Print this page
Saturday, 01 May 2021 13:12

ኮሮና በህንድ 18 ሚ. ሰዎችን ሲያጠቃ፤ ከ200 ሺ በላይ ገድሏል

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

     በህንድ ባለፈው ረቡዕ ብቻ ወደ 361 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች በኮሮና ቫይረስ መጠቃታቸውንና 3 ሺ 293 ሰዎችም ለህልፈት መዳረጋቸውን ተከትሎ፣ በአገሪቱ በቫይረሱ የተጠቁ ሰዎች ቁጥር ወደ 18 ሚሊዮን መጠጋቱንና ለሞት የተዳረጉ ሰዎች አጠቃላይ ቁጥር ደግሞ ከ200 ሺህ ማለፉን ዘ ጋርዲያን ዘግቧል፡፡
በህንድ ባለፈው ረቡዕ የተመዘገበው የ360 ሺህ 960 የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር፣ ወረርሽኙ ከተቀሰቀሰበት ጊዜ አንስቶ በመላው አለም በአንድ ቀን የተመዘገበው ከፍተኛ የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች ቁጥር ነው መባሉን ዘገባው አመልክቷል፡፡
በአገሪቱ ባለፉት ሳምንታት የቫይረሱ ስርጭት በከፍተኛ ሁኔታ ማደጉንና በየዕለቱ የሚመዘገቡ ተጠቂዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ እንደሚገኝ የጠቆመው ዘገባው፤ ይህን ተከትሎም ሆስፒታሎች በከፍተኛ ሁኔታ መጨናነቃቸውን፣ የህክምና አገልግሎት ለመስጠት ማዳገቱንና የኦክስጂን እጥረት መፈጠሩንም አክሎ ገልጧል፡፡
በሌላ የኮሮና ቫይረስ ዜና ደግሞ፣ ደቡብ ሱዳንና ማላዊ የመጠቀሚያ ጊዜያቸው በማለፉ አንጠቀምባቸውም ያሏቸውን 78 ሺህ ያህል የኮሮና ክትባቶች ሊያስወግዱ ማቀዳቸውን የገለጹ ሲሆን የአለም የጤና ድርጅት በበኩሉ፤ አገራቱ ውሳኔያቸውን ተግባራዊ እንዳያደርጉ ቢያስጠነቅቅም፣ አገራቱ ግን ማስጠንቀቂያውን ውድቅ ማድረጋቸውን ኦል አፍሪካን ኒውስ ዘግቧል።
ደቡብ ሱዳን ጊዜው ያለፈበት ነው ያለቺውን 60 ሺህ የኮሮና ቫይረስ ክትባት ለማስወገድ ማቀዷን የጠቆመው ዘገባው፤ ማላዊ በበኩሏ ከአንድ ወር በፊት ከተረከበችው 360 ሺህ የአስትራዜኒካ ክትባት ውስጥ 16 ሺህውን አስወግዳለሁ ማለቷን የገለጸ ሲሆን የአለም የጤና ድርጅት ግን ክትባቶቹ ከተመረቱበት ጊዜ አንስቶ እስከ 36 ወራት ጥቅም ላይ መዋል እንደሚችሉ በመግለጽ አገራቱ ክትባቱን ከማስወገዳቸው በፊት በአግባቡ ሊያጤኑትና አማራጮችን ሊፈልጉ ይገባል ማለቱን አመልክቷል፡፡


Read 1830 times
Administrator

Latest from Administrator