Sunday, 02 May 2021 00:00

በኮሮና ክትባት ሳቢያ ምንም የደረሰ ጉዳት እንደሌለ ጤና ሚኒስቴር ገለፀ

Written by  መታሰቢያ ሳሣዬ
Rate this item
(1 Vote)

  በሀገራችን  ባለፈው መጋቢት 4 የተጀመረው አስትራዚንክ የተባለ የኮሮና ክትባት ለደም መርጋትና ለሌሎች የጤና ችግሮች ይዳርጋል መባሉ ፈጽሞ ከእውነት የራቀ መሆኑን፤ በኢትዮጵያ ክትባቱን በወሰዱ ሰዎች ላይ እስካሁን  ያጋጠመ አንዳችም የጤና እክል አለመኖሩን ጤና ሚኒስቴር ገልጿል።
በኢትዮጵያ እየተስፋፋ የመጣውን የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ለመከላከል መንግስት የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደ መሆኑን ያመለከተው የሚኒስቴሩ መረጃ የኮቪድ መከላከያ ፕሮቶኮል በማዘጋጀትና ዜጎች እንዲተገብሩ በማድረግ ስርጭቱን ለመከላከል ጥረት እየተደረገ መሆኑንም አመልክቷል።
ወረርሽኙን ለመከላከል በሚደረገው ጥረትም በኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባስልጣን ፈቃድ የተሰጣቸው አስትራዚንክና ሳይኖፋርም የተባሉ ሁለት ክትባቶችን በማስገባት ለህብረተሰቡ በመስጠት ላይ ይገኛል።
በዚህ መሰረትም ክትባቱ የጤና ባለሙያዎችና ለቫይረሱ ተጋላጭ ናቸው ተብለው ለተለዩ የህብረተሰብ ክፍሎች እንዲሁም እድሜያቸው ከ60 ዓመት በላይ የሆኑ ዜጎችና እድሜያቸው ከ50 እስከ 60 ዓመት ሆኖ ተጓዳኝ የጤና ችግር ላለባቸው ሰዎች እየተሰጠ ይገኛል።
ከክትባት አሰጣጡ ጋር በተያያዘም ፤በአንዳንድ ቦታዎች ከተቀመጠው የእድሜ ገደብ ውጪ ላሉ ሰዎች ክትባቱ እየተሰጠ መሆኑን ጥቆማ እያደረሰው መሆኑንና ክትትል በማድረግ ላይ እንደሆነ ጤና ሚኒስቴር አመልክቷል።
እንደ ጤና ሚኒስቴር መረጃ  እስከ አሁን 1 ሚሊዮን 71 ሺ 485 ሰዎች ክትባቱን ወስደዋል። ለእነዚህ የመጀመሪያውን ዙር ክትባት የወሰዱ ሰዎች ሁለተኛውን ዙር ክትባት ለመስጠት ዝግጅት በመደረግ ላይ ነው ተብሏል። ለዚህም 5 ነጥብ 5 ሚሊዮን የክትባት ዶዝ ከለጋሽ አገራት ይገባል ተብሎ እንደሚጠበቅ መረጃው አመልክቷል።
በተያያዘ ዜናም፤ በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ መገኘቱ ከተረጋገጠ ወዲህ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር ከሩብ ሚሊዮን ማለፉ የታወቀ ሲሆን። ምርመራ ከተደረገላቸው ከ2 ሚሊዮን 568 ሺ 346 ሰዎች መካከል ነው ሩብ ሚሊዮኑ በቫይረሱ መያዛቸው የታወቀው። ይህም ሀገሪቱን በአፍሪካ ሀገራት  ከግንባር ቀደምቶቹ ረድፍ ያስቀምጣታል።
በአሁኑ ጊዜ 55 ሺ 223 ሰዎች ቫይረሱ ያለባቸው ሲሆን 196 ሺህ 424 የሚሆኑት ከበሽታው አገግመዋል። 3 ሺህ 639 ሰዎች ደግሞ በቫይረሱ ሳቢያ ህይወታቸውን ማጣታቸወን የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።
የአፍሪካ በሽታዎች መከላከያና መቆጣጠሪያ ማእከል መረጃ እንደሚያመለክተው ከደቡብ አፍሪካ፣ ከሞሮኮና፣ ከቱኒዚያ ቀጥሎ” ኢትዮጵያ በርካታ ቫይረሱ የተገኘባት 4ተኛ ሀገር ሆናለች።

Read 10756 times