Sunday, 02 May 2021 00:00

የግብጽ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለ16ኛ ጊዜ ተራዘመ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  የሶማሊያው መሪ ለ2 አመታት የተራዘመላቸውን ስልጣን ገፍተው የምርጫ ጥሪ አቀረቡ

            የግብጹ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ በመላ አገሪቱ ከ4 አመታት በፊት የተጣለውና ለ15 ጊዜያት የተራዘመው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለተጨማሪ ቀጣይ ሶስት ወራት መራዘሙን ባለፈው እሁድ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡
የአገሪቱ መንግስት እ.ኤ.አ በ2017 የተከሰተውንና 44 ሰዎችን ለሞት የዳረገውን የሽብር ጥቃት ተከትሎ የጣለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፤ ከወቅታዊው የአገሪቱ የደህንነት ስጋትና የጤና አደጋ ጋር በተያያዘ መራዘም እንዳለበት በመታመኑ  ለ16ኛ ጊዜ እንዲራዘም መወሰኑን ይፋ ማድረጉን አልጀዚራ ዘግቧል፡፡
በሌላ የጎረቤት አፍሪካ ዜና ደግሞ፣ የሶማሊያ ምክር ቤት ለቀጣይ ሁለት አመታት ስልጣናቸውን ያራዘመላቸው የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሞሃመድ አብዱላሂ ፎርማጆ፤ ጉዳዩ ተቃውሞና ቀውስ መፍጠሩን ተከትሎ በስልጣን ላይ የመቆየት ሃሳባቸውን መሰረዛቸውን በማስታወቅ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የስልጣን ዘመናቸው በየካቲት ወር ላይ ቢያበቃም ምርጫ መካሄድ ባለመቻሉ በአገሪቱ ምክር ቤት ውሳኔ ስልጣናቸውን ለሁለት አመታት ለማራዘም ተስማምተው የነበሩት ፎርማጆ፣ ውሳኔው በእሳቸው ደጋፊዎችና ተቃዋሚዎች መካከል በዋና ከተማዋ ሞቃዲሾ ውጊያ መቀስቀሱን የዘገበው ሮይተርስ፤ ይህን ተከትሎም ፕሬዚዳንቱ ባለፈው ረቡዕ በይፋ በሰጡት መግለጫ ምርጫ እንደሚደረግ አስታውቀዋል፡፡
በታጣቂዎች መካከል የተፈጠረው ውጊያና ግጭት ያሰጋቸው ከ100 ሺህ በላይ የመዲናዋ ነዋሪዎች ከተማዋን ለቅቀው ወደ ሌሎች አካባቢዎች መሰደዳቸውን የጠቆመው ዘገባው፤ አሸባሪው ቡድን አልሻባብ እየተባባሰ በመጣው ግጭትና አለመረጋጋት ተጠቅሞ የከፋ ጥፋት እንዳያደርስ መሰጋቱንም ገልጧል፡፡

Read 2842 times