Saturday, 01 May 2021 14:01

ከአውዳመት ጋር የተያያዙ ሥነልቦናዊ ችግሮች (መፍትሄዎቻቸውስ?)

Written by  ብርሃኑ በላቸው አሰፋ
Rate this item
(5 votes)


            "-በዚህ ፈታኝ ወቅት ታዲያ የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት እያንዳንዳችን የመፍትሄ አካል ልንሆን ይገባል፡፡ በበአል ወቅት በተለይም ብስጭትና ቁጣ የሚቀሰቅሱ ምንጮችን መረዳት ቁልፍ ሚና አለው፡፡ ለሚከሰቱ የስሜት መዘበራረቆች እውቅና መስጠት ያስፈልጋል፡፡--"
                     

            እንደ አሜሪካ የስነልቦና ማህበር ጥናት መሰረት፤ 38 በመቶ የሚደርሱ ሰዎች በበዓል ወቅት በሚፈጠር ጫና ለድበታ፣ ለጭንቀትና ለአልኮል መጠጦች ይጋለጣሉ። ከዚሁ ጋር በተያያዘ ናሽናል አልያንስ በአእምሮ ጤና ላይ ባደረገው ጥናት ደግሞ፣ 68 በመቶ የሚሆኑ ሰዎች በበአል ወቅት የገንዘብ እጥረት ጫና ይኖርባቸዋል፡፡ 66 በመቶ ያህሉ ደግሞ  ብቸኝነት ይሰማቸዋል። በበአል ወቅት ከሚከሰት ግርግር ጋር ተያይዞ 63 በመቶ የስራ ጫና አለባቸው፡፡
ጥናቱ እንደሚጠቁመው፤ ቀደም ሲል የአእምሮ ህመም ከገጠማቸው መካከል 24 በመቶ ለሚሆኑት ከበአል ጋር ተያይዞ የሚመጣ መጨናነቅ ህመማቸውን በከፍተኛ ሁኔታ ያበረታባቸዋል፡፡ 40 በመቶ ለሚሆኑት ደግሞ ቀድሞ የነበረባቸውን ህመም ያባብሳል፡፡
በበአል ወቅት ጭንቀትን ከሚቀሰቅሱ ጉዳዮች መካከል የገንዘብ እጥረት፣ በበርካታ ስራዎች መወጠርና ተግባራዊ ሊሆን በማይችል ፍላጎት መጠመድ ይጠቀሳሉ። ጭንቀትን ሊያባብሱ የሚችሉ ሌሎች አመላካቾችም አሉ፡፡ ለአብነትም ከበአል ቀደም ብሎ የተከሰተ አስጨናቂ ትውስታ፣ በቤተሰብ መካከል የተከሰተ አለመግባባትና ግጭት፣ በህመም አልያም በሞት መለየትን ማንሳት ይቻላል፡፡
ይህም አካላዊና ስሜታዊ መገለጫዎች አሉት፡፡ በዋናነት ከሚታዩት ምልክቶች መካከል የልብ ምት መጨመር፣ ድበታ፣ ግራ መጋባት፣ መነጫነጭ፣ ትኩረት ማጣትና ተስፋ ቢስነት ስሜት ይስተዋልባቸዋል። በአካላቸው ላይ ደግሞ ራስ ምታት፣ ዝለት (ድካም)፣ የልብ ምት መጨመርና ላብ ይታይባቸዋል፡፡ ቀደም ሲል በፍላጎት ያደርጉት የነበረው የእለት ተእለት ልማዳቸው ላይ የመቀዛቀዝ፣ ብቸኝነትን የመምረጥ ሁኔታ ይስተዋልባቸዋል፡፡ በእንቅልፍ ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ፣ በአሁኑ ወቅት ያለው የኑሮ ውድነትና የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ስርጭት መስፋፋት ጋር ተዳምሮ፣ በአእምሮ ጤና ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደረ ይገኛል፡፡
በዚህ ፈታኝ ወቅት ታዲያ የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት እያንዳንዳችን የመፍትሄ አካል ልንሆን ይገባል፡፡ በበአል ወቅት በተለይም ብስጭትና ቁጣ የሚቀሰቅሱ ምንጮችን መረዳት ቁልፍ ሚና አለው፡፡ ለሚከሰቱ የስሜት መዘበራረቆች  እውቅና መስጠት ያስፈልጋል፡፡ የሚስተዋሉትን  እንግዳ ስሜቶችና ድርጊቶች ከሌሎች ጋር በግልፅ መጋራት አንዱ የመፍትሄ አካል ነው።  የአካል ብቃት እንቅስቃሴና መጽሐፍትን  ማንበብም የአእምሮ ጤንነትን ያዳብራሉ፡፡
ሰው እንደ ቤቱ እንጂ እንደ ጎረቤቱ አይኖርም እንዲሉ፤ ህይወት በሰጠችን የመርካትና አመጣጥኖ የመኖር ልማድን ማዳበር ይመከራል፡፡ ይህ አመለካከት አላስፈላጊ ከሆነ የውድድር (የፉክክር) የኑሮ ኡደት ይገላግላል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ፣ በበአል ወቅት ከራስ አልፎ ሌሎችን በበጎ ፍቃደኝነት የመርዳትና የመደገፍ ተሞክሮ፣ ለአእምሮ ጤና መበልፀግ ድርሻው ከፍተኛ ነው፡፡ ምንም እንኳን ከኮቪድ 19 ጋር ተያይዞ ማህበራዊ መስተጋብራችን ክፉኛ ቢጎዳም፣ ከወዳጅ ዘመድ ጋር ቢያንስ በበአል ወቅት የሚደረግ የስልክ ልውውጥ ለአእምሮ ጤና የላቀ አስተዋፅኦ ይኖረዋል፡፡  
መልካም የፋሲካ በዓል!
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊው  በ Holistic Child Development (M.A) የመጀመሪያ አመት ተማሪ ነው፡፡


Read 2388 times