Saturday, 08 May 2021 12:38

አምነስቲ፤ በትግራይ የሠብአዊ መብት ጉዳዮችን እንዳላጣራ ተከልክያለሁ አለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(5 votes)

   መንግስት ወደ ትግራይ ገብቼ ምርመራ እንዳላደርግ ከልክሎኛል ሲል አምነስቲ ኢንተርናሽናል ያስታወቀ ሲሆን አለማቀፍ አካላት በትግራይ የተፈፀሙ የሰብአዊ መብት ጥሠቶችን በቅርበት እንዲከታተሉ ጥሪ አቅርቧል፡፡
በትግራይ ግጭት ከተጀመረ ወዲህ ባለፉት 6 ወራት ውስጥ የሚነገሩ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን አጣርቶ ያቀረበና ተጨባጭ መረጃ የሰጠ አካል እንደሌለ ያመለከተው አምነስቲ፤ በግጭቱ የጦር ወንጀልና በሠብአዊነት ላይ የሚፈፀሙ አደገኛ ወንጀሎች ሳይፈፀሙ አይቀርም፤ ብሎ እንደሚያምን አስታውቋል፡፡  በትግራይ ያለውን ሁኔታ የሚያጣራ የባለሙያ ቡድን በተደጋጋሚ ለመላክ መንግስትን መጠየቁን ነገር ግን በጎ ምላሸ እንዳላገኘ የጠቆመው ተቋሙ፤ በትግራይ ያለውን ሁኔታ አስመልክቶ ለአፍሪካ ህብረትና ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት በኩል በቂ ትኩረት አለ መሰጠቱ አሳሳቢ ነው ብሏል፡፡
በግጭቱ ሁሉም አይነት የሠብአዊ መብት ጥሰቶች ተፈፅመዋል የሚል እምነት እንዳለው ያመለከተው አምነስቲ፤ “በሺዎች የሚቆጠሩ ሠላማዊ ሰዎች ተገድለዋል፣በመቶ ሺዎች ተፈናቅለዋል፤ ከ63 ሺህ በላይ የሚሆኑት ወደ ሱዳን ተሰደዋል፣ ህፃትና ሴቶች ተደፍረዋል፣ የህክምና ተቋማት ተዘርፈዋል ተቃጥለዋል፣ሕዝብ ለረሃብ አደጋ  ተጋልጧል” ብሏል፡፡
በትግራይ ልዩ ሃይል በማይካድራ ሠላማዊ ሰዎች መጨፍጨፋቸውን፤ ለዚህ አፀፋ በሚመስል መልኩም  የትግራይ ተወላጆች ላይ በዚያው  በማይካድራ ንብረታቸውን መዝረፍና የጅምላ እስራትን ጨምሮ ጥቃት መፈፀሙን አምነስቲ በሪፖርቱ አመልክቷል።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በበኩሉ፤ ከተባበሩት መንግስታት ጋር በመተባበር ተፈፅሟል ስለተባሉ የመብት ጥሰቶች ጥልቅ ምርመራ እያደረገ መሆኑን ያመለከተ ሲሆን፤ ውጤቱም በቅርቡ ይፋ ይደረጋል ተብሏል፡፡


Read 11539 times