Sunday, 02 May 2021 00:00

ኢዜማ የብሔራዊ ደህንነት ስጋቶችን ይፋ አደረገ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

  ኢዜማ 99 ገፆች ባሉት የዘንድሮ ምርጫ መወዳደሪያ ቃል ኪዳን ሰነዱ (ማኒፌስቶ) የሃገራዊ ደህንነት ስጋቶች ያላቸው ስምንት የሃገር ውስጥ ጉዳዮችና አምስት የውጭ ደህንነት ስጋቶች በዝርዝር አስቀምጧል፡፡
ኢዜማ ብሔራዊ የደህንነት ስጋቶችን የውጭና የሃገር ውስጥ በማለት በሁለት ከፍሎ ያቀረበ ሲሆን የሃገር ውስጥ ደህንነት ስጋቶች በሚል ያስቀመጣቸው መንግስታዊ  የፖለቲካ ሰርአቱ የተዋቀረበት መንገድ፣ የዘውግ ፅንፈኝነት የክልሎች ልዩ ሃይሎች ደህንነት፣ ኢኮኖሚያዊ አሻጥሮችና ህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር እንዲሁም የበይነ መረብ ወንጀሎች ናቸው፡፡ በመጀመሪያ ከስጋት የተቀመጠው የመንግስታዊ ስርዓት መዋቀሩ ሲሆን ይህም ዘርን መሰረት ባደገ መልኩ ክልሎች መዋቀራቸው በተለያዩ “ዘውግ” ማህበረሰቦች መካከል መቃቃርና ግጭት እንዲቀሰቀስ እንዲሁም ልዩነቶች እንዲስፋፉ በማድረግ እጅግ በርካታ የሆኑ ዜጎችን በከፍተኛ አደጋ በማጋለጥ በሃገሪቱ ላይ ከፍተኛ የብሔራዊ ደህንነት ስጋት ሊደቀን ይችላል ብሏል፡፡
ሁለተኛው ስጋት፤ የዘውግ ፅንፈኛ ሲሆን በቅርቡ እያቆጠቆጠ ያለው የሃይማኖት ፅንፈኝነት በአሁኑ ወቅት ከምናልባታዊ የብሔራዊ ደህንት ስጋት ወደ ተጨባጭ የደህንነት ስጋት እየተቀየረ ይገኛል ይላል ኢዜማ በሠነዱ፡፡
ሶስተኛው የሃገር ውስጥ ደህንነት ስጋት፣ የክልል ልዩ ሃይሎች የተደራጀ የጦር አቅም  እየፈጠሩ ከሌሎች ክልሎች ጋር የመጋጨት ሁኔታን ያስቀምጣል፡፡
አራተኛው ድህንነት ሲሆን ድህነት በብዙ ችግሮች ምክንያት በመሆኑ በተለይ ከፍተኛ የወጣት ስራ አጥነትና የኑሮ ውድነት ተከትሎ ወደ ብሔራዊ ደህንነት ስጋት ደረጃ አየደረሰ ነው ይላል ኢዜማ፡፡
በአምስተኛ ደረጃ የተቀመጠው የኢኮኖሚ አሻጥሮችና ህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር ሲሆን በ6ኛ ደረጃ ደግሞ የበይነ መረብ (ሳይበር) ወንጀሎች እየተበራከቱ መምጣት፣ በብሔራዊ ደህንት ስጋትነት ያስቀምጣል-በሠነዱ
በ7ኛ ደረጃ የብሔራዊ ደህንት አስፈፃሚ አካልት ደካማ የስራ አፈፃፀምና የአቅም ችግርን የሚያስቀምጠው የኢዜማ ሰነድ፤ በ8ኛ ደረጃ የወደብ አለመኖርን ያስቀምጣል፡፡ ሀገሪቱ በአንድ ወደብ ላይ ብቻ ጥገኛ በመሆኗ ለጎረቤት ተፅዕኖ ተጋላጭነት ዳርጓታል፤ ይህም የብሔራዊ ደህነት ስጋት ውስጥ ሊከቱን የሚችሉ ተጨባጭ የደህንነት ስጋቶች ናቸው ይላል ኢዜማ
ኢዜማ በዚህ የቃል ኪዳን ሰነዱ ከውጭ ሊያጋጥሙ የሚችሉ የብሔራዊ ደህንት ስጋች ያላቸው አምስት ዋነኛ ስጋቶችን ይዘረዝራል፡፡
እነዚህም አንደኛ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ የሚገኙ ሃገራት ተለዋዋጭ አሰላለፍ የሚከተሉ  መሆኑ፤ ሁለተኛ ከሌሎች ሃገራት ጋር ከምንጋራቸው የተፈጥሮ ሃብቶች ጋር በተያያዘ ጠላት ሆነው ሊነሱ የሚችሉ ሃጋራት መኖራቸው ሶስተኛ በአፍሪካ ቀንድ የፈረሱ የተጋላጭ ደረጃቸው ከፍተኛ የሆኑና ባህሪያቸው ሊገመት የማይችል ሀገራት የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት በቀጠናው ላይ ግልጽ የሆነ ፍላጎት ያላቸው መሆኑ፣ በአምስተኛ ደረጃ በቀጠናው ድንበር ተሸጋሪ ወንጀሎች እንዲስፋፋ ምቹ ሁኔታ መኖሩ የሚሉትን በስጋትነት  አስቀምጧል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ከሰሞኑ የኢዜማ ሰነድ ነው በሚል  በማህበራዊ ድረ ገፆች ላይ የተሰራጨውና ዝርዝር የብሔራዊ ደህንነት ስጋቶች የሚገልፀው ባለ 17 ገፅ ሰነድ፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች በስም እየተቀሰ የሚፈርጅ ሲሆን  ኢዜማ  በጉዳዩ ላይ በሰጠው መግለጫ፤ “ሰነዱን አላውቀውም፤ የኔ አይደለም” ብሏል፡፡

Read 12087 times