነበር ያወሱት ሃላፊው ፕሬዚዳንት ኢሳያስን ሃሳባቸውን እንዲለውጡ ወይም ስሌታቸውን እንዲያስተካክሉ ማድረግ እንደማይቻል መረዳታቸውን ጠቁመው፤ ይሁን እንጂ ለአካባቢው መረጋጋት ይጠቅማል ያልነውን ከመናገርና ከማግባባት ወደ ኋላ አንልም  ሲሉ አቋማቸውን ገልጸዋል።
በተለይ የትግራይ ቀውስን በተመለከተ የተሳካና ውጤት የሚያመጣ ውይይት እንደሚኖረኝ ተስፋ አደርጋለሁ የሚሉት ፌልትማን “የሶስቱ ሃገራት ልዩነት የማይፈታ ይሆናል ብዬ አላስብም፤ልዩነታቸውን ያጠባሉ የሚል ተስፋ  አለኝ” ብለዋል።

Read 1470 times