Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 01 September 2012 09:57

‹‹እንደ ሰው ልጅነታቸው እና የአገሬ ሰው በመሆናቸው አዘንኩላቸው››

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የአቶ መለስን መታመም ሲሰሙ ምን አሉ?

የመታመማቸው ወሬ በተደጋጋሚ በሚሰማበት ጊዜ የዜናውን እውነትነት ለማረጋገጥ በርካታ ሙከራዎችን አድርጌያለሁ፡፡ከዛ በኋላም የዓለም አቀፍ ብዙሃን መገናኛን ጨምሮ የተለያዩ የዜና ምንጮች የጠቅላይ ሚኒስትሩ መታመም እውነት መሆኑን በሚያረጋግጡበት ጊዜ በተለይ የአፍሪካ ሕብረት ስብሰባ በሚደረግበት ወቅት የሌሎች አገር መሪዎች መታመማቸውን ሲናገሩ ስሰማ እውነት መሆኑን አረጋገጥኩ፡፡በወቅቱም ማንኛውም ሰው ለሰው ልጅ እንደሚመኘው በሕመም እንዳይሰቃዩ ተመኘሁላቸሁ፡፡ የእርሳቸውን መታመም ከአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ጋር አያይዤ ሳስበው ደግሞ በጣም አዝን ነበር፡፡በወቅቱም በመንግሥት በኩል መረጃን እያድበሰበሱ መቆየትን መምረጣቸው፤ እርስ በእርስ የሚጋጩ ሐሳቦች እየተበራከቱ መምጣታቸው፣ከዛም በላይ የአገሪቷን መረጋጋት እና የሕዝቦቿን ደህንነት የሚያረጋግጡ ተቋማዊ ጥንካሬዎች አለመኖራቸው፣የሥልጣን ሽግግርን የሚያደላድሉ የሕግ እና የአሠራር ሁኔታዎች አለመኖር ሊፈጠር ይችላል ብዬ ባሰብኩት ነገር ስጋት ገባኝ፡፡

ኢትዮጵያን የምታክል አገር በመሪዋ ጤና ማጣት ምክንያት የሚናጋ የፖለቲካ ሁኔታ መኖሩ፣በታሪካችን የምናውቀው  ደርሶ ስናየው እስከዛሬም ሳይለወጥ ቆይቶ አሁን ፊት ለፊታችን መጥቶ መጋረጡን ሳስብ በጣም አዝን ጀመር፡፡ሐዘንም ብቻም ሳይሆን ስጋትም ነበረኝ፡፡ይህ ስጋቴ አሁንም ተቀርፏል ማለት አይደለም፡፡በወቅቱ ግን የእርሳቸው መታተመም እንደሰው ካሳዘነኝ በተጨማሪ ለአገሬ እጅግ አድርጌ አስብ ነበር፡፡ የአገራችን የፖለቲካ ሁኔታ ከግለሰቦች ደህንነት በላይ በዘላቂነት የሚያረጋግጡ ተቋሞች አለመኖራቸው አሁንም ያሳስበኛል፡፡

የጠ/ሚሩ ሕልፈተ ሕይወት እንዴት ነበር የሰሙት?ሲሰሙስ ምን አሉ?

እኖርበት ከነበረው ከተማ ወደ ሌላ ከተማ በተዛወርኩ ማግስት ነበር የጠቅላይ ማኒስትሩ ማረፍ የተነገረው፡፡በአጋጣሚ ከተኛሁ በኋላ እንደገና ተነሳሁና ኢንተርኔት ከፍቼ ድረ ገፆችን ማየት ጀመርኩ፣ ዜናውን አየሁት፡፡በእርግጥ ዜናው በተለያየ መንገድ ሲነገረን እና ሲወራ ቢቆይም፤ በተረጋገጠ መልኩ ዜናውን ስመለከት ግን ስሰማው እንደከረምኩት በነበረኝ ስሜት አልነበረም የሰማሁት፡፡ ብዙ ነገሮች ከኋላ ወደፊት መጡብኝ፤በ21 ዓመት ቆይታችን እንደ ሕዝብ ያሳለፍናቸው ነገሮች፣ በግለሰብነቴ በፖለቲካ ሕይወት ውስጥ ያሳለፍኳቸው ነገሮች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በእርሳቸው አመራር ተጽእኖ ያደረባቸው ዘመኖች ነበሩ፡፡እናም እነዛን ጊዜያቶች ወደኋላ ተመልሼ አሰብኳቸው፤እንደ ሰው ሳስበውም ዜናው በጣም አሳዛኝ ሆነብኝ፡፡በዋናነት የሰው ፍጡር በመሆናቸው  ከዚያም በላይ ደግሞ የአገሬ ሰው በመሆናቸው በጣም አዝኛለሁ፡፡ከዚህ ዓለም በሞት በመለየታቸው እንደ ሰው ልጅነታቸው እና የአገሬ ሰው በመሆናቸው አዘንኩላቸው፡፡ለቤተሰቦቻቸውም አዝኛለሁ፡፡ሐዘናቸውን እንዲረሱም መጽናናትን እመኛለሁ፡፡

እንደ መሪ ደግሞ በ21 ዓመታት ውስጥ በእርሳቸው የአመራር ዘመን ያሳለፍናቸውን ሂደቶች እንደገና አሰብኳቸው፤ በእርሳቸው የአመራር ዘመን የዜጐቿን አብሮ መኖር፣ የተለያየ የፖለቲካ አቋም ያላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች አብሮ መሥራት፣ የሕዝባችን ክብር እና ነፃነት በተጨባጭ የሚያረጋግጥ ሥርዓት፣ ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ የኢኮኖሚ ዕድገት የሚኖርባት ኢትዮጵያን መፍጠር ሲችሉ ያንን ዕድል ሳይጠቀሙበት ሕይወታቸው በማለፉ አዘንኩ፡፡

ያ ቢሆን ኖሮ አገራችን ሰላሟም፣ ዲሞክራሲዋም፣ ዕድገቷም የተረጋገጠበት ደረጃ ይደርስ ነበረ፡፡ የእርሳቸው ሕይወት ሲያልፍም ስማቸው በበጎ እና በመጥፎ የሚነሳ ሳይሆን በአብዛኛው በበጎ እንዲታወስ ሊያደርጉት ይችሉ እንደነበር አሰብኩ እና በጣም አዘንኩ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሥልጣን በቆዩባቸው ዓመታት አገራችን ወደተሻለ የፖለቲካ ሥርዓት፣ ሁሉን አቀፍ ወደ ሆነና ዜጎች የሥልጣን ባለቤት እንዲሆኑ ሊያደርጉ የሚችሉበት በርካታ አጋጣሚዎችና ዕድሎች አልፈዋል፡፡እኚህ መሪ በሥልጣን ላይ በነበሩበት ወቅት እና መወሰን መወሰን በሚችሉበት በእነዚያ ዕድሎች ተጠቅመው ቢሆን ኖሮ ዛሬ ይኼ ሐዘን በሌሎች አገሮች ላይ እንደሚሆነው ሁሉ በሞት የተለየው ሰው ስላደረገው ጥፋት፣ ስላደረገው ኃጢያት ወይም ስለወንጀሉ ሳይሆን እንደ መሪያችን አጣነው በሚል እንደ ሕዝብ አንድ ላይ ሐዘን ብንቀመጥ እንችል ነበር፡፡አሁን ያለው ሁኔታ ከዚህ የተለየውን ስለሚያሳይ ዜና እረፍታቸው የበለጠ እንዲያሳዝነኝ አድርጓል፡፡

እርሳቸው ለሁለት ወር ኃላፊነታቸው ላይ ሳይገኙ በሕመም ሲሰቃዩ እንደነበር ሰምተናል፡፡ ይህም መረጃም ለሕዝብ ሳይገለጽ  በከፍተኛ ሥርዓትና ጥንቃቄ መንግሥት በሚስጥር ይዞት ቆይቷል፡፡ ይሄ ደግሞ የሚያሳየው የፖለቲካ ሒደቱ ዜጎች ባለቤትነት ተሰምቷቸው፣ የራሳቸው ጉዳይ አድርገውና ፖለቲካው ላይ ሥልጣን ተሰጥቷቸው ስላልኖሩና አጠቃላይ ሥርዓቱ በግለሰብ ማንነት ላይ የተመሠረተ በመሆኑ ሥልጣን ላይ ያለው ሁሌ ሕዝብን እየፈራ መኖሩን ነው፡፡ይህ መሆኑም በጣም አሳዝኖኛል፡፡ቢልልና መንግሥታችንም የራሳችን መንግሥት ነው፣የአገራችን ጉዳይ የሁላችንም ጉዳይ ነው፣መሪዎቹ ላይ የሚደርሰው ጥፋት ወይም ጉዳት የሁላችንም ጉዳት ነው የምንልበት ስለሕዝብ ብለን የምንኖርበት እና ሐዘናችን የጋራችን የሚሆንበት አገር ማየት ሁሌም የምፈልገው እና የምመኘው ነው፡፡

የሚኖሩት ከስምንት ዓመቷ ልጅዎ ጋር ነው፡፡ልጆት በፖለቲካ ሕይወት ባሳለፉት ውጣ ውረድ ዋና ተካፋይ ነበረች፡፡እንዲሁም አቶ መለስን በዝና ታውቃቸዋለች፡፡ ዜና እረፍታቸውን ስትሰማ ምን አለች?

ሃሌ ስምንት ዓመቷ ቢሆንም ከ10 ዓመት ልጅ በልጣ ነው የምትታየው፡፡ሀሌ በጣም በትኩረት የጠየቀችኝ መጀመሪያ መታመማቸውን ስትሰማ ነበር፡፡መታመማቸውን ደግሞ እኔ አልነገርኳትም ነበር፡፡ በአጋጣሚ ከጓደኞቼ ጋር ተሰባስበን ቡና በምንጠጣበት ጊዜ ሌሎች ሰዎች ሲያወሩ ሰምታ በጣም በደስታ እየዘለለች “መለስ ታሟል አይደል አሁን በጣም ደስተኛ መሆን አለብሽ” አለችኝ “ለምንድነው ደስተኛ የምሆነው?” አልኳት፡፡ “እንዴ ያለጥፋትሽ እስር ቤት ወርውሮሽ የነበረ ሰው እኮ ነው እንዴት አትደሰችም?” በማለት ተገርማ እንደልጅነቷ በውስጧ የሚሰማትን ጠየቀችኝ፡፡በመታመማቸው የማልደሰትበትን ምክንያት ለማስረዳት በጣም ረጅም ሰዓት ወስዶብኛል፡፡የእርሳቸው በሕመም መሰቃየት ለእኔ ምንም የሚፈይደው ነገር እንደሌለ፣ለደረሰብኝ ጉዳት ካሳ እንደማይሆነኝ፤ በሰው ስቃይ በፍፁም መደሰት እንደሌለብን አስረዳኋት፡፡በመጨረሻም “ማሚ በቀል የሚባል ነገር እንዳለ አታውቂም›› አለችኝ፡፡እንደውም በቀልን በእንግሊዘኛ ‹‹ሪቬንጅ›› ብላ ነው የጠራችው፡፡እንደገና በቀል ለማንም እንደማይጠቅም ለማስረዳት ሞከርኩ፡፡በኋላ ላይ ግን በጣም አዘንኩ፤ ሀሌ አገዛዙ በጣም የቅርቧ በሆነ ሰው እንደውም በራሷ ላይ ያደረሰውን ጉዳት ጠባሳ ገና በልጅነቷ በበቀል ስሜት እንድታስብ አድርጓታል፡፡ይህ ደግሞ የእርሷ ብቻ አይመስለኝም ምናልባትም ደግሞ የእስክንድር ልጅ ናፍቆት ይህንኑ ሊያስብ ይችላል፡፡

የበርካታ ኢትዮጵያውያን ተጐጂ ልጆችን በሀሌ ውስጥ ለማየት ሞከርኩ፡፡በጣም ብዙ ሕፃናት ወላጆቻቸው ባላጠፉት ጥፋት በሚሰቃዩበት ጊዜ በደረሰባቸው ስቃይ የሚያርፍባቸው የሥነ ልቦና ክፉ ጠባሳ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ ስመለከት በጣም አዘንኩ፡፡እኔ መቼስ በሕይወት ስላለሁ አጠገቧ አለሁኝ እና የተሳሳተ ሐሳብ ስትይዝ ለማረም እሞክራለሁ፡፡በዚህ 21 ዓመታት ውስጥ ወላጆቻቸው የተገደሉባቸው እና የታሠሩባቸው ሕፃናት፣ልጆቻቸው የተገደሉባቸው እና የታሰሩባቸው እናት እና አባቶች በአተቃላይ በዚህ ሥርዓት በፖለቲካ አመለካከታቸው የተጎዱ እና ለጉዳታቸው እንኳን ይቅርታ ያልተጠየቁ፣ለጉዳታቸው ካሳ ያልተከፈላቸው በርካታ ዜጎች አሉ፡፡

ይሕ ጉዳት ደግሞ አነስተኛ የማይባል የፖለቲካ ሰፊ መሠረት ያላቸው የፖለቲካ አስተሳሰቦች እና የፖለቲካ ቡድኖች ላይ የተቃጣ ጥቃት እንደነበር መዘንጋት አንችልም፡፡በእርግጥ ዛሬ አገሪቱ በሐዘን ላይ ነች  ነገ ወደ መደበኛው ሕይወታችን ስንመለስ፣ ያሉትን ችግሮች እንደገና ስንጋፈጣቸው የፖለቲካ ሂደቱን ስንመረምር እነዛን ነገሮች ሁሉ መቁጠር ሊያስፈልግ ነው ማለት ነው፡፡ 21 ዓመት ትቶት ካለፈው ነገር የሚያሳዝነኝም ይሄ ነው፡፡ሐዘኑን ከፍ የሚያደርገው ደግሞ በፖለቲካ አመለካከታቸው ምክንያት አሁንም እስር ቤት ውስጥ በርካታ ሰዎች መኖራቸው ነው፡፡ ነገም ከነገ ወዲያም በፖለቲካ ልዩነት ሰው እንደማይገደል፣ሰው እንደማይታሰር እርግጠኛ የምንሆንበት ምንም ዓይነት ጠቋሚ ነገር አለማየታችን፣ጉዳቱ ተመልሶ የማይመጣበትን ሁኔታ ማረጋገጥ አለመቻላችን እጅግ አሳሳቢ ነገር ነው፡፡ይህ ቢረጋገጥ ኖሮ ልጆቻችን እና መጪው ትውልድ ከጥላቻ እና ከቁርሾ ጋር አብረው እንዳያድጉ ለማድረግ የተመቻቻ ሁኔታ ይፈጠር ነበር፡፡

የሀሌን አስተሳሰብ ለማረም መሞከሮትን የገለጽሽው ታመው በነበሩበት ወቅት ነው፤ኅልፈተ ሕይወታቸው ሲሰማስ ምን አለቾት?

ዜናውን በሰማሁበት ጊዜ ከእኔ ጋር አልነበረችም፡፡ዘመድ ቤት ነበረች፣ በሚቀጥለው ቀን ስንገናኝ “ሰማሽ?” አልኳት “አዎ ሰምቻለሁ” አለችኝ “ምን ተሰማሽ?” አልኳት፡፡ “አዝኛለሁ አንቺስ?” አለችኝ “እኔም አዝኛለሁ” አልኳት “አንቺ የምትታገይው ስላጣሽ ነው ያዘንሽው?” በማለት በልጅነት ዕድሜዋ ያሰበችውን አስቂኝ ጥያቄ ጠየቀችኝ “አይደለም ሰው ስለሆንኩ ነው ያዘንኩት” አልኳት እና የእኔ ትግል ከሥርዓቱ ጋር እንጂ ከአቶ መለስ ጋር እንዳልሆነ፣ በፖለቲካ ውስጥ የግል ጠብ ሊኖር እንደማይገባ ለዕድሜዋ በሚመጥን መልኩ አስረዳኋት፡፡

ወ/ት ብርቱካን የአቶ መለስ ዜናዊን ኅልፈተ ሕይወት ተከትዬ አስተያየት ሲሰጡ አዲስ አድማስ ጋዜጣ የመጀመሪያዎት አይደለም እና በሌሎች ሚዲያዎች የሰጡትን ቃለምልልስ ተከትሎ አንዳንዶች አስተያየቱን በሳል ሲሉት አንዳንዶች ደግሞ የተለሳለሰ ብለውታል፡፡

እስቲ እኔ ጠያቂ ልሁን፤ላንቺ የትኛው ነው በሳል የትኛው ነው የተለሳለሰ?

የእኔ ሥራ መጠየቅ ነው፤በተለያዩ ማኅበራዊ ድረ ገፆች የሰፈሩትን ብነግሮት በሥርዓቱ ዋናዋ ተጎጂ እርሳቸው ሆነው እያለ አዝኛለሁ ማለታቸው መለሳለሳቸውን ነው የሚያሳየው ሲሉ ይህን ያህል ጉዳት ደርሶባቸው ግለሰብን እና ፖለቲካን ለይተው ሐዘናቸውን መግለጻቸው በሳልነታቸውን ያሳያል ያሉ አሉ፤

እንግዲህ እኔ አዝኛለሁ፡፡ ማዘኔን ደግሞ ልደብቀው አልችልም፡፡በግሎ የተሰማኝን ስሜት በቀጥታ መናገር አለብኝ ብዬ አምናለሁ፡፡ማዘኔ ደግሞ ስህተት ነው የሚባልበት ምክንያት ያለ አይመስለኝም፡፡እንግዲህ ሰው ሁሉ የተለያየ አስተሳሰብ እና የተለያየ ምላሽ ሊኖረው ይችላል፡፡  ለእኔ ግን በጣም መሰረታዊ ነገሮች ናቸው ብዬ ከማምናቸው እሴቶች እና መርሆዎች መካከል አንዱ ለሰው ልጅ ያለኝ በጐ አመለካከት ነው፡፡በዛ ላይ ደግሞ “ሞት” የሚባለው ነገር ለሁላችንም የማይቀር እንደሰው ያለንን የአቅም ውስንነት እና ደካማነት የሚያሳየን በምንም ነገር ታግለን የማናስቀረው እሱ በፈለገ ጊዜ ብድግ አድርጎ የሚወስደን ነገር ነው፡፡‹‹ሞት›› እንደ በሕይወት ያለንበትን ጊዜ ትርጉም ያለው ነገር አድርገን እንድናሳልፍ አንድ ጊዜ ከወሰደን ተመልሰን የምንመጣበት መንገድ ስለሌለን ያለንን ዕድል እንደገና እንድናጤን የሚያስገድደን ነገር ነው፡፡በዚህ ጉዳይ ላይ ማንኛችንም አንዳች ሥልጣን ስለሌለን እንኳንም ሆነ እንኳንም አልሆነ ወደሚል ድምዳሜ መግባት ያለብን አይስመስለኝም፡፡ ሰዎች ከአቅማቸው በላይ በሆነ በተፈጥሮ ችግር በበሽታ ሲሰቃዩ ወይም ደግሞ በሞት ሲያልፉ ማዘን እንጂ መደሰት እኔ ተፈጥሯዊ አይመስለኝም፡፡እንደተባለው በዚህ ሥርዓት ከተጎዱት ሰዎች መካከል አንዷ እኔ ነኝ፡፡ ከእኔም በባሰ ሁኔታ የተጎዱ ሰዎች አሉ፡፡ በዚህ ሰዓትም በእስር ቤት የሚሰቃዩ ሰዎች አሉ፡፡ ሕይወታቸውንም በግፍ ያጡ ሰዎች አሉ፡፡ ነገር ግን ያ እንዲሆን ያደረገ ሰው በሕመም ሲሰቃይ ወይም በሞት ሲያልፍ ማየት የእኛን ጉዳት በፍፁም አይጠግነውም፡፡ ጉዳታችንን በፍፁም የምንረሳ ወደኋላ የምንተወው አይደለም፡፡ የምንካሰው ያሰቃየን ሥርዓትና  አስተዳደር ተሸሽሎ እና ተለውጦ ስናይ ነው እንጂ ሰው ሲሞት አይደለም፡፡ አልሆነም እንጂ ቢሆን ኖሮ አቶ መለስ ሐሳባቸውን፣ አካሄዳቸውንና ፓርቲያቸውን ቀይረው፣ የብሔራዊ እርቅ አካል ሆነውና ነፃነትና ዲሞክራሲ እንዲሁም የኢኮኖሚ ብልፅግና የሰፈነበት አገር አብረን መሥርተን የዚያ አካል ሆነው  ትልቅ ቅርስ ትተው ቢያልፉ ኖሮ ደስታዬ በጣም ትልቅ ይሆን ነበር፡፡

ከአገር ከወጡ ሰነበቱ? ምን ይናፍቆታል?

ሁሉም ነገር ይናፍቀኛል፡፡ከሁሉም በላይ ሰው ይናፍቀኛል፡፡አጠቃላይ ሕዝቡ ይናፍቀኛል፡፡ከአገር ሲወጣ ግን በቃ ሁሉም ነገር ይናፈቃል፡፡እኔም ሁሉን ነገር እናፍቃለሁ፡፡ያደኩበት ሰፈሬን “ፈረንሳይን” እናፍቃለሁ፡፡እንደ ሕዝብ በጋራ የምንይዛቸው፤ እርስ በእርስ የምንደጋገፍባቸው እርስ በእርስ የምንተሳሰብባቸው ነገሮች ይናፍቁኛል፡፡ እኔ ባለሁበት የሰለጠነ በሚባለው ዓለም ከአገሬ ጋር ተቃራኒ ባህል ስላለ በመካከል ያለውን ልዩነት እያየሁ፡፡

እኔ ሁሌም አገሬን እናፍቃለሁ፡፡ውጭ አገር ደርሰው የተመለሱ ድምፃውያን ሀገራችን እንዴት የተለየች አገር እንደሆነች ሲገልፁ፣ እንዴት አይተዋት እንደሆነ አሁን ነው የገባኝ፡፡ ከውጭ ሆነሽ ስታይው በጐ ነገራችን፣ማኅበራዊ ግንኙነታችን፣ ባሕላችን ዋጋቸው ምን ያህል ከፍ ያለ እንደሆነ ይታይሻል፡፡አሁን ሁሉም ነገር በጣም ነው የሚያሳሳኝ፡፡ ሙዚቃችን እንኳን እዚህ ስሰማው እና እዚያ በነበርኩ ጊዜ በሰው መካከል ሆኜ ስሰማው ልዩነቱ አሁን ነው የታየኝ፡፡ እዚህ ሙዚቃ እየሰማሁ እዛ እሰማበት የነበረው ሁኔታ ትዝ ይለኛል፡፡ታክሲ ውስጥ፣ካፍቴሪያ ውስጥ፣ መዝናኛ ስፍራ በቃ ከሰዎች ጋር ተቀላቅዬ እሰማበት የነበረው ነገር ሁሉ ለእኔ ልዩ ነበር፡፡ እነዚህ ነገሮች ሁሉ ይናፍቁኛል፡፡ የበዓል ሰሞን ያለውን ግርግር ሳስብ ያባባኛል፡፡ እዛ ውስጥ ስንኖር እንደተራ ነገር ልንቆጥረው እንችላለን፡፡ርቀሽ ስታያቸው ግን ሁሌም ናፍቆትሽ ናቸው፡፡አገር ሁሌም ይናፍቃል፡፡

 

 

Read 3322 times Last modified on Saturday, 01 September 2012 10:09