Saturday, 01 May 2021 12:13

የአጣዬውን ውድመት የሚያጣራ ቡድን ወደ ስፍራው ተላከ

Written by  መታሰቢያ ሳሣዬ
Rate this item
(2 votes)

      ካለፈው መጋቢት ወር አጋማሽ ጀምሮ በሰሜን ሸዋ ዞን አጣዬና አካባቢዋ ነዋሪዎች ላይ የተፈጸመውን አሰቃቂ የግድያ ወንጀልና የደረሰውን ቁሳዊ ውድመት የሚያጣራ የምርመራ ቡድን ወደ ስፍራው ተላከ። የተላከው ቡድን ከፌደራልና ከአማራ ክልል ጠቅላይ አቃቢ-ህግና ከፖሊስ አባላት የተውጣጡ መሆኑንም የአማራ ክልል ጠቅላይ አቃቢ ህግ አስታውቋል።
ይህም በዞኑ በአጣዬና አካባቢው የተፈጸመውና በሰው ህይወት መጥፋት፣ በአካል መጉደል፣ በንብረት መውደምና በሰዎች መፈናቀል ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሰው ወንጀል ተራ ግጭት ሳይሆን ለዘመናት የተገነባ ከተማን ያወደመ አስከፊ የወንጀል ድርጊት መሆኑንም የክልሉ ጠቅላይ አቃቢ-ህግ አስታውቋል። ወንጀሉን ለማጣራት የተቋቋመው ቡድን ወደ ስፋራው ማምራቱንና ምርመራ መጀመሩም ተገልጿል።
በደረሰው ሰብአዊና ቁሳዊ ሀብት ውድመት ተሳታፊ የሆኑ አካላትን በቁጥጥር ስር በማዋል ለህግ የማቅረብ ስራም እንደሚከናወንና የምርመራ ቡድኑ በማጣራት ሂደቱ ያገኘውን ውጤት በተከታታይ ለህዝቡ እንደሚገለጽ ተጠቁሟል።
ካለፈው መጋቢት ወር አጋማሽ ጀምሮ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ውስጥ በሚገኙ ወረዳዎች ላይ በተፈጸመ ጥቃት የበርካታ ሰዎች ህይወት የጠፋ ሲሆን ከፍተኛ መጠን ያለው ንብረትም መውደሙ አይዘነጋም።


Read 1614 times