Print this page
Sunday, 02 May 2021 00:00

ግብፃውያን በኢየሩሳሌም ዴር ሱልጣንን ወረሩ

Written by  መታሰቢያ ሳሣዬ
Rate this item
(7 votes)

     የኢትዮጵያ ባንዲራን አውርደዋል “ግብፆች ጥሰው ገብተው የያዙትን ቦታ ለቀው እንዲወጡ ተደርጓል”
                   
                   በቅድስት እየሩሳሌም በሚገኘውና የኢትዮጵያውያን ይዞታ በሆነው የዴር ሱልጣን ገዳም ላይ ግብፆች ከትላንት በስቲያ ድንገተኛ ወረራ ፈፀሙ። ወራሪዎቹ ወደ ገዳሙ በሃይል በመግባት የተሰቀለውን የኢትዮጵያ ባንዲራ በማውረድ፣ የራሳቸውን ባንዲራ ለመስቀል ሙከራ አድርገዋል፡፡
የጠቅላይ ቤተ-ክህነት የውጪ ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ መምህር ዳንኤል ሠ/ሚካኤል ግብፆች በየዓመቱ በትንሳኤ ወቅት ገዳሙን የመረበሽ ነገር እንደሚያደርጉ ገልፀው አብዛኛውን ጊዜም በትንሳኤ ዕለት ሌሊት ድርጊቱን ይፈፅሙ ነበር ብለዋል። ይህ የአሁኑ ግን ለየት ባለ ሁኔታ የተፈጸመ መሆኑንና በአሁኑ ወቅት ረብሻው ሙሉ በሙሉ መቆሙን ተናግረዋል። ምናልባትም የትንሳኤ  ዕለት ሌሊት ረብሻ ሊያስነሱ ይችሉ ይሆናል የሚል ስጋት እንዳለና ለዚህም ጥንቃቄ መደረጉን ተናግረዋል።
ብፁህ አቡነ እንባቆም የኢየሩሳሌም ገዳማት ሊቀ ጳጳስና የገዳማቱ ዋና መጋቢ አባ ዘበአማን ሳሙኤል ከአበው መነኮሳት ጋር በመሆን ለምዕመናኑ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ጥሪው ሰምተው የተሰባሰቡት ኢትዮጵያውያንና የገዳሙ  ኃላፊዎች በጋራ በመሆን ገዳሙን  ከግብፆች ሲከላከሉ አድረዋል ነው የተባለው፡፡
በማግስቱም የእስራኤል የአገር ውሰጥ ምክትል የደህንት ሚኒስቴር የሆኑት ትውልደ ኢትዮጵያዊው አቶ ጋዲ ይሻርከን የኢትዮጵያን ይዞታ ጥሰው ገብተው ረብሻ በመፍጠር የሞከሩትን ግብፃውያን በአስቸኳይ ከያዙት የኢትዮጵያ ግዛት ለቀው እንዲወጡ ማድረጋቸውን ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
ስፍራው በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ ጥበቃ ላይ እንደሚገንም ለማወቅ ተችሏል፡፡


Read 12193 times