Saturday, 01 May 2021 12:46

ሦስቱ አህዮች - (መጽሐፍ ቅዱሳዊ ታሪክ)

Written by  ደራሲ - ዴቪድ ኮሶፍ ትርጉም - ዮናስ ታረቀኝ
Rate this item
(0 votes)

"-እድሜ ልኬን የኖርኩት ኢየሩሳሌም ነው፡፡ ይገርማችኋል፣ የማውቀው ግን የጸሎት ቤት ሆኖ ሳይሆን በሚሰዋ ነገር  ሻጮች፣ በገንዘብ ለዋጮችና በሸቀጥ ነጋዴዎች ተወርሮ ነበር፡፡ ከዕለታት በአንዱ ቀን እዚያ ቦታ ላይ ታላቅ ረብሻ ተፈጠረ፡፡ አንድ ወጣት ሰባኪና ተከታዮቹ ሱቆቹን እየገለባበጡ ሰዎቹን አስወጡ፡፡ በዚህ ምክንያትም ያ ሰባኪ ብዙ ችግር ውስጥ ገባ፡፡--"
                        
              አሁን የምነግራችሁ ታሪክ በገነት ስለሚኖሩ ሶስት አህዮች ነው ብዬ ስጀምር፣ ብዙ ሰዎች  ግር ይላቸዋል፡፡ የሚገርመው ነገር ደግሞ በገነት አላምንም የሚሉ ብዙዎች "አህያ ገነት መግባት ይፈቀድለታል" የሚለው ሃሳብ ይበልጥ የሚያናድዳቸው መሆኑ ነው። ይህ ግን አመክኖያዊ አይደለም፡፡ ገነት የመልካም ሰዎች ሥፍራ ከሆነ፣ ስለ ምን ከሰዎች ይበልጥ መልካም የሆኑት አህዮች ሥፍራ አይሆንም? ብዙ እንስሳት እኮ ከሰዎች ይሻላሉ፡፡ እናንተስ  በዚህ አታምኑም?
ለማንኛውም በአንድ ተሲያት በኋላ ሶስት አህዮች በጋራ ሆነው በገነት ውስጥ ጊዜያቸውን እያሳለፉ ነው፡፡ እዚህ ከገቡ ብዙ ጊዜ ሆኗቸዋል፡፡ አያሌ ክፍለ ዘመናት፡፡ በአጋጣሚ ሁሉም በምድር ላይ ሳሉ ከአንድ አይነት አካባቢ እንደመጡ በተመሳሳይ ጊዜ፣ ጥቂት ዓመታትን አገልግሎት ሲሰጡ ወይም ሲቀበሉ ቆይተው፣ ወደ ገነት መግባታቸውን ተረዱ፡፡  ይህንን ጉዳይ ማወቃቸው በጣም አስደሳች ነበር፡፡ ይመሳሰላሉም፡፡ እርግጥ አህዮች ሁሉ ይመሳሰላሉ፡፡ ሶስቱም ከጥላው ጋደም ብለው አንዱ አህያ የምድር ታሪኩን እየነገራቸው ነው፡፡ ሁለቱ አህዮች ታሪኩን ወደውታል፡፡ እናንተስ?
የመጀመሪያው አህያ ታሪክ
"ብዙ ጌቶች ነበሩኝ፡፡  ከሌሎቹ በተሻለ የማስታውሰው ግን አንዱን ነው፡፡ ምንም እንኳን በጣም መልካምና ረጋ ያለ ሰው ቢሆንም፣ በተለየ እሱን የማስታወስ ምክንያቴ ግን ወዲህ ነው፡፡ ለእሱ አገለግል በነበረበት ወቅት በተፈጠሩ  አንድ ወይም ሁለት እንግዳ የሆኑ ነገሮች የተነሳ፡፡ ጌታዬ እንጨት ሰራተኛ ነበር፡፡ የሚሰራውም የሚኖረውም ናዝሬት ውስጥ ነው፡፡ ባለጸጋ ሰው አልነበረም፡፡ ብዙ ንብረት የለውም። እኔን ገዝቶ ያመጣኝ አይመስለኝም፡፡ ነገር ግን ወደ ቤተልሄም እንድሄድ የሚያደርገው የሮማውያንን ትእዛዝ ተላልፎ ነው፡፡ የህዝብ ቆጠራ እየተካሄደ ነበር፡፡ ለማንኛውም የፈለገኝ እመቤቴን ወደ እዚያው እንድወስዳት ነው፡፡ እመቤቴ ደግሞ ድርስ ነፍሰ ጡር  ነበረች፡፡ ይህ የሮማውያን ትዕዛዝ ነው፡፡ ማንም ይህን ትእዛዝ ሊቃወም አይችልምና ወደ እዚያው ሄድን፡፡ በተቻለኝ ሁሉ በቀስ መጓዝ ነበረብኝ፤ ስለዚህ  ረዥም ጊዜ ወሰደብን፡፡
ስንደርስ መሽቶ ነበር፡፡ ከተማው በሰው ተጥለቅልቋል፡፡ የማረፊያ ቤቶችና ክፍሎች በሙሉ ተይዘዋል፡፡ የተረፈ አልነበረም፡፡ ጌታዬ የጠየቀው የመጨረሻው የሚከራዩ ክፍሎች ባለቤት ሊረዳው ሞከረ፡፡ ‹‹የከብቶች በረቱ ደረቅና ሞቃት ነው፣ እዚያ ማደር ትችላላችሁ›› አለን፡፡ እመቤቴ ያለችበትን ሁኔታ አስቤ ጥቂት ተጨነቅኩ። ማለቴ እኔ ህይወቴን ሙሉ የምተኛው በበረት ውስጥ ነው፡፡  እሷ ግን የምታሳሳ፣ በመልካም ሁኔታ ያደገችና ዝምተኛ ሰው ነች፡፡ ጌታዬ በሚችለው ሁሉ እንዲመቻት አድርጎ አዘጋጀላት፡፡ ትልቁን ግርግም (የከብቶች መመገቢያ) ወስዶ ከየቦታው በሰበሰበው የሳር ድርቆሽ ሞላውና እዛ ላይ ጋደም አለች፡፡
አሸልቤ ሳይሆን አይቀርም፤ያነቃኝ የሰዎች ድምፅ ነው፡፡ መጀመሪያ ላይ ሮማውያን መስለውኝ ነበር፤ ነገር ግን እረኞች ነበሩ። እረኞቹ ደግሞ በጣም ደስተኞች ነበሩ፡፡ ጥቂቶቹ ይፀልያሉ። ግርግሙ ላይ እመቤቴ ጋደም እንዳለች በእቅፏ አዲስ የተወለደ ህፃን ይዛለች፡፡ እስከማስታውሰው ድረስ እረኞቹ እመቤቴ በጣም የተለየ ልጅ እንደምትወልድ፣ እኩለ ሌሊት ላይ በመላእክት ሰራዊት ተነግሯቸው ነው የመጡት፡፡ እራሳቸው በአይናቸው እንዲያዩ፤ ከዚያም ይህ ከእኔና ሁለት ሌሎች አህዮች እንዲሁም አንዲት ላም ጋር የከብቶች በረት የተጋራ ሕፃን፤ ዓለምን የሚቀይር እንደሆነ እንደያበስሩ የተነገራቸው ናቸው፡፡
እርግጥ ሰው ሁሉ ተደስቶ ነበር፤ ደስታው ብዙ አልዘለቀም እንጂ፡፡ አስቡት እስቲ አንዱ መልካም ነገር አንድ ወይም ሁለት ሰዎች ጌታዬ ቤተልሄም ውስጥ የሆነ ቦታ ማረፊያ እንዲያገኝ መርዳታቸው ነበር። እመቤቴ እስክትበረታ ድረስ በደህና ቆዩ፡፡ የተፈጠረ ተአምር አልነበረም። ያ አስደሳች ሌሊት አልተፈጠረም ብላችሁ ልታስቡ ትችላላችሁ፡፡ እኔ ረስቼው ሁሉ ነበር፡፡ ከዚያን ምሽት በኋላ ሌላ ታላቅ ምሽት አጋጠመን፡፡ ያኔ እረኞች አልነበሩም። ይበልጥ ልዑላን የመሰሉ ነበሩ፡፡ ሶሰት ናቸው፤ ሁሉም ከተለያየ ሩቅ ቦታ የመጡ፡፡ በዚያን ጊዜ እንደሚደረገው፤ ብዛት ያላቸው አገልጋዮች ተከትለዋቸውና ግመሎች ይዘው ስለነበር መንገዱን ዘጉት፡፡ እነሱም ስለ መላእክትና ወደዚህ ስለመራቸው ትልቅ ኮከብ፣ የተለየ ምልክት ይናገራሉ፡፡ ሦስቱም ጠቢባን ስለሆኑ  ሕፃኑ ልዩ መሆኑ  ገብቷቸዋል፡፡  
"አዳኝ ነው" ይላሉ፡፡ "ንጉሥ ነው" ይላሉ። "ከሄሬዶት የበለጠ ታላቅ ነው" ይላሉ፡፡ ይህንን ስሰማ ችግር እንደሚፈጠር አውቄ ነበር፡፡ ልክ ነበርኩ፡፡ በነጋታው ጠቢባኑ ሰዎች ሄዱ፡፡ እኩለ ቀን ሲሆን ብቻችንን ነበርን፡፡ ፈጣሪ ለጌታዬ "ንጉስ ሄሬዶት እየመጣ ነው፡፡  ይህን ልዩ ሕፃን፣ ይህቺን የልዩ ሕፃን እናት እንዲሁም ይህን የልዩ ሕፃን አህያ በፍጥነት ይዘህ ሽሽ" ብሎ ነግሮት ነው መሰል፤ ወደ ግብፅ መሄዳችን ትዝ ይለኛል፡፡"
የመጀመሪያው አህያ ወደ ሁለቱ ተመለከተ፤ "ልጁን በተመለከተ የሆነ የተለየ ነገር ያለ ይመስለኛል፡፡ ይሁን እንጂ ከቤተሰቡ ጋር በቆየሁባቸው ስድስት ዓመታት ውስጥ ምንም የተለየ ያየሁት ነገር የለም›› አለ፡፡  
ሁለተኛው አህያ
ከሁሉም በእድሜ የገፋው ሁለተኛ አህያ፣ አንደኛው አህያ ሲተርክ የነበረውን ከልቡ ሲያዳምጥ ከቆየ በኋላ ጥቂት ፋታ ወስዶ መናገር ጀመረ፡፡
‹‹እኔም የሰራሁት አንድ እንጨት ሰራተኛ ዘንድ እዚያው ናዝሬት ውስጥ  ነው ብልህ ምን ትላለህ?›› አለው የመጀመሪያውን አህያ።  
‹‹ይገርማል፣ እስቲ አጫውተን›› አለው፤ ለሁለተኛው አህያ፡፡
‹‹እሺ፣ እስከማስታውሰው ድረስ አንተ እንደተናገርከው በረት ውስጥ የተወለዱ ልጆች ወይም የእረኞች ደስታ፣ ጠቢባን ሰዎችና የሚያበሩ ኮከቦች አላየንም፡፡ የምንኖረውም በሰላም ነበር፡፡
ተገዝቼ ስመጣ  ጌታዬ ብዙ ልጆች ነበሩት፡፡ አምስት ልጆች ይመስለኛል፡፡ ስማቸውን አላስታውስም፡፡ አንዱ ወንድ ልጅ ግን ከአእምሮዬ አይጠፋም፡፡ በጣም ዝምተኛ፣ ለሰው አሳቢ፣ እንደ እናቱ ረጋ ያለ ነበር፡፡ እናቱ ማርያም የምትባል ይመስለኛል፡፡ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ለነገሩ ችግር የለውም፡፡ ከእዚህ ቤተሰብ ጋር የቆየሁት ለሶስት ዓመታት ነው፡፡ በዚህን ጊዜ ልጁ የአስራ ሁለት ወይም የአስራ ሶሰት ዓመት ልጅ ቢሆን ነው፡፡ እናም በዚያው ዓመት ኢየሩሳሌም ወደሚገኘው ታላቁ ቤተ መቅደስ ለሚደረገው አስደሳች ጉዞ ከወላጆቹ ጋር ለመሄድ እድሜው በቂ ነበር። በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ወደ እዚያው ይሄዳሉ፡፡ ወቅቱ ፀደይ ነው፡፡ የጉዞው ዓላማ የአይሁድ ፋሲካን ለማክበር ነው። ቤተሰቦች፣ ጓደኛሞች በቡድን በቡድን እየሆኑ ይጓዛሉ፤ በየሜዳው ያድራሉ፤ በአጠቃላይ አስደሳች በዓል ያሳልፋሉ፡፡ በጣም ነው ደስ የሚለው፡፡ ልጁ ለሳምንታት ከዚህ በዓል ውጪ የሚያወራው ነገር አልነበረም፡፡ በተጨማሪም ለጉዞው ዝግጅት ሙሉ ድርሻውን ሲያበረክት ከርሟል። በጣም የሥራ ሰው ነበር፡፡ ዳቦ መጋገርና ምግብ ማብሰል ይችላል፡፡ ከሰዎች ጋር እንዴት መከራከር እንዳለበት ያውቃል። እስከማስታውሰው ድረስ በትምህርቱም ጎበዝ ነበር፡፡
ለማንኛውም ቀኑ ደርሶ ጉዞው ተጀመረ። ብዙ ሰው ነበር፡፡ ቢያንስ የናዝሬት ህዝብ ግማሹ አይሆንም ብላችሁ ነው፡፡ አንዱ ከሌላው ጋር በደንብ ይተዋወቃል፡፡ የልጆቹ ጨዋታ፣ ወላጆች የሚለዋወጡት ወሬና አሉባልታ ማለቂያ አልነበረውም፡፡ ሰዎች ምግባቸውን ያካፍላሉ፡፡ አረጋውያን ጥበቃ እየተደረገላቸው መሆኑን ይከታተላሉ። እያንዳንዱ ሰው አህያ አልነበረውምና እኛንም ይካፈሉናል፣ ይጋሩናል፡፡ የሆነው ሆኖ ደረስን፡፡ በነጋታው የአስራ ሁለት ዓመት ልጆች ሁሉ ንፁህ ልብሶቻቸውን ለብሰው ከአባቶቻቸው ጋር ወደ ታላቁ ቤተ መቅደስ ሄዱ፡፡ ደስ የሚል ትዕይንት ነበር፡፡  በህይወታቸው ታላቁ ቀን፡፡ አባትና  ልጆች፡፡
ለምን ያህል ጊዜ ኢየሩሳሌም እንደቆየን ተዘንግቶኛል፡፡ በሀገሩ ህዝብ ዘንድ ብዙ የሚታይና የሚደነቅ ነገር ነበር፡፡ ነገር ግን ወደ መኖሪያችን ለመመለስ ለአንድ ቀን የሚያክል ጊዜ እንደተጓዝን ነበር ልጁ ከእኛ ጋር እንዳልነበር የሆነ ሰው የተገነዘበው። በእርግጥ ብዙ ቤተሰብና ጓደኛሞች በተሰበሰቡበት ቦታ ላይ እንዲህ ያለ ነገር ሊያጋጥም ይችላል፡፡ ወላጆቹ ተጨነቁ። ተመልሰን ሁሉም ቦታ ፈለግነው፡፡ የት እንዳገኘነው ታውቃላችሁ? ቤተ መቅደስ ውስጥ፡፡ ሽማግሌዎች፣ መምህራንና የጥንት ሊቃውንት በሚኖሩበት የቤተ መቅደስ ክፍል ውስጥ፡፡ እንዳዩት ወደ እነሱ የወሰዱት ይመስላል፡፡ እንደተረዳሁት የእነሱን ጉዳይ በጣም የሚያውቅና በተጨማሪም ሽማግሌዎቹ እንዲደሰቱና እንዲመቻቸው የሚያደርግ የሆነ ነገር እሱ ዘንድ እንደነበረ ነው፡፡ ሲሰናበታቸው አዝነው ነበር። ወደ እያንዳንዳቸው እየሄደ በታላቅ አክብሮት ነበር የተሰናበታቸው፡፡ ሁሉንም  ‹‹ለታላቁ ጥበባችሁና ትምህርታችሁ አመሰግናለሁ›› አላቸው፡፡ ከመካከላቸው በዕድሜ የበለፀጉት በምላሹ የእሱኑ ቃላት ተጠቅመው ተሰናበቱት፡፡ የማይረሳ ቅፅበት ነበር፡፡
አዎን ደስ የሚል ሁኔታ ነበር፡፡ ልጁ ግን ስለ ወላጆቹ አላሰበም ነበርና በጣም አስጨነቃቸው፡፡ እናቱና ልጁ በጣም ነው የሚቀራረቡት  ‹‹ለምን እንዲህ አደረግህ፤ በጭንቀት ልናልቅ ነበርኮ! በየቦታው ለሶስት ቀናት ያህል ስንፈልግህ ነበር!›› ብላ ጠየቀችው፡፡ ልጁ በጣም በተረጋጋ ስሜት ያልተለመደ ነገር ተናገረ፡፡ ይህን ንግግሩን ፈጽሞ አልረሳውም፡፡ ወደ ቤተ መቅደሱ እያመለከተ፤ ‹‹ለምን ትፈልጊኛለሽ? በአባቴ ቤት መሆን እንዳለብኝ አታውቂምን?›› አላትና እናቱን ስሞ ወደ ቤታችን ወደ ናዝሬት ሄድን፡፡;
ሶስተኛው አህያ
ሶስተኛው አህያ እያንዳንዱን ቃል ሲያዳምጥ ቆይቶ ተንጠራራና ፋታ ወስዶ የራሱን ታሪክ መናገር ጀመረ፡፡ ‹‹ቤተ መቅደሱን በደንብ አውቀዋለሁ፡፡ እድሜ ልኬን የኖርኩት ኢየሩሳሌም ነው፡፡ ይገርማችኋል፣ የማውቀው ግን የጸሎት ቤት ሆኖ ሳይሆን በሚሰዋ ነገር  ሻጮች፣ በገንዘብ ለዋጮችና በሸቀጥ ነጋዴዎች ተወርሮ ነበር። ከዕለታት በአንዱ ቀን እዚያ ቦታ ላይ ታላቅ ረብሻ ተፈጠረ፡፡ አንድ ወጣት ሰባኪና ተከታዮቹ ሱቆቹን እየገለባበጡ ሰዎቹን አስወጡ፡፡ በዚህ ምክንያትም ያ ሰባኪ ብዙ ችግር ውስጥ ገባ፡፡
‹‹ከመጀመሪያው ጀምር እስቲ›› አለ የመጀመሪያው አህያ፡፡
‹‹እሺ!›› አለና ሶስተኛው አህያ ቀጠለ፤ "እንደሚመስለኝ ዕለቱ እሁድ ነበር። የወጣቱ ሰባኪ ሁለት ጓደኞች፣ እኔና ሌሎች ሶስት አህዮች እምንኖርበት ሥፍራ ይመጣሉ። ለኪራይ የተዘጋጀን ነበርን፡፡ አውጥተው በአደባባዩ በኩል አድርገው ወደ ሰባኪው ዘንድ ወሰዱኝ። ሰባኪው ሊጋልበኝ ይችል ዘንድ ልብሳቸውን እያወለቁ ጀርባዬ ላይ ደለደሉለት፡፡ በእርግጥ ገና ወጣት ነበርኩ። ተጋልቤ አላውቅም፡፡ ጋሪ ጎታች አህያ ነበርኩ፡፡ እና መፈንጨት ጀመርኩ። ወጣቱ ሰባኪ እጁን እላዬ ላይ ሲያሳርፍ ግን ተረጋጋሁ፡፡ ከዚያ ጀርባዬ ላይ ወጣና መሄድ ጀመርን፡፡ በጣም ዝነኛ መሆን አለበት፡፡ እንዲህ ያለ የሰው ብዛት በፍፁም አይታችሁ አታውቁም፡፡ በጣም ነው የሚወዱት! ልስልስ ብሎኝ እንድራመድ ልብሳቸውን መንገዱ ላይ ይወረውሩ፣ ዘንባባ ያነጥፉ  ነበር፡፡ ‹ንጉሥ›፣ ‹ነቢይ›፣ ‹የዳዊት ልጅ› እያሉ ይጠሩታል፡፡ አያሌ ድምጾች ይሰሙ ነበር፡፡
ወደ ቤተ መቅደሱ ሄደና ቅድም እንደነገርኳችሁ ይገለባብጥ፣ ያባርር ጀመር። ከወዳጆች ይልቅ ብዙ ጠላቶች የነበሩት ይመስለኛል፡፡ በሳምንቱ መጨረሻ ላይ ሞተ። በቃ ሞተ፡፡ የማይታመን ነገር ነው። ሁለቱ አህዮች በፀጥታ እያንዳንዷን ቃል እያዳመጡ ነው፡፡ ይሄ ሁሉ እንደተከናወነ አላውቅም ነበር፣ ነገር ግን ቤተ መቅደሱን ካፀዳ በኋላ እዚያው ቆየ፡፡
ብዙ በሽተኞችም ወደ እሱ በመሄድ ፈውስን አገኙ፡፡ የፀሎት ስብሰባዎችን እያካሄደ የሚያስደንቁ ታሪኮችን ይናገራል፡፡ በእርግጥ ነጋዴዎቹና ካህናቱ እንዲሁም ባለሥልጣናቱ አልወደዱትም ነበር፤ ክፉኛ ጠልተውታል። እሱ ግን አላቆመም፡፡ በመጨረሻም ሮማውያን ያዙት፡፡ ወጣቱ ሰባኪ ተከሰሰና ሞት ተፈረደበት፡፡ በሽተኞቹን በመፈወሱና አስደናቂ ታሪኮችን በመናገሩ ካልሆነ በስተቀር  ለምን እንደተፈረደበት አላውቅም።  
ሰቀሉት፡፡ ሲሰቀል እኔ እዚያው ነበርኩ። እያንዳንዱ አህያ በዚያን ዕለት በሥራ ተጠምዶ ነው የዋለው፡፡ ደርዘን ያህል ሰዎችን ወደ ጎልጎታ ሳላመላልስ የቀረሁ አይመስለኝም፡፡ አስደንጋጭና አስፈሪ ሁኔታ ነበር፡፡ እንደሞተ - ረዥም ጊዜ ወስዷል- ሰማዩ ጠቆረ (ገና ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ነበር)፣ ምድር ተናወጠች! ነፍሴ አውጪኝ ብዬ ሸመጠጥኩ፡፡ ይሁን እንጂ የወጣቱን ሰባኪ አስከሬን ተሸክሜ ወደ አንድ የድንጋይ መቃብር ቦታ ለመውሰድ አርማቲያ ከምትባል ቦታ ለመጣ አንድ ሃብታም ሰውዬ ተከራይቼ፤ በዚያኑ ምሽት ተመልሼ ወደ እዚያ ቦታ መሄድ ነበረብኝ፡፡  ይህ ሃብታም ሰውዬ የሰባኪው ጓደኛ ሳይሆን አይቀርም። ሰባኪውን አሳልፎ የሰጠው ለገንዘብ ሲል አንዱ "ጓደኛው" እንደሆነ ታምናላችሁ!
ኋላ ላይ ይህ ጓደኛው እራሱን አጠፋ አሉ። ባያጠፋ ነው የሚገርመው፡፡ የቱ ላይ ነበር ያቆምኩት? አዎን፣ የመቃብር ሥፍራው! ባለሥልጣኖቹ ምን እንዳደረጉ ታውቃላችሁ? መቃብሩን በትልቅ ድንጋይ አሸጉትና ጠባቂ ወታደሮች አቆሙበት። ለምን እንደሆነ ፈጽሞ አልገባኝም፡፡ መቃብሩ ውስጥ ወርቅም ሆነ ሌላ ጌጣጌጥ አልነበረም፡፡ ድንጋዩ ደግሞ ግዙፍ ነው፡፡ በቶኖች የሚመዝን፡፡
የሆነው ሆኖ በቀጣዩ ቀን ቅዳሜ ብዙ ሥራ አልሰራሁም፡፡ ከተማ ውስጥ ያረበበው መንፈስ ያልተለመደ ነበር፡፡ በጣም ፀጥ ያለ፣ ሐዘን ያጠላበት፡፡ በነጋታው ሌሊት፣ ጎህ ከመቅደዱ በፊት አሳዳሪዬ ፈታኝና ለሁለት ሴቶች ሰጠኝ፡፡ አንዷ ጀርባዬ ላይ ስትፈናጠጥ ሌላዋ እየጎተተች መራችኝ፡፡ በጀርባዬ ላይ የተፈናጠጠችው እድሜዋ ገፋ ያለ ነው። ሁለቱም በሐዘን የተሞሉ ይመስላሉ፡፡ ከተናገሯቸው ጥቂት ቃላት እንደተረዳሁት፤ ሁለቱም የወጣቱ ሰባኪ ተከታዮች ሳይሆኑ አይቀሩም፤ የሁለቱም ስም ማርያም እንደሆነ ሰምቻለሁ፡፡ የመቃብር ቦታ ስለሰጠው ሃብታም ሰውዬ፣ ስለ ግዙፉ ድንጋይና ስለ ጠባቂዎቹ ወታደሮች ሰምተዋል። የሚሄዱት የመጨረሻውን ክብር ለመስጠት ነበር፡፡ በመንገዱ ትክክለኛነት እርግጠኞች አልነበሩም፡፡ እኔ ግን አውቅ ነበር፤ ትክክል ነው፡፡  
አሁን የምነግራችሁን ነገር እንድታምኑኝ አልጠይቃችሁም፤ ግን የመቃብሩ ሥፍራ ስንደርስ ጠባቂዎቹ አልነበሩም፤ ድንጋዩ ወደ አንድ ጎን ተንከባሏል፣ በብርሃን የተሞላ የሚመስለው መቃብር ደግሞ  …. ባዶ ነበር።"

Read 2057 times