Print this page
Saturday, 01 May 2021 13:42

ፅዮን ሚካኤል አንዶም ፋሽን ዲዛይነርና የንግድ ስራ ፈጣሪ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

"--በግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴና በእቴጌ መነን ለመጀመሪያ ጊዜ የተዋወቀውን ባህላዊ ካባችንንም፣ ደማቅ ቀለማት ፣ የተዋቡና የረቀቁ ጥልፎችን በመጠቀም በዘመናዊ መንገድ ነበር የሰራሁት። የማስታወቂያ መርኼ፤ “ዘመናዊና ፍፁም ኢትዮጵያዊ ለመሆን ከፈለጉ፣ ምርጫዎ የፅዮን ጥበብ ይሁን” የሚል ነበር።--"
 
               የፋሽን ሥራዬን እንደ ጉድ ነበር የምወደው። ምንም እንኳን “ጽዮን ጥበብ” የተሰኘውን የንግድ ድርጅቴን ያቋቋምኩት በ43 ዓመት ዕድሜዬ ላይ ቢሆንም፣ ከዚያ በፊት በነበሩት ጊዜያትም የጥልፍና የልብስ ዲዛይነሮችን ማውጣትና መስራት ያስደስተኝ ነበር። የልብስ ስፌት ስራን አሃዱ ብዬ የጀመርኩት፣ ለአሻንጉሊቶቼ ትንንሽ ልብሶችን በመስፋት ነበር። በኋላ ላይ ደግሞ የራሴን ልብሶች እየሰፋሁ መልበስ ጀመርኩኝ። አባቴ ገና የ12 ዓመት ልጅ ሳለሁ፣ የሰጠኝ ቆንጆ የስፌት መኪና ዛሬም ድረስ አብሮኝ አለ። ሰዎች ሁሌም አለባበሴን ያደንቁልኝ ነበር። በየእለቱ በዘመናዊ መንገድ ተሽቀርቅሬ መልበሴ፣ ንግድ ከመጀመሬ በፊት ለ25 ዓመታት ገደማ ያከናወንኩትን ገንዘብ የማሰባሰብ የበጎ ፈቃደኝነት ሥራ ጨምሮ በብዙ ነገሮች ስኬታማ እንድሆን አግዞኛል ብዬ አምናለሁ። አንድ ወዳጄ በአንድ ወቅት፣እኔ የምለብሳቸውንና የማደርጋቸውን ባርኔጣዎች ለማየት ስትል ብቻ ቤተ-ክርስቲያን ትመጣ እንደነበር ነግራኛለች።
የንግድ ስራዬን ከመጀመሬ በፊት ባሉት ጊዜያት ግን ፣ የኢትዮጵያን ባህላዊ ዲዛይነሮችና ጥሬ እቃዎች በመጠቀም ዘመናዊና ተመራጭ አልባሳትን ለመፍጠር እንደምችል አስቤ አላውቅም። ፅዮን ጥበብን ከከፈትኩ በኋላ የፈጠርኩትን ዓይነት ሞድ (ስታይል) ማለቴ ነው። ይሄንንም የጀመርኩት በ1946 ዓ.ም ባለቤቴ በዲፕሎማትነት በተመደበበት በለንደን የቤኪንግሃም ቤተ-መንግስት የእራት ግብዣ ላይ በተከሰተ አጋጣሚ ነው። በእለቱ ድንቅ ቪልቬትና የሐር ቀሚስ ነበር የለበስኩት። ራሴ በቪክቶሪያን ሞድ ዲዛይን አድርጌ የሰራሁት ነበር። የህንዱ ኮሚሽነር ሚስት ወደ እኔ መጣችና፣ “ኦ! በጣም ተውበሻል!” አለችኝ። እኔ ደግሞ ማድነቋ መስሎኝ ነበር። “ባህላዊ የሀገር ልብስ የላችሁም እንዴ?” ብላ ስትጠይቀኝ ነው፣ ለማለት የፈለገችው በደንብ የገባኝ። እሷና በህንድ ቡድን ውስጥ የተካተቱት ሴቶች በሙሉ፣ የአገራቸውን ባህላዊ ልብስ “ሳሪ” ነበር የለበሱት። ያን ጊዜ ነው የኢትዮጵያ ባህላዊ ጥሬ እቃዎችንና ሞዶችን ተጠቅሜ እንዴት ዘመናዊ የፋሽን ልብሶችንም መፍጠር እንደምችል ማሰብ የጀመርኩት።
“ፅዮን ጥበብ”ን ስከፍት የኢትዮጵያ ዕፁብ ድንቅ የእጅ ፈታዮች፣ ሽማግሌዎችና የእጅ ጥልፍ ሙያተኞች በአስደናቂ ክህሎት የሚሰሩትን ግሩም ንድፍ በመጠቀም፣ ዘመናዊ ልብሶችን ዲዛይን ማድረግ ጀመርኩ። ባህላዊ ቀሚሶችና ነጠላዎች ጥለት ላይ የምናየውን ውብ የእጅ ጥልፎች እየተጠቀምኩ በባህላዊው የኢትዮጵያ ጥበብ ተራቀቅሁበት። በእርግጥ የቀሚሱን ቅርፅ ዘመናዊ ገፅታ  አላብሻለሁ። ቀለማቱን፣ ዲዛይኖቹንና ጥበቡን አጠቃቀም ኢትዮጵያዊ መልኩን እንደጠበቀ ከዘመኑ ጋር እንዲጣጣም ለማድረግ ጥሬአለሁ።
በግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴና በእቴጌ መነን ለመጀመሪያ ጊዜ የተዋወቀውን ባህላዊ ካባችንንም፣ ደማቅ ቀለማት ፣ የተዋቡና የረቀቁ ጥልፎችን በመጠቀም በዘመናዊ መንገድ ነበር የሰራሁት። የማስታወቂያ መርኼ፤ “ዘመናዊና ፍፁም ኢትዮጵያዊ ለመሆን ከፈለጉ፣ ምርጫዎ የፅዮን ጥበብ ይሁን” የሚል ነበር። እጅግ ብዙ ሠርገኞችን በጥበብ ሥራዎቼ ሞሽሬ ድሬአለሁ። የንጉሳውያን ቤተሰቦችን ጨምሮ አብዛኞቹ የአዲስ አበባ ቱጃር ወይዛዝርት፣ የጥበብ አልባሳትን ለመግዛት ወደ እኔ ይመጡ ነበር። ብዙ ጊዜ ሱቄ እየመጡ ይጎበኙኝም ነበር። እኔም እስከ ሌሊቱ አጋማሽ ድረስ  በትጋት ነበር የምሰራው።
ያኔ ሃሳቤ ሥራዬ ላይ ብቻ ነበር ማለት እችላለሁ። በሥራ  የማሳልፋትን እያንዳንዷን ደቂቃ፣ በጣም ነበር የምወዳት። ለዚያም ይመስለኛል በህልሜ ሳይቀር የተለያዩ የጥበብና የጥልፍ ንድፎችን የማየው፣ ጠዋት የምነቃው ደግሞ ዲዛይኖቹ በአዕምሮዬ ቅርፅ ይዘው ነበር። የቀጠርኳቸው ሃምሳ የሽመና ባለሙያዎች፣ እኔ በተከራየሁትና ሁላችንም በምንሰራበት ግቢ ውስጥ ነበር የሚኖሩት። በሳምንት አንዴ በግ እያረድንም አብረን ምሳ እንበላለን። በእውነቱ ጥሩ ጊዜ ነበር ያሳለፍነው። ጥልፎቹ ሙሉ በሙሉ የሚሰሩት ለዚሁ ተብለው በተመረጡ ወንድ የጥልፍ ሙያተኞች እጅ ነበር። እያንዳንዱን ልብስ የምሰፋው ደግሞ ራሴ ነበርኩ። ያኔም እንደ አሁኑ  በስራዬ ቅንጣት እንከን ማየት አልፈልግም ነበር። እንደሚመስለኝ ይሄንን ባህርይ የወረስኩት ከአባቴ ነው። አባቴ አይበገሬና ጠንካራ ሰው ነበር። አብዛኛውን የአዋቂነት ህይወቱን ባሳለፈበት በሱዳን ሃገር “ጥቁር አንበሳ” እያሉ ይጠሩት ነበር። በደርግ አገዛዝ ለሰባት ዓመታት በታሰርኩበት ጊዜ ካልሆነ በቀር፣ የንግድ ሥራዬን ለአርባ ዓመታት ያህል አንዴም ላላቋርጥ ገፍቼበታለሁ። በ2003 ዓ.ም በ89 ዓመት እድሜ ላይ ነው የመጨረሻ ልብሶቼን የሰፋሁት።
ወላጆቼ በእኔ ብቻ ሳይሆን በወንድሞቼና በእህቴ ሕይወት ውስጥም አዎንታዊ ተፅእኖአቸው ከፍተኛ ነው። አባቴ በወጣትነቱ ከኤርትራ በመሸሽ ትምህርቱን ለማጠናቀቅ በሄደባት የካርቱም ከተማ ውስጥ ነበር በ1914 ዓ.ም የተወለድኩት። እስከ 18 ዓመቴ የኖርኩትም እዚያው ነበር። አባትና እናቴ እስከ አራተኛ ክፍል የተማሩት፣ ኤርትራ አስመራ አቅራቢያ በሚገኘው ቤሌዛ የተባለ የስውዲናውያን ሚሽን ትምህርት ቤት ውስጥ  ሲሆን አምስት ቋንቋዎችን የሚናገረው እጅግ ብሩህና ብልሁ አባቴ፣ ሱዳን ውስጥ በቅኝ ገዢው የእንግሊዝ መንግሥት የመቀጠር እድል አግኝቷል። መጀመሪያ በደህንነት አገልግሎት ውስጥ የሰራ ሲሆን፣ በመቀጠልም የሱዳን ገዢ ቤተ-መንግስት ዳሬክተር በመሆን አገልግሏል። በመጨረሻም የሱዳን  አንድ ክፍለ ሃገር ዋና አስተዳዳሪ ሊሆንም በቅቷል። እናቴም የቀለም ትምህርት የዘለቃት ነበረች። ለሃይማኖቷ ያደረችና መጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪም ስለነበረች፣ አምስታችንንም ታታሪዎችና ሃይማኖተኞች አድርጋ ነው ያሳደገችን፤ ከእንቅልፋችን ስንነሳ ጸሎት አድርሰን መዝሙር እንዘምራለን። በምግብ ሰዓት እንጸልያለን። ማታ ፀሎትና መዝሙር እናደርሳለን። ብዙዎቹን የቤት ውስጥ ስራዎች እናቴ ራሷ ነበረች የምትሰራው። ምግብ ታበስላለች፣ ልብስ አጥባ ትተኩሳለች፣ ቤት ታፀዳለች… ብቻ የሚቀራት ነገር አልነበረም። እኔም ተግቶ መስራትን የተማርኩት ከእሷ ነው። ዛሬም እንኳን በ90 ዓመት ዕድሜዬ ምግቤን የማበስለው ራሴው ነኝ። ብረት ድስቶችንና መጥበሻዎችን እስኪያብረቀርቁ ድረስ እፈትጋለሁ። ቤት አፀዳለሁ። እተጣጠባለሁ። እንደ ወንድሞቼ ሁሉ ለሀገር የማገልገል ፋይዳን ከአባቴ ተምሬአለሁ።
“ልጆቼ በውጭ ሀገር ትምህርታቸውን ከጨረሱ በኋላ፣ ወደ ሀገራቸው ተመልሰው ኢትዮጵያን ለመገንባት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ያበረክታሉ” በማለት አባቴ ለንጉሱ ቃል ገብቶላቸው ስለነበር፤ ኢትዮጵያ ነጻነቷን ከጣሊያን ስትቀዳጅ ሁላችንም ተሰባስበን አገራችን ገባን።
በ1933 ዓ.ም ትዳር ይዤና የበኩር ልጄን እርጉዝ ሆኜ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ ስመጣ፣ አዲስ አበባ ከአሁኑ ፍጹም የተለየች ነበረች። አንዳንድ ሰዎች ግን ያንን እውነታ ለማስታወስ የሚፈልጉ አይመስሉም። ሆኖም ሀቁን ማወቅ በጣም አስፈላጊ ነው ብዬ አምናለሁ። ከተማዋ በጣም ድሃ፣ ያልሰለጠነችና ያላደገች ነበረች። አብዛኛዎቹ ነዋሪዎች ያልተማሩና መሀይማን ነበሩ። ህጻናት ፊደል የሚቆጥሩት ዛፍ ስር ነበር። የግል ንጽህናን በመደበኛነት መጠበቅ፣ ለጥቂቶች ካልሆነ በቀር ለአብዛኛው ህዝብ ቅንጦት ነበር። ሀገሪቱን በመገንባት ረገድ እጅግ በርካታ የሚከናወኑ ስራዎች ቢኖሩም፣ ብዙዎች  ልብ አላሏቸውም ነበር። ሀገሬን በምን መልኩ መርዳት እንደምችል እስክገነዘብ ድረስ፣ እኔም እንደነዚህ ሰዎች ነበርኩ። የማታ የማታ ግን፣ ከፋሽን ዲዛይን ባሻገር ሌላውን ትልቁን ተሰጥኦዬን ለማወቅ ችያለሁ። ይኸውም ሌሎች ትኩረት የተነፈጋቸው ማህበራዊ ጉዳዮችን ለማገዝ የሚውል ገንዘብ በእርዳታ ማሰባሰብ ነበር።  አዲስ አበባ ከገባሁ በኋላ በነበሩት የመጀመሪያዎቹ 25 ዓመታት  የሰራሁት ይሄንን ነው።
ለንደን የተመደበው ባለቤቴ፣ ሀገሬ ገብቼ ጥቂት እንደቆሁ ነበር፣ ለእኔና ለህጻኑ ልጃችን ከእንግሊዝ ጥቂት ስጦታዎችን ከጣሊያን ወረራ በፊት በነበረው የእንግሊዝ አምባሳደር ሚስት በእመቤት ባርተን በኩል የላከልኝ። ባርተን ወዲያው ነበር ለበጎ አድራጎት ስራ የመለመለችኝ። ልክ እንደ እሷ የቆርቆሮ ኩባያ አንገቴ ላይ አስራልኝ፣ በኢትዮጵያ የቀይ መስቀል ቻርተርና የሴቶች ማህበር እንዲቋቋም ለማገዝ፣ ተዟዙሬ ገንዘብ እንዳሰባስብ አሰማራችኝ። እኔ ግን ገንዘብ ለማሰባሰብ ምን ማድረግ እንዳለብኝ የማውቀው ነገር አልነበረም፡፡ አንዳንድ ነገሮች እንዲነግረኝ ብዬ ወደ ወንድሜ አማን ቢሮ አመራሁ። ከዚያም የጦር ሰራዊቱ አዛዥ ጋ ሄድኩኝ። የመጀመሪያውን የድጋፍ ገንዘብ የሰጠኝ ይሄው አዛዥ ሲሆን፣ ተጨማሪ ድጋፍ ማግኘት እንድችል ወደ ሌሎች ጓደኞቹ ወሰደኝ። ከዚያ በፊት ከወንዶች ጋር አውርቼም ሆነ ውዬ ባላውቅም፣ ገንዘብ በመለመን በኩል ግን እጅጉን የተዋጣልኝ ሆንኩኝ። ከዚያ በኋላማ ማን ይቻለኝ! እየተሽቀረቀርኩ ወደ ንግድ ተቋሟት፣ ሱቆችና ልሂቃን መኖሪያ ቤት እየሄድኩ ድጋፍ መጠየቅ፣ የገንዘብ ማሰባሰቢያ ፕሮግራሞችንና ፓርቲዎችን በበጎ ፈቃደኝነት ማዘጋጀት ቀጠልኩ። “ፍቃድ ያልወጣለት ልመና” እያልኩ በምጠራው በዚህ የበጎ አድራጎት ስራ ላይ፣ ለ25 ዓመታት ገደማ ከቆየሁ በኋላ፣ ለብዙዎቹ መዲናዋ ነዋሪዎች ዘንድ ታዋቂ ሆንኩ፤ ይህም ለፋሽን የንግድ ድርጅቴ ደንበኞችን በማፍራት ረገድ በእጅጉ ጠቅሞኛል።
ከእነዚያ ጊዜያት ሁሉ በኋላ አገራችን በከፍተኛ ሁኔታ ተለውጣለች። አገሪቱ እያደገችና እየዘመነች ነው። እኔ ግን ያ አይደለም ትኩረቴን የሚስበው፤ በቤት ውስጥ ያለው ጉዳይ እንጂ። በወላጆቼም ሆነ በእኔ ጊዜ፣ ወንዶች እኛ ሴቶች ላይ ጉልበተኛ ነበሩ። ያ ጥሩ አልነበረም። አሁን ወንዶች እንደ ቀድሞ ዘመን ሴቶችን ባለመጨቆናቸው በጣም ደስተኛ ነኝ። ሆኖም አሁን ደግሞ ነገሩ መረን የለቀቀ ይመስላል። ሴቶቹም ከወንዶቹ እኩል ውጪ እየዋሉ ነው የሚገቡት። በዚህም የተነሳ የቤቱ ነገር ሙሉ በሙሉ ተዘንግቷል። ቤቱ ሲዘነጋ ደግሞ ቤተሰቡም አብሮ ይዘነጋል። ሴት ልጅ የቤተሰቡ ዘውድ ናት፤ ቤት ውስጥ በጣም ትፈለጋለች። እኛ ሴቶች ትኩረት ነፍገነው የቆየነውን የቤተሰብ ጉዳይ መልሰን ትኩረት እንሰጠዋለን ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። ያለ ቤተሰብ ባህል የለንም፤ያለ ቤተሰብ ሀገር የለንም፤ ያለ ቤተሰብ የወደፊት ተስፋ የለንም።
ሴቶች ለህብረተሰብ ግንባታና ለልማት የሚያበረክቱትን እጅግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ፣ ፓርላማው በቅጡ ይረዳው ዘንድ ብገዳደረው ደስ ይለኛል። በሀኪምነት፣ በህግ ባለሙያነት፣ በኢንጅነርነት፣ በንግድ ስራ ፈጣሪነት ወዘተ... ከቤት ውጭ የሚሰሩ ሴቶች ግማሽ ቀን እየሰሩ፣ የሙሉ ቀን ክፍያ ሊታሰብላቸው ይገባል ብዬ አምናለሁ። ያኔ ግማሹን ቀን ለቤታቸውና ለቤተሰባቸው ያውሉታልና።
"--አሁን ደግሞ ነገሩ መረን የለቀቀ ይመስላል። ሴቶቹም ከወንዶቹ እኩል ውጪ እየዋሉ ነው የሚገቡት። በዚህም የተነሳ የቤቱ ነገር ሙሉ በሙሉ ተዘንግቷል። ቤቱ ሲዘነጋ ደግሞ ቤተሰቡም አብሮ ይዘነጋል--"


Read 1346 times
Administrator

Latest from Administrator