Saturday, 01 May 2021 13:49

ከክብና ከአጽም ጋር የመቆዘም ጣጣ (ገብረክርስቶስ ገጣሚውና ሰዓሊው)

Written by  ያዕቆብ ብርሃኑ
Rate this item
(2 votes)


                ‹‹…ለእኔ ኢትዮጵያዊ እንደ ኢትዮጵያዊ ነው መኖር የሚችለው፡፡ ቀላል ምሳሌ ልስጥህ… ብሔራዊ ባንክን ሲሰራ አርክቴክቱ ከመስራቱ
በፊት በየክፍለ ሀገሩ እየተዘዋወረ አጥንቶ ነበረ፡፡ ከዚያ ውስጥ የተረዳው ነገር ቢኖር ክብ ሰርተን የምንኖር ህዝቦች መሆናችንን ነው፡፡ ክብ ሰርተን እሳት እንሞቃለን፡፡ ክብ እንጀራ እንበላለን፡፡ ክብ ምጣድ አለን፡፡ ክብ ምድጃ አለን፡፡ አምባሻችን ክብ ነው፡፡--"
                  
                …ለመሆኑ አንተ የጥበብ ወዳጅ ነህን? እናስ ያን አደገኛ ጀብደኛውን፣ ከእኛ ቢሊዮን ቢሊዮን ምንትስ ጊዜ የሚገዝፈውን ኮከብ እንደ ኳስ መጫወቻ ጠጠር የናቀውን፤ ሲፈልግ በቀለም ሲሻው በፊደል ተራቆ ያለፈውን ትንታግ ትንፋሽ፤ የፒካሶ ዘመነኛ ጠቢብ ታውቀዋለህ? ገብረክርስቶስ ደስታ ነገዎን ማለቴ ነው፡፡
ከአንድ ዓመት በፊት አንድ የመጻሕፍት ነጋዴ ወዳጄ ከአንባቢ እጅ የሚሸጡ መጻሕፍት አግኝቻለሁና በመምረጥ እርዳኝ ብሎ እያንደረደረ ወደ አንድ የተረሳ ቤተ መንግስት የሚመስል ግቢ  አስገባኝ፡፡ ለካ ችላ ሲባል አንጀት የሚያላውሰው ሰው ብቻ አይደለም፡፡ ቤትም ጭምር ነው፡፡ የቤቱ ባለቤት አርመናዊ ነበረች አሉ፡፡ አሉ ነው እንግዲህ፡፡ በቅርቡ ሞተች ያሉም መሰለኝ። ቤቱ መብራት እንኳን አጥቶ በመጎሳቆሉ እየተጥበረበርኩ፣ ከተደረደሩ የሚያታክቱ የፈንሳይኛ ቋንቋ መጻሕፍት መካከል ትርጉም ያለው የሚነበብ ነገር መፈለግ ጀመርኩ፡፡ ከዚያ ሁሉ የተደረደረ መጽሐፍ መሀል በእንግሊዝኛ የተጻፈ የሆነ ነገር ማየት አለመቻሌ እየገረመኝ እያለ፣ ድንገት በእንግሊዝኛና በፈንሳይኛ ቋንቋ African Art በሚል ርዕስ በ1969 እ.ኤ.አ የተዘጋጀ መጽሔት ነገር አገኘሁ፡፡
ገላልጬ ስመለከት በዚሁ መጽሔት ላይ ገብሬ በህይወት ዘመኑ የሰጠው ብቸኛው (?) ቃለ ምልልስ ተካቶበት አየሁ፡፡ ያስደነቀኝ መች ይሄ ሆነና፡፡ ገብሬ ከመጽሔቱ አዘጋጆች ጋር ያደረገውን ቃለ ምልልስ ለአንድ Herbert M. Cole ለተባለ ወዳጁ  ፈርሞ መስጠቱንም ተመለከትኩ፡፡ በቃ በአካል የጨበጥኩት፣ ኸረ እንዲያውም ለእኔ ለራሴ ፈርሞ የሰጠኝ ሁሉ መሰለኝ፡፡ ኢንተርኔት ተጠቅሜ ባደረግሁት ማጣራት፣ ይሄው ኸርበርት የተባለው ግለሰብ skip በሚለው ቅጽል ስሙ የሚታወቅ  በuniversity of California Santa Barbara ለ35 ዓመታት የአፍሪካን ስነ ጥበባት ያስተማረ  emeritus professor of art history and architecture የነበረ ግለሰብ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ መጽሔቱ በምን ተዓምር ከእጁ ወጥቶ እዚህ ስርቻ እንደተገኘ ግን እግዜሩ ይወቀው፡፡
ቃለ ምልልሱን ማንበቤ ግን ስለ ገብረክርስቶስ በጥልቀት እንዳስብ አነሳሳኝ። ለሰው አውሼው ያልተመለሰልኝን የግጥም መጽሐፉን የማንበብ ፍላጎቴ አገርሽቶብኝ፣ በማግስቱ አሳድጄ ግማሽ ሺህ በተጠጋ ገንዘብ ገዛሁት፡፡ ለዚያውም ቅጂውን እኮ ነው… ስድስት ኪሎ የሚገኘውን በስሙ የተከፈተውን የስዕል ሙዚየም ጎበኘሁ፡፡ ስለ እሱ ተጽፈዋል የተባሉ አንዳንድ ሂሶችና አጫጭር ትንተናዎችን ለማየት ሞከርኩ፡፡  
አንድ ነገር ግን ከሁሉም  በላይ ነፍሴን ሰቅዞ ያዛት፡፡ ለመሆኑ ገብረክርስቶስ ደስታና ክብነት፣ በክብ የመራቀቅ መሻት ምንና ምን ናቸው? በሙዚየሙ ውስጥ ካየኋቸው 30 የሚሆኑ ስዕሎች በተለይ ከ1966 ዓ.ም በኋላ ከተሳሉት 90 በመቶ ያህሉ ከክብ ጋር የሚላፉ፣ ከክብ ጋር የሚጋፉ፣ ለክብነት የሚያጎነብሱ፣ ተመልሶ ለሚመጣ ሲሲፐሳዊ ሰቀቀን የተጣሉ ናቸው፡፡ ግጥሞቹንም ተመልከቱ - አብዛኞቹ እንደ ተለምዷዊው የስንኝ አደራደር ‹ደደደደ … ደደደ› ብለው በdead end የሚጨርሱ ሳይሆኑ ተመልሶ፣ ተመላልሶ በሚመጣ በሚዘመር አዝማች ዓይነት ተንጠልጥለው የሚቀሩ ይሆኑባችኋል፡፡ ተዘበራርቀው (evenly) የቀረቡ ዓይነተ ብዙ ቀለበቶች…
‹‹ግማሽ ቀልድ አላውቅም!
           ...
መንገድ ስጡኝ ሰፊ
          …
የመሬት ቁራጭ ነኝ
ታሪኳን የምጽፍ
በጥቁር ወረቀት በሰማይ ብራና፣
ስጓዝ እተዋለሁ በጠፈር ላይ ፋና፣
ስሄድ እኖራለሁ…
ሰማየ ሰማያት እመዘብራለሁ።
የተዘጋውን በር እበረግዳለሁ፡፡
የሌለ እስቲፈጠር፣ የሞተ እስኪነቃ፣
በትልቅ እርምጃ ከመሬት ጨረቃ
                      ከጨረቃ ኮከብ፣
ካንዱ ዓለም ወደ አንዱ፣
                        ስጓዝ እፈጥናለሁ…
በጸሐይ ላይ ቤቴን ጎጆ እቀልሳለሁ፡፡
ግማሽ ቀልድ አላውቅም!
ከሲዖል ሚሊዮን ቢሊዮን ልቃጠል፡፡
ከገሃነመ እሳት ሚሊዮን ነበልባል፡፡
መንገድ ስጡኝ ሰፊ…
የሚከተለውን ግጥም የጋበዟችሁ ዶክተር ዮናስ አድማሱ ‹ለመንገድ ሥጡኝ ሰፊ› የገብሬ የግጥም መጽሐፍ በጻፉት መግቢያ ላይ ነው፡፡ ግጥሙን ብትፈልጉ ከላይ ካሻችሁም ከሥር ጀምራችሁ እንደመሰላችሁ እስኪታክታችሁ በክብ እንድታነቡት ተጋብዛችኋል፡፡ አይገርምም? እንዴትም ብታነቡት ትርጉሙ ቅንጣት ታህል አይዛባም፡፡ ይኸው ካላመናችሁኝ ድረሱበት…
  ለስዕል
  አያልቅም ይህ ጉዞ -------
ማስመሰል------- መተርጎም
በቀለም መዋኘት፡
       በመሥመር መጫወት፤
       ከብርሃን መጋጨት፤
ለማወቅ ለመፍጠር ባዶ መግባት
መፈለግ - - - - መፈለግ - - - - -
አዲስ ነገር መፍጠር፡፡
ከማይታየው ጋር ሄዶ መነጋገር፤
           ሕይወትን መጠየቅ፤
        ሐሳብን መጠየቅ
        ዓለምን መጠየቅ
መሄድ፤ መሄድ፤ መሄድ - - - -
ከጨረቃ በላይ፤
         ከኮከቦች በላይ፤
         ከሰማዩ በላይ፤
መጓዝ ወደ ሌላ ------- ባዶ ቦታ መግባት፡፡
በሐሳብ መደበቅ፤
       መፈለግ------- ማስገኘት፡፡
አያልቅም ይህ ጉዞ - - - - - - - -
እናስ ይሄ ሁሉ ከክብ ጋር የመጫወት፣ ከክብ ጋር የመላፋት፣ በክብ የማርገድ፣ ከክብ ጋር የመቅበጥበጥ፣ በክብ የመቆዘም፣ በክብ የመበርገግ፣ ከክብ ጋር የመባተል አዙሪት እንዲያው ዘፈቀደ ነበር ለማለት እንደፍራለን እንዴ? ዘፈቀደ ካልሆነ ይሄን ሁሉ ከቀለም ወደ ቃል፣ ከቃል ወደ ቀለም የመቁነጥነጥ፤ ከዚያው ወጥቶ ወደዚያው የመውተርተርን የኪነት ዛር ምን እንበለው?
ክብ ዋናውና ሌሎች ምልክቶች ሁሉ ከእርሱ የሚቀዱበት prototype ምልክት ነው፡፡ ክብነት የዑደት አመልካችም ይሆናል። ክብነት ፍጹም ነጻ መሆንን የመሻት ሲቃም ነው፡፡  ጅማሬና ፍጻሜው አንድ የሆነ ነገር ታውቃለህ? እሱ እኮ ክብ ነው! በክብ መጫወት ከእግዜሩ ጋር መነጋገር ነው። ጠፈርን የመፍጠር ሂደት ላይ የመሳተፍ፣ ኸረ እንዲውም ራሱ እግዜሩን የመሆን ሂደትም ይሆናል። ‘God is a circle whose centre is everywhere and whose circumference is nowhere’  እንዲል Hermes Trismegistus –
ይሄን እግዜርን የመጨበጥ፣ ከእርሱ ጋር የመነጋገር፣ ከእርሱ ትንፋሽ ጥቂት የመካፈል ዕድል ያልቀናው ስልብ ምናብ ጠቢብማ በከባድ አንድ እርምጃ ከብርሃን ሁሉ ቀድሞ ከመሬት ጨረቃ፣ ከጨረቃ ጸሐይ ከአንዱ ዓለም ወደ አንዱ መኳተንን፣ ኮከብን የጠጠርን ያህል አሳንሶ የሚያሳይ መግዘፍን ሊያስበው አይችልም፡፡ በክብ ለሚራቀቅ ሁሉ አሁን እና ጥንት የጊዜ ርቀት የላቸውም፡፡ በክብ ወደፊትም ብታነበው ወደ ኋላ ሞትና ሕይወት አፈክሮታቸው አንድ ነው።
Y B:
Y B:
ከላይ የጠራናቸው ዶክተር ዮናስ በተጠቀሰው የመግቢያ ጽሁፋቸው ላይ የገብሬን በክብ የመቁነጥነጥ ኪናዊ ተራክቦ ‹‹አብሮ መሆን፣ ናፍቆት፣ ወደነበሩበት ዳግም ማሰብን፣ ወትሮ መመለስን (the Eternal Return) አመልካች ነው…›› ይሉናል፡፡ ይቀጥሉናም፡፡ ‹‹ምሥጢር››ን ወይም ‹‹ምሥጢራዊነት›› (mystery or mysteriousness) እንያዝ - የትርጓሜ ጓዛችን፣ መሣሪያችንም ስለሚሆን፡፡ አንድም ‹‹ክብን›› ‹‹ክበብን›› የውህድነት ወይም የፍጽምና (unity or perfection) ምልክት አድርገን እናየዋለን፡፡ መግቢያ መውጫውን፣ መጀመሪያ መጨረሻውን እስካላወቅነው የኅምቱነት (immaculateness) ምሳሌ ሊሆን ይችላል… ክብ ወይም ክበብ የሕይወት ዑደትም ሊሆን ይችላል፡፡…››      
ለእኛ ለኢትዮጵያዊያንማ በተለይ ክብ አንድምታው ብዙ ነው፡፡ ሮፍናን ኑሪ በነሐሴ 2011 ዓ.ም ከቴዎድሮስ ተክለዓረጋይ ጋር በታዛ መጽሔት ባደረገው ቃለ ምልልሱ፤ ስለ ክብነትና አትዮጵያዊነት የተናገረውን ለምን አላስነብብህም፡-
‹‹…ለእኔ ኢትዮጵያዊ እንደ ኢትዮጵያዊ ነው መኖር የሚችለው፡፡ ቀላል ምሳሌ ልስጥህ… ብሔራዊ ባንክን ሲሰራ አርክቴክቱ ከመስራቱ በፊት በየክፍለ ሀገሩ እየተዘዋወረ አጥንቶ ነበረ፡፡ ከዚያ ውስጥ የተረዳው ነገር ቢኖር ክብ ሰርተን የምንኖር ህዝቦች መሆናችንን ነው፡፡ ክብ ሰርተን እሳት እንሞቃለን፡፡ ክብ እንጀራ እንበላለን። ክብ ምጣድ አለን፡፡ ክብ ምድጃ አለን። አምባሻችን ክብ ነው፡፡ ድፎአችን ክብ ነው። ቆጮው ክብ ነው፡፡ ጎጆ ቤቶቻችን ክብ ናቸው፡፡ ክብ ሰርተን እንጨፍራለን፡፡ ክብ ቤተ ክርስቲያን አለን፡፡ ክብ መስጊድ አለን። መቀጠል ትችላለህ፡፡ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ ሀገራችንን ስናይ በማንነታችን ውስጥ ክብ ትልቅ ቦታ አለው፡፡ ስለዚህ ከክብ ነገር ተነስቶ ያንን ሕንጻ ሰራው፡፡ ህንጻው በጣም ዘመናዊና በአውሮፓዊያን ደረጃ የተሰራ ነው፡፡ ግን ቅርጹ ፍፁም ኢትዮጵያዊ… ያ ነገር ትክክለኛ ስልጣኔ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡››
የገብሬ ኑረት ግን አሳዛኝ ገጽታም ነበረው፡፡ ቀለሞች ስለ ምን ሁልጊዜ እንከን እንደሚከተላቸው አላውቅም፡፡ በቀለም እየተምነሸነሹ፣ በቀለም እየተራቀቁ ቀለምን የማጣትን፣ ለምጽን የመልበስን ክፉ እጣ አስቡት፡፡ ልክ በድምጽ እየተጠበበ በጊዜ የመስማት ችሎታውን እንዳጣው ቪትሆቨን፣ የገብሬም ነገር የሆነ የጠየመ ቁዘማ ውስጥ ይከታል፡፡ ስራዎቹም ላይ ጎልቶ ይታያል።
የገብሬ ኪናዊ የማቅለም ጉዞ እንዲያው በክብ የመቅበጥበጥ የቅንጦት ሀሰሳ ብቻ አልነበረም፡፡ የሚያርድ ፍርሃት ውስጥ የሚከት የአጽሞች ግትልትልና ቅጭልጭልም ዑደቱን የሚቆራርጥ ሰንሰለት እያሰመረ አልፏል፡፡ አጽም ተምሳሌትነቱ ዘለዓለማዊነት ወይም ዑደት አይደለም፡፡ ይልቁንስ አጽም የሂደቱ ማክተሚያ የራሱ የሞት፣ የመበስበስ (Decadence) ወካይ ነው፡፡ ይህንን ስናይ በገብሬ የኪነት ደመነፍስ ምሪት ላይ አልፎ አልፎ ጣልቃ የሚገባ፣ ኸረ እንዲያውም በእኩያነት የሚተናነቀው ፈታሪ ተስፋ የመቁረጥ ስሜት ነበረበት ይሆን? ብለን ለማሰብ እንገደዳለን፡፡ በእርግጥም በዘለዓለማዊ ጭመታ እና ተመስጦ የረጋውን ውቅያኖስ የሚያንደራፋ ድንገቴ ማዕበል የመሰለ የተስፋ መቁረጥ ስሜት ነበረበት። በስንኞቹና በቡርሾቹ ጫፍ ያቆረዘዙትን ከነፍሱ የመነጩ የዕንባ ጠብታዎች ለግፉዓን ሁሉ ረጭቷል፡፡
ዓጽም
ማነህ የተኛኸው?
እንቅልፍ የደበተህ ስጋህን ጥለኸው፡፡
ምን ኖረሀል አንተ
ንጉሥ ኖረሃል ወይ፤ ኖረሃል ወይ ጌታ?
ወይ ቁረንጮ ለባሽ ለማኙ ከርታታ?
ሚኒስትር ደጃዝማች ወይም ፊታውራሪ
ባለብዙ ገንዘብ አሽከር አሳዳሪ
ኖረሃል ወይ አንተ?
አጥንትህ ወላልቆ እንዲህ የሻገተ!

ከሞት ጋር እየተዳሩ፣ እየተናነቁ፣ እየተነፋፈቁ እንደገና በክብ ለሚወከል ዘለዓለማዊነት መቃተት… ምን ዓይነት ውል የለሽ መብከንክን ነበረ ባካችሁ? ምናልባት ሂደቱ (ድግግሞሹ) የመሰላቸቱን ኩርፊያ ወልዶታል፡፡ ከያኒው እኛንና እራሱን በሌጣ የማሰስ ትልሙም (bareness) አጽሙን ፈጥሮት ሊሆን ይችላል፡፡ ላይሆንም ይችላል… ሁለቱም ሀቲቶች በክብ የመቅበጥበጥና በአጽም የመሸበር ጥሪዎች በገብሬ የኪነት አውድ ውስጥ በእኩያነት የሚተናነቁ የመሆናቸው ነገር በእጅጉ ይደንቃል፡፡  
ገብረክርስቶስ ደስታ በባዕድ ምድር ከሞተ እነሆ 40 ዓመት ሊሞላው ነው፡፡ እስካሁንም ግን የእርሱን ሕይወትና ስራዎች የሚዘክር አንዳችም መጽሐፍ ያለመጻፉ ነገር ግርም ይለኛል፡፡ ስለ ፒካሶ ጥቂት ማንበብ የሚፈልግ ማንኛውም ሰው አነሰ ቢባል በመቶዎች የሚቆጠሩ የሕይወት ታሪኩን የሚዘክሩ መጻሕፍት ለምርጫ ይቀርቡለታል፡፡ ከወራት በፊት New York times የፒካሶን ሕይወት በ3 ቅጽ ጠብደል ጠብደል መጻሕፍት ግሩም አድርጎ ያስነበበው እንግሊዛዊው John Richardson ማረፉንና የእርሱንም የሕይወት ታሪክ ለመጻፍ ሩጫ መጀመሩን አስነብቦኝ ተደንቄ ነበር፡፡ ምክንያቱ እኮ ሌላ አይደለም፡፡ ጆ በፒካሶ ጫማ ላይ ቆሞ ከፍ ብሎ መታየት በመቻሉ ነው፡፡ የሰዎችን ታሪክ መፃፍ ትልቅ ትግልና ጥበብ ይጠይቃል፤ አውቃለሁ። እናስ በገብሬ ጫማ ላይ ቆሞ የሚጎላ፣ ለእኛም ሽንፈቶቹንና ትግሎቹን አበጥሮ የሚያሳየን ጀግና ማን ይሆን? ሂደቱ ግን ክብ! ድግግሞሹ የማያባራ...

Read 1381 times