Print this page
Sunday, 02 May 2021 00:00

“አገራችንን ለመታደግ ልዩነታችንን አክብረን በጋራ መስራት አለብን”

Written by  ናፍቆት ዩሴፍ
Rate this item
(0 votes)

    ባለፉ 30 ዓመታት ዜግነቴን ሳልቀይር በኢትዮጵያዊነቴ ፀንቻለሁ” - አቶ ያሬድ ልሳነ ወርቅ

               ተወልደው ያደጉት  በአዳማ (ናዝሬት) ከተማ ነው። የአፄ ገላውዲዮስ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ተማሪ ነበሩ። በስራ አለም በቀድሞው ቡናና ሻይ ልማት ሚኒስቴር፣ በደቡብና ምዕራብ ኢትዮጵያ ተዘዋውረው አገልግለዋል። አሁን መኖሪያቸው በአሜሪካ ሲያትል ነው። ባለትዳርና የሁለት ልጆች አባት  የሆኑት አቶ ያሬድ ጥዑመ ልሳን ወርቅ፤ በአሜሪካ የግል ህይወታቸውን ከመምራት ባለፈ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ውስጥ ባለችው ተሳትፎ፣ በልጅ አስተዳደግና በቤተሰብ አመራር፣ እንዲሁም በአሁኑ ወቅት የአባይን ግድብ በተመለከተ ግብፅን ጨምሮ ከተለያዩ አገራት ኢትዮጵያ ላይ እየተቃጣ ያለውን ዛቻና ጥቃት በተመለከተ በመሟገት ይበልጥ ይታወቃሉ። የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፤ አሜሪካ ውስጥ ባላቸው ማህበራዊ ተሳትፎ፣ በቤተሰብ አመራራቸው፣ በአባይ ግድብና በተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ አቶ ያሬድ ጥዑመ ልሳንን እንደሚከተለው አነጋግራቸዋለች።

              ከአገር እንደወጡ ቀጥታ አሜሪካ አይደለም የገቡት፡፡ የት ነበሩ? ምንስ ነበር የሚሰሩት?
እውነት ነው፤ መጀመሪያ የሄድኩት አሜሪካ አልነበረም፡፡ እ.ኤ.አ በሜይ 25 ቀን 1990 ዓ.ም ለሶስት ወር ወርክሾፕ ወደ እንግሊዝ አገር ነበር የሄድኩት። ነገር ግን በእንግሊዝ የኖርኩት 6 ዓመት ነው። ከዚያ በኋላ ሁለት ጊዜ ዲቪ ሎተሪ ደርሶኝ ነበርና በሁለተኛው ነው ወደ አሜሪካ የሄድኩት። እንግሊዝ አገር እያለሁ ግን በሆቴል ኤንድ ኬተሪንግ በመሰልጠን በባለ 5 ኮከብ ሬስቶራንት ውስጥ ስሰራ ቆይቻለሁ። ከዚህ ጎን ለጎንም እዛው የምኖርበት እንግሊዝ አገር ባለች ወንጌላዊት ቤተ ክርስያን ውስጥም አገለግል ነበር። እንግሊዝ አገር በነበረኝ ቆይታ ብዙ አሳይለም ሊጠይቁ የሚመጡ ኢትዮጵያዊንን የአሳይለም ኬዝ በመጻፍ፣ አዲስ ህይወት በሚጀምሩበት ወቅት ሳይደናገሩ እንዲለምዱ በመርዳትም በኩል አስተዋጽኦ አድርጊያለሁ። ምክንያቱም አብዛኛዎቹ አሳይለም ለመጠየቀ የሚመጡት በእድሜ ትንንሾች ስለነበሩና  አዲስ አለም እና ባህል ውስጥ ሲገቡ የመደናገር ነገር ይገጥማቸዋል። ይህንን በማስተካከል ወጣቶቹን መስመር በማስያዝና ከአዲሱ ህይወት ጋር በማለማመድና በመሰል ጉዳዮች ኮሙኒቲውን አገልግያለሁ።
አሜሪካ እንዴትና መቼ ነበር የሄዱት?
ወደ አሜሪካ የሄድኩት ጃንዋሪ 1 ቀን 1996 ዓ.ም ነው። 25 ዓመት ሊሆነኝ ነው። ትዳርም የመሰረትኩት ሁለት ልጆቼንም የወለድኩት እዛው አሜሪካ ነው። የመጀመሪያዋ ልጄ በፔንሴልቫንያ ስቴት ዩኒቨርሲቲ የሁለተኛ ዓመት ተማሪ ናት። ሁለተኛው ልጄ  ደግሞ ዘንድሮ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ያጠናቅቃል።
ባለቤቴ ስነ-ጽሑፍ፣ ድራማና ፊልም በመጻፍ ትታወቃለች። እኔ ደግሞ ማህበረሰቡ ውስጥ በተለያዩ ጉዳዮች አገለግላለሁ። በተለይ ደግሞ ኢትዮጵያዊያን እዚያ የሞት አደጋ በሚጋጥማቸው ጊዜ፣ በተለያየ ችግር  ቤት አልባ ሲሆኑ፣ ከማህበረሰቡ ጋ መግባባት ሲያቅታቸው እነዚህን ችግሮች በመፍታት አግዛቸዋለሁ።
በጣም የሚሳዝነው ነገር አንዳንዴ ኢትዮጵያዊያን ሞተው ፖሊስ አስክሬናቸውን ሊያቃጥል ሲል ሁልጊዜ ወደ ኮሚኒቲው ይደወላል። ያን ጊዜ ኮሚኒቲውን በማስተባበር የሟቾቹ አስክሬን ወደ አስመራም ይሁን ወደ መቀሌ፤ ወደ ጎንደርም ይሁን ወደ አፋር ብቻ ወደተለያዩ ክፍላተ ሀገራት ለቤተሰቦቻቸው እንልካለን። በጣም የሚገርምሽ የሲያትል ህዝብ በጣም ደግ ህዝብ ነው። የሆነ ችግር መጣ ሲባል ይተባበራል፤ የአቅሙን ሁሉ ያደርጋል። የትኛውም ኢትዮጵያዊ የሞት አደጋ ሲያጋጥመው ሬሳው እንዲቃጠል አይፈልግም። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በተለይም ሲያትል የሚገኘው ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን  (አቡነ ዜና ማርቆስ በአፀደ ስጋ ይኖሩ በነበረ ጊዜ) ይመሩት የነበረው ማለቴ ነው። አሁንም እነ አቡነ ሉቃስና አቡነ ዮሐንስ የሚመሩት ይሄ ቤተ ክርስቲያን ለእንደነዚህ ያሉ ቤት አልባ ወገኖች ከፍተኛ እርዳታ ያደርጋል። አስክሬኑን ወደ አገር ቤት ከመላካችን በፊት ተገቢው ፍትሃት ተደርጎ፣ ሃይማኖታዊ ክብራቸውንና ሰብእናቸውን ጠብቀን፣ኢትዮጵያዊ ማንነታቸወን አክብረን ነው የምንልከው።
ከዚህ ባሻገር እኛው ተባብረን ከ5-10 ፎቅ የሚደርስ  ህንፃ፣ አዛውንት ለሆነ ኢትዮጵያዊያን መኖሪያ እንዲሆን፣ ከታች መሬቱ የኮሚኒቲው የስብሰባ አዳራሽ፣ ሱቆች፣ ማዕከላት ያለው በኢትዮጵያ ኮሙኒቲ ስም ለማሰራት በጅማሬው ላይ ነን። ኮሚኒቲው ብዙ እንቅስቃሴ በማድረግ እየተባበረ ይገኛል። እኔም እንግዲህ በዚህ ውስጥ የድርሻዬን አበረክታለሁ።
ብዙ ጊዜ በውጪ የሚኖሩ ኢትዮጵያን አብዛኛውን ጊዜያቸውን በስራ ላይ ስለሚያሳልፉ በልጅ አስተዳደግ ላይ ክፍተት ይፈጠራል። ልጆች ኢትዮጵያዊ ማንነታቸውን በቅጡ ሳያውቁ ያድጉና የማንነት ቀውስ ውስጥ ይገባሉ ይባላል።  እርስዎ በዚህ በኩል ክፍተት ሳይፈጥሩ ልጆችዎን እንዳሳደጉ ነው የሰማሁት በአሜሪካ ህይወት ይሄን ማድረግ እንዴት ቻሉ? አሁንም በሼፍነት ሙያ ነው የሚሰሩት ወይስ ስራ ቀይረዋል?
አመሰግናለሁ፡፡ አንቺም ልጆች እንዳለሽ ስለነገርሽኝ፤ የልጅ ነገር ይገባሻል ብዬ አስባለሁ። ልጆች በጣም ጥንቃቄ ይፈልጋሉ። በአሜሪካ አገር ልጆችን የሚጎትታቸውና የሚያታልላቸው ነገር ብዙ ነው። በአደንዛዥ ዕፅ፣ ፖርኖግራፊና በተለያየ መጥፎ ብልሹ ስነ-ምግባራት ሊያዙ ይችላሉ።
እኔና ባለቤቴ ልጆቻችንን ለማሳደግ ያደረግነውን ተሞክሮ ስነግርሽ፣ ባለቤቴ የመጀመሪያዎቹን አምስትና ስድስት ዓመታት ቁጭ ብላ ልጆቹን በማጥባትና በማሳደግ  በማስተማር ብዙ ቆይታለች። ምንም ስራ አትሰራም ነበር። እኔ ደግሞ ሼፍ በመሆን መቀጠል አልተመቸኝም። ምክንያቱም ሁልጊዜ ተቀጥረሽ ስትሰሪ፣ መግቢያሽና መውጫሽ በሰዓት ነው ከዛ ውጭ ንቅንቅ የለም፡፡ ያ እንዳይሆን ሁሉንም እርግፍ አድርጌ ትቼ ታክሲ መንዳት ጀመርኩኝ። በታክሲው ስራ በፈለግኩት ሰዓት እወጣለሁ፤ በፈለግኩት ሰአት እገባለሁ። ይህ የሰዓት ነፃነት በሰጠኝ እድል ልጆቹን ከልጅነታቸው ጀምሮ የመፅሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲያገኙ  በማድረግ እንዲሁም 6 ያህል አብያተ ክርስቲያናትን ሄደን አይተንና መርምረን፣ ከእኛ እምነት ጋር የሚዛመዱ ቤተክርስቲያናት ውስጥ በማስገባት የእግዚአብሔርን ቃል እንዲያጠኑ አድርገናቸዋል።
ሁለተኛው ጉዳይ በራሴ የምወስነው ጊዜ ስላለኝ በካናዳ፣ በሜክሲኮ፣ በአሜሪካም ውስጥ ባሉ ህጻናት በሚጫወቱባቸው ቦታዎች ከዲዚኒላንድ እስከ ካናዳው ማውንትግሬብ ተራራ ድረስ ልጆቻችንን በዕድሜ ደረጃቸው ይዘን በመሄድ ተገቢውን ትምህርትና ልምድ እንዲያገኙ አድርገናል። ለምሳሌ በአንድ ወቅት ወደ 2 ሺህ ማይል በኦሬጎን ስቴት ኮስት ፎርትላንድ በሚባለው ዋና ከተማ ዳርቻዎች በመንዳት፣ ውቅያኖስ ጠለቅ የሆኑ አእዋፋትንና አሳዎችን እንዲያውቁ አድርገናል። በዚሁ በኦሬጎን ስቴት ውስጥ 11 ፏፏቴዎች ያሉት ፓርክ አለ። ያንን ሁሉ በእግር ጉዞ እንዲጎበኙ አድርገናል። ይሄ እንግዲህ ብዙ ጊዜ ለልጆቻችን በመስጠትና የእኛን ፍቅር እንዲገኙ በማድረግ ከጥፋት አትርፈናል። ይህንን የምናደርግበትን ሰአት ስራ ብለንሰራበት እርግጥ ነው ብዙ ገንዘብ እናገኝበታልን። እኛ ከገንዘብ ይልቅ ልጆቻችን ገንዘብ በማድረግ ጊዜያችንን ሰጥተናል፡፡ ውጤቱንም አሁንም በልጆቻችን ስነ ምግባርና ግብረ ገብነት እያየነው ነው። የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ምንም እንኳን በጣም ውድ ቢሆንም የግል ት/ቤት በማስተማር ቅድሚያ ሰጥተናቸዋል። ይሄ ደግሞ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ሲገቡ ተወዳድረው ነፃ የትምህርት እድል እንዲያገኙ አግዞናል። ለምሳሌ የአሜሪካ መንግስት ልዩ ችሎታና ተሰጥኦ ያላቸውን ልጆች ወደሚልክበት የተለየ ት/ቤት ወንዱ ልጃችን ተወዳድሮ በማሸነፍ እዚያ ት/ቤት ገብቶልናል። ይህን ሁሉ በማድረጋችን ፍሬ አፍርተናል። ለዚህ ነው ፍሬ እያየን  ነው ያልኩሽ።
እርሶዎ ከአገር ከወጡ በአጠቃላይ ከ30 ዓመታት በላይ ሆኖዎታል። ሆኖም ጭልጥ ብለው አልጠፉም፡፡ ለቤተሰብ ጥየቃም ሆነ ለአንዳንድ ጉዳዮች ወደ አገር ቤት ቶሎ ቶሎ ይመጣሉ። ይሄ ደግሞ አገርዎ ኢትዮጵያ ያለችበትን ተጨባጭ ሁኔታ በግልጽ እንዲረዱ ያደርገዎታል። ከዚህ አንጻር አሁን ኢትዮጵያ በአባይ ጉዳይ፣ በህዳሴው ግድብና በተለያዩ ሌሎች ጉዳዮች በውስጥም በውጭም የገጠማትን ችግር እንዴት ያዩታል? በዚህ ዙሪያ ከኮሚውኒቲው ጋር የሚሰሩት ነገር አለ?
ጥያቄሽን በሁለት መልኩ ብመልስልሽ ይሻላል። በመጀመሪ በ1999 ዓ.ም ከባለቤቴ ጋር ስንገናኝ፤ እሷ ስዊድን አገር ነበረች። ከዚያ ከመጣች በኋላ በኢትዮጵያ ከ15 በላይ ዋና ዋና ከተሞችን ነው ይዣት የዞርኩት። ከዚያ በኋላ ነው ለመጋባት የወሰንነው። የጎንደርን ጃንተከል ዋርካውን አይተናል። የፍቅርን ትርጉም ብርሃኑ ዘሪሁን እንደጻፈውድሬደዋን ሃረርን ጅማ ቡናው ተክል ሥር፤  ተንሸራሽረናል። አጋሮ ከተማን አይተናል። በዚህ መሀል የህይወት ትርጉሙ ምንድን ነው እየተባባልን ተወያይተናል። በ2001 እ.ኤ.አ እግዚአብሔር በሁለት ልጆች ሲባርከን፣ በ2011 እ.ኤ.አ ልጆቻችንን ይዘን መጥተን ከአዲስ አበባ ባህርዳር፣ ከባህር ዳር ጎንደር፣ ከጎንደር ላሊበላ፣ ከዚያ በኋላ አርባ ምንጭ ሄደን ነጭ ሳር ብሄራዊ ፓርክን …በጥቅሉ ዋና ዋና የሚባሉትን የኢትዮጵያን ቦታዎች ልጆቻችን እንዲጎበኙ አድርገናል።
ይሄን የምነግርሽ ለጉራ ሳይሆን ቀድሞውኑም ከአገራችን ርቀን አለመራቃችንን ለመግለጽ ነው። ልጆቻችን አሜሪካ ቢወለዱም አገራቸውንም በቅርበት እንዲያውቁ ማድረግ የውዴታ ግዴታችን ነው ብዬ አምናለሁ። እኛም ከአገራችን እልም ብለን የመጥፋት ፍላጎት የለንም። በ2011 ዓ.ም ልጆቻችንን ይዘን መጥተናል። አየሽ ያልዘራሽውን አታጭጂም። ያልተከልሽውን ፍሬ አትጠብቂም፡፡ ያልተንከባከብሽውን ነገር ውጤት አትጠብቂም። ይህንን የእኛን ተሞክሮ እንደ ክፍል አንድ ውሰጂው። ልጆቻችን በዜግነታቸው አሜሪካዊ ናቸው፤ ያንን ፍላጎታቸውን እንጠብቃለን። አንጠብቅም ብትይም አትችይም። እነሱ በሚማሩበት ት/ቤት  ለአሜሪካና ለባንዲራዋ በየቀኑ ቃለ መሃላ ይፈጽማሉ። ነገር ግን በትውልድ ኢትዮጵያዊ ስለሆኑ ስለ ሀገራቸው፣ ስለ አክሱም ስልጣኔ፣ የፋሲል ቤተ-መንግስትን ያነጹ ቅድመ አያቶች እንዳሏቸው እንዲያውቁ፣ የላሊበላን ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ከአንድ ድንጋይ ፈልፍለው ከሰሩ ጥንተ ሊቃውንት እንደተገኙ እንዲገነዘቡ፣ በአጠቃላይ የማንነት ቀውስ ውስጥ እንዳይገቡ  ለማድረግ ጥረናል።
ወደ ሁለተኛውና በዋናነት ወደጠየቅሽኝ ነገር ስመጣ፣  በአባይና በህዳሴው ግድብ ዙሪያ በግሌ ብዙ እሳተፋለሁ። በዙም ስብሰባዎችም ሆነ በአካል በሚካሄዱትም ቢሆን በመሳተፍ የበኩሌን እወጣለሁ። በነገራችን ላይ እኔ ባለፉት 30 ዓመታት በዜግነት ኢትዮጵያዊ ነኝ። ዜግነቴን እንግሊዝ አገርም ሆነ አሜሪካ አልቀየርኩም። እንግሊዝም በስድስት አመት ውስጥ መቀየር እችል ነበር- አልቀየርኩም። አሜሪካም 25 ዓመት ስኖር አልቀየርኩም።
በወረቀትም በደምም ኢትዮጵያዊ ነኝ ነው የሚሉት?
ትክክል ነው፤ በሁሉም ነገር ኢትዮጵያዊ ነኝ። እንደ ኢትዮጵያዊነቴ በአባይ ጉዳይ ላይ በማተኮር የተለያዩ  ጽሁፎችን፣ በተለያዩ ዌብሳቶችና  ፌስቡክ ላይ በሳምንት ሁለት ጊዜና ከዚያ በላይ ስለ አባይ አጫጭር መጣጥፎችን ሰዎች ሊረዱ በሚችሉበት መልኩ እጽፋለሁ። ይህንን ሳደርግ የነበረው ከፈረንጆቹ  2011 ዓ.ም ጀምሮ ነው። አሁን እንዳለው  የድል አጥቢያ አርበኛ ለመሆንም አይቃጣኝም። የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳት ትራምፕ ስለ ግድቡ ከተናገሩ በኋላ የመጣሁ አይደለሁም ለማለት ነው፡፡ አሁንም በህዳሴው ግድብ ላይ ጠላቶቻችን እያሴሩ ያለውን ሴራ ለማክሸፍና ኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ የበላይነትና በአባይ የመጠቀም መብቷን ለማስከበር በሚደረገው ትግል የምንችለውን ሁሉ እያደረግሁ ነው አሁንም እቀጥልበታለሁ።
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ከውስጥም ከውጭም የገጠማትን ተግዳሮቶች ለመመከት በተለይም በህግ ማስከበሩ ሂደት የደረሰውን ሰብአዊ  ቀውስ ተከትሎ የኢትዮጵያን ስምና ገፅታ ለማጠልሸት የተከፈተውን ዘመቻ ለመቀልበስ ኢትዮጵያዊንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በአረብኛውም በእንግሊዘኛውም እየታገሉና የሀገራቸውን እውነታ ለዓለም ለማሳየት ጥረት እያደረጉ ነው። ይህን እንቅስቃሴ እርስዎ እንዴት ይገመግሙታል?
በዚህ ረገድ ሁለት አይነት ሀሳብ አለኝ። በተለይ በአሜሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲ በአምባሳደር ፍፁም አረጋ የሚመራው ቡድን ከፍተኛ እንቅስቃሴ እያደረገ ነው። ድሮ የማናየውም ባህል እየታየ ነው። ምን ማለት ነው? የአምባሳደሩ ምክትል አምባሳደር ሴት ናቸው። በየሪጅኑም እንዲሁ በተለይ በሎስ አንጀለስ ያሉት ወ/ሮ አልማዝም ሆነ ሌሎቹ ሀይለኛ የሆነ እንቅስቃሴ በማድረግ ለአባይ ከፍተኛ የገቢ ማሰባሰብያ እያደረጉ ይገኛሉ። ይሄ በጣም ደስ የሚልና ተስፋ ሰጪ ጅምር ነው። በሌላ በኩል፤ በዲፕሎማሲው ረገድ የኢትዮጵያ እንቅስቃሴ ምን ይመስላል ላልሽኝ፣ 80 ሺህ ግብፃዊያን ከፍተኛ ፕሮፌሽን ላይ ያሉ… በመላው አለም ተሰራጭተው ይሰራሉ።
እነዚህ 80 ሺህ ግብፃዊያን ልሂቃን አሁን ካሉት የግብፅ መሪ ጋር ከፍተኛ የሆነ የፖለቲካ  ልዩነት ያላቸው ናቸው። ከፕሬዚደንት አልሲሲ ጋርም ብዙም ስምምነት የላቸውም። ነገር ግን በአባይ ጉዳይ ቀፎው እንደተነካ ንብ አንድ ሆነው ተደራጅተው እየሰሩ ነው። እኛ ብድር እንዳናገኝ፣ ሌሎች ተቋማዊ ምክሮች እንዳናገኝ፣ ተደማጭነት እንዳይኖረን እንቅልፍ አጥተው እጅ ለእጅ ተያይዘው እየሰሩ ነው። ከዚህ አንፃር በኢትዮጵያ የሚሰራው ስራ እንደምን ያለ ነው ብትይኝና ከግብጾቹ ጋር ቢወዳደር፣ እኛ እዚህ ግባ የሚባልና ለወሬ የሚበቃ ስራ እየሰራን አይደለም። ይሄንን በእርግጠኝነት እነግርሻለሁ።
ሌላው ግብፃዊያኑ የሚያደርጉት በየትምህርት ቤቱ ልጆቻቸውን በመጠቀም “እስኪ ባህላዊ ነገር አምጡ” ሲባል አባይ እንዴት ህልውናቸው እንደሆነ፣ እንዴት እንደሚጠቅማቸው፣ በአባይ የመጣ በአይናቸው የመጣ እንደሆነ… አድርገው አእምሯቸውን በመሙላት ነው የሚሳድጓቸው፡ የእኛ ልጆች ስለ አባይ ከስር ጀምሮ ስለማይነገራቸው ከግብጾቹ ጋር ስናነጻጽራቸው ኋላ እንደቀረን ያሳየናል።
ሌላው በሚዲያ ረገድ ግብፆች ጀምበር ታይታ እስከምትጠልቅ፣ ምሽቱም ሳይገድባቸው ከፍተኛ የፕሮፓጋንዳ ስራቸውን ያጧጡፋሉ፡፡ ካለው መንግስት ጋር ያላቸው ልዩነት እንደተጠበቀ ሆኖ ማለቴ ነው። ከዚህ አንፃር የኢትዮጵያ ሚዲያ ምን ህል እየሰራ ነው? የሚሰራውስ በውጪ ተደራሽ ይሆናል ወይ ብትይኝ፣ የሚጠበቀውን ያህል እየሰራ አይደለም፤ የሚሰራውም ተደራሽነቱ በጣም አናሳ ነው። እኛ በውጪ ሆነን ይህ ክፍተት ስለሚታየን ክፍተቱን ለመሙላት ከፍተኛ ጥረት እያደረግን ነው። እርግጥ ነው አሁን በተለያዩ ቋንቋዎች ሚዲያ በመክፈት በመንግስት እየተሰሩ ያሉ ጥሩ ጅምሮች አሉ ግን ተጠናክሮ መቀጠል አለበት።
ብዙ ኢትዮጵያዊያ አሜሪካ መግባትን ገነት እንደ መግባት ይቆጥሩታል ፤ ሌላው ቀርቶ አንዳንድ ወላጆች ኢትዮጵያ የተረገዘ ልጃቸውን አሜሪካ እንዲወልዱና ዜግነት እዲያገኝ ሲያደርጉ ይስተዋላል። እርስዎ ደግሞ ከ30 ዓመታት በላይ ኖረው ኢትዮጵያዊነቴን አልለቅም ብለው ነው ያሉት? እንዴት ሆነ፡፡ ዜጋ በመሆን የሚገኙ መብቶችና ጥቅማ ጥቅሞች አላጓጉዎትም?
በቀላሉ ይሄ የምርጫ ጉዳይ ነው፤ ሌላው ደግሞ ማንነትሽ ሲቀረጽ እንዴት ሆኖ ተቀረጸ የሚለው ነገር ወሳኝ ነው። እኔ በተወለድኩበት ጊዜና ዘመን፣ እነ ክቡር ከበደ ሚካኤል በጻፉት “ተረትና ምሳሌ”፣ ባንዲራ ሲወጣና ሲወርድ ያለው ስነ-ስርዓት፣ አገር ተኮር መዝሙሮች፣ የምናነባቸው  መፅሐፍት ሁሉ… የአንቺ ማንነት መሥሪያ ግብአቶች ናቸው።
ተመልከቺ የቴዎድሮስን ቴአትር ፍቃዱ ተክለማሪም የተወነበትን የነስነ-ልቦና ልእልናሽ እንዴት ይሰራዋል መሰለሽ! ያለን ታሪክ፣ የጥንት አባቶቻችን ሰርተው ያለፉት ስራ ከኢትዮጵያዊነትሽ አንድ ስንዝር ፈቀቅ እንድትይ አያደርጉሽም፤  እና እንግሊዝ አገር ጥገኝነት ለመጠየቅ ስሄድ፣ ነጭ ናት፤ ፊት ለፊት ቁጭ ብላለች፡፡ እናም ዜግነት ስለመቀየር ስትጠይቀኝ ትዝ ያለኝ…  የቴዎድሮስ ቴአትር ነው። “እጅህን ስጥ አለኝ ፈረንጅ ምን እጅ አለኝ የእሳት ሰደድ” የሚለው የፀጋዬ ገብረ መድህን ግጥም።
ራሳቸው አፄ ቴዎድሮስ የተናገሩት ነው የሚመስለው አይደለም?
አዎ! እኔም እጅ አልሰጥም አልኩኝ ሀገርን መካድ ወንጀል ነው ብዬ አመንኩ። ዋጋ አያስከፍልም ወይ አዎ ብዙ ዋጋ ያስከፍላል፤ ከፍያለሁም። ለምሳሌ በ1999 ዓ.ም ከአሜሪካ ኢትዮጵያ ስመጣ፣ እስራኤል ለመሄድ አስተካክዬ ነበር። ነገር ግን “አይ አንተ ዜግነትህ ኢትዮጵያዊ ስለሆነ ከዚህ ቀጥታ እስራኤል መሄድ አትችልም። ኢትዮጵያ ሄደህ ከዚያ ነው እስራኤል መጓዝ የምትችለው” ተባልኩ። እዚህ ስመጣ ደግሞ የለም “እስራኤል አገር የሚቀበልህ እሱ  ግብዣ ይላክልህ እንጂ እንዲሁ መሄድ አትችልም” ተባልኩ። በዚህ መሃል ሶስት ወር ባክኖ እስራኤልም ሳልሄድ ቀረሁ፤ አሜሪካዊ ብሆን ቀጥታ ያለ ቪዛ እስራኤል እሄድ ነበር። ይሄ ቀላሉና ትንሹ ምሳሌ ነው። ነገር ግን ይሄ ከሀገርና ከማንነት አይልጥም። ይህን ስል ዜግነት የቀየሩትን ማጥላላቴና መኮነኔ አይደለም። ይህ የምርጫና የመብት ጉዳይ ነው። የእኔ ምርጫና አቋም ኢትዮጵያዊ ሁኜ መቀጠል ነው፡፡ የሚከፈለውን ዋጋ እከፍላለሁ አለቀ!
በመጨረሻ ኢትዮጵያ በእርስዎ እድሜ ምን ሆና ምን ላይ ደርሳ ለማየት ይሻሉ? ምንስ ተስፋ ያደርጋሉ?
እንግዲህ አይደለም በሀገር ደረጃ ሰው በትዳም ሲኖር ብዙ ልዩነቶች ይኖራሉ። እኔና ባቤቴ ልዩነት አለን ወይ? አዎ ልዩነት አለን። ልዩነታችንን ጠብቀን፣ ነገር ግን አብረን ነው የምንጓዘው፡፡ ለምን? የጋራ የሆነ አላማና ግብ ስላለን። በሀገር ደረጃም ብዙ ልዩነቶች አሉ? አዎ አሉ። ብዙ አይነት የፖለቲካ አመለካከትና ልዩነቶች  አሉ። ነገር ግን ልዩነታችንን ጠብቀን በአንድነት መጓዝ አለብን። ምክንያቱም የጋራ አገር የጋራ ማንነት አለን። አገር  በማንም አትተካም፡፡ ሁለተኛውና ትልቁ ነገር ኢትዮጵያዊያን እርስ በእርስ እንጋጫለን። የውጭ ጠላት ሲመጣ ግን አንድ እንሆናለን። ለምሳሌ ፕሬዚዳንት ትራምፕ “የህዳሴውን ግድብ ግብፅ ልታፈነዳው ትችላለች” ብለው ሲናገሩ፣ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን ድምጽ ነፈጋቸው፤ በምርጫ እንዳያሸንፉ ኢትዮያዊያን ድምጽ በመከልከል ትልቁን ስራ ሰርተዋል። ይሄ ትልቅ ሀብት ነው። ግን ችግር ሲከሰት ብቻ ከምንተባበር፣ በሌላውም ጊዜ ልዩነታችን አክብረን፣ ተዋደን ተቻችለን ከኖርን ለጠላትም አንመችም። በክፍተታችን የሚገባ የለም፡፡ በሌላ በኩል አዲሱን ትውልድ የሚቀርፁ መምህራን፣ ትውልዱን ከመቅረጽ አኳያ ትልቅ ስራ መስራት አለባቸው፡፡ ት/ቤት ውስጥ እስክሪቢቶ እንጂ ዱላና ድንጋይ ገብቶ ማየት የምን ውጤት ነው? ይሄ ሁሉ መፈተሸ አለበት፡፡  በተለይ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ የሚታየው ነገር ትምህርት ስርዓቱ ላይ ያለውን ክፍተት ያሳያል። ከሚያለያየን ነገር ይልቅ  የሚያቀራርበን ነገር ላይ መሰራት አለበት።
ባህላዊ እሴቶቻችን እንደ እድር ያሉት ተጠናክረው ማህበራዊ ፋይዳቸው መመዘን አለበት። የዛሬ 17 ዓመት አሜሪካ የተቋቋመ እድር አለ፤ ስንት ማህበራዊ ፋይዳ እንዳለው አልነግርሽም።
በመጨረሻ አባይ ተገድቦ በኢትዮጵያ ትልልቅ ኢንዱስትሪዎች አብበው ያቺ የእኔ እናት፣ አክስት  እህት፣ እና ወዘተ ከኩበት ጭስ ወጥታ፤ ከእንጨት ሸክም ተላቃ ኤሌክትሪክ ምጣድ ኖሯት፣ እፎይ ስትል ማየት ነው ህልሜ። ይህ እንዲሆንም የኩሌን አደርጋለሁ፡፡ ሁሉም የበኩሉን ያድርግ አመሰግናለሁ!!

Read 2754 times