Saturday, 01 May 2021 13:29

ደህንነቱ ያልተጠበቀ ጽንስ ማቋረጥን መከላከል፡፡

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(1 Vote)

 ቀደም ባሉት አመታት አንድ ጥናት እንዳስነበበው ባጠቃላይም በብዙ ሀገራት ከ30-60% ከሚሆኑ እርግዝናዎች በተለይም በታዳጊዎችና ወጣቶች እርግዝናው የሚቋረጠው ጽንስና በማቋረጥ ነው፡፡ በጊዜው በኢትዮጵያ ከሚከሰቱ አስር ጽንስን ማቋረጦች ስድስቱ ደህንነታቸው ያልተጠበቀ ነበር፡፡ በተለይም በገጠር በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ከሶስት ወር በሁዋላ ጽንስን ማቋረጥ በጣም የተለመደ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበርም በጊዜው ባደረገው ጥናት እንዳሳየው ሶስት አራተኛ የሚሆኑት ጽንስ ማቋረጦች ከፍላጎታቸው ውጭ በሆነ መንገድ ሲሆን አንድ አራተኛ የሚሆነው ግን ሆን ተብሎ የተቋረጠ መሆኑን ያሳያል፡፡ የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር እንደሚያመላክተው ይህ ቁጥር ትክክለኛ ነው ብሎ ለመውሰድ እርግጠኛ መሆን እንደማይቻልና ለዚህም ምክንያቱ ሴቶች ጽንስ ማቋረጡን ፈልገውት ማድረጋቸውን መናገር ስለማይፈልጉ ወይንም ስለሚደብቁ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡  
በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ጽንስን ደህንነቱ በተጠበቀ መንገድ ማቋረጥ በህግ የተደገፈ በመሆኑ ደህንነቱ ያልተጠበቀ ጽንስን የማቋረጥ ሁኔታ በእጅጉ እንደቀነሰ ያሳያል፡፡ አንዲት ሴት በራስዋ ህይወት ወይንም በልጁ ህይወት ላይ አስቸጋሪ ነገር የሚፈጠር ከሆነ፤ ወይንም እርግዝናውን ተቀብሎ ልጅ ለመውለድ መድረስ ችግር የሚያስከትል ከሆነ፤ ተገዶ መደፈር፤ በዘመድ ወይ ንም በቤተሰብ አባል መደፈር፤ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር የሚያስከትል ከሆነ፤ ሴትየዋ የጤንነት ችግር ካለባት…ወዘተ ጽንሱ በህጋዊ መንገድ በሰለጠነ ባለሙያ እና በህክምና ተቋም ሊቋረጥ እንደሚችል በህግ ተደንግጎአል ፡፡
በአለም ላይ በብዙ ሀገራት ጽንስን ማቋረጥ ደህንነቱ በተጠበቀ መንገድ እንዲፈጸም የሚያስችሉ ድንጋጌዎች ቢኖሩአቸውም በእድሉ መጠቀም ግን ለሁሉም ቀላል አለመሆኑ ይስተዋላል፡፡
 አንዳንድ ጊዜ ሴቶች በተለይም ወጣቶችና ታዳጊዎች ያልተፈለገ እርግዝና በሚከሰት ወቅት ጽንሱን ለማቋረጥ የሚመርጡት መንገድ ደህንነቱ ባልተጠበቀ ሁኔታ የሚፈጸመውን ነው። ለዚህም በምክንያትነት የሚጠቀሰው ደህንነቱ በተጠበቀ መልክ የሚፈጸመው ጽንስ ማቋረጥ የሚጠይቃቸውን ነገሮች ማሟላት ከአለመቻል ጋር ይያያዛል፡፡
የህጎች ጠበቅ ማለት፤
አገልግሎቱ ምቹ ያለመሆኑ፤
ከፍተኛ ዋጋ ወይም ክፍያ መጠየቁ፤
በሁኔታው ከሰው ፊት ለመቅረብ ማፈር፤
የጤና አገልግሎቱን የሚሰጡት ሁኔታውን በቀላሉ የማይቀበሉት መሆኑ፤
አላስፈላጊ የሆኑ መመዘኛዎች …
ለምሳሌም በዚህ ጊዜ ካልሆነ የሚል ወይንም ሌላ ሶስተኛ ወገን በጉዳዩ ጣልቃ እንዲገባ መጠበቅ እና በህክምናው አላስፈላጊ የሆኑ ምርመራዎች እንዲደረጉ ማድረግ እና ባጠቃላይም በተለያዩ ምክንያቶች መዘግየት እንዲኖር ማድረግ…ወዘተ  
የመሳሰሉት ወጣቶቹ ደህንነትን በተጠበቀ መንገድ ጽንስን ወደማቋረጥ እንዳይሄዱ ሊያውኳቸው ይችላሉ፡፡ በአንዳንድ አገራት ኢትዮጵያን ጨምሮ ተገልጋዮች ከላይ የተጠቀሱት ጉዳዮች ብዙም ሳያውኩዋቸው ደህንነቱ በተጠበቀ መንገድ ጽንስን ያቋርጣሉ ቢባልም አሁንም ብዙዎች በራሳ ቸው ምክንያት ደህንነቱ ወዳልተጠበቀ መንገድ መሄዳቸው እየታየ ነው፡፡ ስለዚህም ይህ እንዳይ ሆን አጥብቆ ማስተማርና አሰራሩን ፍትሀዊ ማድረግ እንደሚያስፈልግ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
በአፍሪካ ወደ ግማሽ የሚጠጉት ጽንስ ማቋረጦች ደህንነቱ በተጠበቀ መንገድ ሊባል በማይችል ሁኔታ ስለሆነ በአብዛኛው ደህንነቱ ባልተጠበቀ መንገድ በሚቋረጡ ጽንሶች ምክንያት የሚከ ሰተው ሞት ሴቶችን በእጅጉ ሲጎዳ ይታያል፡፡ አፍሪካ ከአጠቃላዩ 29% ከሚሆነው ደህንነቱ ካልተጠበቀ ጽንስ ማቋረጥ 62% በሚሆነው ሞት ይከሰታል፡፡
ማንኛዋም ሴት ያልተፈለገ እርግዝና ከገጠማት እና ደህንነቱ የተጠበቀ ጽንስን ማቋረጥ ማድረግ ካልቻለች ዞሮ ዞሮ ደህንነቱ ወዳልተጠበቀ ጽንስ ማቋረጥ መሄድዋ አይቀርም፡፡ በተለይም ባላደጉ ሀገራት የሚኖሩት ሴቶች እና በተለይም በግል በኑሮአቸው ድህነት ያላቸው ከሆኑ ደህንነቱ ያልተጠበቀ ጽንስ ማቋረጥን የተሻለ አድርገው እንደሚወስዱ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ በዚህም የተነሳ ጉዳቶችና የሞት መጠኖች ሊያይሉ ይችላሉ። ያልተፈለገ እርግዝናን ለመከላከል የሚወሰዱ መከላከያዎች አገልግሎት ውስን በሆነበት እና ደህንነቱ የተጠበቀ ጽንስን ማቋረጥ ምቹ በሆነ ሁኔታ የማይተገበር ከሆነ ሴቶች በህይወታቸውም ሆነ በአካላቸው ይጎዳሉ፡፡
ጽንስን ስለማቋረጥ ያሉ እውነታዎች፤
በአለም የጤና ድርጅት በ25 September 2020 የወጣው መረጃ እንደሚያሳየው እ.ኤ.አ ከ2015-2019 በአለም ላይ በአመት በአማካይ 73.3 ሚሊዮን ያህል ደህንነቱ የተጠበቀና ያልተጠበቀ ጽንስ ማቋረጥ በፍላጎት ተፈጽሟል፡፡ የዚህ ግምትም 39% በፍላጎት የተፈ ጸሙ ውርጃዎች በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ እድሜአቸው ከ15-19 በሆኑ አንድ ሺህ ሴቶች የተፈጸሙ ነበሩ፡፡
በአለም ላይ ከነበሩ ጠቅላላ እርግዝናዎች ከአስሩ ሶስቱ (29%) እና ከአስሩ ያልተፈለጉ እርግዝናዎች ስድስቱ (61%) በፍላጎት የተፈጸሙ ጽንስ ማቋረጥ ናቸው፡፡
ከላይ ከተጠቀሱት ጽንስ ማቋረጦች ከሶስቱ አንዱ የተፈጸመው ደህንነቱ ባልተጠበቀ ወይንም እጅግ መጥፎ እና ለሕይወት አደገኛ በተባለ ደረጃ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
በአደገኛ ሁኔታ መፈጸማቸው የተነገረላቸው የጽንስ ማቋረጦች ከግማሽ በላይ በአለም ላይ የተፈጸመባቸው ቦታዎች በኤሽያ ብእዛኛውም በደቡብ እና መካከለኛው ኤሽያ ውስጥ መሆኑን የአለም የጤና ድርጅት መረጃ ያሳያል፡፡
በአፍሪካ እና በላቲን አሜሪካ ከተፈጸሙት ከአራቱ ሶስቱ ጽንስ ማቋረጦች ደህንነታቸው ያልተጠበቀ ነበር፡፡
ደህንነቱ ባልተጠበቀ ጽንስ ማቋረጥ ምክንያት የተከሰተው ሞት በአብዛኛው በአፍሪካ ውስጥ ነው፡፡
በየአመቱ ከ4.7%-13.2 % የሚቆጠረው የእናቶች ሞት በዚህ ደህንነቱ ባልተጠበቀ ጽንስ ማቋረጥ ነው ሊባል ይችላል፡፡
እ.ኤ.አ ከ2010-2014 ድረስ ከተፈጠሩት ጽንስ ማቋረጦች ሁሉ 45% በሚል የተመዘ ገበው ደህንነቱ ያልተጠበቀ ነበር፡፡ ይህ ድርጊት ሙሉ በሙሉ በሚያሰኝ ሁኔታ የተፈጸ መው በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት ነበር፡፡
በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት በየአመቱ ወደ 7/ሚሊዮን የሚሆኑ ሴቶች ደህንነቱ ባልተጠ በቀ ጽንስ ማቋረጥ ምክንያት በሆስፒታሎች አልጋ እንዲይዙ ይደረጋል፡፡
ጽንስን ማቋረጥ የአለም የጤና ድርጅት ባወጣው መስፈርት መሰረት በሰለጠነ ባለሙያና በህክምና ተቋማት የሚካሄድ ከሆነ ደህንነቱ የተጠበቀ ይባላል፡፡
ጽንስን ከማቋረጥ ጋር በተያያዘ የሚከሰተው ሞት እና ጉዳት እንዲቀንስ ትምህርትን መስጠት፤ ያልተፈለገ እርግዝና መከላከያ ከጥቅም ላይ እንዲውል ማድረግ፤ ደህንነትን ለማስጠበቅ የሚረዱ ህጋዊ አሰራሮችን ተግባራዊ ማድረግ፤ እና ችግሩ ሲፈጠር ፈጣን ምላሽ መስጠት ያስፈልጋል፡፡

Read 11735 times