Saturday, 01 May 2021 12:28

ይቅርታ እናደርጋለን፤ ነገር ግን አንረሳም (We forgive but we don’t forget)

Written by 
Rate this item
(8 votes)

 አንዳንድ ተረት ተደጋግሞ ካልተነገረን አንጀት አይደርስም።
የሚከተለውን ተረት ከአመታት በፊት ተርከነዋል። ዛሬም ይሄው እንተርከዋለን።  ትምህርታዊነቱ ደግ ነው ብለን ነው። እነሆ!
ከእለታት አንድ ቀን ሌሊት በጠፍ ጨረቃ ሶስት አህዮች ሳር ይግጣሉ።
እንዳጋጣሚ የተራቡ ጅቦች በዚያው ገደማ ያልፉ ኖሮ አህዮቹን አዩአቸው። ከበቧቸውና “ለመሆኑ ማንን ተማምነው ነው በጠፍ ጨረቃ በኛ ግዛት እንዲህ እየፈነጩ ሳር የሚግጡት? ችሎት ተቀምጠን እንጠይቃቸው” ብለው ጅቦቹ ለዳኝነት ተሰየሙ።
የመጀመሪያዋ አህያ ቃል ልትሰጥ መጣች። የመሃል ዳኛው፤ “እሜቴ አህያ፣ ለመሆኑ ማንን ተማምነሽ ነው በኛ ግዛት በጠፍ ጨረቃ ሳር የምትግጭው?”
አህያይቱም፡- “ፈጣሪዬን አምላኬን ተማምኜ ነው፤በእኔ ላይ ጉዳት የሚያደርሱን ሁሉ ፈጣሪዬ ይበቀልልኛል” ስትል መለሰች።
ሁለተኛዋ አህያ ቀረበች፡፡ መሃል ዳኛው፡- #አንችስ ማንን ተማምነሽ ነው በጠፍ ጨረቃ በእኛ ግዛት የምትግጭው?; ብሎ ጠየቃት።
አህያይቱም፡- “ጌታዬን፤ ሀብት የሆንኩትን ባለቤት፤ ለእኔ ክፉ የሰራን ሁሉ የገባበት ገብቶ ይበቀለዋል” አለች።
በመጨረሻም ሶስተኛዋ አህያ ቀረበችና አስረጅ ተባለች። ሶስተኛዋ አህይትም፡- “እኔ በጠፍ ጨረቃ የወጣሁት እናንተኑ ጌቶቼን ተማምኜ ነው” ስትል መለሰች።
ዳኞቹም መከሩና “የመጀመሪያዎቹን ሁለቱን ብንበላ እውነትም አደጋ አለው። ይህቺን እኛን የተማመነችውን ብንበላት ግን ማን ይጠይቀናል!” አሉና ከመቅጽበት ወረዱባት ይባላል።
*   *   *
እነሆ መተማመኛችንን አጥርተን ሳናውቅ መጓዝ ለአደጋ ሊያጋልጠን ይችላል። ሁሉ ነገር ከየጀርባው የስጋት ባለቤት አለው። ያም ሆኖ እጅግ ከባዱን አደጋ ከመካከለኛው አደጋ አመዛዝነን ማጤን ይገባናል። መካከለኛውንም ከትንሹ ማመዛዘን አለብን።
ጉዳዮቻችንን በእውቀትና በብልሃት መከወን ይጠበቅብናል። ነገር ግን የእነ ቶሎ ቶሎ ቤት ግድግዳው ሰንበሌጥ እንዳይሆን በጥንቃቄ መራመድን ግድ ይለናል።
በተለይ ወጣቶች ይህንን ያስተውሉ ዘንድ አዋቂዎችና በሳሎች ሳይታክቱና ሳያሰልሱ ሊያስይዟቸው ይገባል። ሁነኛ ቦታ እንዲውሉም የመንግስት ተዋጽኦ በቅጡ ሊታከልበት ይገባል። ከወዲሁ ካልታሰበበት ይረፍዳል። ሳይቃጠል በቅጠል የሚባለው ይኸው ነው። ይኸውም በዘመነ ኮሮና ያሰፈሰፈውን መአት (The Impending Catastrophi እንዲሉ) አለማየት የእውር የድንብር ጉዞ ነው። ግብዝነትም ነው። ግልጽነትና ተጠያቂነት አይቀሬ መንገድ ነው።
ዛሬ ቢላላ ነገ ይጠብቃል። ቆራጥነትን ግን ይጠይቃል። ሳይታክቱ መታተርን ነግ ሰርክ ማሰብ ወሳኝ ነው። ከጦርነት ወቅት ይልቅ የሰላም ወቅት የሴራና የተንኮል መቀፍቀፊያ ነው። አይንን ገልጦ ማየትና አለመተኛት፤ ጎረቤቶቻችንን ሳንፈራም ሳንዘነጋም ማዳመጥና ማየት ዋና መሆኑን ሌት ተቀን የምንገፋበት ሀገራዊ ሃላፊነት ነው።  ይቅርታ እናደርጋለን። ነገር ግን አንረሳም። We forgive but we don’t forget የምንለው ለዚህ ነው።
መልካም የትንሳኤ በዓል ይሁንላችሁ!
የኢትዮጵያን ትንሳኤም ያፍጥንልን!

Read 13185 times